መንግሥት ላለፉት ሰባትና ስምንት ወራት በትግራይ ክልል የህግ በማስከበር ዘመቻ ላይ እንደነበር ይታወቃል በእነዚህ ጊዜያት ደግሞ በተለይም የጁንታውን ቡድን እንዳያንሰራራ አድርጎ ከመደምሰሱም ባሻገር ለህግ መቅረብ የሚገባቸውን ሰዎችም ወደህግ አቅርቧል በማቅረብ ላይም ይገኛል ።
በዚህ መካከል ግን የትግርይ ህዝብ የመንግሥትን ጥረት እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱን ትጋት ባላገናዘበ መልኩ የደጀንነት ተግባሩ ላይ መዘናጋቱን ተከትሎ በመከላከያው ላይ በተፈጠረው ጫናና ወቅቱም የግብርና ሥራ የሚጀመርበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ ወደ ሥራ እንዲገባ በማለት ከሳምንታት በፊት መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅን አውጆ መከላከያ ሠራዊቱንም ከክልሉ አውጥቷል።ምንም እንኳን ይህ ሁኔታ በትግራይ ህዝብ ላይ የሚያደርሰው ጫና ቀላል ባይሆንም ህዝቡ ግን ወደራሱ ተመልሶ የሚጠቅም የሚጎዳውን ይለይበት ዘንድ የተሰጠው የጥሞና ጊዜ በመሆኑ መተግበሩ የግድ ሆኗል።
እኛም ባለፉት ሰባት ወራት በሥራ ላይ የነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምን ሠራ ?በሥራውስ ላይ ምን ዓይነት ተግዳሮቶች አጋጠሙት? እንዴት ሊያልፋቸው ቻለ? ወደፊትስ ለክልሉና ለህዝቡ ሰላምና መረጋጋት መፍትሔው ምንድን ነው? ስንል በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ለሆኑት ለአቶ ባርያጋብር አባይ ጥያቄዎችን አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፦ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከምስረታው ጀምሮ ያለው ባህርይ በእርስዎ እይታ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ባርያጋብር፦ ህወሓት በእኔ እይታ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ህዝብ እይታ ያለውና የነበረው ባህርይ ይታወቃል። እዚህ ላይ ባለፉት 27 ዓመታት የሠራቸውን የልማት ሥራዎች ሳንክድ ዴሞክራሲን በማስፈን የህዝቦችን ጥያቄ በመመለስ እንዲሁም በሌሎች የህዝባዊ መብቶች ላይ የሚያሳየው አፈናና ጫና ከባድ ነበር።ይህንንም የሚያደርገው የራሱን ስልጣን ለማቆየትና ለማራዘም ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ቡድን አፈናንና ጭቆናን በመላው ኢትዮጵያ ያድርግ እንጂ የጀመረው የራሴ ከሚላቸው የትግራትይ ህዝቦች ላይ ነው። ህዝቡም ተረግጦ ነው የኖረው። የሚገርመው ነገር ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ከትግራይ ክልል በተሻለ ሁኔታ የመማር ፖለቲካዊ አደረጃጀትን በመፍጠር በኩል ሰፊ ዕድል ነበራቸው፤ ትግራይ ላይ ግን በእነዛ ሁሉ ዓመታት የመማርን ዕድል ያገኙ ሰዎች እንኳን በጣም ጥቂት ናቸው።
የመማር ፖለቲካዊ አደረጃጀትን ካለማግኘትም በተጨማሪ ህዝቡ ከህወሓት ውጪ እንዳያስብም ነው ተደርጎ የኖረው፤ ይህ ደግሞ ህዝቡ ሌሎች አማራጮችን እንዳያይ ኢትዮጵያዊነቱን እንዳያጣጥም እንደሌላው ህዝብ በራሱ ላይ የፈለገውን ውሳኔ እንዳያሳልፍ ሆኖ ቀርቷል።
