የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት በሚዳፈር መልኩ በሀገሮች ጉዳይ እጅን መስደድ ከዚያም አለፍ ሲል ጥቃት መሰንዘር ወይም እንዲሰነዘር ማድረግ በዓለማችን በእጅጉ ተለምዷል። ይህ ደግሞ የሰለጠኑ ፣ ነገሮችን ይመዝናሉ፣ ያደጉ የበለጸጉ በሚባሉ ሀገሮች ነው ሲፈጸም የሚታየው፡፡
በዚህ በኩል ምዕራባውያን የሚታወቁ ቢሆንም ልእለ ኃያሏ አሜሪካን የሚደርስባት ግን የለም፡፡ አሜሪካ ክፍለ አህጉሮችንና ሀገሮችን አቋርጣ የአሜሪካ ጥቅሞች አሉባቸው ባለቻቸው ሀገሮች ጉዳይ ጣልቃ ትገባለች፡፡ ይህ ብቻም አይደለም የአሜሪካን ጥቅሞች እየጎዱ ነው ባለቻቸው / ጥቅም የሚባለው መኖር አለመኖሩ ባልታወቀበት ሁኔታም ጭምር/ ሀገሮች፣ ቡድኖች ወዘተ ላይ በማነጣጠርም ጥቃት ትሰነዝራለች፡፡ በዚህም በርካታ ሀገሮች ፈርሰዋል፤ ዜጎቻቸውን ለሞት ለስደት ለደህነት ተዳርገዋል፤ ዕርዳታ ጠባቂ ሆነው ቀርተዋል፡፡
ኑክሌር መታጠቅ ወይም ለመታጠቅ መሞከር የዓለምን ስጋት እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑ ይገባኛል፡፡ ማን ይታጠቅ? ማን አይታጠቅ? የሚለውን መወሰን ያለበት ግን ማነው? ልእለ ኃይሏ አሜሪካ ግን ሁሌም ይህ ጉዳይ ያገባኛል ትላለች፡፡ በደግ ጎኑ ከሆነ ያግባት ግድ የለም፡፡
እሷ ኒውክሌር እየታጠቁ ነው ታጥቀዋል ያለቻቸውን ሀገሮች አፍርሳለች፤ አንዳንዶቹን ደግሞ በማእቀብ ሽባ አድርጋለች፡፡ ፀሐይ ስለሞቃቸው የአሜሪካ የጣልቃ ገብነት እርምጃዎች ነው እየጠቀስኩ ያለሁት፡፡ ኑክሌር አላት ብላ ያፈረሰቻት ኢራቅ ኑክሌር እንዳልነበራትና እርምጃው በስህተት እንደተፈጸመ ከዓመታት በፊት አንድ የሀገሪቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መግለጻቸውን ከመገናኛ ብዙሃን የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ በዚያ እርምጃ ኢራቅ እንደ ጧፍ ነዳለች፤ ፈርሳለች፡፡
ምእራባውያኑ መንግሥታት በጦር ቃል ኪዳናቸው /ኔቶ/ አማካይነት ሊቢያን እንደ እባብ ቀጥቅጠዋል፤ ሀገሪቱን ኦና አስቀርተዋታል፡፡ በዚህ ውስጥ የአሜሪካ ሚና ጉልህ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኢራንንም ከኑክሌር መሳሪያ ጋር በተያያዘ አንዴ በማእቀቦች ሌላ ጊዜ የተለያዩ እጆችን በመጠቀም ሰንጋ ይዛታለች፡፡ የሶሪያ ፣ የየመን እና ሌሎች ሀገሮች እስከ መበተን መድረስም ምክንያቱ የጣልቃ ገብነት ነው፡፡
ይህን የተመለከቱ ታዲያ አሜሪካ ምን አገባት ፤ ማን የዓለም ፖሊስ አረጋት ፤ለምንድነው ክፍለ አህጉር፣ ሀገር አቋርጣ ሀገሮችን የምታፈርሰው፣ ልጆቻቸውን የምትጨርሰው ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ጥያቄው ፊትም ይጠየቅ ነበር ፤ ዛሬም እየተጠየቀ ነው፡፡
