በትግራይ ክልል የተደረገው ህግ የማስከበር ዘመቻ ስምንት ወራትን የፈጀ ሲሆን በሰብዓዊና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ ነበር። በክልሉ የሚደረገው ህግን የማስከበር ዘመቻ ነዋሪው ላይ እክል በመፍጠሩ መንግስት መከላከያ ሰራዊት እንዲወጣ አድርጓል። ሽብርተኛው የህወሀት ቡድን ግን አሁንም ድረስ ወደ ጦርነት ወጣቱን እየማገደ ይገኛል። የአገር መከላከያ ሰራዊት በስምንት ወራት ውስጥ ለትግራይ ህዝብ አስፈላጊ የሚላቸውን ስራዎች ያከናወነ ሲሆን በቀጣይ አስፈላጊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርግ መንግስት አሳውቋል። መከላከያ ሰራዊቱ ለሰላም የከፈለውን መስዋዕትነት ለማመስገን በአዲስ አበባ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ናቸው። ከዚህም ውስጥ ባሳለፍነው ሳምንት በየካ ክፍለ ከተማ መሰብሰቢያ አዳራሽ የተከናወነው የወጣቶች የውይይት መድረክ ይጠቀሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ክብር ለሀገር አንድነትና አብሮነት ለተሰው ጀግኖች የመከላከያ ሠራዊት አባላት” በሚል ከከተማችን ወጣቶች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል። ‹‹ለየትኛውም የመከላከያ ጥሪ ዝግጁ ነን›› ሲሉ አዲስ አበባ ወጣቶች በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከአገሬ በፊት ያስቀድመኝ የሚሉላት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች አገር መሆኗን ተናግረዋል። ወጣቶቹ መከላከያ ሀይሉ የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ስነልቦና ከፍታ ማሳያ ነው። ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የባዕዳንን ጣልቃ ገብነት መከላከል ይገባል። የትኛውም ምድራዊ ሀይል ኢትዮጲያን ማፍረስ አይቻለውም። የመከላከያ ሰራዊት ተከፍሎ የማያልቅ ውለታ ሁሉም ህዝብ አለበት የሚሉ ጠንካራ መልዕክቶችን ወጣቹ አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ያሸነፈችበት ትልቅ የድል ምዕራፍ በመሆኑ እነዚህ የድል ምዕራፎችን በተለይ ወጣቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ሁልጊዜ አዲስ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ በማድረግ የሚታወቁ ታሪክ ያላቸው ናቸው። ይሄ ታሪክ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረና የመጣን የወጣቶች ሚናን ታሳቢ ያደረገ ትልቅ መስዋዕትነት የተከፈለበት ለውጥ ነው። ይህን ለውጥ በወጣቶች መስዋዕትነት መጥቶ ውጤታማ እንዳይሆን በተፈለገው መንገድ እንዳይሄድ ሊያደናቅፍ የተነሳውን ሀይል የአገር መከላከያ ሰራዊት ሂወቱን ገብሮ በትልቅ የጀግንነት ታሪክና ተግባር ለውጡ እንዲቀጥል ለማድረግ ሰርቷል። የአገር መከላከያ ሰራዊቱ መስዋዕትነት የከፈለበት ድል ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ የቻለና በድሉ ላይ እንቅፋት ለመሆን የተነሳውን ሀይል አንኮታኩቶ ኢትዮጵያ ድሏ እንዲቀጥል ማድረግ በመቻል ነው። አንዱ አሸናፊነት ይሄ ነው።
