ባለፈው መንግሥት ሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ውሳኔ ከመወሰኑና ሠራዊቱን ከማስወጣቱ ጋር በተያያዘ ያሉ ጉዳዮችን መግለጻችን ይታወቃል:: በዛሬው ዕለትም ያንኑ ታሳቢ በማድረግ በሀገር ውስጥም በዓለምአቀፍ ሁኔታውም ላይ የሚስተዋሉ አጠቃላይ አዝማሚያዎችን ታሳቢ ያደረገ የፌዴራል መንግሥቱን ምልከታ እና አቋም በተመለከተ አጭር ማብራሪያ ለመስጠት ነው::
እንደሚታወቀው ባለፉት 8 ወራት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ግጭት እና በዚሁ ሳቢያ መንግሥት ተገዶ በገባበት የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ በዜጎች ህይወት ንበረት እና የሀገር ገጽታ ያስከተለው ጉዳት ግዙፍ እንደሆነ ይታወቃል:: መንግሥት ተጨማሪ ኪሳራ፣ የህዝብ ጉዳት እና እልቂት ለማስቀረት ሲባል መሰረቱን ሰብዓዊነት ላያ ያደረገ ነገር ግን ሌሎችን ማህበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የሀገር ሉአላዊነት ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን ግምት ውስጥ ያስገቡና ተያያዥነት ያላቸውን ምክንያቶችን ታሳቢ ያደረገ የተናጠል የተኩስ አቁም መወሰኑና ማወጁ ይታወቃል:: ይህንኑ ተከትሎ ሠራዊቱን ከግጨቱ አካባቢ እንዳስወጣም ግልጽ ነው::
ይህ ዕርምጃ ደግሞ ለበርካቶች መልስ የሰጠ ነበር:: ይሄም በአንድ በኩል አታጅቡን፤ አትከተሉን፤ እኛው በተመቸን መንገድ ተንቀሳቅሰን ለብቻችን ሆነን ዕርዳታችንን ማድረስ አለብን የሚል ውትወታ ሲያካሂዱ ለነበሩ አካላት ምላሽ የሰጠ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር በተያያም የፍተሻ ኬላዎች ይነሱልን፤ በፍተሻ የሚስተጓጎል ሰዓት አይኑር፤ ምን እንደያዝንም ማንን እንደጫንም ለማወቅ አትሞክሩ፤ ነፃ አድርጋችሁ ልቀቁን የሚል በርካታ ግፊቶች ያካሂዱ ለነበሩ አካላትም ምላሽ የሚሆን ነበር::
በተመሳሳይ ግጭቱን ጋብ በማድረግ የተኩስ አቁም ወስኑና ዕርዳታ በቀላሉ መድረስ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠር፤ አርሶ አደሩም ይረስ ሲሉ ለነበሩ አካላት፤ እንዲሁም አዝመራው እና የእርሻው ጊዜ ካለፈ ረሀብን እንደመሳሪያ ተጠቅማችኋል ብለን እንከሳችኋለን እና አዝመራው ሳያልፍ የእርሻ ጊዜው ሳይስተጓጎል ተኩስ አቁማችሁ አርሶ አደሩ ማረስ የሚችልበት ዕድል መፈጠር አለበት የሚል ውትወታ ሲያካሂዱ ለነበሩ አካላትም መሰል መልስ የሰጠ ነበር::
በዚህ ረገድ መንግሥት የወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ፣ እነዚህ አካላት ምክንያታችው፣ ዋናው መሻታቸው፣ ዋናው ፍላጎታቸው ምንም ይሁን ምን እንዚህን ጉዳዮችን በዓለም አደባባይ በተናጠልም በጋራም ሲያስተጋቡ ለነበሩ አካላት ምላሽ የሚሆን ነበር ተብሎ ይታሰባል:: በእርግጥም ለህዝቡ እና ለኢትዮጵያ ደህንነት እና መረጋጋት ተጨንቀው ለነበሩ አካላት ደግሞ እፎይታ የሚሰጥ የሚያስፈግግ አዎንታዊ ውሳኔ ነበር ተብሎ ይታሰባል::
