ሁላችንም እንደምናስታውሰው መንግሥት የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ ወስኖ፤ ሠራዊቱም ይሄንኑ የተኩስ አቁም ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ያመች ዘንድ ከትግራይ/ ከመቐለ የመውጣት እንቅስቃሴ እንደጀመረ ሁላችንም እናስታውሳለን::ይሄ የሠራዊቱ ከትግራይ/ከመቐለ የመውጣት እንቅስቃሴ በዋነኛነት፣ አንደኛው ሠራዊቱ የት ቦታ ነው መቋቋም የሚገባው፤ የሚቋቋምበት ቦታም ቢያንስ ቢያንስ ለትንኮሳ የማይመች ቦታ መሆን አለበት፤ ሁለተኛው ደግሞ፣ ምናልባት ትንኮሳ የሚመጣ ከሆነ ለትንኮሳው አጸፌታዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ምቹ የሆነ ቦታ መሆን አለበት በሚል ነበረ እንቅስቃሴ የተጀመረው፡፡
እንግዲህ ወታደር ሳይሆን ማንኛውም ሰው እንደሚያውቀው አንድ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ጊዜ ጥበቃ ይደረጋል::ይሄ ጥበቃ የሚደረገው ዋናውን እንቅስቃሴ የሚያውክ ነገር ካለ፤ በዚህ በጥበቃ ለመከላከል ታስቦ የሚደረግ ነው::ከዚህ የተነሳ እኛ ሁሉም የሠራዊት አባላት ማን የት ቦታ ሆኗል የሚለውን እንቅስቃሴ ውስጥ እያለን፤ ያው እንደምታውቁት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔውን ጁንታው እና የጁንታው ውጫዊ ኃይል (ገዢዎቻቸው ማለት ነው፤ እነሱ ተላላኪዎች ናቸው) ገዢዎቻቸው ይሄንን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በተለያየ አኳኋን ትንኮሳዎችን በማድረግ እኛ ለጥበቃ፣ ለሳተላይት ያስቀመጥናቸውን አሃዶች፣ የክልል የጸጥታ ኃይሎችን ማጥቃት እንደ አንድ ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
በዚህ መሰረት በዋነኛነት እኛ በደቡብ በራያ አካባቢ የነበረውና ሠራዊቱ የወጣበት አካባቢ እንደመሆኑ፤ በራያ የት ቦታ እንሆናለን ተብሎ ውሳኔ ተሰጥቶ የምንሰፍርበት አካባቢ ማስፈር (ሁሉም እንደሚያውቀው ድሮም አላማጣ ኮረም አካባቢ ሠራዊት አልነበረንም፤ ነገር ግን ደግሞ ለዚሁ ሥራ ያመች ዘንድ ቅድም እንዳልኩት አነስተኛ ኃይሎችን ማስቀመጥ ነበረብን፤ እንደገናም የአካባቢ ኃይሎችን ማስቀመጥ ነበረብን)::እናም (የተቀመጡት የእኛ የመከላከያ ኃይል እና የአካባቢ ኃይሎች) ያው የወያኔ ገዢዎች እና ጁንታው አጋጣሚውን በመጠቀም እኛ መቋቋም ሳናደርግ እናጠቃለን በሚል ይሄን ኃይላችንን አጥቅቶ ለመደምሰስ ሙከራ አድርገዋል፡፡
በዚህ ሙከራቸው ባለፈው ጊዜ እንዳልነው፣ አንደኛው ከመቐሌ ስንወጣ ለምን ወጣችሁ ለሚባለው ከህዝብ ጋር አንዋጋም፤ ህዝቡም ይረስ በሚል ነው::ከማዕከላዊ ትግራይ የተለያየ ቁጥር ያላቸው ሲቪሎች አንቀሳቅሰውና አነሳስተው መሳሪያ ታገኛላችሁ፣ ንብረት ታገኛላችሁ፣ ገንዘብ ታገኛላችሁ በሚል በዚህ ቦታ ላይ አሰማርተዋል::መንግሥት በተናጥል የወሰነውን የተኩስ አቁም ውሳኔ ወያኔ ለምንድን ነው የማይቀበለው? ከተባለ፤ ጁንታው ይሄን የማይቀበልበት መሰረታዊ አመል እና ባህሪዎች አሉት፡፡
አንደኛው እና የመጀመሪያው ነገር፣ ጁንታው ከችግር እና ከቅራኔዎች ውጪ መኖር አይችልም::ሰላማዊ ሁኔታ ለጁንታው ህይወት መኖር፣ መደራጀት፣ ማደግና መስፋፋት ምቹ አይደለም::ከዚህ የተነሳ በአገራችን ባለፉት ጊዜያቶች የዚህን ቡድን ባህሪ ካየን በግጭት ውስጥ የኖረ ቡድን በመሆኑ ምን ጊዜም ግጭት ለእሱ መፋፊያና ማደጊያ በመሆኑ በተናጥል የተወሰነውን የተኩስ አቁም ውሳኔ አይቀበልም፡፡