ሁለተኛው አሸናፊነት ደግሞ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁ ነው። ይህ ትውልድ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መባል በሚችል ደረጃ አገርን ባስቀደመ በአንድነት ድምፄ አገሪቱን የሚመራውን መሪ ለመምረጥ መወሰን ይችላል በሚል በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ መንገድ ፍፁም በሆነ ነፃነት ምርጫ በማካሄድ በታሪክ አዲስ ነገር መፍጠር ተችሏል። ከሁሉ በላይ ይህን ታሪክ እንድናውቅ ያደረገን አገሪቱ በብዙ ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት በመሆኑ ነው። ከምንም ነገር በላይ ህዝቡ መወሰን እንደሚችልና ምርጫ የሉአላዊነት መገለጫ መሆኑን በተግባር የታየበት ወቅት ነው። ለዚህ መብቃት የተቻለው ወጣቱ በአግባቡ በመንቀሳቀሱ ነው።
በሶስተኛ ደረጃ የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ የሁሉም ነው በማለት የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም የተነሳው ጥያቄና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ይኑር መባሉ ያስቆጣቸውና የፍትሀዊነት ጥያቄ ያልተዋጠላቸው አካላት በአለም መድረክ ክስ አቅርበው ነበር። ክሳቸው ሚዛን የማይደፋ በመሆኑ ጉዳዩን አፍሪካ በውስጥ አቅም እንድትፈታውና በራስ እንዲታይ እንዲሁም በራስ በፍትሀዊነት መፈታት ይቻላል በማለት ኢትዮጵያ በመሟገቷ ኢትዮጵያና እውነቷ አለም ላይ ተቀባይነት ያገኘበት ወቅት ላይ ነን። ይሄ ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ለአፍሪካም ትልቅ ድል ነው። አፍሪካውያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው መሰወን እንደሚችሉ ያሳዩበት ነው። ይሄንንም ለማንም አሳልፎ መስጠት እንደማይገባና ኢትዮጵያ እንደትናንቱ የነፃነት አርማ መሆን መቻሏ የታየበት ነው። ለዚህ ድል የታደለ ወጣት በመኖሩ ትልቅ እድል ነው።
የህዳሴ ግድቡ ውሃ ሙሌት አንደኛው የተሞላ በመሆኑና በዚህ ትውልድ መገንባቱ እንዲህም በብዙ ችግሮች ውስጥ ቢያልፍም ለሙሌት ደረጃ ደርሶ በሁለት ተርባይነሮች ወደ ሀይል ማመንጫነት የደረሰበት ነው። ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ደግሞ እውን እየሆነ ያለበት የድል ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። የኢትዮጵያውያን ደስታ ሙሉ የሚሆነው በነዚህ ድል በመኩራት ብቻ አይደለም። እነዚህ ድሎች መቻል የሚያሳዩ ሲሆን ከዚህ በላይ ለመስራት የሚያነሳሱ ናቸው። ብልፅግና እስኪመጣ ድረስ ምንም አይነት እረፍት አይኖርም። በእልህና በቁርጠኝት መሰራት አለበት። መቻልን በመሰነቅ የአገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ በሁሉም ዘርፍ እጅ ለእጅ በመያያዝ መሰለፍና መትጋት ይገባል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት በከፈለው ዋጋ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተጠናቋል። በተጨማሪም ሌሎች የልማት ስራዎችን ማከናወን ተችሏል። እንዲሁም በሰላም መውጣትና መግባት ተችሏል። መከላከያ ሰራዊቱ ከራሱ በላይ ለህዝብና ለአገር እየሞቱ ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያ ወደ ፊት እየቀጠለች እድገቷና ለውጧ እንዳያቋርጥ ማድረግ የተቻለበት ሁኔታ አለ። የመከላከያ ሰራዊቱን ለማዳከም ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል። በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ግጭት በማስነሳት ከእናቶች በተሰረቀ ገንዘብ በተለያዩ መንገዶች ግጭት ሲስፋፋ ነበር። በዚህም የአገር መከላከያ ሰራዊት በተለያየ ቦታ እንዲበታተን በማድረግ ያለ አግባብ መስዋዕት እንዲከፍል ተደርጓል። መከላከያ ሰራዊቱን ለመበተን በተደረገው ጥረት ከጀርባው በመውጋት ከአንድ ዜጋ የማይጠበቅ ነገር ተደርጎበታል። በተደረገበት ደባ መከላከያ የበለጠ ጠንካራ ሆነ እንጂ አልተበተነም።
በማንኛውም ዜጋ ላይ አልተኩስም ብሎ የማይገባ ስምሪትን በመቃወም ከህዝብ ጋር የቆመ ሰራዊት ነው። ቀደም ብሎ ወጣቱ ጥያቄውን በማቅረቡ ኢ-ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ተበድሏል። መከላከያ ሰራዊቱ የፖለቲካ ፓርቲ ጠባቂ እንዲሆን ተደርጎም ነበር። የአገሪቱ ለውጥ በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ተገቢውን ተልዕኮ ህዝቡንና አገሪቱን በመጠበቅ እያሳየ ነው። በትግራይ ክልል ለሚገኙ ህዝቦች የፅሞና ጊዜ የተሰጠው መከላከያ ሰራዊቱ ከስነምግባሩ ውጪ ምንም አይነት እርምጃ ላለመውሰድ በመፈለጉ ነው። አንዳንዴ ሰራዊቱ ለህዝቡ ሲል ያልተገባ መስዋዕትነት ከፍሏል። ይህንንም ወጣቱ ልብ ሊል ይገባል። በማህበራዊ ሚዲያው የሚደረገው የሀሰት ዘመቻ ህዝብንም በተሳሳተ መንገድ የገዛ ወገኑ ላይ እንዲተኩስ ተደርጓል።
እረጅም ጊዜ በሀሰተኛ መንገድና በውሸት የተገነቡ አካላት አሁንም ከስራቸው ባለመታቀባቸው ይህንን በመታገል አገሪቱን መገንባት ያስፈልጋል። ህዝቡንም መታደግ የሚያስፈልግ ሲሆን በተሳሳተ መንገድ ወደ ጦርነት እንዳይገቡ መከላከያ ሰራዊቱ አልተኩስባችሁም ብሎ የወጣው የትግራይ እህትና ወንድም ለመታደግ ነው። የሽብርተኛ ቡድኑ ከህዝቡ ይነጠላል የሚል እምነት አለ። እውነት እያደር ስለሚገለጥ እውነቱን ለማየት እድሉን ስላገኙ ለመከላከያ ሰራዊቱ ክብር እየሰጡ ጠባቂያቸውን በቅርብ ደጀንም እንደሚሆኑት በቅርቡ ይታያል። ኢትዮጵያዊነት በዚህ ስሪት ላይ የመጣ ነገር ነው።
ሌላው የመከላከያ ሰራዊቱን ማጠናከር የሚገባ ሲሆን በሎጂስቲክስ፣ በገንዘብ፣ በሞራልና በሰው ሀይል ሊጠናከር ይገባል። መከላከያ ሰራዊቱ የአገሪቱ አርማ በመሆኑ ሉዓላዊነትና ሰላም የሚያሰፍን በመሆኑ በአሁን ሰዓት የተለያዩ ብሄራዊ ስጋቶች ስላሉ መጠናከር ይገባል። ወጣቱ በጋራ ሆኖ መከላከያ ሰራዊቱን ማጠናከር አለበት። ለዚህም የተጀመረውን እንቅስቃሴ መጠናከር አለበት።
ሌተናንት ጀነራል ባጫ ደበሌ በውይይቱ ወቅት መከላከያ ሰራዊቱ ከመቀሌ የወጣበትን ምክንያት አስረድተዋል። መከላከያ ሰራዊቱ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን እንዲያደርግና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ላይ የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን በጀግንነት መክቶ ሙሌቱ ስኬታማ እንዲሆን ተልዕኮ ተሰጥቶት ነበር። ይህን ግዳጅ በአግባቡ እየተወጣ ነው። መከላከያ ሀይሉ ከመቀሌ የወጣበት ምክንያት በጣም ግልፅ ነገር ነው። ወጣቱ በዚህ ጉዳይ ብዥታ ውስጥ መግባት እንደሌለበት ተናግረዋል። የመጀመሪያ ግዳጅ የነበረው ትጥቅ ወስዶ፣ የሰሜን እዝን አጥቅቶና የሚበትነውን በትኖ፣ መሳሪያ ወስዶና አገሪቱን ለመበተን በመሀል አገር ግጭት ሲያቀጣጥል ነበር። ሽብርተኛው ህወሃት የከፈተውን ጦርነት መመከትና በቁጥጥር ስር ለማዋልና የአገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ መከላከያ ሰራዊቱ ግዳጁን ለመፈፀም እንቅስቃሴ ተደርጓል።
ጠላትን ለመቆጣጠር ዋና ከተማዋን መቀሌ መያዝ አስፈላጊ በመሆኑ ወደዛ ሰራዊቱ እንዲጓዝ ተደርጓል። መቀሌ በቁጥጥር ስር ከገባች በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች የተበታተኑ የጦር መሳሪያዎችን እንዲሰበሰቡ ተደርጓል። በተደረጉ ተደጋጋሚ ውጊያዎች ጠላት ያሉትን ነገሮች እንዲያጣ ተደርጓል። መጀመሪያ መቀሌ መያዝ አለበት በተባለበት ወቅት ሽብርተኛ ቡድኑ ለአገሪቱ ስጋት ነበር። በሁሉም ክልሎች የራሱ የሆነ ተላላኪ በመፍጠሩ ስጋቶች አጭሮ ነበር። ነገር ግን ጠላት በተደረገበት የመመከት ስራ ያሉትን መሳሪያዎች እንዲያጣ መደረጉን ይናገራሉ። ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ወደ ሽምቅ ውጊያ ገብቷል። በአሁን ወቅት ለአገሪቱ ምንም አይነት ስጋት አይደለም። የኢትዮጵያ መንግስት የክልሉን ህዝብ መግቦ መኖር አይችልም። የክልሉ አርሷደር ወደ እርሻው እንዲገባ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ወስኗል።
የተናጠል የተኩስ አቁሙ ሲወሰን ትግራይ ውስጥ ተሁኖ ተኩስ አቆማለው ተብሎ እንቅስቃሴ ቢጀመር ለውጥ ስለማይመጣ ከመቀሌና ከክልሉ መከላከያ ሰራዊቱ እንዲወጣ ተደርጓል። ህዝቡ ከአገር መከላከያ ጋር የመዋጋት ባህሪ እንቅፋት ፈጥሯል። በየትኛውም አገር ህዝብ ከመከላከያ ሀይሉ ጋር አይዋጋም። ተደጋጋሚ ቦታዎች ላይ ህዝቡ ከአገር መከላከያ ሰራዊቱ ጋር እንዲጋጭ ተደርጎ ነበር። ከህዝብ ጋር ሲዋጉ ጥለው ስለሚሄዱ ሂወታችን ይተርፋል ብለው አሰቡ። ህዝቡም የቀረበለትን ጥሪ በመቀበል የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀም ጀመሩ። መንግስት ከህዝብ ጋር መዋጋት አላስፈላጊ መሆኑ በመታመኑ እንዲለቅ መደረጉን ያስታውሳሉ።
በውይይቱ ላይ የተገኙ ወጣቶች እንደተናገሩት፤ የአገር መከላከያ ሰራዊት ሽብርተኛውን የህወሀት ቡድን መደምሰሳቸው ኩራት ተሰምቷቸዋል። በዚህም የሽብርተኛው ህወሃት ቡድን አባላት በአገሪቱ ላይ ምንም አይነት ችግር መፍጠር አይችልም። በአገሪቱ ሰላም በማስፈን አርሷደሩ አርሶ የሚበላበትና ወጣቱ ሰርቶ የሚለወጥበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል። በማንኛውም የአገር የመከላከያ ሰራዊት የግዳጅ ጥሪ ለመሳተፍ ዝግጁ ናቸው። የአዲስ አበባ ወጣቶች ምርጫው ሰላማዊና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ በገቡት ቃል መሰረት ምርጫው በሰላም ተጠናቋል። የአዲስ አበባ ወጣት በማንኛውም ሁኔታ ከአገር መከላከያ ጎን የሚቆም ሲሆን የክተት አዋጅ ሲታወጅ ወጣቱ ለመሳተፍ ዝግጁ ነው።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013