መርጠናል..ደስ በሚልና የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ሊወስን በሚችል መልኩ ሀገራዊ ምርጫ አድርገናል። ቀጣዩ ሂደት ይሄን ብዙዎችን ያሳተፈውንና በአይነቱ ልዩ የሆነውን የምርጫ ውጤት በጸጋ መቀበል ይሆናል። እንደሚታወቀው በውድድር ዓለም ውስጥ ማሸነፍና መሸነፍ ያለ ነው፡፡ ወደ ውድድር ስንገባ በአቋማችን ልክ፣ ለሀገርና ህዝብ በሰነቅንው ራዕይ ልክ ወይ እናሸንፋለን አሊያም ደግሞ እንሸነፋለን፡፡ በዚህ እውነት ውስጥ በመኖር የምርጫ ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል ራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል እላለሁ። በምርጫ ሰሞን ያሳየንውን ጨዋነት በውጤቱም ላይ መድገም አለብን፡፡ እኔ ሲገባኝ የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲ አላማ አንድ ነው እርሱም ሀገርና ህዝብ ነው፡፡ አላማውን ሀገርና ህዝብ ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ ደግሞ በምርጫ ውጤት ሳቢያ በሀገርና ህዝብ ላይ የሚደርስን አላስፈላጊ ጥፋት ይከላከላል እንጂ አያባብስም። ህዝብ እንዲመርጥ፣ ህዝብ እንዲወስን ስልጣን እስከሰጠን ድረስ ውጤት ያጣላናል ብዬ አላስብም፡፡ የምንወዳደረው ሀገር ለማሻገር እስከሆነ ድረስ ከአሸናፊ ፓርቲ ጋር ተጋግዞ መስራት ያቅተናል ብዬ አላስብም። አሸነፍንም ተሸነፍንም ለሀገር በጎ ነገር መስራት እንችላለን፡፡
ለሀገር በጎ ነገር ለመስራት የግድ መንግስት መሆን አይጠበቅብንም፡፡ አላማውን ሀገርና ህዝብ ያደረገ ፓርቲ እኔ ካላሸነፍኩ በሚል በድሀ ወገኑ ላይ ሞትን አያውጅም፡፡ የሰሞኑ የምርጫ ሂደት ለህዝብ ቅድሚያ የሰጠ፣ ሁሉም ፓርቲዎች በእኩልና በአስተማማኝ መንገድ ቅስቀሳ ያደረጉበት በመጨረሻም በታላቅ ህዝባዊ ተሳትፎ ውጤት የታየበት ምርጫ ሆኖ አልፏል፡፡ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ፖለቲካ ፓርቲዎች ያደርጉት አስተዋጽኦ በእጅግ የሚደነቅ ነው፡፡ በዚህ የመምረጥና የመመረጥ ስርዓት ውስጥ ህዝብ የማያውቀው አንድም ነገር አለ ብዬ አላስብም። የመረጠው ህዝብ ነው ውጤቱም የህዝብ እንደሆነ በማመን ለአሸናፊ ፓርቲ ክብርና እውቅና መቸር ይገባል። የህዝብ ጽምጽ ደግሞ አሽናፊና ተሸናፊ የሚለየበት ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ያሳዩትን ጨዋነት በማስቀጠል ውጤቱንም በጸጋ መቀበላቸው የዲሞክራሲ መሠረት የሚጥል ይሆናል ባይ ነኝ፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ መንግስትና ተፎካካሪ ፓርቲ ያመኑበትን ህዝባዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ አድርገናል። ውጤቱም በዚህ ልክ የተቃኘ እንደሆነ ተጠራጣሪ አለ ብዬ አላስብም። ውጤት ታከው ነውጥ የሚፈጥሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካሉ ድሮም አላማቸው ሀገርና ህዝብ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ውጤትን በጸጋ መቀበል የፖለቲካ ፓርቲ ግዴታ ብቻ ሳይሆን የህዝብም ግዴታ ጭምር ነው፡፡
የኢትዮጵያ የመንጋት ዘመን ላይ ቆመው ምክንያት እየፈለጉ ችግር መፍጠር ሀገር ከመሸጥ ባንዳነት ተለይቶ አይታይም፡፡ በምርጫም ሆነ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውሸትና ማስመሰል በቃን ብለን ለጋራ ለውጥ በጋራ በተነሳንበት ብርሃናማ ሰሞን ላይ ወደ ኋላ መመለስ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ ወደፊት በሚያስኬዱን ጉዳዮች ላይ መበርታት እንጂ ወደ ኋላ በሚመልሱን ነገሮች ላይ አንባክንም።