ህወሓት ሌላው አረመኔያዊ ባህርይው ደግሞ እነዚህም ጥቂት የተማሩ ሰዎች በስልጣኑና በፖለቲካው የሚመጡበት ወይም የመጡበት ከመሰለው አሳድዶ ወይ ከአገር ያስወጣቸዋል አልያም ደግሞ ይገድላቸው ነበር።
በጠቅላላው የተላያዩ ጥያቄዎችን አንስታችኋል የተባሉ የትግራይ ልጆች ያለምንም ፍርድ እስከ አስርና ከዚያ በላይ ዓመት በእስር ቤት ያሳለፉም ብዙ ናቸው፤ የሞቱትንም ቤት ይቁጠራቸው። ይህም ቢሆን ግን መጨረሻው አሁን ያለበት የውንብድና ባህርይው ላይ ደርሷል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሸባሪው ቡድን ከለውጡ በኋላ የተሰጡትን ተደጋጋሚ ዕድሎች አለመጠቀሙ በትግራይ ህዝብ ላይ ይዞት የመጣው አደጋ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ባርያጋብር፦ ይህንን ዕድል ማባከኑማ ከምንም በላይ እኮ የትግርይ ህዝብን ነው እየጎዳ ያለው፤ በትግራይ ህዝብ ላይ ይዞት የመጣው ስቃይና መከራማ ማንንም የሚያሳዝን ብሎም የሚያበሳጭ ነው።
እኔ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ነበርኩኝ። የነበረው ሁኔታ እጅግ ያሳዝናል። ባለፉት 27 ዓመታት በህዝቡ መካከል ተፈጥሮ የነበረው የተስፋ ብርሃን አንድ ቀን ለውጥ እናያለን የሚለው ስሜት እንኳን እንዲጠፋ ነው የሆነው፤ በዚህም የትግራይ ህዝብ በፖለቲካም፤ በኢኮኖሚውም፤ በሌላውም ነገር እንዳይጠቀም ሆነ። ይባስ ብለው እነዚህ አሸባሪዎች ከኤርትራ እህት ወንድሞቹ ጋር ያቃቡት ደም ሳይበቃቸው ከአማራ ቤተሰቦቹ ጋር ደግሞ እንዲናከስ አደረጉት። ይህ የሚያሳየው ቡድኑ በራሱ ሰላም የማይሰማው በመሆኑ ህዝቡም በሰላም ተረጋግቶ ኑሮውን እንዲኖር ሥራውን እንዲሠራ አለመፈለጉን ነው።
በሌላም በኩል አሸባሪው ቡድን በመንግሥት የቀረበለትን “ወደ ሰላማዊ መንገድ ኑና አብረን አገራችንን እናሳድግ” የሚል ጥሪ ያልተቀበለው ስግብግብ በመሆኑና ተደራድሮ በእኩልነት መኖርን እንደ ውድቀት የሚያስብ በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ክልሉንና ህዝቡን ወዳልሆነ ነገር ከመምራቱም በላይ እስከ አሁን ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል።
ሌሎች ክልሎች ላይ ያሉ ወጣቶች ብዙ አማራጭ አላቸው፤ ቢፈልጉ አርሶ አደር ሆነው መኖር ይችላሉ፤ ካልሆነም ከብት ማርባት። ትግራይ ላይ ግን ለመኖር መማር ያስፈልጋል። ምክንያቱ ደግሞ የክልሉ ተፈጥሯዊ ሁኔታና አቀማመጥ ለዚህ ምቹ አይደለም። በመሆኑም ወጣቱ ተምሮ ራሱን እንዳይቀይር ከፍተኛ የሆነ የትምህርት ጥራት ችግር በክልሉ እንዲከሰትም አድርጓል። ይህ ደግሞ ወጣቱ አገሩን ለቅቆ እንዲሰደድ አድርጎታል።
ይህ አልበቃ ያለው አሸባሪው የህወሓት ቡድን ያለፉትን ሦስት የለውጥ ዓመታት ህዝቡን ሲያነሳሳ ብሎም የለውጡን መንግሥት ጥላሸት ሲቀባ ነው የከረመው። ይህ ደግም ለውጡ ህዝቡ ላይ እንዳይሰርጽ ቢያደርግም የለውጡ መንግሥት ግን ዕድል ከሰጠነው ሊለወጥ ይችላል በማለት ብዙ ዕድሎችን ሰጥቷል፤ መጨረሻው ግን ሳያምር ቀርቷል።
