
በጤናው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ዘጠነኛው የኢትዮ ኸልዝ ዓውደ ርዕይ እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የመድኃኒት አቅራቢዎች ጉባኤ በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። ዓውደ ርዕዩ በጤና ዘርፍ የተሠማሩ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በማገናኘት ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበትንና የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበትን ሁኔታ መፍጠርን ያለመ ነው።
ያነጋገርናቸው የዓውደ ርዕዩ ተሳታፊ ድርጅቶችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። ድርጅቶቹ ዓውደ ርዕዩ ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ከማስተዋወቅ ባሻገር የገበያ ትስስር እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
‹‹ሲጂኤፍ ሜዲካል ግላቭ ቢዝነስ ግሩፕ›› የተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅት በዓውደ ርዕዩ ተሳትፏል። ድርጅቱ ሌሎች ግብዓቶችን የሚያመርት እህት ኩባንያ ያለው ሲሆን፣ ‹‹ሲጂኤፍ ሜዲካል ግላቭ›› ግን በጤናው ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል።
የድርጅቱ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ ወይዘሮ መሳይ ኃይሉ እንዳለችው፤ ፋብሪካው ከተመሠረተ አስር ዓመት በላይ ሆኖታል፤ የፋብሪካው የማምረቻ ቦታ ቡራዩ ሲሆን፣ በቀን 100 ሺ ያህል ግላቮችንም ያመርታል።
በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛ ግላቭ አምራች ፋብሪካም ነው። ፋብሪካው እያመረተ ያለው ‹‹ኤግዛሚኒሽን ግላቭ›› የተሰኘውን የግላቭ ዓይነት ሲሆን፣ ግላቩ ለመጀመሪያ የሕክምና ርዳታና ለተለያዩ አገልግሎቶችም መዋል ይችላል፤ ግላቩን ማንኛውም ሰው ሊጠቀመውም ይችላል።
ፋብሪካው ቀደም ሲል ፓውደር ያላቸውን ግላቮች ያመርት እንደነበር ጠቅሳ፤ ፓውደር ያላቸው ግላቮች ተፈላጊነታቸው እምብዛም እየሆነ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ደግሞ ፓውደር የሌላቸውን ማምረት ጀምሯል ብላለች። ምርቶቹ ገና ገበያ ላይ ያልወጡ መሆኑን ትገልጻለች። በተለይ ፓውደር የሌላቸው ግላቮችን ማምረት በመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የሚደግፍና የሚበረታታ እንደሆነ ጠቅሳ፣ የኅብረተሰቡ ፍላጎት ፓውደር ካላቸው ምርቶች ይልቅ ወደ ፓውደር የሌላቸው ምርቶች እንደሚያዘነብል ተናግራለች።
ፋብሪካው ለምርት ግብዓትነት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች አቅርቦት እጥረት እያጋጠመ ነው የምትለው ወይዘሮ መሳይ፤ አሁን ለግብዓትነት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ከታይላንድ እንደሚመጡ ትገልጻለች። ለዚህ ምርት በግብዓትነት የሚውለው የጎማ ዛፍ በሀገር ውስጥ ያለና እዚሁ ማምረት የሚቻል ሆኖ ሳለ እስካሁንም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ እየገባ መሆኑን አመልክታ፣ ይህ ሁኔታም ፋብሪካው የግብዓት እጥረት እንዲገጥመው እያደረገ መሆኑን አመላክታለች።
ጥሬ እቃ ከውጭ በማስመጣቱ ሂደት ውስጥ ፈተናዎች እንደሚገጥሙም ተናግራ፣ ከተግዳሮቶቹ መካከል የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲሁም ግዥ ከተፈጸመ በኋላ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚወስደው ብዙ ጊዜ እንደሚጠቀሱ ገልጻለች።
ቀደም ሲል የኤግዛሚኒሽን ግላቭ ከውጭ ሀገር በውድ ዋጋ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባ እንደነበረ አስታውሳ፤ አሁን በሀገር ውስጥ መመረቱ ምርቱን ለማስመጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ የሚያድን ከመሆኑም በላይ ዋጋውም ቢሆን ተመጣጣኝና የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘበ ነው ስትል አብራርታለች።