ውሳኔውን ተከትሎም እንደመንግሥት ያታዘብናቸው ጉዳዮች እና አዝማሚያዎች አሉ:: በዚህም የምናቃቸውንም፣ የራሳቸውንም አፍራሽ ዝንባሌዎች፤ የምንጠረጥራቸውንም በግል የምናውቃቸው የነበሩም አፍራሽ ዝንባሌዎችን ስፋት እና ተያያዥነት፤ እንዲሁም ቀጣይነት መንግሥት ለማረጋገጥ የቻለባቸውን አዝማሚያዎችን ታዝቧል:: እነዚህን ትዝብቶችም አጠር ባለ መልኩ ማስቀመጥ ይቻላል::
አንደኛው፣ የመንግሥትን ውሳኔ ተከትሎ መሳሪውን አዘቅዝቆ እና ጭኖ ከግጨት ቀጠና እየወጣ የነበረውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመከተል ግጭቱ እንዳይቆም ይደርስ የነበረውን ትንኮሳያወገዘ አካል ብዙ አልነበረም:: ዋናው ውትወታ ግጭት አቁም፣ ተኩስ አቁሙ፣ ሰላም ለመፍጠር ሞክሩ፣ ህዝቡ ፋታ ማግኘት አለበት፤ ዕርዳታ ማድረስ ነበረብን ይል ለነበረ አካል እውነተኛ ፍላጎቱ ይሄ ነበረ ወይ? የሚለው ነው::
ምክንያቱም ፍላጎቱ ይህ ከነበረ መንግሥት ይሄንኑ ተቀብሎ በራሱ ውስጣዊ ምክንያቶችም፣ በራሱ ሰብዓዊ ምክንያቶችም፣ በራሱ ሀገራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችም ቢወስነው፤ በሌላም በማንኛውም ምክንያት ተንተርሶ ቢወስነው፣ ውሳኔው ግን የእነዚህን አካላትን ተከታታይ ጥያቄ ይመልስ የነበረ መሆኑ ነው:: እናም ይህን ውሳኔ የሚያስተጓጉል ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ከሌላ አካል ሲፈጸም ማስቆም መውቀስ መኮነን እና ማጋለጥ ይጠበቅ ነበር ተብሎ ይታሰባል:: በዚህ ረገድ ያየነው ተነሳሽነት አናሳ ነው::
ሁለተኛው፣ የተወሰኑ አካላት ውሳኔውን ገና እንደተወሰነ ለማጣጣል፣ ለማሳነስ እና ለማንኳሰስ ሲሽቀዳደሙ ታይተዋል:: የምዕራባውያን ሚዲያዎችም ይሁን አንዳንድ የምዕራቡ ሀገር ባለስልጣናት በተናጠል ያሳዩአቸው ዝንባሌዎች አዎንታዊ ውሳኔውን ተከትሎ አዎንታዊ ድጋፍ ለማድረግ ሳይሆን፤ ብዙዎች ሲንቀሳቀሱለትና ሲጠይቁን የነበረውን ውሳኔ መንግሥት ወስኖ ሳለ፤ ይሄን ከማድነቅ እና የጎደለውን ከመሙላትና ከማድነቅ ይልቅ ለዚህ አፍራሽ እና አሉታዊ ምክንቶችን በመደርድር የውሳኔውን አነስተኛነት ለማጉላት ተንቀሳቅሰዋል::
ሦስተኛው፣ በጦር ወንጀል ዓለም የፈረጃቸውን ሕፃናትን ለጦርነት የመመልመል እና የማሰለፍ እንቅስቃሴ በግላጭ በሌላኛው ወገን እየተደረገ፣ በኢግዚቢትነትም እየታየ ዓለምአቀፍ ሚዲያውም ሆነ አንዳንድ አካላት መንግሥትን በተለያየ መንገድ ሲወቅሱ ሲከሱ የነበሩ አካላት ሁሉም ሰው ሊያወግዘውና ስህተት ነው ሊለው የሚገባው ጉዳይ ተፈጽሞ እያለ ባላየ ባልሰማ የማለፍ ዝንባሌዎች ታይተዋል::
አንዳንድ የምእራቡ ሚዲያዎች ይህንኑ ዓይተው እንደ ወታደራዊ ሚዛን ማስተካከያነት እየተጠቀሙበት መሆኑን በማጉላት በአዎንታዊ መልክ ለመዘገብ ያሳዩት ዝንባሌም ጎላ ያለ ትዝብት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው::
