የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ምሽት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ምክክር አድ ርጓል ። የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በሆነችው ቱኒዚያ ጠሪነት እና በወቅቱ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ፈረንሳይ ሰብሳቢነት የተካሄደው ውይይት ላይ በኢትዮጵያ በኩል የኢፌዴሪ የውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ፤በግብጽ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሽኩሪ ፣በሱዳን በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ መርየም አልሳዲቅ ተገኝተዋል። የምክር ቤቱ አባል አገራት በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን አቋም ካንጸባረቁ በኋላ የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ እና የሱዳኗ አቻቸው መርየም አልሳዲቅ ረዘም ያለ ትችት እና ስሞታ በኢትዮጵያ ላይ አቅርበዋል። የስብሰባው የመጨረሻ ተናጋሪ የነበሩት ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ ለሁለቱም አገራት ስሞታ ተመጣጣኝ የሆነ ታሪካዊ መልስ ሰጥተ ዋል። ሚኒስትሩ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለ17 ደቂቃ ያሰሙትን ንግግር እንደሚከተለው ወደ አማርኛ ተርጉመነዋል
……….
አመሰግናለሁ ክቡር ፕሬዚዳንት!
ክቡር ፕሬዚዳንት በሐምሌ ወር የጸጥታው ምክር ቤት ሥራዎችን እንዲመሩ ስለተመረጡ የተሰማኝን ደስታ እና መልካም ምኞቴን እንድገልጽ ይፍቀዱልኝ!
ለተከበሩ የጸጥታው ምክር ቤት ሰላምታዬን አቀርባለሁ!
ለወንድሜ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ እና ለእህቴ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርየም አልሳዲቅ እንዲሁ ልባዊ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ!
በተጨማሪም የተከበሩ ኢንገር አንደርሰን እና ልዩ ልዑክ ፐርፊት ጆኦግሪ ለነበራቸው ተሳትፎ ላመሰግናቸው እወዳለሁ!
የአፍሪካ ሕብረት ፕሬዚዳንት ተወካይም በዚህ ስብሰባ ላይ ስለተገኙ አመሰግናለሁ!
በዚህ ስብሰባ ግድባችን ባልተለመደ መልኩ የስሞታ መንስኤ ሆኗል። በዚህም የተነሳ በዚህ ምክር ቤት ላይ ተገኝቼ ንግግር ያሰማሁ የመጀመሪያው የውሀ ሚኒስቴር እኔ ሳልሆን አልቀርም። ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ለጸጥታው ምክር ቤት ውይይት መቅረቡ የምክር ቤቱን ሰዓት ማባከን እንደሆነ ታምናለች። ቢሆንም ለዚህ የተከበረ ምክር ቤት የአገሬን ኢትዮጵያ እውነተኛ እና አሳማኝ ነጥቦች ለማቅረብ መቻሌ ክብር እንደሆነ አምናለሁ።
ከዓመት በፊት በጁን 29/2020 እ.ኤ.አ በእርስዎ የፕሬዚዳንትነት ዘመን የዚሁ ምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ፤ ግብጽ እና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የጀመሩትን ምክክር አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ለዚህም የጸጥታው ምክር ቤት ለሕብረቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር። ስለዚህም ኢትዮጵያ በድርድሮቹ ተቀባይነት ያለው ውጤት እንዲገኝ በአዲስ መንፈስ እና በቀናነት በድርድሮቹ ላይ ስትሳተፍ ቆይታለች። በዚሁ አጋጣሚ ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ሕብረት መሪነቷ በፌብሩዋሪ
