በሕይወታችን በበሽታም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ከተፈጠረው ችግር ይበልጥ ለዚያ በሽታ ወይም አጋጣሚ ያለን ግንዛቤ አናሳ ከሆነ በቀላሉ ተስፋ እንድንቆርጥና ከባድ ህይወት እንድናሳልፍ ያደርገናል።በተለይ ደግሞ በኢኮኖሚና በስልጣኔ ብዙም ያላደጉ ሃገራት የተለያዩ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በቀላሉ ሲያጠቃቸው እና በተጠቁበት አጋጣሚም የእውቀት ማነስ ይሁን ለማወቅ ዝግጁነት አለመኖር ይበልጥ በሽታው ተሰራጭቶ ማህበረሰብንና ሃገርን ሲጎዳ ይታያል።ቫይረሱን በተመለከተ በኢፌዴሪ የኤች.አይ.ቪ.ኤድስ መከላከያና መቆጣጠርያ ፅህፈት ቤት የማይታይ መጠን = የተገታ መተላላፍ ‹‹የ-የ›› በሚል
ፅንሰ ሃሳብ ላይ ለጋዜጠኞች ከሰጠው ስልጠና ያገኘነው መረጃ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ኢንፌክሽን በዓለም ላይ ከታየበት ወቅት ጀምሮ ብዙ የማህበረሰብ ክፍልን ያጠቃ ሲሆን፤ በየጊዜው የሚደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ስርጭቱ እንዲቀንስ እንደተደረገ የሚታወቅ ነው።ነገር ግን ቀንሷል ባልን ቁጥር ማህበረሰቡ ላይ የሚታየው ቸልተኝነት እንደ አዲስ እንዲያንሰራፋ በር የሚከፍት ሆኗል።መድሃኒት ማግኘት በዓለም ላይ የሚደረግ ምርምርና ጥረት እንዳለ ሆኖ በየጊዜው የሚወጡ አዳዲስ ግኝቶች ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ ባያጠፋም እንዳይተላላፍ እስከ ማድረግ የሚያስችሉ እየሆኑ ነው።
ለበርካታ አሥርት ዓመታት በኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ላይ ሥር የሰደደ ፍርሃትና እንዴት መከላከል እንደሚቻል ከሚሰጠው ትምህርት ባሻገር ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ያለ ሥቃይና ያለ ህመም ህይወታቸውን መምራት እንደሚችሉ እንዲሁም ለትዳር ጓደኞቻቸውን ለአደጋ ማጋለጥ እንደማይችሉ፣ቫይረሱ በደማቸው ላለባቸውም ለሌለባቸውም ማስተማር እና ማሳመን አስቸጋሪ ነው። ከዚያ በፊት ስለ ወረርሽኙ ያለው ግንዛቤ በመከላከል ላይ ያተኮረ የነበረ በመሆኑ አሁን ባለንበት ጊዜ ደግሞ ቫይረሱን ስለመግታት ማስተማር የአመለካከት፣ የእምነትና የባሕርይ ለውጥ ለማምጣት ጊዜን እና በሃላፊነት መስራትን ይጠይቃል።
በርካታ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥርዓታዊ መሰናዶዎች በደማቸው ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ባላቸው ሰዎች ስለማህበራዊ፣ ጾታዊና የመራቢያ ጤንነታቸው ትክክለኛና ትርጉም ያለው መረጃ እንዳይገኝ እንቅፋት ሆነዋል። ወረርሽኙ ከመጀመሩ ከረጅም ጊዜ በፊት የነበሩትን ጨምሮ በእነዚህ መሰናክሎች የተነሳ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ሊያጋጥማቸው የሚችለው አደጋ የተጋነነ ሆኗል። ይህ የተጋነነ አደጋ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ለጉዳትና ለፍትሕ መጓደል ያጋልጣቸዋል።
አደገኛ የሆኑ አደጋዎችን የማጋነን ተግባር የሰዎችን ሕይወት በእጅጉ ለማሻሻልና ወረርሽኙን ለማስቆምየሚያስችሉ ጠቃሚ አጋጣሚዎች ያባክናል።