ህወሓት አሁንም ግጭቱን በአፋርም በአማራም በኩል ለማንቀሳቀስና ለማስፋት የሚያሰደርገው እንቅስቃሴም፤ መንግሥት ከወጣ በኋላ በአካባቢው ላይ የሚደረጉ አሉታዊ እንቅስቃሴዎችንም ለማወቅም ለማጋለጥም ለመኮነንም የሚደረገው ሙከራ አነስተኛ ሆኖ ታይቷል::
መንግሥት ተኩስ አቁሞ አካባቢውን ለቅቆ የወጣው ለህዝቡ ዕረፍት ለሰላሙም ዕድል ለመስጠት እንጂ የግጭቱን ቀጠናና ስፍራ ለመቀየር አልነበረም:: ይህ ኡደት በግላጭ እየታየ ባለበት ሁኔታ፤ ሁላችንም ስንጠይቀውና ስንወተውትለት የነበረውን የተኩስ ማቆምና ለህዝቡ እፎይታ የመስጠት፤ ዕርዳታ ለመስጠት የያስችል መደላድል የመፍጠርን አስፈላጊነት ይጎዳልና መቆም አለበት ብሎ የሚኮንን አካል ብዙ አለመሆኑ፤ በእርግጥም የግጭቱ መቆም ይፈለጋል ወይ? የሚል ጥያቄ መንግሥት እንዲያነሳ አስገድዶታል::
አምስተኛው፣ በተለይም የአብዓዊ ዕርዳታ እናቀርባለን ወይም እናስተባብራለን የሚሉ አንዳንድ አካላት ቀድም ሲል ሲወተውቱላቸው የነበሩ ጥያቄዎቻቸው በሙሉ ተመልሰው እያለም አሁንም መንግሥት በአካባቢው በነበረበትና ግጭት ይካሂድ በነበረበት ወቅት ያሰሟቸው የነበሩ ስሞታዎችን፣ ክሶችንና ወቀሳዎችን ያለምንም መስተጓጎል አጠናክረው የቀጠሉበት ሁኔታ ይታያል:: ይህም በእርግጥም መጀመሪያም መሰናክል ስለነበረ ነው ወይ ያ ሁሉ ስሞታ ይቀርብ የነበረው የሚል ጥያቄ እንዲያነሳ መንግሥት አስገድዶታል::
ስድስተኛው፣ መንግሥት በስፍራው በነበረበት ወቅት የሚስተጋባው ክስ መቀጠሉ አብዛኛዎቹን ችግሮች ፈትቶም እያለ፤ በረራም ተፈቅዶ እያለ በረራ ታግዷል ማለት፤ በተለይ በአፋር እና በአማራ በትግራይ ደቡባዊ ክፍል አካባቢ ላይ እህል ማስገባትና ዕርዳታ ማስገባት የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ፤ የጋራ ኮሚቴም ተዋቅሮ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ አካላትና መንግሥት የተቀናጀ ሥራ እየተሠራ ባለበት ሁኔታ፤ አንዳንዶች ብራስልስም ኒውዮርክም ጄኔቫም ተቀምጠው አሁንም ያንኑ ክስና ስሞታ ለማስተጋባት ያላቸው ፍላጎት እና ተነሳሽነት ሲታይ፤ መሰረታዊው ፍላጎቱ ዕርዳታ የማቅረብ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ለማንሳት የሚጋብዝ ነው::
ሰባተኛው፣ አንዳንድ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ባለስልጣኖች እንዲሁም አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ግለሰብ ባለስልጣኖች ጉዳዩ የግላቸው እስኪመስል ድረስ ለአንድ ወገን ያደላ አቋምና አመለካከት በቋሚነት በማስተጋባት ኢትዮጵያን የማዋከብና የማጨናነቅ አቋማቸውን አጠናክረው የቀጠሉበት ሁኔታ እጅግ አስተዛዛቢ ሆኖ ቀጥሏል::
ሰሞኑን ጄኒቫ ላይ የተካሄደው ተቀናጀ ማእቀብ ለመጣል ቅድመ ሁኔታ የሚሆን ለጊዜው በአንዳንድ አካላት አሁንም ፍንጭ እየታየበት ያለው፤ ነገር ግን የጋራ ምርመራን በተመለከተ በአካባቢው ላይ ግጭት ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በማንም ይፈጸም በዜጎች ላይ ደረሱ የሚባሉ ጉዳቶችን የማጣራት ጉዳይን መንግሥት አንድም፣ ለአፍሪካ የአብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ ሁለትም ለተባበሩት መንግሥታት አብዓዊ መብት ኮሚሽን ግብዣ በማቅረብ በተለይም ከተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በጋራ ምርመራ አካሂዶ ሰው መድቦ ምርመራውም አንድ መልክ ይዞ እየተካሄደ ባለበት የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ጥያቄ ባላቀረበበት፤ መንግሥት አልተባበረኝም የሚል ስሞታ በሌለበት፤ ከባድ ድራማ በመሥራት፤ አንዳንድ ሀገሮችንም በማስፈራራት አንዳንዶቹንም በማባበል የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ በኢትዮጵያ ላይ የአቋም መግለጫ እንዲወጣ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተደርጓል::
በዚህ እንቅስቃሴም መንግሥት የወሰዳቸውን አዎንታዊ እውነታዎችን በሙሉ በመካድ ነገር ግጭቱ በነበረበት ወቅት የነበረውን መንግሥትን የማካለብ ሁኔታ አጠናክሮ የመቀጠል ሁኔታ ታይቷል:: ሆኖም በርካታ ሀገሮች ጉዳዮችን ስላላመኑበት፣ ይሄ ነገር በተያዘው መንገድ ቢቀጥል የተለየ ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም የሚል አቋም ወስደዋል:: ለዚህም መንግሥት እጅግ አድርጎ ያመሰግናል::
አንዳንዶችም በጉዳዩ ባያምኑበትም ከኢትዮጵያ ጋራ ቆመው ትክክለኛ አቋም ለመወሰን በመቸገራቸው ድምፅ ባለመስጠት የተወሰኑ ሀገሮች መኖራቸው ይታወቃል:: እነዚህም ቢያንስ እውነታውን በመገንዘባቸው ልናመሰግን እንወዳለን::
በአንጻሩ አንዳንድ ሀገሮች እና አንዳንድ አውሮፓ ህብረት ግለሰቦች በከፍተኛ ሁኔታ የ24 ሰዓት ሥራቸው አድርገው በኢትዮጵያ ላይ ይሄን ዘመቻ ለማስኬድ የሞከሩበት መንገድ አፍራሽ ነው፤ ገምቢ አይደለም፤ ወዳጅነትን አያመለክትም የሚል አቋም አለን:: ይሄንንም መንግሥት በአጽንኦት ለመግለጽ ይወዳል::
ስምንተኛው፣ አንዳንድ የአብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪዎች በሌሎች ሀገሮች እንደተለመደው እና በሀገራችንም ከዚህ በፊት ታይቶ እንደሚታወቀው በዕርዳታ እህል እና ከዕርዳታ አቅርቦታ ጋር በማያያዝ ሌላኛውን ወገን የማስታጠቅ፤ በዚህም ምክንያት እንቅስቃሴው እንዳይቆም እና ቀውሱ እንዳይበርድ ለማስደረግ የሚያስችል ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል:: ይሄው በሀገራችን ከዚህ በፊት ተፈጽሞ እንደሚታወቅ፤ በዚህ ግጭትም ባለፉት ስምንት ወራትም አጋጥሞ እንደሚያውቅ፤ ስለዚህም መልክ መያዝ እንዳለበት መንግሥት ሲያሳስብ ቆይቷል::