2021 እ.ኤ.አ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድርድሮችን በሚገባ ለማካሄድ ላደረገችው ጥረት ላመሰግናት እወዳለሁ። በተመሳሳይም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሰብሳቢ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ድርድሩ በተደጋጋሚ ቢቋረጥም ድርድሩን ለማስቀጠል ለምታደርገው ጥረት ምስጋናዋን ታቀርባለች ።
ክቡር ፕሬዚዳንት አሁን እየሰራን ያለነው ግድብ በአፍሪካም ሆነ በዓለም በአይነቱ የመጀመሪያው አይደለም። እየገነባን ያለው ተርባይኖችን በውሀ በመምታት ኃይል ማመንጨት የሚችል የውሀ ግድብ ነው። ለእርስዎ መረጃ እንዲሆንዎ ለመግለጽ ያህል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከግብጹ የአስዋን ግድብ ከ2 ከግማሽ እጥፍ በታች ያነሰ ነው። ምናልባትም ታላቁ የህዳሴ ግድብ በልዩ ሁኔታ እንዲታይ ያደረገው 65 ሚሊዮን በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጣሉበት ተስፋ ነው ። ሌላኛው ልዩ የሚያደርገው ነገር ደግሞ ይህ በ5 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው ይህ ግድብ በኢትዮጵያውያን እንባ ፤ ላብ እና ደም የተገነባ መሆኑ ነው። ግድቡ በትክክለኛው ሰዓት በትክክለኛው ቦታ የተገነባ፤ ለቀጠናው ተስፋ የሚሰጥ ግድብ ነው።
የዓባይ ወንዝን መጠቀም አለመቻላችን በሕዝባችን ሥነልቡና ውስጥ ትልቅ ቅሬታ ፈጥሯል። ይህንንም አንድ ታዋቂ የኢትዮጵያውያን አባባል ይገልጸዋል። እሱም “የዓባይን ልጅ ውሀ ጠማው” የሚል ነው። ትርጓሜውም በወንዝ መሀል ቆሞ ውሀ የሚጠማን አንድ ገበሬ ሊያመለክት ይችላል። ይህን ትልቅ ቅሬታ ለመፍታት ከኢትዮጵያ የውሀ ሀብት ሁለት ሶስተኛውን የያዘውን የዓባይ ወንዝ
ከማልማት ሌላ ምንም አማራጭ የለንም። በዚህ ከጎረቤቶቻችን ጋር በምንጋራው ግዙፍ ወንዝ ላይ ሕዝባችንን ራሱን ከጨለማ የሚያወጣበት እና የሚያድግበትን ተስፋ እያየ ነው። ይህ ግድብ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ኑሮቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች፤ አርብቶ አደሮች፤ ተማሪዎች ፤ የቀን ሰራተኞች እና ዲያስፖራው አሻራ ያረፈበት ነው።
ኢትዮጵያውያን ለግብጽ እና ለሱዳን ሕዝብ በጎ ሀሳብ አለን ። በሰላም እና ለጋራ ጥቅም በጋራ በመስራት በትብብር ለመኖርም ጽኑ ፍላጎት አለን። በዚህም የተነሳ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአፍሪካ ሕዝቦች የጋራ ትብብር መገለጫ ከሆኑ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።
ክቡር ፕሬዚዳንት የሰው ልጅ መገኛ የሆነችው አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ከአህጉራት ሁሉ ወጣቷ አህጉር ናት። በአህጉሪቱ ያለውን የወጣት ኃይል በመጠቀም ለመልማትም ከፍተኛ ፍላጎት አለ። በተመሳሳይም አገሬ ኢትዮጵያ ከሕዝቧ 70 በመቶው ከ30 ዓመት የእድሜ ክልል በታች የሚገኝ ወጣት ነው። በየዓመቱ ከ100ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይመረቃሉ። ያ ብቻ ሳይሆን ወደ 30 ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ደረጃ በትምህርት ቤት ውስጥ ይገኛሉ።
ይህን እያደገ ያለ ፍላጎት በአግባቡ ማስተናገድ ደግሞ ለአገሬ የህልውና ጉዳይ ነው። ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሰሀራ በረሃ የሚሰቃዩት፤ ለቤተሰቦቻቸው የተሻለ ህይወት ለመፍጠር በአረብ ሀገራት ህይወታቸውን የሚገብሩት፤ በአፍሪካ እና ሌሎች ሀገራት በወህኒ የሚማቅቁት፤ በባዶ እግራቸው ከአረብ ሀገራት የሚባረሩት ኢትዮጵያውያን የተከበረ መልካም ህይወት ይገባቸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሕዝብ ግድብ ነው። ስለዚህም የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች ሁሉ እየተጋፈጥን ለመቀጠል ቆርጠናል። በነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች መሐከልም ቀስ በቀስ እያሸነፍን ነው።