በነገራችን ላይ ህወሓት ከነጀሌዎቹ ለውጡን እንዲቀላቀሉ ሰላም ሚኒስቴር፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ባለሀብቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ወዘተ ወደ መቀሌ መጥተው ተማጽኖ ቢያደርጉም የጁንታው ቡድን “ትግራይ ሰላም ነው፤ ሌላ ችግር ወዳለበት ክልል ሂዱ” ብለው ነው በትዕቢት የሸኟቸው።
ይህ ትዕቢት እነሱን ብቻ ሳይሆን ህዝቡን ነው እየጎዳ ያለው። ባለፉት ስድስት ወራት መከላከያ ክልሉ ላይ ስለነበር ህዝቡ ያን ያህል ፍርሐት አልገባውም። አሁን ግን መከላከያም የለም፣ የህዝቡም ሆነ የክልሉ ተስፋ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚያውቅ የለም።
ለምሳሌ እኔ የብልጽግና ፓርቲ አባልና ከፍተኛ አመራርም ነኝ ። እኔ በህወሓት ብገደል ምንም ላይሆን ይችላል ፤ነገር ግን አሁን እነሱ እየገደሏቸው ያሉ ንጹሐን ወጣቶች ምንም የፖለቲካ አመለካካት የሌላቸው ብሎም በፍቃደኝነት ህዝቤን አገለግላለሁ በማለታቸው ብቻ እየተገደሉ ነው። ይህ ደግሞ የቡድኑን አረመኔነትና ምንም የማያስብ መሆኑን እንደውም ሥራው ሁሉ አላማቢስ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያጋጠሙ ዋና ዋና ችግሮች ምን ነበሩ?
አቶ ባርያጋብር፦ በሚገርም ሁኔታ ህዝቡ ለመከላከያ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ነበረው። የዚህ ማሳያው ደግሞ መቀሌ ሳይያዝ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች የሽሬን ህዝብ ሰብስበን ነበርና በዚያ ስብሰባ ላይ ሙሉ የከተማው ነዋሪ ከመገኘቱና ከመደሰቱ የተነሳ አዳራሽ ጠቦን በየትምህርት ቤቱ ተከፋፍለን ህዝቡን ስናወያይ ነበር፤ ከዚያም በኋላ ባሉት ጊዜያት ለመገናኛ ብዙሃንም የሚሰጡት አስተያየት እጅግ አስደሳች ነበር። ይህ እንዳለ ሆኖ ሰላም ሚኒስቴር ያሰለጠናቸው ወጣቶችም ሌሎችም በጣም ብዙ ሥራዎችን እየሠሩ ነበር።
ይህም ቢሆን ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ አራት አምስት ፓርቲዎች እንዲሳተፉ ቢሆንም ትልቁ የትኩረት አቅጣጫው ግን ህዝቡን ማገልገል፣ ሰላሙን መመለስ ከህወሓት ቁጥጥር ነፃ ማውጣት በመሆኑ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ሥራ አልተሠራም። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ድክመት መስሎ ይሰማኛል።
ሌላው ደግሞ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ የነበሩ አብዛኞቹ የህወሓት አመራሮች አልተነኩም ነበር፤ መጨረሻ ላይ ዶክተር አብርሃም ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በሹመኞች በኩል ያለው ሁኔታ ቀይረውታል። ከዚህ በፊት ባለው ግን አመራሩን ለማብቃት ሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ የሆኑ ስልጠናዎችን እስከ አዲስ አበባ ድረስ በማስመጣት ቢሰጥም ወደ ሥራው ላይ ሲኬድ የሚያጋጥሙት የቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎችም የህወሓት አመራሮች በመሆናችው ስልጠናውም ፍሬ አላፈራም ማለት ይቻላል።
