
አዲስ አበባ፡- መከላከያ ሰራዊት ትዕዛዝ በሚደርሰው ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ አስታወቁ። ።
የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አንዳንድ አሉባልተኞች ያላወቁት ነገር የተኩስ አቁም እርምጃ በክላሽና በመድፍ ብቻ አይደለም ። ከቃላት መወራወርም መቆጠብን ጭምር ያካተተ ነው።
መቼና ምን ማድረግ እንዳለብንም ጠንቅቀን እንውቃለን ያሉት ኮሎኔል አዳነ፤ መከላከያ ሰራዊት ትዕዛዝ በሚደርሰው ጊዜ አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስድ የሚችልበት አቋም ላይ እንዳለ አስታውቀዋል።
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር በሚያራግቡት ወሬ አንደናገርም ያሉት ኮሎኔል ጌትነት ፣ ከአወጣነው አዋጅ ጋር የሚጻረር ስራ ላለመስራት ስንል ብዙ ከመናገር ተቆጥበናል ብለዋል።
እንደ ኮሎኔል ጌትነት ገለጻ፤ ሰራዊቱ የት ላይ ምን ማድረግ እንዳለበት እና ምን አይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያውቃል፣ የተዛቡ መረጃዎች በተለቀቁ ቁጥር ምላሽ መስጠቱ አስፈላጊ አይደለም የሚል አቋም ተይዟል።
የተዛቡ መረጃዎች ቢሰራጩም በእነሱ ፕሮፓጋንዳ ልክ ወሬ ባለማብዛት ጨዋነታችንን ማሳየት ይጠበቅብናል ያሉት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ፤ችግሮች የሚባባሱ ከሆነ ግን የመንግስትን ውሳኔ ተከትሎ የሚተላለፉ እርምጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
መንግስት የጥሞና ጊዜውን ውጤት አይቶ ችግር እየተባባሰ ከመጣ የተኩስ አቁም አዋጅ ሊያነሳ ይችላል። ያን ጊዜ በሙሉ አቅማችን ስንነሳ በቃላትም ሆነ በመሳሪያ የምናደርገው ልውውጥ ሊኖር ይችላል ብለዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ በአሻባሪው ህወሃት የሚሰነዘሩ ተጨባጭ ትንኮሳች መኖራቸውን ያረጋገጡት ኮሎኔል ጌትነት ፣ በመከላከያ ደረጃ ግን በጉዳዮቹ ላይ ብዙ ማለት አያስፈልግም። ሰራዊቱ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመመከት በሚያስችል ዝግጅት ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል።
መቀሌንም መያዝ ያስፈልጋል የሚል ውሳኔ ካለ ሌተናንት ጄኔራል ባጫ ደበሌ እንዳሉት ለሰራዊቱ የሚቸግር ጉዳይ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2013