አርሶ አደር ህይወቱ በእጅጉ ከመሬት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ መሬቱን ቧጭሮ እና ጭሮ የዓመት ቀለቡን እርሾ ይጠነስሳል፡፡ አርሶ፣ ዘርቶ እና አርሞ ምርቱ ሲደርስ አጭዶ ጎተራውን ይሞላል፡፡ ከቀለብ አልፎ ለዓመት ልብሱ ከጎተራው ዕህል ሽጦ ኑሮውን ይመራል። ኑሮው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ህልውናው ከመሬት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ለልጆቹ የሚያወርሰው ያው መሬቱን ነው፤ ልጆቹን የሚያበላው እና የሚያለብሰው ከተሳካለትም የሚያስተምረውም በዚያው ከመሬቱ በሚገኝ ሀብት ነው፡፡ የሀብቱ መለኪያ የኑሮው መመዘኛ መሬቱ ደግሞ ለአገራዊ ልማት ከተፈለገ ግን ከልማትና ከሀገር በላይ ምንም የለምና መረቱን በተገቢው ካሳ ለልማቱ አሳልፎ መስጠቱ ግዴታ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ሀብቱን ለልማት የሰጠው ባለሀብት መተኪያ ካሳ ማግኘቱ ግን የግድ የሚል ነው፡፡
የእነአርሶ አደር ዋለ መነሳት
አርሶ አደር ዋለ አለባቸው በአማራ ክልል በሜጫ ወረዳ እናምርት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ጭረው የሚያድሩበት የገጠር የእርሻ መሬታቸው ለቆጋ መስኖ ልማት ሊወሰድ መሆኑ ተነገራቸው፡፡ የእርሻ መሬታቸው ብቻ አይደለም፡፡ በወቅቱ የመኖሪያ ቤታቸው እና የጓሮ የአትክልት ስፍራቸው በአጠቃላይ ይዞታቸው ለቆጋ መስኖ ልማት አገልግሎት በመፈለጉ ይዞታችሁን ልቀቁ ተባሉ፡፡ ተነሺው እርሳቸው ብቻ አልነበሩም፤ 233 የሚሆኑ አባወራዎች ለመስኖ ልማቱ መነሳት እንዳለባቸው ተነገራቸው፡፡
በ1999 ዓ.ም በሰኔ ወር በቅድሚያ የጓሮ የአትክልት ስፍራቸው እና ቤታቸው ተለክቶ ካሳ ተከፈላቸው። ይህንን ተከትሎ አንዳንዶቹ ወደ ከተማ ሌሎቹም ወደ ጫካ እና ወደ ተለያየ አካባቢ ቦታውን ለቀው ሔዱ። በ2000 እና በ2001 ዓ.ም ለገጠር የእርሻ መሬቱ በአጎራባች ቀበሌ ምትክ ቦታ ተሰጠ፡፡ ቦታው ተለክቶ የሦስት ዓመት ካሳ ዘግይቶም ቢሆን በ2003 ዓ.ም ይከፈላል ተባለ፡፡
የእነ አቶ ዋለ ማረሚያ ቤት መግባት
በጊዜው አርሶ አደር ዋለ እንደሚናገሩት፤ እርሳቸው የመሬት አባሪ የካሳ ገማች እና አስከፋይ ነበሩ፡፡ የአትክልት ካሳ ሲከፈል ሰዎች አጭበርብረው አትክልት ማስቆጥራቸውን ደረሱበት፡፡ ክፍያው ሲፈፀም፤ ‹‹አትክልቱ በትክክል አልተቆጠረም፤ በድጋሚ መቆጠር አለበት›› ማለታቸውን ተከትሎ፤ አጭበርብረው አትክልታቸውን ያስቆጠሩ ሰዎች በፊት ካስገመቱት ብር አንደኛው 80 ሺህ ሁለተኛው 90ሺህ ብር ተቀንሶ ተሰጣቸው፡፡ በዚህ ያኮረፉት ሰዎች እነ አቶ ዋለን ለመበቀል ሥነምግባር እና ፀረ ሙስና ‹‹ያለአግባብ ካሳ አስከፍሏል፡፡ ለጓደኞቹም አስጥቷል፡፡›› በማለት ከሰሷቸው፡፡ ይህን ተከትሎ አቶ ዋለ አለባቸውን ጨምሮ፤ ይቴ አቸንፍ፣ ማዘንጊያ አለባቸው፣ ምህረት አታላይ፣ ጋሻው ዋለ እና ዘላለም ቸርነት የተባሉ አርሶ አደሮች ታሰሩ፡፡ በዚሁ በ2003 ዓ.ም በጥቅምት ወር ክስ ቀረበባቸው፡፡ ሥነምግባር እና ፀረ ሙስና ያቀረበውን ክስ ተከትሎ ፍርድ ሳይሰጥ አርሶ አደሮቹ ማረሚያ ቤት ቆዩ፡፡
የእነ አቶ ዋለ ካሳ መከልከል
እነ አቶ ዋለ ማረሚያ ቤት ሆነው ሲከራከሩ፤ ለአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ያለፍርድ ቆዩ፡፡ በመሃል ለሌሎች ተነሽዎች ለገጠር የእርሻ መሬታቸው ካሳ ሲከፈል እነርሱ ግን ማረሚያ ቤት በመሆናቸው፤ መቀበል ስላልቻሉ የሦስት ዓመት የሰብል ካሳ እንዲሰጣቸው ሰው ወከሉ፡፡ የወረዳው ፋይናንስ ቢሮ እና የወረዳው አመራርን ጨምሮ ማረሚያ ቤት መቆየታቸውን ተከትሎ፤ ‹‹ በማረሚያ ቤት ውስጥ ናቸው›› በሚል ሰበብ በመከልከላቸው ለገጠር የእርሻ መሬታቸው ካሣ ሳይከፈላቸው ቀረ። ‹‹ዳኛው የገጠር የእርሻ መሬትን ካሳ ሳያግድ ከፋዩ አካል አልከፍልም ማለቱ ተገቢ አይደለም ›› ቢሉም ሰሚ አለማግኘታቸውን አቶ ዋለ ይናገራሉ፡፡