በነገራችን ላይ ያለፉትን ሦስት ወራት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀር 16 ሚኒስትሮች መቀሌ ነበሩ፤ ብዙ ሥራዎችንም ሠርተዋል። ይህም ቢሆን ግን መጀመሪያ የተሾመው ጊዜያዊ አስተዳደር የህወሓት አመራር የነበሩትን ባለመንካቱና አሠራሩን ባለማሻሻሉ ውጤት ለማምጣት ሳይቻል ቀርቷል።
በተለይም የጸጥታ ቢሮ ውስጥ የነበረው አሠራር በግሌ እስከ አሁን ያናድደኛል። ምንም ዓይነት ሥራን አይሠሩም፤ ለመሥራትም ፍላጎት አልነበራቸውም። ለዚህ ደግሞ ማሳያው ከፌዴራል መንግሥት የተላከ የዕርዳታ እህል ሁለትና ሦስት መኪና ይሰረቃል፤ የፀጥታ አካላቱ ግን ይህንን እንኳን ተከታትሎ ለመያዝ አይፈልጉም። ሌላው ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ሌብነቶችን ተከታትለን ይዘን ስንሰጣቸው ሁለት ግፋ ቢል ሦስት ቀን አስረዋቸው ገንዝብ ተቀብለው ይለቋቸዋል። በመሆኑም የጸጥታ ቢሮው ከህወሓት ጋር ወግኖ ሲሠራ መቆየቱም ለዚህ ችግር ዳርጎናል።
ሌላው ደግሞ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ አራትና አምስት ፓርቲዎች ይሰባሰቡ እንጂ በባለቤትነት ስሜት መንቀሳቀስ ላይ ትልቅ ክፍተት ነበር። የትግራይ ህዝብንና የጁንታውን ቡድንም የተረዳንበት መንገድም ትክክል አልነበረም። ምክንያቱም ጁንታው ቡድን ከዚህ ቀደምም በነበረው አካሄድ ለህዝቡ 20 በመቶ የእህል ዕርዳታ የሚያቀርብ ከሆነ 80 በመቶውን ፖለቲካዊ ትምህርት ነው የሚሰጠው። በዚህ የተነሳ ደግሞ ህዝቡ ፖለቲከኛ ሆኗል፤ እኛ ደግሞ በዚህ ላይ ትኩረት አድርገን አልሠራንም። ህወሓት ደግሞ ይህንን ድክመታችንን ተጠቅሞበታል። በጎንም በርካታ ፖለቲካዊ ሥራን ሠርቷል። በዚህ ደግሞ የመከላከያ ኃይሉ ደጋፊ የነበረው ህዝብ ለጁንታው ቡድን ከሚሰጠው ዕርዳታ ማካፈል መድሃኒት መላክ ጀመረ።
ደግሜ እናገራለሁ፣ የክልሉ ጸጥታ ቢሮ እንድ ለውጥ ኃይል እራሱን አስቦ ባለመንቀሳቀሱ ብሎም መከላከያን ሊያግዘው ፍቃደኛ ባለመሆኑ መከላከያ በትንሹም በትልቁም ህዝብ ጋር እየደረሰ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥም እንዲገባ አድርጓል። ለምሳሌ የሆነ ነገር ይሰረቃል፤ ጸጥታ ቢሮው ዕርምጃ አይወስድም፤ መከላከያ ይገባል፤ ከወጣቱ ጋር ይጋጫል፤ በዚህ ደግሞ ህዝቡና መከላካያ እንደጀመሩት መቀጠል ሳይችሉ ቀሩ፤ በመካከላቸውም ክፍተት ተፈጠረ። ፖለቲካዊ ኪሳራውም መጣ። የትግራይ ህዝብ ለ30 እና 40 ዓመት የተመኘው ምኞትም ተጨናገፈ፤ ዕድሉም ተበላሸ።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቆራጥ አመራር ያለመስጠት እና የፀጥታ ቢሮው ዳተኝነት ተደማምሮ መከላከያ በሁሉም ነገር እንዲገባ አስገደደው። አንድ ሌባን ለመያዝ ብዙ ሰዎችን ማፈስም ተጀመረ። ይህ ደግሞ ከህዝቡ ጋር አቃቃረው። ጁንታው ቡድን ደግሞ ዕድሉን ተጠቀመበት።