በታላቅ ልዕልና መርጠናል፣ የምርጫ ውጤታችን ንም በሰላማዊ መንገድ እንጠብቃለን፡፡ ይሄ ሀገርና ህዝብን ከፊት ያስቀደመ ሁሉ ሊከተለው የሚገባ ህይወታዊ መርህ ነው፡፡ ታይቶ በማይታወቅ ህዝባዊ ተሳትፎ ህዝብ የሚሆነውን በመረጠበት በዚህ የለውጥ ማለዳ ላይ ሆነን በምርጫ ሰበብ ዳግም ህዝብና ሀገር የምናወናብድበት ሞራል ላይ አይደለንም፡፡ ስንወዳደር አንድም ለማሸነፍ አንድም ደግሞ ተሸንፈን ልምድ ለማግኘት ነው፡፡
በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲ ህዝብ እንደመረጠውና እድል እንደሰጠው ሊያውቅ ይገባል፡፡ ያልተሳካለት የፖለቲካ ፓርቲም በማናቸውም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ለራሱም ሆነ ለወገኑ የተሻሉ እድሎችን መፍጠር ይችላል፡፡ አሸነፍን ማለት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ቦታ የለንም ማለት አይደለም፡፡ ተሸነፍን ማለትም በሀገር ጉዳይ ላይ አያገባንም ማለት እንዳይደለ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ መሸነፍን የምንረዳበት መንገድ የተሳሳተ ሆኖ እንጂ በመሸነፍ ውስጥ ያለውን ሀይልና ጉልበት ልንረዳ ይገባል፡፡ ደግሞም ሀገርና ህዝብን በጥሩ መንፈስ ሊመራ የሚችል ተሸንፎ ያሸነፈ ነው።
ጉዳዩን ሀገርና ህዝብ ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ መሸነፍ ምኑም ነው፡፡ ሽንፈታችንን በጸጋ በመቀበል ካሸናፊው ፓርቲ ጋር ተግባብተንና ተስማምተን ለጋራ ጥቅም በጋራ የምንሰራበትን ጥበብ ማበጀት እንጂ እኔ ካላሸነፍኩ በሚል ኋላ ቀር አመለካከት ተስፋና ራዕያችንን ማበላሸት አይኖርብንም፡፡ ካለፈው መማር አለብን፡፡ ያለፉት ምርጫዎች በህዝብ ስነ ልቦና ላይ ያሳደሩት ተጽዕኖ ምን ያክል እንደሆኑ የምታውቁት ታሪክ ነው፡፡ ሀገርና ትውልድ ከሚያበላሽ ከዚህ ኋላቀር እሳቤ መውጣት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ፓርቲ ያስፈልገናል ባይ ነኝ፡፡
በቅንነት ከተራመድን አሸነፍንም ተሸነፍንም ለሀገራችን የሚሆን ብዙ ነገሮች አሉን፡፡ ይሄ የሚሆነው ግን ሽንፈትን የምናይበት እይታ መስተካከል ሲችል ነው፡፡ መሸነፍ ማለት መክሰር እንደሆነ አምነን ከተቀብለን በመሸነፋችን ባለፈ ለሀገራችንም ሆነ ለራሳችን የምናመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡ መሸነፍ በቀጣይ ተስተካክሎ መምጣት ነው፡፡
መሸነፍ በብዙ ልምድና በብዙ እውቀት ለሌላ ድል መዘጋጀት ነው፡፡ አስተዋዮች ሽንፈታቸውን በጸጋ በመቀበል ለሌላ ለውጥና ስኬት ይዘጋጃሉ እንጂ ለምን ተሸነፍኩ በሚል እሳቤ በድሃ ህዝባቸው ላይ ጥፋት አይሰሩም፡፡ ለማሸነፍ መበርታትና ተቀባይነት ያለውን ሀሳብ ማፍለቅ ትልቁ የቤት ስራ ነው፡፡
በዚህ እሳቤ ውስጥ በመመላለስ በተሰማራንበት የሙያ መስክ ሁሉ ውጤታማ ስራ ማከናወን ይቻለናል እላለሁ፡፡ ደግሞ እንደሚታወቀው ሀገራችን ከፊቷ በርካታ ብርሀናማ ነገዎች እየጠበቋት ነው፡፡ እኚህ ብሩህ ነገዎቿ ይፈኩ ዘንድ ህዝብ የመረጠውና በህዝብ ዘንድ ይሁንታ ያገኘ መንግስት ግድ ይላታል፡፡ ለለውጥ በተጋ መንፈስ ኢትዮጵያ ሊመራት የሚችለው አሸናፊ ፓርቲ ነው፡፡ የምርጫ ውጤት ደግሞ ለሀገራችን ይዞት የሚመጣው በረከት ብዙ ነው፡፡ ውጤቱ ተቀብሎ ከመገፋፋትና ከመተቻቸት ወጥተው አሸናፊውም ሆነ ተሸናፊው ፓርቲ በአንድነትና በቅንጅት ለድሀ ሀገራቸው በጋራ ቢሰሩ መልካም ነው ባይ ነኝ፡፡ በእያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ሀገር ሊለውጡ የሚችሉ በርካታ ሀሳቦች አሉ፡፡ በእኚህ አዎንታዊ ሀሳቦች የማትፈርስ ሀገር እንገንባ እላለሁ፡፡