እንደአቶ ዋለ ገለፃ፤ በ2004 ሰኔ 8 ቀን በነፃ ሲለቀቁ፤ የገጠር የእርሻ መሬት የሦስት ዓመት ካሳ አለማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ ካሳ እንዲከፈላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አልተሰጣቸውም፡፡ ሃምሌ ላይ ለወረዳው ሲጠይቁ እየተገፋፉ ኃላፊነት አልወስድ አሏቸው፡፡ ከወረዳ አልፈው ለአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ አመለከቱ፡፡
የአርሶ አደር ዘላለም አቤቱታ
ሌላው ተበዳይ ነን ባይ የእናምርት ቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ዘላለም ቸርነት በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ‹‹ከአመራሩ ጋር ችግር አለ፤ የአትክልት ያለአግባብ ካሳ ወስዳችኋል›› ተብሎ ክስ ተመስርቶ፤ ተሰቃዩ፡፡ ዋስትና ተከልክለው ለአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ከታሰሩ በኋላ በመጨረሻ ጥፋተኛ ባለመሆናቸው ነፃ ተብለው ተለቀቁ፡፡ በተጨማሪ መሬት ምትክ አግኝተው ነበር፡፡ ነገር ግን የገጠር የእርሻ መሬት ካሳ ዝርዝሩ ሲታይ ካሳ አልተሰጣቸውም፡፡ እስር ቤት ቢሆኑም ሰው ወክለው ነበር፤ ነገር ግን በጊዜው ተከልክለዋል፡፡
‹‹ ለምን ተከለከልን፤ ያገደው ማን ነው? የታገደው እንዴት ነው? እንዴት እናስለቅቅ?›› ቢሉም በወረዳው በኩል ‹‹ሂዱ አናውቅላችሁም›› መባላቸውን እና ብሩ የት እንደደረሰ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡
‹‹ከፋዮቹ አውጥተው ይጠቀሙት፤ ለሌላ ሰው ይክፈሉት፤ ገንዘቡ የት ይደረስ የት ማወቅ አልተቻለም።›› የሚሉት አርሶ አደር ዘላለም፤ በ2003 ዓ.ም እርሳቸው እንዲቀበሉ ተገምቶላቸው የነበረው ብር 20 ሺህ ብር ነበር፡፡ መከፈል በነበረበት ጊዜ በሰዓቱ ገንዘቡ ቢከፈላቸው ኖሮ፤ በጊዜው የተሻለ ዋጋ ስለነበረው ብዙ ነገር ለማድረግ ያስችል ነበር፡፡ እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም እስከ 40 ሺህ ብር የተገመተላቸው ሰዎች ገንዘቡን ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ አሁን እስከነቤተሰባቸው የቀን ሥራ የሚሠሩበት ሁኔታም ጭምር መኖሩን ተናግረዋል፡፡
‹‹ህግ ባለበት አገር የእናንተ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ ገንዘቡ የተከለከለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ብሎ ቀርቦ የሚያወያይ አንድም ሰው መጥፋቱ ያሳዝናል፡፡ ›› ይላሉ።
የወረዳው የአካባቢ ጥበቃ
በሜጫ ወረዳ የገጠር መሬት ኃላፊ አቶ አስማማው ጌትነት በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ለቆጋ መስኖ ልማት ካሳ ከተከፈለ ረዥም ጊዜው ነው፡፡ በወቅቱ ካሳውን የሚከፍለው ሌላ አካል ነበር፡፡ የእኛ ሥራ ይዞታውን አጣርቶ መስጠት ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር፡፡ የአባይ ተፋሰስ የሚባል ተቋም ሲከፍል ነበር፡፡