አዲስ ዘመን፦ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር በክልሉ ያለውን ችግር በአግባቡ ተረድቶታል? ይህንን ያልኩት በችግሩ ግዝፈት ልክ የሚናበብ አልነበረም ስለሚባል ነው፤ እርስዎ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ባርያጋብር፦ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራ እየሠራሁ ነው ብሎ ያስብ ነበር። ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ወራት የክልል አመራሮችን በመቀበል ከክልሎች የሚመጡ ድጋፎችን ወደህዝቡ በማከፋፈል እና ሌሎች ሥራዎችን በማከናወን ላይ ቆይቷል። ግን እነዚህ ሥራዎች ጊዜያዊ መሆናቸውና ለእነዚህ ብቻ ትኩረት መስጠቱ ደግሞ ዋጋ አስከፍሎታል።
ለምሳሌ የካቢኔ ስብሰባ እናደርጋል። የምንነጋገረው ግን እከሌ ዕርዳታ ደርሶታል አልደረሰውም የሚለውን ብቻ ነው ፤በእርግጥ ይህ ሥራ በቀጥታ የሚመለከታቸው እንደ ማህበራዊ ቢሮ ግብርና ቢሮና ሌሎችም መሥራት ሲገባቸው ስላልሠሩ ነው ካቢኔውም በዚህን ያህል ደረጃ ወርዶ እየሠራም እያሰበም የነበረው።
እዚህ ላይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ጥንካሬ ምንም እንኳን የሚመጡ ዕርዳታዎች ቢዘረፉም የተረፈውን ግን ህዝብ ጋር ለማድረስ ከፍተኛ የሆነ ጥረትን አድርጓል። በዚህም ብዙ ሰዎችን ከከፋ ችግር መታደግ ችሏል።
እንዳልሽው ጊዜያዊ አስተዳደሩ እሳት የማጥፋት ሥራ ከመሥራት ባለፈ የተናበበ ህዝቡ ጋር ሊደርስ አመለካከቱን ሊቀይር የሚችል ሥራን አልሠራም። ለምሳሌ የፌዴራል መንግሥት ለክልል ምን ዓይነት ድጋፍ እያደረገ ነው የሚለው በፍጹም አልተሠራበትም። ህዝቡም ምንም የሚያውቀው ነገር የለም።
የሚገርምሽ ከተለያዩ የክልል አካባቢዎች ተፈናቅለው መቀሌ የሚገኙ ሰዎች እየመገባቸው ያለው የፌዴራሉ መንግሥት ሳይሆን የመቀሌ ህዝብ ነው የሚመስላቸው። እስከዚህ ድረስ ክፍተት ያለው ሥራ ነው የሚሠራው። አሁን በቅርቡ እንኳን መንግሥት ለትግራይ ክልል ከመቶ ቢሊየን ብር በላይ ዕርዳታን አድርጌያለሁ፤ ሲል ብዙዎች በጣም ነው የደነገጡት፤ አንዳንዶችም የፌዴራል መንግሥት እያገዘን ነበር እንዴ? በማለት ነው የጠየቁት እስከዚህ ድረስ ሥራዎች አልተሠሩም ማለት ነው።
በክልል ቆራጥ የሆነ አመራረ ነበር የሚያስፈልገው። ምክንያቱም ክልሉ ላይ ከሌብነት ግድያ የተለያዩ ወንጀሎች ነበሩ። እነዚህን እንኳን ቆራጥ አመራር ሰጥቶ ለማስተካከል አልተሞከረም። በመሆኑም እንደ እኔ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተጣለበትን ኃላፊነት ተረድቶት ነበር የሚል ግምት የለኝም።
አዲስ ዘመን፦ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሰሞኑን የመከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በህዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ዕርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ይነገራል፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው?