እሷ እንዳስታወቀችው፤ በሀገር ውስጥ እየተመረተ ያለው ግላቭ በጥራትም ሆነ በዋጋ ከውጭ ከሚመጣው ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ነው፤ መቶ ፍሬ የሚይዘውን አንድ ሳጥን ኤግዛሚኒሽን ግላቭ በስድስት ሺ ብር የሚሸጥ ሲሆን፣ ግብዓቶቹ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ቢሆን ደግሞ ከዚህም በተሻለ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ ይቻል ነበር።
የሲጂኤፍ ሜዲካል ግላቭ ቢዝነስ ግሩፕ ኤግዛሚኒሽን ግላቮች በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ትገልጻለች። ድርጅቱ ከ75 በላይ ለሆኑ ሰዎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሳ፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የምርት ዓይነቱን በመጨመር ሰርጂካል ግላቭ ጭምር ለማምረት ማቀዱን ጠቁማለች። ለእዚህም ድርጅቱ 24 ሰዓት ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግራ፣ በዚህ ሥራም ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቃለች።
እሷ እንደምትለው፤ ድርጅቱ ከተመሠረተ ረጅም ጊዜያት ያስቆጠረ ቢሆንም፣ እምብዛም አይታወቅም ነበር። በዓውደ ርዕዩ ላይ መቅረቡ ራሱን ለማስተዋወቅ አስችሎታል። ቀደም ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓውደ ርዕይ ላይ በመገኘት ራሱን ያስተዋወቀ ሲሆን፣ ይሄኛው ሁለተኛው ዓውደ ርዕዩ ነው።
ግላቩን ከመጠቀም ውጭ በሀገር ውስጥ ስለመመረቱ የማያውቅ በጣም ብዙ ሰው እንዳለ ገልጻ፣ እንደዚህ አይነት ዓውደ ርዕይ የድርጅቱን ምርቶች ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራሉ ብላለች። ከሌሎች ጋር እንዲተዋወቅና የገበያ ትስስር እንዲፈጥር የሚያስችል መሆኑን አመልክታ፣ ይህ ዓውደ ርዕይ ከብዙ ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር አስችሎታል ትላለች።
ድርጅቱ ኤግዛሚኔሽን ግላቮችን እያመረተ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ወይዘሮ መሳይ ጠቅሳ፣ ሙሉ በሙሉ የሀገር ውስጥ ፍላጎት የሚሸፈኑ ምርቶች ማምረት አለመቻሉንም ገልጻለች። በዚህ የተነሳም አሁንም ምርቶቹ ከውጭ እንዲመጡ እየተደረገ መሆኑን ትገልጻለች። ግብዓቶቹን ሀገር ውስጥ ማምረት ቢቻል ከውጭ የሚመጣውን ምርት ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር ይቻላል ስትል ተናግራለች።
ሌላኛው የዓውደ ርዕዩ ተሳታፊ ‹‹ብራውን ፋርማሲቲካል›› የተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅት ነው። የሜዲካል ጋዝ ምርቶች (እንደ ኦክስጂን፣ ቫክዮም ኤር፣ ዓይነቶችን) በተቀላጠፈ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል ሥርዓት የያዘ አገልግሎት ይዞ ቀርቧል።
የድርጅቱ ባዮሜዲካል ኢንጂነር አቶ ብሩክ አብርሃም እንደተናገረው፤ ድርጅቱ ከተመሠረተ ረጅም እድሜን አስቆጥሯል። በመድኃኒትና ቁጥጥር ባለሥልጣንም ፈቃድ ተሰጥቶታል። በኤግዚቢሽኑ ላይ ይዞ የቀረበው እንደ ኦክስጂን፣ ቫክዩም ኤር ዓይነት የሜዲካል ጋዝ ምርቶችን በሲሊንደር ከማጓጓዝ ይልቅ በተቀላጠፈ ሥርዓት ለሕሙማን እንዲቀርብ የሚያስችል አሠራር ነው። ለዚህ የሚሆኑ ግብዓቶችን፣ በማቅረብ ከዲዛይን ጀምሮ እስከ መትከል ያሉ ሙሉ ሲስተም የመዘርጋት የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት እንዲኖር የማድረግ ሥራን ይሠራል።
ድርጅቱ ይህንን አገልግሎት ለመስጠት ዒላማ አድርጎ እየሠራ ያለው ከግል ሆስፒታሎች ጋር ነው። ምክንያቱም ይህ አገልግሎት ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ ስለሆነ በብዙ የሚደፍሩት የግል ሆስፒታሎች በመሆናቸው ነው።
