
ስለ ሌባ ብዙ ማለት ይቻላል።አንዳንዱ በትናንሽ ነገሮች ስርቆት ውስጥ አይገኝም። የማይገባበት ገብቶ ወይም አይደፈሩ ደፍሮ ይሰርቃል። ትላልቅ ነገሮችን ይሰርቃል፤ እንዲህ አይነቱ ሌባ ድፍረቱ! ተብሎ ይገለጻል። ግዙፍ ነገር ጭምር አይምርም።ለእሱ ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ነገር የለም።
አንዳንዱ ደግሞ ስርቆት አመል ሆኖበት በትናንሽ ነገር ስርቆት ውስጥ ይገኛል። ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል እንደሚባለው ማለት ነው። ከብዙ ጥሩ ነገር መካከል አንስቶ የሚሄደው የማይረባውን ነው። እንዲህ አይነቱ ሌባ ሲያዝ ህብረተሰባችን ልክስክስ ሲል ይጠራዋል። ለምን የረባ ነገር አልሰረቅክም ለማለት ይሁን እንጃ።
ያገለገሉ የሴት ጫማዎችን ብቻ ፈልጎ የሚሰርቅ ሌባ እንዳለ ቢሰሙስ ምን ይላሉ። ኦዲቲ ሴንትራል ወደ ጃፓን ሆነ በሚል በድረ ገጹ ያስነበበው ዘገባ ይህን ይመለከታል።
በጃፓኗ ሙራካሚ ከተማ በሚገኝ አንድ የቢሮ ህንጻ ላይ የሴት ጫማ ስርቆት በተደጋጋሚ ይፈጸማል።ስርቆቱ ሰራተኞችን ክፉኛ ያስቆጣል፤ ጉዳዩ የህንጻውን ባለቤትም ያሳስበዋል።የህንጻው ባለቤት ሌባውን አጥምዶ ለመያዝ ይወስንና የደህንነት ካሜራ ያስገጥማል።እየታደነ መሆኑን ያላወቀው ሌባ አንድ ቀን እንደለመደው ሁለት ጫማዎችን ሰርቆ ይሄዳል።
ወጥመዳቸው መስራቱን የተገነዘቡት የህንጻው ባለቤት ካሜራው ያቆያቸውን መረጃ አፈፍ አድርገው ለአቅራቢያቸው ፖሊስ አመለከቱ።ፖሊስም መረጃውን ይዞ ወዲያውኑ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ይንቀሳቀሳል።በቅድሚያ ቀደም ሲል ተመሳሳይ ወንጀል የፈጸመ ግለሰብን በወንጀሉ ይጠረጥራል፤ ከዚያም የግለሰቡን ቤት ለመበርበር ይወስናል።በቀጥታም የተጠርጣሪውን ቤት ለመፈተሽ የሚያስችለውን ዝግጅት አድርጎ ወደ ብርበራ ይገባል።እንዳሰበውም በተጠርጣሪው ቤት 139 የሴት ነርሶች ጫማዎችንና ሌሎች ምርጥ ጫማዎችን ያገኛል።
የሚገርመው ነገር ደግሞ ጫማዎቹ ያገለገሉ መሆናቸው ነው፤ አንድም አዲስ ጫማ የለባቸውም። ሁሉም ጫማዎች በሚገባ ጸድተው በስነ ስርአት ተደርድረው ነው የተገኙት።
በጫማዎቹ ስርቆት የተጠረጠረው ጹኔሂቶ አይሶቤ የተባለው የ47 አመት ጎልማሳ የቢሮ ሰራተኛ ሲሆን፣ ያገለገሉ የሴት ጫማዎችን በመሰረቅ የሚታወቅ ነው።ተጠርጣሪው ከሰባት አመት በፊትም ሁለት መቶ የሴት ጫማዎችን ሰርቆ ቅጣት የተጣለበት መሆኑን ዘገባው አመልክቶ፣ በወቅቱ ጫማዎቹ በሙሉ መወረሳቸውን ጠቁሟል።
አሁን ደግሞ 139 ጫማዎችን ሰርቆ ነው የተያዘው። ጹኔሂቶ ከአንድ የቢሮ ህንጻ ገብቶ 500 የን /የጃፓን ገንዘብ/ የሚያወጡ ሁለት ሰንደል ጫማዎችን ሲሰርቅ በደህንነት ካሜራ ክትትል ባይያዝ ኖሮ ከተያዙት ጫማዎች በላይ ሊሰርቅ ይችል እንደነበር ተጠቁሟል።
ጼኔሂቶ አይሶቤ በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮም ለምርመራ ለዘጠኝ ቀናት እስር ላይ እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን፣ ከእነ ኤግዚቢቱ ስለተያዘ ሌላ ማድረግ የሚችለው ምንም ነገር አልነበረምና መስረቁን አመነ።
ግለሰቡ የሴቶች ለዚያውም ያገለገለ ጫማ መስረቅን ለምን ወደደ ነው ሌላው ጥያቄ። ተጠርጣሪው ለፖሊስ በሰጠው ቃል ‹‹ ከህጻንነቴ አንስቶ የተደረጉ የሴት ጫማዎች ይማርኩኛል፤ በዚህ አይነት ህይወት ውስጥ ነው ያደኩት›› ሲል ገልጿል።ለሰባት አመታት በዚህ አይነቱ ስርቆት ውስጥ መቆየቱን ተናግሮ፣ ለሴቶች ያለውን ፍቅር ከጫማዎቹ ጠረን እንደሚያገኝ አስታውቋል።
ይህ ሰው እአአ በ2014 በግምት 244 የሚሆኑ የሴት ጫማዎችን በመስረቅ ታስሮ እንደነበር ዘገባው አመልክቶ፣ ከእነዚህ ጫማዎች መካከል 200ዎቹ የሴት ነርሶች ጫማዎች እንደነበሩም ጠቁሟል። ግማሽ ያህሉን ጫማዎች የሰረቃቸው ከነርሶች መኖሪያ ቤቶች፣ የጥርስ ሆስፒታሎችና የህክምና ተቋማት ውስጥ መሆኑን አመልክቷል።
ተጠርጣሪው ለፖሊስ እንዳስታወቀው፣ በኤግዚ ቢት ከተያዙት 139 ጫማዎች መካከል ከተለያዩ ሴቶች የተሰረቁ መሆናቸውን አምኗል፤ የተቀሩት ግን ያገለገሉ የሴት ጫማዎች ከሚሸ ጡባቸው መደብሮች የገዛቸው ናቸው።
በእርግጥ ይህን ወንጀል በተደጋጋሚ ፈጽሜያለሁ፤ ይህን ያደረኩት ግን በጫማዎቹ በማገኘው ደስታ ሳቢያ ነው ያለው ተጠርጣሪው፣ እንደ እኔ አይነት ወንጀለኛ ሰዎች ጫማዎቻቸውን በማጣታቸው ሊደርስባቸው የሚችለውን ፈተና አይረዳውም ብሏል።አሁን ጫማቸው የሚሰረቅባቸው ሴቶች ሊሰማቸው የሚችለውን መጥፎ ስሜት መረዳት እንዳለብኝ ተገንዝቤያለሁ ሲል ተናግሯል።
ፖሊስ በኤግዚቢትነት የያዛቸውን በተጠርጣሪው ቤት የተገኙ ጫማዎችን ለህዝብ ይፋ ቢያደርግም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 13 ሴቶች ብቻ ጫማቸው እንደተሰረቀባቸው በማመልከት ለመውሰድ መቅረ ባቸውን ዘገባው አመልክቷል ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2013