ሀገሪቱ ጥቅሜ ተነክቷል ካለች ዛሬውኑ የትኛውም ሀገር ትገባለች፡፡ ከልካይ የለባትም፡፡ ጥቅምሽ የታለ ብሎ የሚጠይቃትም የለም፡፡ ቢጠይቃትም ጉዳይዋ አይደለም። በተለያዩ የዓለም ክፍሎችና ሀገሮች አሉኝ የምትላቸውን ጥቅሞቿን ለመጠበቅ ሀገሮችን ማፍረስ ፣ ዜጎቻቸውን መጨፍጨፍ አለባት ወይ? ሌላ ጥቅሞቿን የማስጠበቂያ መንገድ የለም ወይ? የሚሉት ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
እሺ ይህ ይሁን እንበል፤ ለማለት ያህል፡፡ ይህ ጥቅም አለ ተብሎ በማይታሰብበት ቢኖርም እንኳ እዚህ ግባ በማይባልበት ሀገር እየገባች የምትፈተፍተውስ ለምንድን ነው? እስቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን የሚጠቀስ ኩባንያ አላት። እሺ ይኑር እንበል፤ ኩባንያዬ የምትለው ምኑ ተነክቶ ነው ኢትዮጵያን ይህን ያህል ሰነጋ የያዘቻት?
ሀገሪቱ ጎንበስ ስል ጎንበስ ፣ ቀና ስል ቀና አላሉም የምትላቸውን ሀገሮች ለመጉዳት መንግሥቶቻቸውን ለማንሳት ስታስብ አስቀድማ ጦር ጭና አትመጣም፤ ከጎን ባላገራ ታበቅልባቸዋለች፡፡ ተቃዋሚ መደገፍ የተካነቸው እኩይ ተግባር ነው፡፡ ለእዚህ ስትል ሰይጣንንም ቢሆን ታሰልፋለች፡፡
ለትህነግ ድጋፍ እያደረገች ያለችበት ሁኔታም ከዚህ አይለይም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የአሜሪካ መንግሥት ትህነግን እንደ ጥቅሙ፣ ኩባንያው ቆጥሮ ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ ከፍቷል ማለት ይቻላል፡፡ ሀገሪቱ ጥቅሜ የምትለውን ለማስከበር ምን ያህል ርቀት እንደምትሄድ ለትህነግ እየሰጠች ያለችው ድጋፍ በግልጽ ያመለክታል፡፡
የትህነግ የክፋት ጥግ በሚገባ ይታወቃል፡፡ አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ፣ የኢትዮጵያን መንግሥትና ህዝቦች ለ27 ዓመታት ግጧል፡፡ ትህነግ ከለውጡ መንግሥት አፈንግጦ በመውጣትም በዚህች ሀገር ላይ ያልጠነሰሰው ሴራና ያልወሰደው ዕርምጃ የለም፡፡ በተላላኪዎቹ በመጠቀም ሕፃን፣ ሴት፣ አዛውነት ሳይቀሩ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲጨፈጨፉ አርጓል፡፡ ይህ በየሳምንቱ ይፈጸም የነበረ ድርጊት ነው። ሁኔታውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአንድ ወቅት ሲገልጹ ኢትየጵያውያን ካንዱ ለቅሶ ሳይነሱ ለሌላ ለቅሶና ዋይታ ይዳረጉ እንደነበር ማስታወቃቸውን አስታውሳለሁ፡፡
ሀገራችን በታሪኳ ተሰምቶ በማያውቅ መልኩ በሀገር ውስጥ መፈናቀል ከእነ ሶሪያ ተርታ እስከ መሰለፍ የደረሰችው በእነዚህ የግጭት ወቅቶች ነበር፡፡ ይህን ሁሉ እያደረገ መንግሥት የሕግ የበላይነት ሊያስጠብቅ አልቻለም ፤ በትግራይ ክልል ኮሽታ የለም፤ የተቀረው አካባቢ ጉዳይ ያሳስብኛል ይለን ነበር፡፡ ራሱ ምን ብሎ ራሱ አለቀሰ እንደሚባለው፡፡
ህዝብ የመንግሥት ያለህ አለ፡፡ መንግሥት መንግሥት አልሸት አለ ፤ አረ የህግ የበላይነት ይጠበቅ ሲል በየመድረኩ በየመገናኛ ብዙሃኑ ጮኸ፡፡ መንግሥት መከላከያ ሠራዊትን ጭምር እያሰማራ ኮማንድ ፖስት እያቋቋመ ችግሩን ለመፍታት ባከናወነው ተግባር ውጤታማ ሥራ ቢሠራም ዘላቂ መፍትሔ ግን ማምጣትን የግድ ይል ነበር፡፡