ቀደም ሲል የሜዲካል ጋዝ ምርቶቹን የሚጠቀሙ ሆስፒታሎችም ሆኑ የጤና ተቋማት ምርቶቹን ከተለያዩ አምራች ድርጅቶች በሲሊንደር ገዝተው ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሶ፤ ድርጅቱ የሚያቀርባቸውን ምርቶች ሲጠቀሙ ግን ኦክስጅን በራሳቸው ማምረት የሚችሉበን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይገልጻል።
አቶ ብሩክ እንዳብራራው፤ ድርጅቱም ለዚህ የሚሆኑ መሣሪያዎችን /ዲቫይሶችን/ ያቀርባል። እነዚህን ዲቫይሶች ሆስፒታሎችም ሆኑ የጤና ተቋማት ሲጠቀሙ ሲሊንደር ማጓጓዝ አይጠበቅባቸውም፤ ራሳቸው አምርተው ለሕሙማን ተደራሽ ማድረግ ይቻላሉ። በዚህም በሲሊንደር ለማጓጓዝ ይወጣ የነበረውን የሰው ጉልበት፣ ጊዜና ወጪ ይቀንሳሉ። ከዚህ በተጨማሪም የአገልግሎት ጥራታቸው ይጨምራል።
ሲስተሙ የተሠራው ብዙ ነገሮች ታሳቢ አድርጎ ነው፤ ቀጣይነት ያለው አቅርቦት እንዲኖር እንዲሁም ተደራሽነትን ለመጨመርም ታሳቢ ተደርጓል። ይህ ሲባል ለአብነት ኦክስጅንን የሚያመርተው ማሽን ቢበላሽ ምን መደረግ አለበት የሚለውንም እንዲሁ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁሟል። ማሽኑ ሲበላሽ ሊጠቀሙት የሚችሉት ኦክስጅን በሲሊንደር በማስቀመጥ ወዲያውኑ /አውቶማቲካሊ/ በሲስተም አማካኝነት ኦክስጅኑን ለማግኘት የሚያስችልም መሆኑን ተናግሯል።
ድርጅቱ እነዚህን አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያስችሉ ቁሳቁስ ማስመጣት ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱን ማቀላጠፍ የሚችሉበትን ሲስተም ከዲዛይን ጀምሮ መትከልና ከዚያ በኋላ ያሉ አገልግሎቶች ያካተተ ሥራ እንደሚሠራም አስታውቋል።
ድርጅቱ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚሠራ ጠቁሞ፣ ደንበኞችን ማግኘት ፈታኝ እንደሆነበትም ይገልጻል። በዓመት አንድም ሆነ ሁለት ፕሮጀክት ከሠራ ለድርጅቱ እንደ ትልቅ ስኬት እንደሚታይ አመላክቶ፤ ለአብነትም ዘንድሮ የሁለት ሆስፒታሎችን ፕሮጀክቶች መጀመሩን አስታውቋል።
‹‹ድርጅቱ የመንግሥት ሆስፒታሎች በሚያወጡት ጨረታ ላይም እንዲሁ ይወዳደራል፤ እስካሁን ከተወዳደረባቸው ጨረታዎች መካከል ስድስትና ሰባት ወራት ያህል ጊዜ የወሰዱ ጨረታዎች አሉት፤ በእዚህም አሸናፊ እንሆናለን ብለን እንጠብቃለን›› ሲል አመልክቷል። አሁን ግን በአብዛኛው ከግል ሆስፒታሎች ጋር እየሠራ መሆኑን ጠቅሶ፣ በዓውደ ርዕዩ ላይ የኛ አይነት ሥራ የሚሠራ ድርጅት አላየንም። የእኛ ድርጅት የሜዲካል አክሰሰሪዎች የያዘ ብቸኛው ድርጅት ነው›› ብሏል።
አቶ ብሩክ እንዳብራራው፤ ሜዲካል ዲቫይሶቹ ጥቅም ላይ የሚውሉት መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች (ድንገተኛ፣ የኦፕሬሽን፣ የመሳሰሉት ክፍሎች) ነው። የእነዚህ ዲቫይሶች ከአገልግሎት ውጭ መሆን ሕሙማኑ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህ እንዳይሆን ደግሞ በጥንቃቄ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ደኅንነታቸውን መጠበቅ ያስፈልጋል፤ ድርጅቱ ለደንበኞቹ ደኅንነታቸው የተጠበቀ የተሟላ አገልግሎት ይሰጣል። አክሰሰሪዎችን በማቅረብና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን ሁሉ ይሰጣል።
እነዚህ መለዋወጫዎች /አክሰሰሪዎች/ በጣም ትንሽ የሚመስሉ ግን ገበያ ላይ የማይገኙ በመሆናቸው የተነሳ ሲስተሙ ሙሉ ለሙሉ ቆሞ የሚገኝባቸው በርካታ የመንግሥት ሆስፒታሎች እንዳሉም ተናግሯል። ድርጅቱ መለዋወጫዎቹን ማቅረቡ ይህን ችግር እንደሚፈታ አስታውቋል።
ድርጅቱ እነዚህ ቁሳቁስ በማስመጣት የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት እንዲኖር ለማድረግ ወደ ሥራ ሲገባ ብዙ ተግዳሮቶች ገጥመውት እንደነበር የሚያስታወሰው አቶ ብሩክ፤ የመጀመሪያው የግንዛቤ ክፍተት መሆኑን አመልክቷል። ይህ ችግር ለሥራ እንቅፋት መሆኑን አንስቷል።