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ እዚህ የተገኘነው ግብጽ እና ሱዳን ስሞታ ስላቀረቡ ነው። ሁለቱም ጎረቤቶቻችን ግን ትላልቅ እና ትናንሽ ግድቦች ያለ ተፋሰሱ አገራት እውቅና እና ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የእንመካከር ጥያቄ ወደጎን በመተው መገንባታቸው ማወቅ ተገቢ ነው። አሁን እንደተረዳነው ግን ተቃውሞአቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በምንም መልኩ ውሀዋን እንዳትጠቀም ለማድረግ ነው።
እውነታው ግን እኛ ሌላ አማራጭ የለንም። እኛ እንደ ግብጽ እና ሱዳን በመሬት ውስጥ ውሃ የለንም። አጣርተን የምንጠቀመው የባህር ውሀም የለንም። ከአገሬ ውሀ 70 በመቶው በአባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ ነው። ስለዚህም የዓባይን ውሀ አለመጠቀም ብንፈልግ እንኳን አንችልም። ደግሞም ግድብ መገንባት አንደኛው ዓላማችን ነው እንጂ ዋናው አላማችን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ አነሳሽነት በተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተፈጥሮን በመንከባከብ ያለንን መጠነኛ የውሀ ሀብት ማብዛት ነው።
በ5 አመታት 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል አስበን ባለፉት 2 ዓመታት 2 ቢሊዮን ችግኝም ተክለናል ። ይህ ዘመቻችንን ለጎረቤት የአፍሪካ አገራት ችግኝ በመለገስ የቀጠለ ሲሆን ይህምየአፍሪካ ሕብረት የአረንጓዴ ቀበቶ ዘመቻ አካል ነው። በዚሁ አጋጣሚ ግብጽ እና ሱዳን ይህን ለተፈጥሮ አደጋ ያለንን ተጋላጭነት የሚቀንስ እና የውሀ ሀብትን ለመጨመር የሚያስችል ዘመቻ እንዲቀላቀሉ ጥሪ እናቀርባለን።
ክቡር ፕሬዚዳንት ፤ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና በቀናነት የመደራደር ፍላጎት ካለ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ታምናለች። እስካሁንም በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰናል። የአፍሪካ ሕብረት ጉዳዩን የያዘው ሲሆን ድርድሩን በአግባቡ እየመራውም ይገኛል ። ለዚያም ነው ጎረቤቶቻችን ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ማምጣታቸው አሳዛኝ የሚሆነው።
እኔ ስለ ቴክኒካዊ ጉዳዮች በመዘርዘር ላታክታችሁ አልፈልግም ። ነገር ግን የምናውራው ስለ ውሀ ግድብ ነው። የጸጥታው ምክር ቤት ከተመሰረተ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ በውሀ ፕሮጀክት ላይ እንዲወያይ እየተደረገ ነው። የጸጥታው ምክር ቤት የፖለቲካ እና የጸጥታ ጉዳዮችን የሚመለከት ምክር ቤት ነው። ስለዚህም ለዚህ ምክር ቤት የውሀ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን የሚመለከት ጉዳይ ማቅረብ አግባብ አይደለም።
ክቡር ፕሬዚዳንት በእኛ እና በሁለቱ ሀገራት መሀከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት የነሱ የቅኝ ግዛት ውልን ለማስቀጠል ያለ ፍላጎት ነው። ችግር በፈጠረው እሳቤ ችግሩን ለመፍታት መሞከር ነው ድርድሩን እያደናቀፈ ያለው። የጸጥታው ምክር ቤት አሁን ኢትዮጵያውያን የአባይ ወንዝን የማልማት መብት አላቸው ወይስ የላቸውም ከሚለው ጥያቄ ጋር ተፋጧል። ስለዚህም ይህን ጥያቄ ለዚሁ ምክር ቤት ላቀርብ እወዳለሁ። ኢትዮጵያውያን የዓባይን ውሀ የመጠጣት መብት የላቸውምን ?
