ሀገሬ የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቤተኛ ሆናለች ። በ15 ቀናት ሁለት ጊዜ በተከሳሽ ሳጥን ቁማለች ። እውነቷን ሀቋንና ፍትኋን ለመከላከል። መጀመሪያ በትግራይ ወቅታዊ ጉዳይ፤ አሁን በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ። በቤልጅየም እስቶኒያ ፈረንሳይ ጀርመን አሜሪካ እንግሊዝና ኦቻ አነሳሽነት በትግራይ የሰብዓዊነት ጉዳይ ላይ መክሮ መግለጫ የማውጣት ቅዠት ምስጋና ለወዳጅ ሀገራት ይግባና የትግራይ ነገር የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንጂ የዓለም የሰላምና የደህንነት ስጋት አይደለም በሚል ውድቅ አድርገውታል ። ባለፈው ሀሙስ ደግሞ በዓረብ ሊግ ጥያቄ በቱኒዚያ የውሳኔ ሀሳብ አቅራቢነት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የግርጌ ተፋሰስ ሀገራትን ስለሚጎዳና በህልውናቸው ላይ አደጋ ስለደቀነ የዓለማቀፍ የሰላምና የደህንነት ስጋት ስለሆነ ኢትዮጵያ በስድስት ወራት ውስጥ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር የናይልን አጠቃቀም በተመለከተ አስገዳጅ ስምምነት ልታስር ይገባል ። ይህን ፍርደ ገምድል አጀንዳ ለማሳካት ግብፅና ሱዳን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው አማካኝነት ፤ ኢትዮጵያ በውሃ በመስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሯ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል ። አምስቱ የምክር ቤቱ ቋሚና 10ሩ ተለዋጭ አባላት የግድቡ ጉዳይ የሦስቱ ሀገራት ጉዳይ ስለሆነ በአፍሪካ ኅብረት የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ለሁለተኛ ጊዜ ወስነዋል ። ግብፅና ሱዳን ለሁለተኛ ጊዜ ተረትተዋል ። ሆኖም የሕዳሴ ግድብም ሆነ የትግራይ ጉዳይ ያለ ሰገባው በስፖንሰር ጸጥታው ምክር ቤት መድረሱ ከጀርባ ስውር አጀንዳ ስለመኖሩ ብናነፈንፍ አይፈረድብንም።
ለውጡ ከባተ ከመጋቢት 2010 ዓም ጀምሮ ህወሓት ይቺን ሀገር ወደለየለት ቀውስ ትርምስና የእርስበርስ ግጭት ለመዝፈቅ የሄደበትን እርቀት አይደለም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ለዚህ አሸባሪ ድርጅት ጥብቅና የቆሙት ዓለማቀፍ ሚዲያዎች የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች በአሜሪካ የሚመራው ምዕራባዊዋ እና ተቋማት ልቅም አርገው ያውቃሉ። ህወሓት የሀገሪቱን 80 በመቶ የያዘ ሠራዊትና የጦር መሣሪያ የታጠቀውን የሰሜን ዕዝን ማጥቃቱንና የጦር መሳሪያ ዘርፎች ወደ ሥልጣን የመመለስ ቅዠት እንደነበረው ከማወቅ አልፈው አንዳንዶቹ ደግሞ ሴራውን አብረው ዶልተዋል። ደግፈዋል። ሳምሬ የተባለው የህወሓት ገዳይ የወጣት ክንፍ /ኢትዮጵያዊ ኢንተርሀሙዬ/ከ1000 በላይ ንጹሐን አማራዎችን በደም ምድሯ ማይካድራ በግፍ ጨፍጭፎ በመላ ሀገሪቱ የሩዋንዳ አይነት የዘር ፍጅት ደግሶ እንደነበር እነዚሁ የአሸባሪው ጠበቃዎች ግጥም አርገው ያውቃሉ። አዲስ አበባ የተኮለኮሉ ኤምባሲዎቻቸው እና በየክልሎች የተበተኑ የ”እርዳታ”ድርጅቶቻቸው ሳይቀሩ መረጃዎችን ያደርሷቸዋል። በእነዚህ ድርጅቶች የሲአይኤ የኤምአይ 5/6 የሞሳድ ሰላዮች በረድኤት ድርጅት ሠራተኝነት እንደሚንቀሳቀሱ ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነውና ። አለማቀፉ ማህበረሰብና ምዕራባውያን ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ሀገር ድንበር ተሻጋሪ የሆነውን የዓባይ ወንዝ በፍትሐዊነት በምክንያታዊነትና የግርጌ ሀገራት ላይ ጉልህ ተፅዕኖ በማያደርስ መልኩ የመጠቀም መብት እንዳላት ጠንቅቀው ያውቃሉ ። ታዲያ የአሸባሪው ህወሓትን ሀሰተኛ የተዛባና የተበረዘ መረጃ እንዲሁም የሱዳንንና የግብፅን ጩኸት ለምን ማመንና ማስተጋባት ፈለጉ !? መልሱ ቀላል ነው። ለዴሞክራሲ ለሰብዓዊ መብት ለዓለም ሰላምና ደህንነት ወይም እሴቶቻችን የሚሏቸውን መርሆዎች ለማስከበር አይደለም። ስውር አጀንዳዎቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን ለማስፈጸም እንጂ ። ለዚህ ደግሞ ምንም ከማድረግ አይመለሱም።
እነዚህ ስውር አጀንዳዎቻቸውና ጥቅሞቻቸው ደግሞ በሦስት አእማድ የተዋቀሩ ናቸው ። በእስራኤል፣ በዓለማቀፍ ሽብርተኝነትና በቻይና ። እነዚህ አእማድ ደረጃው ቢለያይም በሀገራችን የውጭ ግንኙነት የዲፕሎማሲ የኢኮኖሚና የፓለቲካ መልክዓ ላይ ጥላቸውን ሲያጠሉ ታዝበናል ። አሜሪካ በተለይ ከ9/11 የአሜሪካ የሽብር ጥቃት በኋላ በሶማሊያ በኢትዮጵያ ውክልና ለምታካሂደው ዓለማቀፍ የጸረ ሽብር ዘመቻ ውለታ ስትል ህወሓት መሩ አገዛዝ የሰብዓዊ መብትን በገፍ ሲጥስ እያደረ ፓለቲካዊ ምህዳሩን እየጠረቀመ የለየለት ፈላጭ ቆራጭና ዘራፊ ሲሆን አይታ እንዳላየች በማለፍ ፓለቲካዊ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ከለላና ድጋፍ ትሰጠው ነበር ። ነጻ ተአማኒና ፍትሐዊ ላልነበሩ አምስት ተከታታይ መረጣዎች/selection/ ቀድማ እውቅና በመስጠት በመባረክ ለ27 ዓመታት ላየነው አበሳ ታሪክም ትውልድም ሲወቅሳት ይኖራል። ለነገሩ ህወሓት የትጥቅ ትግል ያደርግ የነበረው ከሶሻሊስቱ የደርግ አገዛዝ ጋር ስለነበር በወቅቱ በነበረው የሶሻሊዝምና የኢምፔሪያሊዝም የቀዝቃዛው ጦርነት ርዕዮተ ዓለማዊ አሰላለፍ ከአሜሪካና ከአጋሮቿ ያገኘው የነበረው ያልተቆጠበ ወታደራዊና ኢኮኖሚያው ድጋፍ ለአራት ኪሎው መንበር እንዳበቃው አይዘነጋም ።
ለ40 ዓመታት ያህል ሲካሄድ የኖረው የቀዝቃዛው ጦርነት አንጎቨር/hangover/ከ30 ዓመታት በፊት በአሜሪካ መር የካፒታሊዝም ጎራ አሸናፊነት ከተደመደመ በኋላም ዛሬም መልኩን ቀይሮ ቀጥሏል። ዛሬ በአሜሪካና በቻይና መሀከል እየተካሄደ ባለ ቀዝቃዛው ጦርነት አከል ፉክክር ከቻይና ጋር የቆመ የሰራና ጥብቅ ግንኙነት የፈጠረ ሁሉ”ከእኛ ጋር ካልሆናችሁ፤ ከጠላቶቻችን ጋር ናችሁ ።”በሚል የአሜሪካ ገዳዳ የውጭ ግንኙነት ፓሊሲ የተነሳ አፍሪካ በተለይ ሀገራችን ጥርስ ውስጥ ከገባች ሰነባበተች ። ሰሞኑን እየመጣብን ያለው የጫና ናዳ እየወረደ ያለው ከዚህ የቀዝቃዛው ጦርነት ተራራ ነው ።