እርሳቸው ባላቸው መረጃ መሰረት ያልተከፈለው አርሶ አደር የለም፡፡ ሙሉ ሰነዱ በክልል ገጠር መሬት ቢሮ አለ፡፡ እዚያ ላይ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እነርሱ ጋር ግን ምንም መረጃ የለም፡፡ ካሳ የሚመለከታቸው የተከፈላቸውም ሆነ ካሉ ያልተከፈላቸው ሰዎች መረጃ ተጠቃሎ ክልል ገብቷል፡፡ ስለዚህ ክልሉ የተሻለ መረጃ ሊሰጥ ይችላል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ከዚህ በላይ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ እና በወቅቱ የነበሩ ባለሞያዎች አሁን አለመኖራቸውን፤
ነገር ግን ክልል ላይ የማን መሬት ምን ያህል ሔደ ማን ምትክ አገኘ የሚለው ሙሉ መረጃ መኖሩን ተናግረዋል። በወቅቱ ምን ያህል ይዞታ ነበራቸው ምን ያህሉ ተከፈላቸው የሚለውን መረጃ የክልል ገጠር መሬት ላይ ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል፡፡
እነ አቶ ዋለ ጉዳዩን ወደ ክልል በማምራት በደላቸውን ቢገልፁም፤ የክልሉ ምክትል የመሬት ኃላፊ፤ ‹‹ካሳ ቀረብን ብለው አቤቱታ በማቅረባቸው ወረዳው ካሳውን እና አጠቃላይ መረጃውን ይላክልን›› በሚል ለሜጫ ወረዳ ደብዳቤ መላኩን አቶ ዋለ ይገልፃሉ፡፡ ከተላከ በኋላ የወረዳው አካባቢ ጥበቃ ደግሞ ‹‹እኛ በጊዜው መረጃ ከማሰባሰብ ውጪ ስለክፍያው የምናውቀው ጉዳይ የለም›› ብሎ ወረዳው ጉዳዩን አድበስብሶ በማለፉ ለዕንባ ጥበቃ ለማመልከት መገደዳቸውን አቶ ዋለ ያስረዳሉ፡፡
ለዕንባ ጥበቃ የቀረበው አቤቱታ
እነአቶ ዋለ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ያመለክታሉ፡፡ “የእርሻ መሬታችን ለቆጋ መስኖ ልማት አገልግሎት በመፈለጉ ይዞታችንን እንድንለቅ ተደርጎ፤ ለሌሎች ተነሽዎች ካሣ ሲከፈል እኛ በማረሚያ ቤት ውስጥ ስለነበርን የካሣ ክፍያው ሳይከፈለን ቀርቷል፣ ከማረሚያ ቤት ከወጣን በኋላም እንዲከፍለን ብንጠይቅ ምላሽ ሊሰጠን አልተቻለም›› በማለት፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ለባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አቤቱታቸውን አቀረቡ፡፡
ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱም የክልሉን ገጠር መሬት አጠባበቅ እና አስተዳደር ቢሮን፣ የአባይ ተፋሰስ ባለሥልጣን እና ከወረዳው አካባቢ ጥበቃ ማስረጃዎችን በመሰብሰብ፤ አቤቱታ አቅራቢዎቹ እነ አቶ ዋለ በትክክልም በክፍያ ዝርዝሩ ላይ ካሳ እንዳልተከፈላቸው አረጋግጦ፤ “የካሣ ክፍያውን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዲከፍል” የመፍትሔ ሃሳብ ሰጠ፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተቃውሞ
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባቀረበው ምላሽ በዋናነት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ያቀረቡት አቤቱታ “ይዞታችን ለልማት ሲወሰድ የካሣ ክፍያ አልተፈፀመልንም” የሚል በመሆኑና የዚህ አይነት ቅሬታም ሊስተናገድ የሚችልበት አግባብ በወቅቱ በሥራ ላይ በነበረው “ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ካሣ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 አንቀፅ 11 መሠረት እንጂ የአመልካቾች ቅሬታ አስተዳደራዊ በደል ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሰጠው የመፍትሔ ሃሳብ በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣን በላይ ነው›› በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተቃውሞ ተጨምሮ እንደተገለፀው፤ ይዞታቸው ለቆጋ ግድብ ፕሮጀክት በመፈለጉ ከይዞታቸው እንዲነሱ መደረጉን፣ ከይዞታ ቸው ሲነሱም ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ካሣ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 መሰረት አመልካቾችን ጨምሮ ለ233 አርሶ አደሮች በካሣ ገማች ኮሚቴ አማካኝነት በየስማቸው የተሠራውን የካሣ ገንዘብ በካቢኔ ፀድቆ እንደተላከ አመልክቷል፡፡
በካቢኔ ፀድቆ እንደተላከ እና የቅሬታ አቅራቢዎች ስም ዝርዝር እና የተሠራላቸው የካሣ ገንዘብ መጠን ጋሻው ዋለ በተራ ቁጥር 99 ላይ፤ ብር 6ሺህ 181፤ ማዘንጊያው አለባቸው በተራ ቁጥር 128 ብር 39ሺህ 485፤ ምህረት አታላይ በተራ ቁጥር 141 ብር 37ሺህ 305፤ ዋለ አለባቸው በተራ ቁጥር 18 ብር 17ሺህ 304 ብር ፤ ይቴ አቸንፍ በተራ ቁጥር 205 ብር 14 ሺህ 170 እና ዘላለም ቸርነት በተራ ቁጥር 206 ላይ ብር 21 ሺህ 310 መሆኑን በመግለፅ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቤቱታ አቅራቢዎቹን ጨምሮ ለ 233 ተነሺዎች የሚገባውን የካሣ ገንዘብ ለዚሁ ዓላማ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ በድምሩ ብር አስራ ሦስት ሚሊዮን አንድ መቶ አስራ ዘጠኝ ሺህ ሁለት መቶ ሠላሳ ዘጠኝ ብር ገቢ ማድረጉን እና ይህን ገንዘብ ለእያንዳንዳቸው የማከፋፈል ኃላፊነትም የወረዳው ፋይናንስ ቢሮ መሆኑን በመግለፅ ምላሽ አቅርቧል ፡፡
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚያቀረበውን መቃወሚያ ከግምት ሳያስገባ “ለቅሬታ አቅራቢዎች የካሣ ክፍያ ያልተፈፀመ በመሆኑ ይህም አስተዳደራዊ በደል ሊሰኝ የሚችል ነው ስለሆነም በአዋጅ ቁጥር 455 /97 መሠረት ለአቤቱታ አቅራቢዎች የካሣ ክፍያ ሊከፈል ይገባል” በማለት የመፍትሔ ሃሳብ መቅረቡ ተገቢነት ይጎድለዋል ብሎ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መልስ ሰጠ፡፡ የእርሱን መልስ ተከትሎ ጉዳዩ ወደ ፌዴራል ኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አመራ፡፡
አርሶ አደር ዘላለም ቸርነት በበኩላቸው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገንዘቡን ልኪያለሁ ቢልም በዝርዝር የላከበትን የደብዳቤ ቁጥር ገልፆ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ገንዘቡ በእነርሱ ስም መጥቶ የት እንደደረሰ አቅጣጫውን ማሳወቅ ሲገባው ይህንን ማድረግ አለመቻሉ ያሳዘናቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡
‹‹የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካሳውን በስማችን ልኪያለሁኝ ማለት ብቻውን መልስ አይሆንም፡፡ ለሚገባው አካል አለመድረሱን መረጃ ከደረሰው ለምን አልተከፈላቸውም፤ ባለመከፈሉም ወደ መንግሥት ካዝና ፈሰስ መሆን አለመሆኑን አረጋግጦ፤ ለሚመለከተው አካል የመጠየቅ ግዴታ አለበት፡፡›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ምርመራ