ሁለተኛው ባህሪው፣ የመንግሥት የተኩስ አቁም የተናጠል ውሳኔ መሠረቱና ዋነኛው ትግራይ ውስጥ ህዝቡ እርሻ ማረስ አለበት፤ አርሶ ለሚቀጥለው ዓመት ስንቁን ማዘጋጀት አለበት፤ ይሄ ካልሆነ ረሃብ ይመጣል፤ ረሃብ ብቻም አይደለም ረሃብም ወደ ቸነፈር ገብቶ ህዝቡ ህይወቱን ሊያጣ ስለሚችል ለዚህ ሲባል የተኩስ አቁም የተናጠል ውሳኔ ተወሰነ::ወያኔም ይሄን የማይቀበለው ይሄን ተቀብሎ መቐሌ ውስጥ ከተቀመጠ ሽማግሌዎቹ ሳይሞቱ ወጣቶቹን አንስቶ የማገዱትና ያስፈጁ በመሆናቸው ከህዝቡ ጥያቄ ይቀርባል::ህዝቡ የሚበላውንና የሚጠጣውን ነገር በሰላማዊ መንገድ ማግኘት ይፈልጋል፤ ይሄንን ጥያቄም ያቀርባል::በዚህ ምክንያት ይሄን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን ወያኔ እንዲቀበል ባህሪውም አይፈቅድለትም፡፡
እርግጥ ነው የኢትዮጵያ መንግሥትም ወያኔ እንዲቀበል ሳይሆን የዓለም ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግሥትን ተኩስ አቁም እንዲያደርግ ሲወተውት ስለነበር እና የኢትዮጵያ መንግሥትም በወቅቱ እና የተኩስ አቁም ውሳኔ መወሰን ባለበት ሰዓት ላይ ውሳኔውን ሰጥቷል::በዚህ መሰረት የወያኔ ትንኮሳ በዋናነት በግጭትና በግጭት ውስጥ የመኖር ባህሪና ተፈጥሮ ስላለው ነው፡፡
በዚህ ግጭት ውስጥ ለመኖር ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ፣ መላው የዓለም ማህበረሰብም እንዳየው ያሰማራቸው ወይም የመለመላቸው ወጣቶችን አይታችኋል::የ14 ዓመት፣ የ15 ዓመት፣ የ13 ዓመት ወጣቶች ናቸው::እነዚህ ናቸው ጠመንጃ ይዘው ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር፣ ከአካባቢ የጸጥታ ኃይሎች ጋር እንዲዋጉ ያዘመቷቸው::ከኋላቸው ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ የማዕከላዊ ትግራይ ህዝብ ልክ ተንቤን ላይ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸሙትን ዓይነት ነገር ለመፈጸም አብረው ተከትለው መጥተዋል፡፡
ስለዚህ የወያኔ ዋንኛው ይሄንን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔውን የማይቀበልበት አንደኛው ባህሪው ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ከትግራይ ህዝብ ከፍተኛ ጥያቄ ስለሚቀርብበት እና ምናልባትም ከህዝብ የሚነጥለውና መቀበሪያው ዋነኛና ምሰሶ በመሆኑ ውሳኔውን ያለመቀበል እና ትንኮሳውን እንዲቀጥል ገፋፍቶታል::ትንኮሳውንም እየቀጠለበት ነው፡፡
አንዱ ህዝባችንና ወገኖቻችን መረዳት ያለባቸው ወታደራዊ ሥራ በወታደሮች ብቻ የሚከናወን እንጂ በአክቲቪቲ/አክቲቪስቶች የሚከናወን ሥራ አይደለም::በዚህ የተነሳ የት ቦታ መቼ መከላከል አለብኝ፤ መቼ ማጥቃት አለብኝ የሚለውን ነገር እኛ በውሳኔ ወስነን እየሠራን ያለነው ነገር ነው::ጉዳዩ ውጊያ ነው::ውጊያው ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ አገር የማስቀጠል፤ እንደ ሃገር ወያኔ የፈለገውን ኢትዮጵያን የመበተን ፍላጎት የማይሳካ መሆኑን ማሳየት ብቻ ሳይሆን ማረጋገጥም አስፈላጊ ስለሆነ ሁሉንም ኃይላችንን በመጠቀም መቼ የት ቦታ ማጥቃት አለብን የሚለውን ነገር እየሠራን እንገኛለን::እየተዋጋን ያለነው ለኢትዮጵያ ድንበር ነው::የኛ ድንበር መረብ ነው::የመረብ ድንበር ድረስ ማንም አጉራ ዘለልና የመንደር ዱርዬ ተነስቶ ኢትዮጵያን ለመበጣጠስ የሚፈልገው የማይቻል መሆኑን ማሳየት እንጂ::እኛ እንደ መከላከያ ሠራዊት የት ቦታ መቀመጥ እንዳለብን