ሌላው የግብፅ ጦስ ነው ። እስራኤል እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር በ1948 ዓም እንደ ሀገር ከመቆሟ በፊት ግብፅ ከፒራሚዶቿ ከባህር ዳርቻዎቿ ከቅሪተ አካል የምርምር እና ከእስልምና የትምህርትና የስነ ጽሑፍ ማዕከልነቷ ውጭ በዓለማቀፉ ፓለቲካ ያን ያህል ባለከባድ ሚዛን አልነበረችም ። እስራኤል እንደ ሀገር ከቆመች በኋላ ግን መጀመሪያ በጸረ እስራኤል የተቃውሞ ማዕከልነት ፤ በኋላም በተናጠልና ከዓረብ ሀገራት ጋር ጦርነት በማካሄድ የእስራኤል የህልውና ስጋት መሆኗ ለየላት ። ሆኖም ከአንዴም ሁለቴ አሳፋሪ ሽንፈት በመከናነቧ ከነበራት ጅኦፓለቲካዊ ስፍራ ተንሸራታለች ። በጋማል አብድል ናስር እግር የተተካው አንዋር ሳዳት እኤአ በ1979 ዓም ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈራረመና በእስራኤል ፓርላማ/ከነሴት/ተገኝቶ ንግግር ማድረጉ በዜጋውና በዓረብ ሀገራት በከሀዲነት በመታየቱ ብዙ ሳይቆይ በመገደሉ ሆስኒቭ ሙባረክ ተተክቶ የሳዳትን ፖሊሲ አስቀጥሏል። ከዛን ጊዜ አንስቶ እስራኤልና እንደ አሜሪካ ያሉ አጋሮቿ ባለዕዳና ባለውለታ በመሆን ዛሬ ድረስ የግብፅ ወታደራዊ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ መከታ ሆነው ቀጥለዋል። ግብፅ በምላሹ ሀማስ ፋታህና ፒልኦ ከገደባቸው እንዳያልፉ ፤ ዓረብ ሀገራትን ጨምሮ ዓረብ ሊግ ከመሬት እየተነሱ ጠባጫሪ እንዳይሆኑ ታቅባለች ። አሜሪካ ምዕራባውያንና ዓለማቀፍ ተቋማት አንድ ጊዜ የትግራይን ሌላ ጊዜ የናይልን ነገር እያነሱ ሀገራችንን ቁም ስቅሏን የሚያሳዩን የግብፅን ውለታ ለማወራረድ መሆኑን ልብ ይሏል። የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትና የአውሮፓ ሕብረት ሳንወድ ቤተኛ የሆነው ለዚህ ነው።
ባለፈው ሀሙስ ለዓርብ አጥቢያ በምክር ቤቱ በገዛ የተፈጥሮ ሀብቷ ተከሳ በፍርድ አደባባይ የቆመችው ፤ አሜሪካ ሽንጧን ገትራ ስለ አሸባሪው ህወሓት የምትንገበገበው ፤ ከሳውዲ 40ሺህ እህትና ወንድሞቻችን የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ሳይቀር እየተንገላቱና እየተዳፉ በባዶ እግራቸው እርቃናቸውን እየወጡ ያሉት የግብፅን ውለታ ለመመለስ ሲባል ኢትዮጵያን እንደ ጎን ውጋት ቀስፎ የመያዝ የታላቁ ሴራ ፕሮጀክት አካል ነው። ሆኖም ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ እርዳታ የሕዳሴዋን ሁለተኛ የዝናብ ውሃ መያዝ/pooling/ እያካሄደች፤ አሸባሪውን ህወሓት አከርካሪውን ሰብራ እያሽመደመደች ፤ በአንጻራዊነት ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫዋን በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ ችላለች። የተደገሰላት ሴራ ሁሉ አንድ በአንድ እየከሸፈ ነው። ኢትዮጵያ በአጋሮቿና እንደ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሯ ኢንጅነር ስለሽ በቀለ (ፒኤችዲ) ባሉ የቁርጥ ቀን ልጆቿ በዓለም ፊት ሌላ ተጨማሪ ግዳይ ጥላለች ። ሀገራችን ገና ከጅምሩ በምክር ቤቱ በውሃ መሐንዲሱ ሚኒስትሯ ብቻ እንድትወከል ማድረጓ የዓባይ ውሃ ግብጽና ሱዳን እንደሚለፍፉት የዓለም የደህንነትና የሰላም ስጋት ሳይሆን በማንኛውም ሀገር እንደሚካሔድ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ መሆኑን በገደምዳሜ መልዕክት እንድታስተላልፍ አስችሏታል። ግብጽና ሱዳን ግን ገና ከጅምሩ ነገሩን የማጦዝና አግዝፎ የማሳየት ግብ ስለነበራቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው ከመወከላቸው በላይ ቀድመው ከእነ ልኡካቸው በኒውዮርክ በመገኘት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አድርገዋል ። 17 ደቂቃ ከወሰደው የሚኒስትሩ አስደማሚ ታሪካዊ ንግግር “አዲስ ዘመን”ወደ አማርኛ ከመለሰው ቀንጨብ አድርጌ ላስታውስ ።
“በዚህ ስብሰባ ግድባችን ባልተለመደ መልኩ የስሞታ መንስኤ ሆኗል። በዚህም የተነሳ በዚህ ምክር ቤት ላይ ተገኝቼ ንግግር ያሰማሁ የመጀመሪያው የውሀ ሚኒስቴር እኔ ሳልሆን አልቀርም። ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ለጸጥታው ምክር ቤት ውይይት መቅረቡ የምክር ቤቱን ሰዓት ማባከን እንደሆነ ታምናለች። ቢሆንም ለዚህ የተከበረ ምክር ቤት የአገሬን ኢትዮጵያ እውነተኛ እና አሳማኝ ነጥቦች ለማቅረብ መቻሌ ክብር እንደሆነ አምናለሁ ። ከዓመት በፊት በጁን 29/2020 እ.ኤ.አ በዚሁ ምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ ፤ ግብጽ እና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የጀመሩትን ምክክር አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ለዚህም የጸጥታው ምክር ቤት ለሕብረቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር። ስለዚህም ኢትዮጵያ በድርድሮቹ ተቀባይነት ያለው ውጤት እንዲገኝ በአዲስ መንፈስ እና በቀናነት በድርድሮቹ ላይ ስትሳተፍ ቆይታለች ። …አሁን እየሰራን ያለነው ግድብ በአፍሪካም ሆነ በዓለም በአይነቱ የመጀመሪያው አይደለም። እየገነባን ያለው ተርባይኖችን በውሀ በመምታት ኃይል ማመንጨት የሚችል የውሀ ግድብ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከግብጹ የአስዋን ግድብ ከ2 ከግማሽ እጥፍ በታች ያነሰ ነው ። ምናልባትም ታላቁ የህዳሴ ግድብ በልዩ ሁኔታ እንዲታይ ያደረገው 65 ሚሊዮን በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጣሉበት ተስፋ ነው ። ሌላኛው ልዩ የሚያደርገው ነገር ደግሞ ይህ በ5 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የሚሰራው ግድብ በኢትዮጵያውያን እንባ ላብ እና ደም የተገነባ መሆኑ ነው።…
ግድቡ በትክክለኛው ሰዓት በትክክለኛው ቦታ የተገነባ ለቀጠናው ተስፋ የሚሰጥ ፕሮጀክት ነው ። የዓባይ ወንዝን መጠቀም አለመቻላችን በሕዝባችን ሥነልቡና ውስጥ ትልቅ ቅሬታ ፈጥሯል።…”
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር ! ! !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013