አንዳንድ አካላትም በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ ዕርዳታ እናስተባብራለን የሚሉ አንዳንድ ወገኖች በተናጠል እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጠው እንዲያስተባበሩ ከተመደቡት ሰዎቻቸው ውጪ ከርቀት ላይ ሆነው ከዕርዳታ ይልቅ ፕሮፖጋንዳ የማስተባበር የኢትዮጵያን መንግሥት የማካለብና የማጠልሸት ዘመቻ በስፋት ከፍተው ይገኛሉ::
ይሄንንም መንግሥት ለማስጠንቀቅ ሞክሯል:: ጉዳዩ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ሀገር የማዳን ኃላፊነቱን ስለሚወጣ ከአንዳንዶቹ ጋር አብሮ መሥራት ሁኔታውን እንደገና እንደሚቃኘው አንዳንዶቹንም ከሀገር ለማስወጣት የሚገደድበት ምቹ ሁኔታም እየተፈጠረ ነው:: በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ማንኛውም ኢትዮጵያን እረዳለሁ፤ ዕርዳታ አቀርባለሁ የሚል ሰው ዕላይ የመታጠር፤ ሰብዓዊነት ላይ ታጥሮ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባው ለማሳሰብ ይወዳል::
በድምሩ ሲታይ ሀገራችን በታሪኳ ካጋጠሟት መሰረታዊ የሆኑ ፈተናዎች በአሁኑ ወቅት የምታልፍበት ሁኔታ አንደኛው እና ከጥቂቶቹ ዋነኛው ተብሎ ሊወሰድ እንደሚችል ይገመታል:: ግድባችንን አስታኮ፤ ድንበራችንን አስታኮ፤ ፖሊሲዎቻችንን አሳብቦ፤ ባለንበት መልክአምድራዊ አካባቢ የተነሳ ያለንን ተፋለጊነት ግምት ውስጥ አስገብቶ፤ ያለንንም እምቅ አቅም ታሳቢ አድርጎ፤ በህዝባችን ውስጥ ያለውን አለመግባባትና ያለውን ዝቅተኛ ሀገራዊ መግባባትን ታሳቢ ያደረገ፤ በዚህም አንዳንድ ጥቃቅን ልዩነቶችን በማጉላት የሌሉትንም በመፍጠር አንድ ሆነን እንዳንቆምና ተበትነን እንድንቀር፤ ሸብረክም እንደንል የሚደረገው ወከባ ተጠናክሮ ቀጥሏል::
በእርግጥ ይህም ቢባል በርካታ ወዳጆችም አሉን:: ወዳጆቻችን እሚደርስብንን ዘመቻ አውቀው እንዲመክቱልን እና እንዲያግዙን፤ ሌሎችም ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በጽናት ተቋቁማ እንዳለፈች ሁሉ ይሄን ጊዜም እንደምታልፈው በማወቅ ራሳቸውን ከእውነት ጋር እንዲያስታርቁ ጥሪ እናቀርባለን::
መላው የኢትዮጵያ ህዝብም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ እንዳለፈው ሁሉ በግድባችንም በምርቻችንም ያሳየነውን ዓይነት ጠንካራ ተሳትፎና ተያያዥነትን ይዘን መዝለቅ አለብን የሚል ጥሪውን ያስተላልፋል::
ችግራችን በጣም ብዙ፤ ወቃሾቻችን በጣም በርካታ፤ ሴራውና ሽረባውም በጣም የተሰናሰለ በመሆኑ ምክንያት፤ ይህን ወቅት የምናልፈው በመደማመጥ፣ በመቻቻል፣ በመተጋገዝ በመስከን ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው::