በፊትም መቀመጥ ያለብን ቦታ ስንወስን እገሌ የሚባል ቦታ ነው የተቀመጥነው ብለን ከማንም ጋር ኮሚዩኒኬት አላደረግንም፤ አልተነጋገርንም፤ እና ስለዚህ ይኼ የወያኔን የጊዜያዊ ፉከራ በመስማት ለሱ ሰለባ መሆን አያስፈልግም::ስለዚህ በማንኛውም ሰዓት የሚያስፈልገውን መሬት ትተን ወደ ውስጥም ሆነ ወደውጭ በፈለገው ዓይነት መንገድ እንቅስቃሴ አድርገን የወያኔን ግብአተ መሬት፣ የአሸባሪውን ጁንታ ግብአተ መሬት የምናረጋግጥ ካልሆነ በስተቀር እሱ በሚፈጥረው ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆኖ ማንኛውም የህዝባችን ጆሮ ሊሰጠው የሚገባው ነገር አይደለም::የመጀመርያውና ዋነኛው ነገር ይኼ ነው፡፡
ከዚህ የተነሳ የት ቦታ መቼ ትዋጋላችሁ የሚለው ነገር ወታደራዊ ጉዳይ ስለሆነ ይህንን ልገልጽላችሁ አልፈልግም::ነገር ግን ይህ የተናጠል የተኩስ አቁም ወይም ተኩስ አቁመናል የሚለው የመንግሥት ውሳኔ ለወያኔዎች ዕድል ስለሰጠ ይህንን ባለፈው ጊዜ እንደተነጋገርነው መቼ፣ እንዴት፣ የት ቦታ ምን ዓይነት ሥራ ይሠራል የሚለው ነገር እየሠራንበት ይገኛል::ህዝባችን ይህንን መከታተል አለበት::ከዚህ የተነሳ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደለመድነው ከሠራዊታችን ጎን ሊሰለፍ ይገባል::
ባለፈው ጊዜም ስታደርጉት እንደነበረው፤ጉዳዩ ውግያ ነው:: በሰው ኃይል በማቴሪያል፤ በሞራል ከሠራዊታችን ጎን መቆም ያስፈልጋል::ማንም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል፣ ኢትዮጵያን የሚወድ፣ ከዚህ ሰራዊት ጎን ሊቆም ይገባል::እኛ ስንናገርም፣ ስንሠራም ኃላፊነት ያለብን የሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ነን::የሃገር መከላከያ ሠራዊት ተቋም ነው::ወያኔ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመወንጀል ይሁን የኢትዮጵያን መንግሥት ለመወንጀል እውነቱን መፈለግ የለበትም::እነሱም በፕሮፓጋንዳ ቲማቸው እንዳስቀመጡት የኢትዮጵያን መንግሥት ለመወንጀል የሚፈለገውን ነገር መፈብረክ አለብን ብለው እየሠሩ ነው ያሉት::ስለዚህ እነሱ ውሸት ቢናገሩም ተጠያቂነት የለባቸውም::በየበረሃው የሚንቀሳቀሱ፣ የሚያስተዳድሩት ቦታ የሌላቸው፣ ጠያቂ የሌላቸው፤ ሰዎች ናቸውና::እኛ መዋሸት አንፈልግም::ኃላፊነት አለብን::የምናስተዳድረው ሃገር አለን::ኢትዮጵያ ናት::ኢትዮጵያ ደግሞ በአንድነቷ፣ በግዛት አንድነቷ፣ በሉአላዊነቷ፤ ህዝቦቿ ባሉበት ሰላም አግኝተው መቀጠል አለባቸው::በዚህ መሰረት ለእያዳንዱ የምናደርገው እንቅስቃሴ ህይወት ገብረን፣ መስዋዕትነት ከፍለን፣ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል እየሠራን ነው የምንገኘው::ከዚህ የተነሳ ህዝባችን ወጣቱ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን ሆናችሁ ባለፈው ጊዜ ወይም እንደተለመደው ድጋፋችሁን እንድትሰጡን ጥሪዬን አቀርባለሁ::
የመከላከያ ሠራዊትም ሃገራችንን፣ የሃራችንን አንድነት፣ ሉኣላዊነትና የግዛት አንድነቷን ለማረጋገጥ ከማንኛውም ጊዜ በላይ መስዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁ የሆነ መሆኑን አረግጋጣለሁ::የወያኔ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆን አይገባም:: ስለዚህ ከጎናችን ቁሙ እላለሁ:: አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2013