አቶ ባርያጋብር፦ በነገራችን ላይ ህወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጠረው አስተሳሰብ በጣም ከባድ ነው። በዚህ የተነሳ ደግሞ ቀድሞም ሲያስተዳድራቸው በነበረ ጊዜ ያዩትን የሰሙትን ለመናገር እንዲቸገሩ በፍርሐት ውስጥ ጸጥ ብለው እንዲኖሩ አድርጓቸው ቆይቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ላለፉት ሦስት ዓመታት መከላከያ /የአብይ ሠራዊት/ ገዳይ ነው፤ እንድትራቡ ነው የሚፈልገው፤ እያለም ሲጠመዝዛቸው ነው የቆየው። ከዚያ ደግሞ እነ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ከስልጣን ሲወርዱ ለእሱ ትልቅ መጠቀሚያ ሆነ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተደማምረው ደግሞ አሁን ህዝቡ መንግሥትንና ደጋፊዎቹን እንደ ጥላት ህወሓትን ደግሞ የነብሳቸው ጌታ አድርገው ነው የሚያስቡት። በመሆኑም አሁን እኛን አልደገፋችሁንም እያለ ሰዎችን በየሜዳው ሲገድል ህዝቡ ከጠላት ወገን ናቸው ብሎ ነው የሚያስበው እና ምንም እንዳልሆነ ነው እየተ ሰማው ያለው።
እነዚህ ሰዎች ከዚህ ቀደም ያጠፉት ጥፋት ወይም የሰሩት ወንጀል ሳይበቃቸው አሁንም ሌላ ጥፋት ሌላ ህዝብን መበደልና እስከ መግደል የደረሰ አስከፊ ሥራን እየሠሩ ነው። አሁንም የትግራይን እናቶች ልጆቻቸውን እየቀሙ እያስለቀሱ ነው፤ በመሆኑም መንግሥት ምንም እንኳን ብዙ ነገሮችን ሠርቶ እኛ ስላላገዝነው ብቻ ውጤታማ ሳይሆን ቢቀርም አሁንም ግን በትግራይ እናቶች መጨከን የለበትም፤ ከዚህ መከራና ስቃይ ሊያወጣቸው ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ጁንታው መንግሥት ያደ ረገውን የተናጠል ተኩስ አቁም ተከትሎ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን እያስቀመጠ መግለጫዎችን እያወጣ ይገኛል ይህንን እንዴት ያዩታል?