ቫይረሱ ‹‹የማይታይ መጠን = የተገታ መተላላፍ›› (የ=የ) በሣይንሳዊ ማስረጃዎችና በጠንካራ መሠረት ላይ የተመሠረተ ቀላል ግን በጣም አስፈላጊ ዘመቻ ነው። በዚህ ዘመቻ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ያለ ሰዎች (እንዲሁም ጓደኞቻቸውና ቤተሠቦቻቸው) ረጅም ዕድሜ፣ ጤናማ ሕይወት መምራት፣ ልጆች መውለድ እንዲሁም ኢንፌክሽን ለሌሎች ማስተላለፍ ፈጽሞ እንደማያስጨንቃቸው እንዲገነዘቡ በማድረግ በሕዝብ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ማሳደ ር ተችሏል።
በቀላሉ የማይታይ መጠን = የተገታ መተላላፍ ‹‹የ-የ›› መልዕክት ተግባራዊ ቢደረግ የሚያስገኙት ጥቅም በኤች. አይ.ቪ የተጠቁና የተጎዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለመለወጥና ማህበረሰቡ በቫይረሱ ላይ ያለውን አክብዶ የማየት አስተሳሳብ እንዲያቀልና ሰው ተመርምሮ ራሱን እንዲያውቅ ትልቅኣጋጣሚ ነው፡፡
እኤኣ 2017 የማይታይ መጠን = የተገታ መተላላፍ ‹‹የ- የ›› ስምምነት መግለጫ ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ በፓሪስ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኤድስ ማህበር ጉባኤ ላይ ከ16 ሀገሮች የተውጣጡ ‹‹የ=የ›› ደጋፊዎች ስብሰባ አካሂደው ነበር። ‹‹የ=የ›› ማህበረሰብ ማዕከላዊ መድረክ ላይ ወጥቶ መልዕክቱን ለማፅደቅ እና ህይወትን ለማዳን አዳዲስ ለሚያዙት ለመከላከል የህክምናና የእንክብካቤ እድል እንዲያገኙ ጥሪ ለማቅረብ ከዓለም አቀፍ መሪዎች ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቶ ነበር፡፡
‹‹የ=የ›› ዘመቻ መጀመሪያ ላይ ሲጀመር የህክምና አቅራቢዎችና የምርምር ማህበራት፣ ብዙዎች በሣይንሱ ቢስማሙም ‹‹የ=የ››ለታካሚዎቻቸው በደማቸው ኤች.አይ.ቪ ያለባቸው ሰዎች ኮንዶም መጠቀማቸውን እንዳያቆሙ ማድረግ ለሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ተጋላጭነት እንደሚኖር ሥጋታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም በደማቸው ኤች.አይ.ቪ ያለባቸው ሰዎች ታካሚዎች ሊታወቅ የማይችልና በቀላሉ ሊተላለፍ የማይችል ሕክምና ማግኘት ሕክምናውን በጥብቅ መከተል እንደሚያስፈልግ አይገነዘቡም የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልፀው ነበር። በመሆኑም ‹‹የ=የ››ን ላለማካፈል ወይም “ኃላፊነት” አለባቸው ብለውላሰቧቸው ታካሚዎች ማካፈል ብቻ የተሻለ እንደሆነ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።
የማይታይ መጠን= የተገታ መተላላፍ ‹‹የ-የ›› ሕክምና ለማድረግ የመጀመሪያ ርምጃ ራስን ተመርምሮ ማወቅ ያስፈልጋል።ቫይረሱ በደማችን ውስጥ መኖሩ ከተረጋገጠ ፀረ ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ መድሀኒት በመውሰድ እና በባለሞያ በሚሰጠው ምክር መሠረት ቫይረሱ በማይታይበት ደረጃ እስኪደርስ ክትትል ማድረግ ትልቅ ሃላፊነት መውሰድ የግድ ይላል።
በየስድስት ወር እና አንድ ዓመት ክትትል በማድረግ ቫይረሱ በማይክሮስኮፕ በማይታይ ደረጃ ከደረሰ ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፋችን ሙሉ በሙሉ የተገታ ይሆናል ማለት ነው።