አቶ ብሩክ እንዳለው፤ ድርጅቱ አሁን ስድስት ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፤ ፕሮጀክቶች በሚኖሩበት ጊዜ ደግሞ ከ15 እስከ 20 ለሚሆኑ ሠራተኞች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ፕሮጀክቶቹ እየሰፉ በመጡ ቁጥር የሚፈጥረው የሥራ ዕድል እየጨመረ ይመጣል።
ድርጅቱ በዓውደ ርዕዩ ላይ ሥራዎቹንና ምርቶቹን ማስተዋወቁን አቶ ብሩክ አመልክቷል፤ ይህም በእንዲህ ዓይነት ሲስተም ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች በጣም ጥቂት የሚባሉ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ድርጅቱ በሜዲካል ዘርፉ እየሠራ መሆኑ ከብዙ ድርጅቶች ጋር እንዲገናኝና ብዙ ደንበኞችን እንዲያፈራ ዕድሉን ፈጥሮለታል ብሏል። ከተለያዩ ደንበኞች ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር አስችሎታል ሲል ተናግሯል።
‹‹የኔ ኸልዝ›› የተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅትም ሌላው በዓውደ ርዕዩ የተሳተፈ ኩባንያ ነው። የድርጅቱ ማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ ወጣት ረድኤት ዓለማየሁ እንደምትለው፤ ‹‹የኔ ኸልዝ›› ከተመሠረተ ከሁለት ዓመታት በላይ የሆነው ስታርትአፕ ድርጅት ነው። በጤናው ዘርፍ ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል። ‹‹ታይምቴክ›› የተሰኘ የጤናውን ዘርፍ ላይ የተካተተ አገልግሎት አለው። ‹‹ታይምቴክ›› ሞባይልና ዌብ ሳይት በመጠቀም ዲጂታል ሶልሽን አገልግሎትን ለሴቶች መስጠት ያስችላል።
በሞባይል መተግበሪያው የእርግዝና ወቅት መከታተያ የጊዜ ሰሌዳ እንዳለው ጠቅሳ፤ በዚህም አንዲት ሴት ከመጀመሪያው የእርግዝና ሳምንት እስከ መጨረሻው ድረስ የጽንሱን እድገት ለመከታተል እንደሚያስችል ትገልጻለች። ሴቶች የወር አበባ ሊመጣና ሊያቆም የሚችልባቸውን ጊዜያት በመተግበሪያው መከታተል እንደሚ ችሉም አብራርታለች። ድርጅቱ አንዲት ሴት ስለራሷ ማወቅ የምትፈልገው ጥያቄ ካሏት በዶክተሮች እገዛ እንድትማርና እንድታወቅ የሚያስችል መተግበሪያ እንዳለውም ጠቁማለች።
እሷ እንዳለችው፤ ከዚህ በተጨማሪ ኦንላይን የፋርማሲ አገልግሎት ይሰጣል። በዚህም አንድ ሰው የታዘዘለትን መድኃኒት ቤቱ ድረስ የማቅረብ አገልግሎት ይሰጣል። መድኃኒት የማከፋፋል ሥራም ይሠራል። መተግበሪያውን እስካሁን 35ሺ የሚጠጉ ሴቶችና ዌብሳይቱንም እንዲሁ በወር ከ10 እስከ 11 ሺ የሚገመቱ ሰዎች ይመለከቱታል።
የኔ ኸልዝ ለሃያ ስድስት ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሳ፤ አሁን በብዛት ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ገልጻለች። በቀጣይ ወንዶችን በማካተት ለመሥራት እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን አመላክታለች። በአዲስ አበባና ትልልቅ ከተሞች ላይ ብቻ የተወሰነው አገልግሎት በማስፋት ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ዓላማ እንዳለው አስታወቃለች፤ ይህን ሥራውን ከሰሐራ በታች ወዳሉ የአፍሪካ ሀገራት የማስፋት እቅድ እንዳለውና በሩዋንዳም ቅርንጫፍ ከፍቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሳለች።
ድርጅቱ በዓውደ ርዕዩ ተሳታፊ መሆኑ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ እንደሚያደርገውም ረድኤት ገልጻ፤ ‹‹በተለይ የኦንላይን ፋርማሲ አገልግሎቱ ከተለያዩ ፋርማሲዎችና አስመጪ ድርጅቶች ጋር እንዲተዋወቁና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም አስታውቃለች። ድርጅቱ ብዙ ሰዎች እንዲያወቁትና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያስችልም ተናግራለች።
ኤግዚቢሽኑ በጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶክተር) እንዲሁም በሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ተጎብኝቷል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም