አቶ ኢሳያስ ዳኘው ከ 44 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሚሆን ከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሰረተባቸው።
ተከሣሽ በኢትዮ ቴሌኮም የኤን ጂ ፒ ኦ ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩ የተጣለባቸውን ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ወደጎን በመተው በተሰጣቸው የሥራ ሥልጣን መሠረት ዜድ ቲ ኢ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር የ44 ሚሊየን 510 ሺህ 971 የአሜሪካ ዶላር የግዥ ውል ለጊዜው ካልተያዘ ግብረአበራቸው ጋር ቀጥታ ግዥ እንዲፈጸም አድርገዋል ተብሏል።
በዚህም በስውር ጥቅም በመመሳጠር በመንግሥትና በኮርፖሬሽኑ የተሰጣቸውን ሹመት፣ ሥልጣን በግልጽ ተግባር ወይም በግድፈት ያለአግባብ በመገልገል እንዲሁም ከተሰጣቸው ሥልጣን በላይ አልፎ በመስራት ለራሳቸውና ለዜድ ቲ ኢ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት እንዲሁም በመንግሥትና በኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬሽን ጥቅም ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው ተጠቅሷል።
አቅራቢው ኩባንያም ካቀረባቸው ቴክኒካል ሰነዶች ሊገዛ የታሰበውን ዕቃ ወይም አገልግሎት በተጠየቀው ቴክኒካል ዝርዝር መሠረት በግልጽና በተሟል መልኩ ለማቅረብ ወይም ለመሸጥ መስማማቱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ፥ የዕቃውን ወይም የአገልግሎቱን የማቅረቢያ ጊዜ፣ የቅድመ ክፍያ ዋስትና፣ የአከፋፈል ሁኔታ፣ የመልካም ሥራ አፈጻፀም ዋስትና በገምጋሚ ኮሚቴ ባልተገመገመበት ሁኔታ ተከሣሽ ግዥ እንዲፈጸም ፈቅደዋልም ነው የተባለው።
በተጨማሪም ለዩኒቨርሲቲዎች የኔትዎርክ ግንባታ የአገልግሎት ግዥ ውል ኤን ጂ ፒ ኦ ሊጠቀምበት ይገባ የነበረውን የግዥ ማንዋል እንዳልተጠቀሙም ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈም በኢትዮ ቴሌኮም የግዥ መመሪያ፣ ፖሊሲና የሥነ-ሥርዓት ማንዋል እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው የግዥ ሕጎች መሠረት በግልጽ ጨረታ በማወዳደር ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ተወዳዳሪዎች በመጋበዝ መግዛት ሲገባቸው፥ የግዥ ሥራን በማያመች አኳኋን በመምራትና በማስፈፀም በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆናቸው በመላ ሃሳባቸውና በወንጀል ድርጊቱና በውጤቱ በሙሉ ተካፋይ በመሆን በዋና ወንጀል አድራጊነት የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
በሌላ በኩል መርማሪ ፖሊስ ከዚህ ቀደም አቶ ኢሳያስ ዳኘው ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ያለውድድርና ጨረታ ኢ ዲ ኤም የተባለ የውጭ አማካሪ ድርጅት ጋር ውል በመፈጸም መጠርጠራቸውን ገልጿል።
በዚህም አዲስ የምርመራ መዝገብ ከፍቶ ክርክር ያደረገ ቢሆንም በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በ50 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ተፈቅዶላቸው የነበረ ሲሆን፥ መርማሪ ፖሊስም ግለሰቡ በዋስ መውጣት የለባቸውም በሚል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጅ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ጠዋት በዋለው ችሎት ከዚህ ቀደም በተወሰነው መሰረት ከሃገር እንዳይወጡ በተጣለ እገዳ በ50 ሺህ ዋስ እንዲለቀቁ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔውን አጽንቷል።
ዛሬ ከሰዓት ዐቃቤ ህግ በተከሳሹ ላይ ባቀረበው ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሳሹ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሳቸው ተነቦ እንዲረዱት የተደረገ ሲሆን፥ የክስ መቃወሚያቸውን ይዘው ለመቅረብ ለየካቲት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በዚህም መሰረት አቶ ኢሳያስ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ እንደሚቆዩ ከፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።