በእያንዳንዳችን ሰፈር ብቻ ያሉ ጉዳዮችን በማጎን አብረን ለመሄድ የሚያስችለውን ዕድል እንዳንዘጋ ሁላችንም ከፌዴራል መንግሥቱ ከሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ጋር በመሆን ለአጠቃላይ ለህዝባችን ሰላም ለአጠቃላይ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚሆነውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ሁላችንም ሚጠበቅብንን ድርሻ መወጣት እንዳለብን መንግሥት ያሳስባል::
በዚህ ረገድ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ኢትዮጵያ መታገዝ ትፈልጋለች፣ ማደግ ትፈልጋለች፤ ድህነት አለባት፣ ድህነቷን ለመሻገርም ሰላሟን ለማጠንከርም የሚደረገው ድጋፍ መጠንከር መቻል አለበት:: በዚህ ረገድ ግን መንግሥት የወሰነው ውሳኔ በተለይም ሰብዓዊነትን ተላብሶ ወታደሩን በማስወጣት፣ ተኩስ በማቆም ህዝቡ ዕረፍት እንዲያገኝ ለሰላምም ዕድል እንዲገኝ በማድረግ ተኩስ አቁሞ ሠራዊቱን ማስወጣቱ ከወታደራዊ እይታ አንጻር ዋጋ እንደሚያስከፍለውም እያስከፈለው እንዳለም ይታወቃል::
ይሄ ለሰላም የሚከፈል ዋጋ ስለሆነ መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔ ወስኖ ዋጋ ከፍሏል:: አሁን ያለውን ሁኔታም በትዕግስት ለማለፍ እየሞከረ ነው:: በሌላኛው ወገን የሚደረገው ትንኮሳ በዚሁ ከቀጠለ ግን መንግሥት ያሳለፈውን ውሳኔ እንደገና ለማጤን፤ በዚህም ምክንያት ሁሉን አቀፍ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚገደድበት ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል:: እውነትም ለሰላም የሚተጋ ፤ በእርግጥም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲፈጠር የሚያስብ፣ በእርግጥም የሰብዓዊ ቀውስ እንዳይፈጠር የሚሰጋ፣ በእርግጥም ኢትዮጵያ ስትቸገር እኛም እንቸገራለን ብሎ የሚያስብ የዓለም ማህበረሰብ አካል፤ በሌላኛው ወገን የሚደረገውን ትንኮሳ እንዲኮንን፣ እንዲያጋልጥና እንዲያስቆም መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል::
ይሄ በዚሁ ከቀጠለ ግን በየትኛውም ሰበብ በየትኛውም ምክንያት ሀገራችን እንድተፈርስ የሚል መንግሥት ስለማይኖር፤ በዚህ ምርጫም የኢትዮጵያ ህዝብ የወሰነው ውሳኔ ይህንኑ ስለሚያረጋግጥ፤ መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል:: በዚህም ምክንያት መላው ህዝባችን ለሰላም አጥብቆ ይቁም ፤ መላው የዓለም ማህበረሰብም ኢትዮጵያ ያለችበትን መሰረታዉ ውሳኔ እና የኢትዮጵያን ህዝብም መሰረታዊ ፍላጎት ተገንዝቦ ከጎናችን እንዲቆም፤ ክፋትንና ሽብርተኝነትን እንዲያወግዝ፤ በዚህ ረገድ መንግሥት ለሰላም የዘረጋው እጅ እንዳይታጠፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ያቀርባል::
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2013