ተቋሙ የቀረበለትን አቤቱታ መርምሮ ተገቢውን የመፍትሄ ሃሳብ ለመስጠት ያስችለው ዘንድ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግ፤ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ህጎች መመልከቱን መርማሪው ሃይሌ ተፈራ ይገልፃሉ፡፡
የካሳ ይከፈልን ጥያቄን ተቀብሎ መስሪያ ቤቱ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የካሳ ገንዘብ በአካውንት ገቢ ማድረጉን ቢገልጽም፤ ለአቤት ባዩች ካሳ ስለመክፈሉ በተጠሪ መሥሪያ ቤቱ በኩል በሰነድ በማስደገፍ ማስረዳት ባለመቻሉ አቤቱታ አቅራቢዎች ካሳ ያልተከፈላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል ይላሉ፡፡
አቤት ባዮች ካሳ ተከፍሏቸዋል አልተከፈላቸውም የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ባለመሆኑ ከማረሚያ ቤት ቅጣታቸውን ጨርሰው ከወጡ በኋላ ካሳ ለምን አልተከፈላቸውም የሚለውን መመርመር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱም በህዝብ ዕንባ ጠባቂ በኩል ተገልጹዋል፡፡
የወረዳው ፋይናንስ ቢሮ በወቅቱ ካሳ የተከፈለው ወረዳው ላይ ሳይሆን ከተማ አስተዳደሩ ላይ በመሆኑ ወረዳው በአርሶ አደሮቹ ካሳ ክፍያ ላይ ምንም ዓይነት ኃላፊነት የለበትም ሲል ያሳወቀ መሆኑ የወረዳው ገጠር መሬት አስተዳደርም ቢሆን ካሳ እንዲከፈላቸው ማስተላለፍ እንጂ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ከአሠራር ኣንጻር ኃላፊነት የሌለበት እንደሆነ መግለፁን የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የምርመራ ግኝት ያመለክታል፡፡
አባይ ተፋሰስ ጽህፈት ቤት በበኩሉ በ2003 እና 2004 ዓ.ም ካሳ ክፍያ በቆጋ ፕሮጀክት በኩል እንደተፈጸመ ሆኖም ለአርሶ አደሮች በተለያየ ምክንያት ካሳ ሊከፈላቸው እየተገባ ሳይከፈላቸው ከቀረ ግን ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገንዘቡ ተመላሽ ሊደረግ እንደሚችል ማሳወቁንም ዕንባ ጠባቂ ተቋም አጣርቷል::
በእነዚህ ምክንያቶች አቤቱታ አቅራቢዎች ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ የካሳ ክፍያ ሳይፈጸምላቸው እንደቀረ መረዳት የተቻለ ሲሆን፤ በተጠቀሱት ምክንያቶች ካሳ ካልተከፈላቸው ካሳ የመክፈል ግዴታ እና ኃላፊነት ያለበት የአርሶ አደሮቹን ይዞታ ለግንባታው ያዋለው አካል በመሆኑ ካሳውን መክፈል እንዳለበት የሚታመን መሆኑን በማመልከት፤ ለአርሶ አደሮቹ ካሳ ክፍያው እንዲፈጸም የተላለፈላቸው አካላት ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተገቢውን ማጣራት አድረጎ ህጋዊ እርምጃ መውስድ እንደሚኖርበት ወይም ለሚመለከተው የህግ አካል ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረግ እንዳለበት መርማሪው ጠቁመዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ በቀጥታ በሚመለከታቸው አካላት ቸልተኝነት ወይም ጉዳዩን እንዳማያወቁትና እንደማይመለከታቸው በማሰብ እየተፈጸመ በሚገኘው ተግባር ዜጎች ለህዝብ ጥቅም በሚል ከይዞታቸው ሲነሱ ሊያገኙ የሚገባውን ተገቢ ካሳ እንዳያገኙ የሚያደርግ ተግባር በመሆኑ፤ በህገ መንግሥቱና በሌሎች ዝርዝር ህጉች የተሰጣቸውን ካሳ ክፍያ የማግኘት መብትም የሚያሳጣ ሆኖ መገኘቱ ተገልጹዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በአቤት ባዩች ላይ አስተዳደራዊ በደል መፈፀሙን እንዳረጋገጠ የፌዴራል ዕንባ ጠባቂ አመላክቷል፡፡