አቶ ባርያጋብር፦ አዎ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታ ዎችን እያስቀመጠ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በህግ ይጠይቁልኝ እያለም ስለመሆኑ እየተሰማ ነው። ይህ ለእኔ ምናልብትም እንደ ጊዜ መግዣ አድርጌ ነው የማስበው። ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት አሁንም ምንም የማያውቁ በትምህርት ያልገፉ ሕፃናትን እየለቀመ ወታደራዊ ስልጠና እየሰጠ ለእሳት እየማገዳቸው ነው። አሁን ከተማ ገብተው አመራርና ንጹሐንን እየገደሉ ያሉትም እነዚሁ ሕፃናት ናቸው። በመሆኑም ይህ የሚያስቀምጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሁሉ ተከታትሎና አጥርቶ የትግራይን ህዝብ ማገዝ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩልም የትግራይ ህዝብ ያለፉትን ሦስት ዓመታት አዕምሮው ላይ ከባድ ሥራ በመሠራቱ አሁን ቀደም ብሎ የሚያስብበት ጊዜ ያስፈልገዋል። ይህንን የምልሽ ለምን መሰለሽ፣ የትግራይ ህዝብ በተፈጥሮው ለመውደድም ለመጥላትም በጣም ጊዜ የሚፈልግ ነው። አሁን ደግሞ ፌዴራል መንግሥቱ የእናንተ ጠላት ነው ተብሎ ተደጋግሞ ስለተነገረው ከዚህ መጥፎ እሳቤ በቶሎ መውጣት ይቸገራል። በመሆኑም መንግሥት አሁንም ትንሽ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል።
ከዚህ በኋላ በተለይ መንግሥት ሙሉ ትኩረቱን በመስጠት ለክልሉ ጉዳይ እልባት መስጠት አለበት፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ጊዜ ባገኙ ቁጥር የመደራጀት ዕድላቸው በጣም ሰፊ ነው። አሁን ላይ ወጣቱ ውስጥ ብዙ ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት ስላለ ይህ ስሜት ደግሞ ጁንታው ሊጠቀምበት ይችላልና መጠንቀቁ አይከፋም።
በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ጁንታው ቡድን እነ ወልቃይትና ሌሎችንም ለድርድር ያቀርባል። ይህ ግን ካለው ነገር ጋር የሚገናኝ ካለመሆኑም በላይ በህግ ሊፈታ የሚችል ነገር ነው። በመሆኑም ህወሓት ድፍን ሠላሳ ዓመት የበደለውን ህዝብ ለመካስ ብሎ ወደሰላሙ ቢመለስ ሁላችንም ፍላጎታችን ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ ክልልና በኤርትራ ላይ የሚያደርገውን ትንኮሳ እንደሚቀጥልበት አስታውቋል፤ በዚህ ደግሞ ትግራይን የግጭት ቀጠና አድርጎ እየሠራ ነው፤ ይህ ምን ያሳያል?
አቶ ባርያጋብር፦ በነገራችን ላይ ይህ ቡድን በጊዜው አልባት እንዲያገኝ ካልሆነ ሌላ ታሪካዊ ስህተት ሊፈጠር ይችላል፤ እስከ አሁን ችግሮች እየተስተዋሉ ያሉት ምናልባትም በመሪዎች ደረጃ ብቻ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ችግሩን በዚህ መቋጨት ካልተቻለ ወደህዝብ ይወርድና የማንወጣው ችግር ውስጥ ሊያስገባን እንችላለን።
እንደሚባለው በአማራና በትግራይ መካከል ችግሮች ከከረሩ ደግሞ ለመላው አገሪቱ የሚያሰጋ እንደሚሆን አስባለሁ፤ መንግሥትም በጥንቃቄ ቢያየው የሚልም አቋም አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ የውጭ ኃይሎች በትግራይ ጉዳይ ላይ የያዙትን አቋም እንዴት ያዩታል? የትግራይ ህዝብንስ መታደግ የሚያስችል ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ባርያጋብር፦ ህወሓትን የሚደግፉ ኃይሎች አሉ፤ እንደ አሜሪካን ያሉ አገሮችም ከጎኑ የቆሙ ይመስላል፤ በመሆኑም መንግሥት በተለይም ህወሓት ማነው የሚለውን ነገር በደንብ ማስረዳት የሚሰጡትን የተዛቡ መረጃዎች ማጥራት ይገባዋል።
በሌላ በኩልም በውጭ አገር ሆነው እየተዝናኑ ጁንታውን በገንዘብና በወሬ እየደገፉ የምዕራባውያኑን ሃሳብ የሚያስቀይሩ አሉ። እነዚህ ሰዎች ፍላጎታቸው ከጁንታው ሲያገኙ የነበረው ጥቅም እንጂ የትግራይ ህዝብን ወደው አይደለም። ይህንን ደግሞ መንግሥት ለዓለም ማሳወቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ አሜሪካን በተደጋጋሚ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ስትወተውት ቆይታ አሁን ደግሞ መከላከያ ሠራዊት መውጣቱ ትክክል አለመሆኑን እየገለጸች ትገኛለች፤ ይህ በእርስዎ እይታ ምን ማለት ነው?