እንደሚታወቀው ከዚህ በፊትም እንዳየነው በምርጫ ውጤት ላይ በርካታ ጉዳቶች በሀገር ላይ ደርሰዋል፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ተዓማኝና ፍትሀዊ ምርጫ ባለመካሄዱ ነበር፡፡ ስድስተኛው ምርጫ ግን በብዙ ነገሩ ካለፈው የተሻለ ስለሆነ እንደዚህ አይነት ክፍተቶች ይፈጠራሉ ብሎ ማሰብ የማይታሰብ ነው። በታላቅ ክብር በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንደመረጥን ሁሉ ውጤቱንም በጸጋ መቀበል ግዴታችን ነው። የምርጫ ውጤቶችን በጸጋ መቀበል ህዝብና ሀገርን በታማኝነት ከማገልገል ለይቼ አላየውም፡፡
ምርጫን በጸጋ መቀበል የእውነተኛ ፓርቲ ባህሪ ነው ብዬ አስባለሁ። እንዲያውም ኢትዮጵያን ብለውና ራሳቸውን ብለው የተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚለዩበት ነው እላለሁ፡፡ ለዚህም ነው ከምርጫ በፊት ያሳየናቸው ህዝባዊም ሆነ መንግስታዊ ጨዋነት የምርጫ ውጤት በመቀበል መደገሙ የላቀ ዋጋ አለውና ጨዋነታችን በዚሁ መቀጠል አለበት ስል አደራ እላለሁ፡፡ እጅግ በሚያኮራና ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ እንደመረጥን ሁሉ የምርጫ ውጤቱንም በዚህ ስርዓትና ጨዋነት ውስጥ ለመቀበል ያሳየነው ተነሳሽነት ለወደፊቱ ምርጫ መሠረት የጣለ ነው፡፡
ከምርጫ መልኮች ውስጥ አንዱ ማሸነፍና መሸነፍ ነው፡፡ ከምርጫ ባህሪያት ውስጥ አንዱ ያሸነፈን መርቆና አወድሶ መልካም እድል ተመኝቶ መለየት ነው፡፡ ሀገር ለመምራት ፓርቲ አቋቁሞ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት ይሄ ይጠፋዋል ብዬ አላስብም።
በእኛ ሀገር ሲሆን ግን ይሄ ሌላ ነው፡፡ አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ለማሸነፍ ብቻ ሲሉ የሚወዳደሩ ናቸው። ከእነሱ የተሻለ በህዝብ ይሁንታ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመጣ ከማድነቅና ከማበረታታት ይልቅ በወቀሳና በነቀፋ ሆድና ጀርባ መሆንን የሚመርጡ ናቸው፡፡ ምርጫ ከንግግር ባለፈ የሀሳብ የበላይነት የሚያይልበት በማሸነፍና በመሸነፍ፣ በመብለጥና በመበለጥ የተቃኘ ሂደት ነው።በዚህ የሀሳብ ፍጭት ውስጥ በሀሳብም ሆነ በተግባር የላቀ ያሸንፋል፡፡ በዚህ የምረጡኝ ቅስቀሳ ውስጥ በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያገኘ እርሱ መንግስት ይሆናል።ምርጫ ከዚህ የዘለለ ተልዕኮ አለው ብዬ አላምንም፡፡ እርግጥ ባሳለፍናቸው አምስት የሚሆኑ ሀገራዊ ምርጫ ላይ ያየናቸው በርካታ ስህተቶች ነበሩ፡፡ እኚህ ስህተቶች ለሀገር እዳ ሆነው በህዝብና በመንግስት መካከል፣ በገዢውና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ጠብንና መለያየትን የፈጠሩ ሆነው ያለፉ ናቸው። የዘንድሮው ምርጫ ግን ስልጣንን ለህዝብ የሰጠ፣ ሁሉንም ተፎካካሪ ፓርቲ በእኩል ደረጃ ያሳተፈ ምንም አይነት የማስመሰል ድርጊቶች ያልተስተዋሉበት በሁሉ ነገሩ የሰመረ ምርጫ ነበር፡፡ አብዛኞቻችን መሸነፍ እንዳለ የማናውቅ ነን። ውጤትን አምኖ ለመቀበል በሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የታየው ጨዋነት ሊቀጥል የሚገባው ነው፡፡