የህዝብ እንባ ጠባቂ የመፍትሔ ሃሳብ
ተቋሙ በዋናነት ተግባርና ኃላፊነቱ ለዜጎች በህገ መንግሥቱ እና በሌሎች ህጎች የተሰጧቸውን መብቶች ወይም ጥቅሞች በአስፈጻሚው አካል ተግባራዊ መደረጋቸውን በምርመራ ሂደት በማረጋገጥ የአሠራርም ሆነ የህግ ክፍተት ካለ አስፈላጊው የእርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ የመፍትሔ ሃሳብ መስጠት በመሆኑ በተያዘው ጉዳይም አቤቱታ አቅራቢዎች ካሳ የማግኘት መብታቸውን ህግ በሚያስፈጽመው አካል ያልተከበረ እና በምርመራ ሂደትም ይህንን ማረጋገጥ እንደቻለ ዕንባ ጠባቂ ተቋሙ አስታውቋል፡፡
ስለሆነ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትንና ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 እና ሌሎች አግባብነት ባላቸው ህጎች መሰረት ካሳ ሊከፈል ይገባል በማለት፤ በተሰጠው የመፍትሔ ሃሳብ መሰረት ፈጽማችሁ የደረሳችሁበትን ውጤት በአንድ ወር ውስጥ እንድታሳውቁን እናሳስባለን ሲል ጥቅምት 12 /2012 ዓ.ም ለውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ደብዳቤ መላኩን ዕኝባ ጠባቂ ተቋሙ አስታውቋል፡፡
የመርማሪ ሀይሌ ገለፃ
የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጉዳዩን የያዙት መርማሪ ሀይሌ ተፈራ እንደተናገሩት፤ አርሶ አደር ዋለ አለባቸውን ጨምሮ፤ ይቴ አቸንፍ፣ ማዘንጊያ አለባቸው፣ ምህረት አታላይ፣ ጋሻው ዋለ እና ዘላለም ቸርነት ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ወደ ተቋሙ የአስተዳደር በደል ደርሶብናል ብለው አቤቱታ ይዘው ቀርበዋል፡፡
በደል አድርሶብናል ያሉት የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ነው፡፡ አርሶ አደሮቹ ይዘው በቀረቡት አቤቱታ ለቆጋ መስኖ ልማት በሚል ከይዞታቸው ተነስተዋል፡፡ ሆኖም ግን አግባብ ባለው መልኩ የካሣ ክፍያ ሳይፈፀምላቸው ቀርቷል፡፡ አቤት ባዮች በአማራ ክልል በሜጫ ወረዳ እናምርት ቀበሌ ነዋሪ መሆናቸውን ገልጸው የገጠር የእርሻ መሬታቸው (ይዞታቸው) ለቆጋ መስኖ ልማት ሲወሰድ በወቅቱ ለሌሎች ባለይዞታዎች ካሳ ክፍያ ሲፈጸም አቤት ባዮች ማረሚያ ቤት በመሆናቸው ካሳ ሳይከፈላቸው በመቅረቱ እንዲከፈላቸውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ቢጠይቁም ሊከፈላቸው ባለመቻሉ አስተዳደራዊ በደል ደርሶብናል በማለት ጉዳዩ ተመርምሮ መፍትሔ ይሰጠን ሲሉ ለህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባህርዳር ቅርንጫፍ አቤቱታቸወን አቅርበው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጉዳዩን መርምሯል፡፡ ሆኖም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መፍትሔ ያልሰጠ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ተበዳይ ነኝ ባይ አርሶ አደር ዋለ እንደሚናገሩት፤ የፌዴራል ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጉዳዩን መርምሮ የመፍትሔ ሃሳብ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ለእነርሱም ለአቤት ባዮቹ አሳውቋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ በፅሑፍ ለህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በሰጡት ምላሽም ‹‹እናንተ ካሳ ይከፈል ብላችሁ መጠየቅ አትችሉም፡፡›› ማለቱን ተናግረዋል፡፡