አቶ ባርያጋብር፦ እንደው የመንግሥት ውሳኔ ስለሆነ መቀበል ያስፈልጋል እንጂ አሁን አሜሪካን ስላለችም ሆነ ስላላለች ብቻ በጠቅላላው አሁን የተወሰነው የተኩስ ማቆም ውሳኔ ለህወሓት የሚገባው አልነበረም። ለማንኛውም ግን አሜሪካን በየቀኑ የምትቀያይረው አቋም የራሷ ጉዳይ በመሆኑ ፌዴራል መንግሥት የእሷ የአቋም መዋዠቅ ብዙም ሊያሳስበው የሚገባ አይደለም። በእርግጥ የዲፕሎማሲ ሥራችን መሠራት እንዳለበት እኔም አምናለሁ፤ ግን ደግሞ እነሱ እንዳሻቸው ለሚወላውሉት አቋማቸው የሚረበሽ መንግሥት ግን ያለን አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ባለው ሁኔታ የትግራይ ህዝብ ወደሰላሙ እንዲመለስና ህብረተሰቡም የተረጋጋ ህይወቱን እንዲመራ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
አቶ ባርያጋብር፦ እኔ በበኩሌ አሁን ላይ ህወሓት አይደለም አስተሳሰቡ እራሱ በትግራይ ላይ እንዲኖር አልፈልግም፤ ምናልባት ይህንን አስተሳሰብ የሚያራምዱትን ሰዎች ግን መጨረስ ባንችል እንኳን አስተሳሰቡን ግን እንዳያራምዱ ማድረግ መቻል ያስፈልጋል። ምክንያቱም አስተሳሰቡ በራሱ ፀረ ትውልድና ገዳይ በመሆኑ እንጃ ብቻ እኔ መናገር ይከብደኛል፤ ግን በጠቅላላው ይህ አስተሳሰብ መመታት ያለበት ነው።
በአሁኑ ወቅት ትግራይ ላይ የፖለቲካ ጉዳይ አጀንዳ የሚሆንበት ስለ ስልጣን የሚታሰብበት አልነበረም፤ ሳይፈልግ ችግር ውስጥ የገባውን ህዝብ መታደግ የሚያስፈልግበት ወቅት ነበር። ነገር ግን ይህ ስግብገብ ቡድን ይህንን እያደረገ ካለመሆኑም በላይ ቤት እያንኳኳና እየፈተሸ ንብረት እየዘረፈ ሰዎች እየገደለ ነው።
የትግራይ ህዝብ ብዙ አደናጋሪ ኃይል ያለበት በጣም እንዲፈራ የሆነበት ሁኔታ ስላላ መጀመሪያ ህዝቡን ከዚህ ስሜት ማውጣት ወደትክክልኛው መንገድ ማምጣትና እንደተባለውም ጊዜ መስጠቱ መልካም ነው።
በመሆኑም የትግራይ ህዝብ ህወሓት ከዚህ በኋላ ክልልን ለመምራት የሚያስችል ምንም ዓይነት አቅም የሌለው መሆኑን እንዲረዳ ማድረግ መንግሥትም አጥፊ ሳይሆን ለህዝቡና ለክልሉ ሰላም መሆን ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ መሆኑን ማስረዳት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ባርያጋብር ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2013