ይህን ሁሉ የሚሠራው ማን እንደሆን መንግሥት በሚገባ ያውቅ ነበር፡፡ ችግሩን ከሰንኮፉ እንቀላለሁ ፤ እመኑኝ ሲልም ቆየ፡፡ ቡድኑ በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የመከላከያ ሠራዊቱ በወሰደው ዕርምጃ ያ ጦርነት የባህል ጨዋታችን ነው ያለው ቡድን እንደ ጉም በነነ፡፡ ከአውራዎቹ ጥቂቶች ሲተርፉ የተቀረው በወረንጦ ተለቀመ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀርቶ ለመገናኛ ቴክኖሎጂ ብዙም ቤተሰብ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ሳይቁሩ ያውቃሉ፡፡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ምዕራባውያኑ በሙሉ በሀገሪቱ የሆነውን በሙሉ ያውቃሉ። አብዛኞዎቹ ችግሮች በእነሱ ስፖንሰር አድራጊነት የተፈጠሩ አይደሉም ተብለው የሚታሰቡ አይደሉም፡፡ የእነዚህ ኃይሎች ጫና እየበረታ የመጣውም ይህ ቡድን እንደ እባብ ተቀጥቅጦ ዋሻ ከገባ በኋላ ነው፡፡
እነዚህ ኃይሎች ይህን ያህል የደከሙት ጠንካራ ኢትዮጵያን ማየት ስለማይፈልጉ ነው፡፡ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትኖር ለማድረግ ደግሞ ዴሞክራሲን ያመጣል የተባለውን ምርጫ ማኮላሸት፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተጓጎልን አጠናክረው ቀጠሉበት፡፡
ለእዚህ ደግሞ በቀጥታ እነሱ መምጣት አይችሉምና ማን ይሻላል ሲሉ አሸባራውን ትህነግን እንደ መሳሪያ ይጠቀሙበት ጀመር፡፡ ቡድኑን ያስቀመጡትም እነሱ ነበሩ፤ ፊትም የእነሱ አጀንዳ አስፈጻሚ ነበር፤ ፊቱንም ለኢትዮጵያ የቆመ ሳይሆን፣ ትግራይን ነፃ ለማውጣት የሚዘጋጅ ቡድን ነበርና ፍላጎታቸው ሰመረ፡፡ ቡዱኑ የግጭት ነጋዴም ነውና ነገን ማሰቡን ትቶ ኢትዮጵያን ለመበታተን ወይም ደካማ የሚያደርጋትን የእነዚህን አካላት አጀንዳ ማስፈጸሙን ቀጠለበት፡፡
ይህም ማስፈጸም ውስጥ መግባት የአሜሪካ ኩባንያ ከመሆን ምን ይለያል ታዲያ፡፡ አሜሪካ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን መንግሥት ጥላ እንዴት ብታስበው ኢትዮጵያውንን ለእዚህ ሁሉ ምስቅልቅል የዳረገን አሸባሪ ቡድን በመደገፍ ይህን ያህል ትንቀሳቀሳለች?
የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመጉዳትና ኢትዮጵያ ቀና እንዳትል ለማድረግ ሲባል አሸባሪን ለእዚህ እኩይ አላማ ከጎን ማሰለፍ ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በግፍ የጨፈጨፈን፣ የሀገር ሉአላዊነት እንዲደፈር ያረገን ቡድን ሞቶ ከተቀበረበት አስወጥታ እስትንፋስ ዘርታ ከጎኗ ማቆሟ አሸባሪን ኩባንያ እና ጥቅሟ አርጋ ቆጥራለች እንደማለት ነው፡፡
ዘካርያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2013