‹‹ፍርድ ቤት ሳያግደን ከተከሰስንበት ወንጀል ነፃ መውጣታችንን ብናቀርብም ምላሽ አልተሰጠንም፤ እስር ቤት ሆነን ያመለጠን ካሳ አልተከፈለንም፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገንዘቡን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ተቀብሏል። የተቀበለውን እንዲከፈል ልኳል፡፡ ካልከፈሉ አለመከፈሉን አጣርቶ ማስከፈል ሲገባው፤ ለማስከፈል ልኬያለለሁ ብሎ መልስ ሳይሰጥ መዝጋት የለበትም፡፡›› ብለዋል፡፡
ጉዳዩ ወደ አባይ ተፋሰስ ተዘዋውረዋል የሚል ወሬ መስማታቸውንም አመልክተው፤ የቆጋ መስኖ ጉዳይ ወደ አባይ ተፋሰስ ከገባም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምላሽ መሰጠት አለበት ብለዋል፡፡ የአባይ ተፋሰስም ሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ዕንባ ጠባቂ ተቋም ቢወስንም እነርሱ ወደ ወረዳ እና ወደ ክልሉ ክልሉ ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያንከባለሏቸው እላይ ታች እያሉ መቸገራቸውን ይገልፃሉ፡፡
የአማራ ክልል የመጨረሻ ምላሽ
የአማራ ክልል ገጠር መሬት ኃላፊንም ሆነ ባለሞያን በስልክ ማግኘት ባንችልም የክልሉ አካባቢ ጥበቃ በሰጠው ምላሽ ከፋይ የነበረው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ሌላም ጉዳዩ የሚመለከተው የክልሉ የውሃ ቢሮ መሆኑ ተጠቅሶ፤ የክልሉን የውሃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማማሩን በስልክ አግኝተን እንዳነጋገርናቸው፤ ሥራው ላይ ያሳለፉት ጥቂት ጊዜ ቢሆንም፤ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ሆኖ የአባይ ተፋሰስ የቆጋ መስኖ ልማትን ጉዳይ ይከታተለው እንደነበር መረጃ እንዳላቸው በመጠቆም፤ ነገር ግን ወደ ሥራው በቅርብ በመምጣታቸው ካሳውን አስመልክቶ የተሟላ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ማማሩ እንደገለጹት፤ አሠራሩ ካሳ ሊከፈል ሲል ቀድሞ ወረዳው ይገምታል፡፡ በዋናነት የሚመለከተው መሬት አስተዳደር አረጋግጦ ለመስኖ ኮሚሽን ይላካል፤ በዚያው መልኩ ይከፍላል፡፡ ስለዚህ አሁንም የሚደረገው ጥናቱ ተጠንቶ ወደ ግንባታ ሲገባ በጥናቱ መሰረት ለግንባታው የሚፈለገው የመሬት ስፋት እና የሚነሳው ሰው ቁጥር በዝርዝር ይህን ያህል ነው ይባላል፡፡ ያንን በመያዝ ከወረዳ እስከ ክልል መሬት አስተዳደር ያለውን ሁኔታ ያጣራል፤ ግምቱ ይካሔዳል።
በክልሉ የሚሠራ እና ክልሉ የሚከፍለው ከሆነ ለካቢኔ ቀርቦ ይወሰንና ይከፈላል፡፡ ፌዴራል የሚያሠራው ከሆነም ግምቱ ለፌዴራል ይላክና ፌዴራል ይከፈላል፡፡ ስለዚህ ይኼኛው የቆጋ መስኖ ልማት የፌዴራል በመሆኑ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አባይ ተፋሰስን የሚመለከት ቢሆንም ከፋዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ነው ካሉ በኋላ፤ ለማንኛውም ከሚመለከተው አካል መረጃ ሰብስበው ምላሽ እሰጣለሁ ቢሉም ጋዜጣው ለህትመት እስከ ገባበት ሰዓት ድረስ በስልክ ለማገኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡ ምላሽ ከሰጡን በቀጣይ ጊዜ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2013