እንደሚታወቀው ካለፈው የምርጫ ሂደትም እንደታዘብንው ከሆነ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሽንፈትን የማይፈልጉ ናቸው፡፡ ስር በሰደደ እኔነት ተውጠው እኔ ካልመራሁ እኔ ካላሸነፍኩ ሀገር ሰላም አታገኝም በሚል አጉል አመለካከት ህዝብ የሚያውኩ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እናውቃለን።ስልጣን የህዝብ ነው እያልን ህዝብ ያልመረጠው ፓርቲ መንግስት መሆን አይችልም እያልን፣ አይተን በማናውቀው ድንቅ የምርጫ ሂደት ውስጥ ተሳትፈን ውጤትን በጸጋ የማንቀበል ከሆነ ልፋታችን ትርጉም አይኖረውም። ለህዝብ ስልጣን እስከሰጠን ድረስ ውጤቱ ምንም ሊሆን ይችላል። ከገዥውም ሆነ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚጠበቀው ትልቁ ነገር ውጤትን በጸጋ ተቀብሎ በመመሰጋገንና በመጨባበጥ መለያየት ነው።
ከዚህ ባለፈ ውጤትን ተከትሎ የሚመጣ ማንኛውም ረብሻ ሀገርና ህዝብን ከማወክ ባለፈ ፋይዳ አይኖረውም። በእውን እንዳየነው የምርጫ ስርዓቱ ለህዝብ ቅድሚያ በሰጠ አካሄድ ተጀምሮ የተጠናቀቀ ነው፡፡ ምንም አይነት ቅሬታዎች እንዳይነሱበት ጤናማነት በተላበሰ መልኩ በብዙ ከጅማሬው እስከ ፍጻሜው ድረስ የተጓዘ እንደሆነ አይተናል፡፡ በታሪካችን ምርጫን ተከትለው በመጡ ውጤትን በጸጋ ያለመቀበል አባዜ በርካታ ጥፋቶች ደርሰውብን ብዙ ነገሮች ተበላሽተውብናል። ይሄ ታሪካዊ ስህተት እንዳይደገም ፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን ከማነሳሳትና መሰረት የሌለው ያልተገባ አካሂዶችን ከመጠቀም መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለማሸነፍ እንደተወዳደሩ ሁሉ መሸነፍም እንዳለ ማወቁ በሀገርና ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ይሽራል እላለሁ፡፡ ከትላንት እስከዛሬ ሀገራችን ላይ የተፈጠሩ ጥፋቶች ሁሉ ለራስ ቅድሚያ በመስጠት የተፈጠሩ ናቸው፡፡ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ተወዳድረን ለማሸነፍ ወደ ፖለቲካው ሜዳ ስንገባ ከእኔነት ወጥተን ሀገርና ህዝብን ማስቀደም ይኖርብናል፡፡ አላማችን አሸንፈን ሀገርና ህዝብን ማሻገር ከሆነ አይደለም በእኔነት ስም ችግር ልንፈጥር ቀርቶ በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰው እያንዳንዱ ነገር የሚያመን ነው የሚሆነው፡፡ ችግሩ ግን ስንወዳደርም ሆነ የምረጡኝ ቅስቀሳ ስናደርግ ከሀገርና ህዝብ ይልቅ ለራስ ክብርና ስም ትልቅ ቦታ የሰጠን መሆናችን ነው፡፡ አላማው ሀገርና ህዝብ የሆነ በሀገሩ ላይ ምንም ነገር እንዲደርስ አይሻም፡፡ በታማኝ ምርጫና በታማኝ ውጤት ሀገር ለማሻገር ይሄ ትክክለኛ ጊዜያችን ነው፡፡ ለዚህም ነው ምርጫ ቦርድ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት የስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ውጤት ይፋ አድርጓል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጤቱን በፀጋ በመቀበል የተሰጣቸው የህዝብ ድምፅ ማክበራቸውን የገለጹበት ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ውጤቱን ከመቀበል ባሻገር ሀገራችን ወደፊት አንድ እርምጃ የሚያሻግር ተግባር በመሆኑ ሊቀጥልና ሊበረታታ የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ቸር ሰንብቱ።
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2013