በተጨማሪም በሽታውን የመከላከል አቅማችን ከፍ በማድረግ ቫይረሱን ተከትሎ የሚመጣ የጎንዮሽ በሽታ እንዲቀንስ በማድረግ ከሥቃይና ከህመም ነፃ በመሆን ጤናማ ህይወት እንድንመራ ይረዳናል።ከኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ውጪ ያሉትን የአባላዘር በሽታዎች ግን መከላከል አይችልም፡፡
የሰዎች ደህንነት በተመለከተ በደማቸው ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች ከሃፍረትና ከፍርሀት የተነሳ ተመርምረው ራሳቸውን አውቀው ቫይረሱን የተገታና የማይተላላፍ ማድረግ ካልቻሉ ቫይረሱን ወደ የትዳር ጓደኞቻቸው በማስተላለፍ የማህበራዊ፣ የወሲብ ህይወት ላይ ችግር ይፈጠራል። ተመርምሮ ራስን ማወቅና ህክምና መከታተል መቻል ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሰዎችን ሕይወት እያበላሸና በመስኩ እድገት ሲያደናቅፍ የቆየውን ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ እነዚህን እንቅፋቶችን የማስቀረት አቅም አለው።
ከህክምና ግብዓቶችና ከምርመራ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ጭንቀት የሚቀንስ ሲሆን በኤች አይ ቪ የተያዙ ሰዎች በህክምናው ላይ ቆይተው ጤናማ ሆነው እንዲቆዩ እና ስርጭቱን እንዲከላከሉ ያበረታታል። አግባብነት ያለው የህዝብ ጤና የህክምና፣ እንክብካቤ እና የምርመራ እንቅፋቶችን በማስወገድ የሰዎችን ሕይወት ለማዳን እና አዲስ ተጠቂዎችን ለመከላከል የሚያስችል በማህበረሰብ ትልቅ ተስፋ ይዞ የመጣ ነው፡፡
በተለይ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት የማህበረሰብ ክፍሎች ሾፌሮች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ወጣት ሴቶች ላይ የምንደርስበትን የግንዛቤ ስፋት ላይ ትልቅ ስራ መስራት ከቻልን የኤች፣አይ፣ቪ ቫይረስ ኢንፌክሽን መቀነስ እንችላላን።ነገር ግን እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ራስን ለማወቅና ያላቸው ፍላጎትና ወደ ህክምና ተቋም የሚያመሩበትን መንገድ ከፍተኛ መሆን ኣለበት።ስለዚህ እንዲመረመሩ ምቹ የሆነ ኣጋጣሚ መፍጠር አለብን። ወደ ‹‹የ-የ›› የሚያመጣው መንገድ ተመርምሮ ቀድሞ ራስን ማወቅ ነው።
ለዚህ ሰዎች ስራዎችን በስፋት መስራት አለባቸው።ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በመከላከል ማንም ህጻን ፖዘቲቭ ሆኖ እንዳይወለድ ማድረግ ይቻላል።ለዚህ ደግሞ ተመርምሮ ራስን ማወቅና ህክምናውን መጀመር የግድ ይላል።ህክምና መጀመሩ ብቻ ግን በቂ አይደለም።መመሪያዎችን በመከተል ወደ ሌላ ሰው እንዳናስተላላፍ በማድረግ ጤናማ ትውልድን መፍጠር እንችላላን፡፡
ከኛ የሚጠበቀው ማስተዋል ብቻ ነው።ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ትኩረት ከተሰጠውና የህክምና ክትትል ከተጀመረ ወደ ሌላ ሰው መተላላፍ በማይችልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል።ይህ ቫይረሱን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት ትልቅ ዕድል ነው።ከእኛ የሚጠበቅብን ወደ ህክምና ተቋም ጎራ በማለት ራሳችንን ማወቅ ነው።ቫይረሱ በደማችን ኖረም አልኖረም ጤናማ ህይወታችንን መኖር እንቀጥላለን፡፡
መሰረት ገ/ዮሃንስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2013