ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እየተሰሩ ካሉ አበይት ሀገራዊ ስራዎች መካከል የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ይገኝበታል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም ማህበረሰብ ባሳተፈ መልኩ በየዓመቱ የክረምት ወቅትን ታሳቢ በማድረግ የሚተከሉ ችግኞች ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ ‹ኢትዮጵያን እናልብሳት› በሚል የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ሁሉን አቀፍ በሆነ እንቅስቃሴ ተጀምሮ በመተግበር ላይ ይገኛል።ኢትዮጵያን እናልብሳት በሚል መርሀ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ በያዝነው የክረምት ወር የሚተከል ስድስት ቢሊዮን የሚደርስ ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ጨምሮ በሁሉም የክልል ከተሞች እስከ ወረዳ ድረስ በሚደርስ የተቀናጀ ስራ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ፊታውራሪነት ኢትዮጵያን በአረንጓዴ የመሸፈን ተግባር በሁሉም የሀገራችን ክፍል ተጀምሯል፡፡በያዝነው 2013 ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት የተናገሩት ንግግር የመርሀ ግብሩን አላማ በግልጽ ያሳየ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ‹የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ የአካባቢ ብክለትንና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ሀገራዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍና ለመመከት የወጣው የአራት ዓመት እቅድ አካል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህ ማለት መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የሰጠው ቦታ ምን ያክል እንደሆነ የሚያሳይ ንግግር ነው፡፡ መንግስት ለጉዳዩ ከሰጠው ትኩረት አንጻር በችግኝ ተከላው ገና ረጅም ርቀትን እንደሚጓዝ የታመነ ነው፡፡ ከሀገር አልፎ ሌሎች የውጪ ሀገራትንም በእቅዱ ውስጥ አስገብቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የጎረቤት ሀገራት ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሆነ በመቀበል የችግኝ ተከላው መርሀ ግብር ከሀገር አልፎ እስከ ጎረቤት ሀገራት እንዲደርስ እየተሰራ እንደሆነ ይሄንንም እናውቃለን፡፡ እንደ ሀገር ከተያዘው ስድስት ቢሊዮን ችግኝ በተጨማሪም አንድ ቢሊዮን የሚሆን ችግኝ ለጎረቤት ሀገራት ለመስጠት መንግስት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ሀቅ ነው፡፡ በመርሀ ግብሩ መሰረትም ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ኬንያን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደታቀደ ታውቋል፡፡ እኛ ለምተን ጎረቤቶቻችን በርሀ ቢሆኑ ችግሩ ወደ እኛ መድረሱ አይቀርምና በጋራ መልማትን እንደ ጥሩ ነገር በመውሰድ ጎረቤቶቻችንን በአረንጓዴ ለማልበስ እየተኬደበት ያለው መንገድ አዋጪ እንደሚሆን አንጠራጠርም፡፡
ችግኝ ተከላን በተመለከተ አብዛኛውን ጊዜ የምንታማበት አንድ ነገር አለ ፡፡ እርሱም ምንድነው ለመትከል የተነሳሳነውን ያክል ለእንክብካቤ አለመነሳታችን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ተክለን ከእንክብካቤና ከክትትል ማነስ ብዙ ችግኞች ከስመው እንደቀሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ የአሁኑ ህዝባዊ መነሳሳት ግን ከዚህ በፊት እንደነበረው አይደለም። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተከለውን ችግኝ እንዲንከባከብና እስኪጸድቅ ድረስ ሀላፊነቱን ወስዶ እንዲከታተል በሚያስችል ልክ የተገነባ ህዝባዊ እንቅስቃሴ በመሆኑ ብዙም ስጋት አለው ብዬ አላስብም፡፡ እርግጥ ነው የተከልነውን ያክል ጸድቆልን አያውቅም፡፡ የአሁኑ መነሳሳት ግን ከነበረው ሁሉ ይለያል፡፡
መንግስት ከእቅዶቹ አንዱ በማድረግ ብዙ ሀይልና ገንዘብ መድቦ የሚያንቀሳቅሰው ስለሆነ በብዙ ሀላፊነት የታጀበ ነው፡፡ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ብናይ እንኳን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ አብዛኞቹ የጸደቁ ሲሆን ይሄም ማለት በመቶኛ ሲሰላ 87 ከመቶ የሚሆኑት ችግኞች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ በመንግስት ደረጃ የተገለጸበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ የምንለፋው የምንደክመው ለለውጥ ነውና ወደፊት መቀጠሉ አዋጭነት አለው ማለት ነው፡፡
በየዓመቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መንግስት ችግኝ መትከልን እንደ ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ነው የሚገኘው፤ ይህ ደግሞ የመንግስት ግዴታ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ እኩል ሀላፊነት ነው፡፡ እየገነባንው ላለንውና ወደ ፊትም ሊገነቡ እቅድ ለተያዘላቸው ትልልቅ የኤሌክትሪክ ግድቦች ዛሬ ላይ ችግኝ መትከላችን የውሀ እጥረትን ከመከላከል ባለፈ ጤናማና የተስተካከለ አካባቢ እንድናገኝ ስለሚረዳን ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ሰዓት ዓለም ከተቸገረችባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኛው የዚህ ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል ድሀ ሀገራት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ይህ ማለት ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ መሰል ታዳጊ ሀገራት የገፈቱ ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ናቸው ማለት ነው፡፡
ችግሩ ይሄ ብቻ አይደለም ከአየር ንብረቱ ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ ሀገራዊ ችግሮችም አሉ፡፡ የዝናብ እጥረትን በማስከተል ድርቅና መሰል ኢኮኖሚያዊ እንቅፋቶችን በመፍጠር በሀገርና ህዝብ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ የት የለሌ ነው። ይሄ ብቻ አይደለም ተለምዶአዊ የአካባቢ ምህዳርን በመዛባት በሰው ልጅ ላይ እና ህይወት ባላቸው ማናቸውም ፍጡራን ላይ መጥፎ አሻራውን በማሳረፍ ህልውና አደጋ ላይ ይከታል፡፡ እንኳን እንደዚህ አይነት ተጨማሪ እንከኖች ታክለውብን ይቅርና ወትሮም ኑሯችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡ ሀላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ግን ከመንግስት ጎን በመቆም በአረንጓዴ አሻራው ላይ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ብናደርግ አንድም ለራሳችን አንድም ለሀገራችን መትረፍ እንችላለን እላለሁ፡፡ ክረምቱ ሳያልፈን ወቅቱም ሳይሄድብን መንግስት በጀመረው በዚህ የአረንጓዴ መርሀ ግብር ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ነጋችንን ብሩህ ማድረግ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ አረንጓዴ መልበስ የእኔና የእናንተ የነገ ዋስትና ነው፡፡ ዛሬ ላይ የምንተክላትና የምንከባከባት አንድ ችግኝ ነገ ላይ ለኔና ለእናተ ብሎም ለልጆቻችን የህይወት ዋስትና ሆና መምጣቷ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህም በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያን ማልበስ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚህ ጋር አያይዤ አንድ ያስገረመኝን ነገር ላውጋችሁ፡፡ ከሰሞኑ አምስት ኪሎ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ጎራ ብዬ ነበር፡፡ ግድግዳው ላይ ሌላ ዓለም፣ ሌላ ሰማይና ምድር የሚመስል ፍጹም የሚደንቅ አረንጓዴ የለበሰ አንድ ፎቶ ግራፍ ግድግዳው ላይ ተሰቅሎ ተመለከትኩ፡፡ ቀርቤ አየሁት..ከስሩ ያለውን ጽሁፍ ሳነበው ለካ ከሚሊዮን ዓመት በፊት የነበረችው የኛ ምድር ፎቶግራፍ ነበር። ከጎኑ በበርሀ የተዋጠችው አሁናዊ የምድራችን ገጽታ አለ፡፡ የሁለቱን ልዩነት በአግራሞት ነበር ያየሁት። በነገራችን ላይ ዓለም ትጠፋለች ተብሎ በሳይንሱ ከሚተነበይባቸው እውነታዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡ ይህ ማለት የዓለም ፍጻሜ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚመጣ ነው ማለት ነው፡፡ ለመጪው ትውልድ የተራቆተችን ሀገር ማስረከብ የለብንም፡፡ ተባብረን ኢትዮጵያን ማልበስ አለብን፡፡ አረንጓዴ መሬት፣ አረንጓዴ ምድር ታስፈልገናለች፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ሁሉንም ማህበረሰብ የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡ ዋናውና ብቸኛው መከላከያ መንገድ ዛፍ መትከል፣ ችግኞችን መንከባከብ ብቻ ነው። መንግስት በያዘው የአረንጓዴ ልማት መርሀ ግብር ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያንና ምድሯን ከበርሀማነት መታደግ እንችላለን፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት የሚመጡ ጉዳቶችን ለመከላከል ከድሀ ሀገራት ይልቅ የበለጸጉ ሀገራት የተሻለ አቅም ቢኖራቸውም ሙሉ በሙሉ ከችግሮ መላቀቅ ግን አይችሉም፡፡
