በምርምር ሥራ ውስጥ የወንዶችን ያህል የሴቶች ቁጥር ከፍተኛ አይደለም፡፡ ክፍተቱ በዓለም ደረጃ የሚስተዋል ቢሆንም በታዳጊ ሀገሮች ደግሞ የጎላ ነው፡፡ ሴቶች በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብዛት ያላቸውን ያህል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ቁጥራቸው እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በምርምር ሥራ ውስጥ ደግሞ እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ናቸው የሚሳተፉት፡፡ ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም የትምህርት ዕድል ከማግኘት ጀምሮ በብዙ ችግር ውስጥ ማለፋቸው በዋና ምክንያት ይጠቀሳል፡፡
የትምህርት ዕድሉንም ካገኙ በኋላ በቤት ወስጥ የሥራ ጫና ምክንያት ከወንዶች እኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ስለማያገኙ ለብዙዎቹ ውጤታማ አለመሆን መንስዔ ሆኖ ይነሳል፡፡ በጥረታቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የደረሱትም ቢሆኑ ቤተሰብ ሲመሰርቱ ልጅ ወልዶ በማሳደግና የቤተሰብ ኃላፊነትን የመወጣት ጫናው ከምርምር ሥራው እንዲርቁ ያደርጋቸ ዋል፡፡ ለዚህም ነው እንደፈረንጆች አቆጣጠር ጥቅምት 2ቀን2018 ከሦስት ተመራማሪዎች መካከል በፊዚክስ የኖቤል ሽልማት የወሰደችው እንስት መነጋገሪያ የሆነችውና እንደ ብርቅ ታይታ ሰፊ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን የተሰጣት፡፡
የኖቤል ተሸላሚዋ ዶክተር ዶና ስትሪክላንድ (Donna Strickland) በካናዳ ሀገር በሚገኘው ዋተርሉ (Waterloo) ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስና በአስትሮኖሚ የትምህርት ዘርፎች ረዳት ፕሮፌሰር ናት፡፡ እንዲህ መነጋገሪያ ሆና የብዙዎችን ቀልብ የሳበችው ከሁለት ወንዶች መካከል ብቸኛና ከ55ዓመታት በኋላ በፊዚክስ የኖቤል ሽልማት ሦስተኛዋ ሴት ተሸላሚ በመሆኗ ነው፡፡ ለሽልማት ያበቃት ዘርፍም በጨረር ለሚካሄድ ህክምና የሚረዳ የ«laser physics» የምርምር ውጤት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከእርሷ በፊት የተሸለሙት ሁለቱ ሴቶች እ.ኤ.አ. በ1903 እና በ1963 በተካሄደው የኖቤል ሽልማት ያሸነፉ ናቸው፡፡
ዶክተር ዲና እስከዛሬ ተሸላሚዎቹ ሦስት ሴቶች ብቻ መሆናቸው ቢያስደነግጣትም ከእነዚህ መካከል አንዷ ለመሆን መቻሏም ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷታል፡፡ በአንድ ላይ ሆነውም በልዩ ሁኔታ ማክበር እንዳለባቸውና ሴቶች መበረታታት እንደሚገባቸው ሀሳብ ሰጥታለች፡፡
በምርምሩ ዘርፍ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የሴቶች ተሳትፎ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴውን አሳስቦታል፡፡ በተለይም የኖቤል ፋውንዴሽን ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ጎራን ሀንሰን «Goran Hansson» ላለፉት ዓመታት ሲሸለሙ የነበሩት ወንዶች ብቻ እንደነበሩ መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ብዙ ሴቶችን ማሳተፍ እንደሚያስፈልግና በዚህ ላይም የሚችሉትን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
በእ.ኤ.አ. በ1959 በካናዳ ቶሮንቶ የተወለደችው ዶክተር ዲና በግሏ ድረ ገፅ አለመኖሩ አነጋግሯል፡፡ በዚህም ስለግለህይወቷ በጽሁፍ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ሽልማትዋን አስመልክቶ የዘገቡት የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ይህንንም ክስተት በተለየ ሁኔታ አይተውታል፡፡ የኖቤል ሽልማቱ በየዓመቱ « ዘ ሮያል ስዊዲሽ አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ» በሚባል ተቋም የሚካሄድ መሆኑንም የመረጃ ምንጮቹ ያመለክታሉ፡፡
ምንጭ፡- ቢ.ቢ.ሲ.