የበለጸጉ ሀገራት በኢኮኖሚያቸው ልክ እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመመከት የሚያስችል አቅም ያዳበሩ ቢሆንም የጉዳቱ ሰለባ ከመሆን የሚያድናቸው አንዳች ሀይል ግን የለም፡፡ ምክንያቱም የአየር ንብረት ለውጥ በጋራ የምንከላከለው የዓለም ሁሉ የጋራ ችግር ስለሆነ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ታኮ የሚመጣ ነው፡፡ ለዚህም ነው ባለጸጋ ሀገራት በለኮሱት ድሀ ሀገራት የሚጨሱት፡፡ በሀብታም ሀገራት የስልጣኔ ገፈት ድሀ ሀገራት አሳራቸውን የሚያዩት። የአየር ንብረት ለውጥ የሁሉም ሀገራት የጋራ ችግር ቢሆንም ቀደም ብዬ እንዳልኳችሁ በድሀ ሀገራት ላይ በይበልጥ ያይላል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ከትላንት እስከዛሬ የዓለም የቤት ስራ ሆኖ ያለ ትልቅ ጉዳይ ነው። እልባትና መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ግን አብዛኛው ሀገር ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው። በተለይ በኢኮኖሚያቸው አደጉ የሚባሉ ሀገራት ለችግሩ መፈጠር የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ከፊት የሚሰለፉ ናቸው፡፡ ከትላንት እስከዛሬ ለዓለም ሰላም ማጣት ተጠያቂዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡ አፍሪካና ህዝቦቿ ምንም በማያውቁት ባለጸጎቹ በፈጠሩት ችግር ስቃይ ላይ ይገኛሉ፡፡
በዓለም ዙሪያ በተለያየ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ የበለጸጉ ሀገራት ለድሀ ሀገራት ድጎማ ማድረግ አለባቸው የሚሉ በርካታ መከራከሪያ ሀሳቦች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ድረስ እኚህ ሀሳቦች መቋጫ አላገኙም፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ መንግስታችንም ይሄን ተገንዝቦ እያደረገ ያለው የቅድመ መከላከል ተግባር እጅጉን የሚደነቅ እንደሆነ ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡ ልክ እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉም የዓለም ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የበኩሉን ማድረግ ቢችል ምድራችን በዚህ ልክ ሲኦል አትሆንብንም ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ግን መንግስታችንን ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ በእያንዳንዱ ኩነት ላይ ህዝብ ችግኝ እንዲተክል በማድረግ ሀገራዊ ሀላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ ዓለም በሁለት እጁ ምርጫ ሲመርጥ እኛ ግን በአንድ እጃችን ችግኝ እየተከልን በአንድ እጃችን ስንመርጥ ነበር፡፡
ችግኝ በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ጎን ለጎን መንግስት ማህበረሰቡ ለምግብ የሚሆኑ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችንም እንዲተክልና ራሱን በምግብ እንዲችል እያደረገ ያለውም ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ አሁን ላይ ከችግኝ ተከላው እኩል ሁሉም በየደጁና በየጓሮው በከተማ ግብርና ራሱን ከወጪ ተከላክሎ ከጓሮው ቀጥፎ የሚበላበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በርካቶች በዚህ የመንግስት መርሀ ግብር ውስጥ በመሳተፍ በጓሮአችውና በግቢያቸው ውስጥ ለምግብ የሚሆኑ አትክልቶችን በመትከል ራሳቸውን በመደጎም ላይ እንደሆኑ በተለያየ ሚዲያ ላይ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ አድምጫለሁ፡፡
በቀላል መንገድ፣ በትንሽ ቦታ ላይ ራስን ከወጪ መታደግ ዘመናዊነት ነው፡፡ ይሄ ተግባር በስፋት ተሰርቶበት ማህበረሰቡ ከጓሮው ቀጥፎ መብላትን ልምድ እንዲያደርግና ድህነትን አሸንፎ እንዲወጣ መንግስት በያዘው በጎ መንገድ መቀጠል አለበት ፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ችግኝ እየተከሉ በዛውም ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ ፍራፍሬና አትክልቶችን በመትከል ራስን በምግብ መቻል፡፡ ይህ ተግባር መንግስትን እንደ መንግስት ሲያስመሰግነው ማህበረሰቡን ደግሞ ከመጠበቅና ከልመና ወጥቶ በህይወት ለመኖር የተለያዩ አማራጮችን እንዲፈልግ መንገድ ይጠቁመዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ህይወት በብዙ አማራጮች የተከበበች ናት፡፡ ከመጠበቅ ወጥተን ለመኖር የሚያስችለንን ቀላልና አዋጪ ዘዴ ማየት ይኖርብናል፡፡ ገንዘብ አውጥተን መርካቶና አትክልት ተራ ድረስ ሄደን ጊዜና ጉልበታችንን ከምናባክን በአንድ እጃችን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ችግኝ እየተከልን በአንዱ ደግሞ የዕለት ፍጆታችንን የምናሟላበት አትክልትና ፍራፍሬ መትከልን ባህል ማድረግ ይኖርብናል፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2013