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ በአፍሪካ ህብረት እየተመራ ያለው ድርድር አሁን ያለበትን ደረጃ እንድገልጽ ይፍቀዱልኝ። በጁን 24 ቀን 2020 እ.ኤ.አ የአፍሪካ ሕብረት የስብሰባ ቢሮ በህዳሴው ግድብ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመምከር ተሰብስቦ ነበር። የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ፕሬዚዳንት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ቲኪሼዴ ቀጣይ ድርድርን እንዴት ሊያስኬዱ እንዳሰቡ ለቢሮው በዝርዝር አብራርተውም ነበር። ይሁንና በአሳዛኝ ሁኔታ ይህን በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ የተካሄደ ስብሰባ ሱዳን አልተካፈለችም። በዚህ የሱዳን አለመገኘት ምክንያት ሁለቱ አገራት ቀጣይ ዘጠኝ ስብሰባዎችን እንዳይደረግ አደናቅፈዋል።
አሁን ላይ ሁላችንም ኢትዮጵያ ላልተገባ ፖለቲካዊ ጫና እንደማትንበረከክ ማወቅ አለብን። ኢትዮጵያ እስከ መጨረሻው የምትታገስ እና ትብብር የምታደርግ ሲሆን ይህም በዚህ ግዙፍ ወንዝ ሁላችን በመተሳሰራችን ነው። ወደድንም ጠላንም ሁላችንም ከወንዙ ውሀ የምንጠጣ ሲሆን ተባብሮ መኖርንም የግድ መልመድ አለብን።
እዚህ ላይ ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ችግራቸውን መፍታት የሚችሉበት አቅም እና ቴክኒካዊ እውቀት እንዲሁም የተደራጀ አካል እንዳለን እንደምታምን አበክሬ ልገልጽ እወዳለሁ። ግብጽ እና ሱዳን ሊያስቀጥሉት በሚፈልጉት የቅኝ ግዛት ውል ምክንያት የተደናቀፈው ድርድር በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ፕሬዚዳንት አደራዳሪነት እንሚፈታም ሙሉ እምነት አለን።
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ብዙ ስለተባለለት የሁለተኛው ዙር የውሀ ሙሌት እንዳብራራም ይፍቀዱልኝ። የሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት በዚህ የሐምሌ እና የነሐሴ ወር ይካሄዳል። የግድቡ አሞላልን በተመለከተም መረጃዎችን ቀድመን ለሁለቱም አገራት እያሳወቅን ነው። ግልጽ ላድርገውና፤ የግድቡ ሙሌት የግድቡ ግንባታ አንድ አካል ነው ።
ይህም በማርች 2015 እ.ኤ.አ የሶስቱ አገራት መሪዎች በፈረሙት የመርሆዎች ስምምነት ላይ በግልጽ ሰፍሯል። የግድቡ ሙሌት ግልጽ ፊዚክስ ነው። ግድቡ የሚፈለገው ከፍታ ላይ ሲደርስ ውሀው በማስተንፈሻ ቱቦዎቹ ወይም በግድቡ በላይ ይፈስሳል ። ግድቡ ሱዳን እና ግብጽ በተስማሙበት የውሀ አሞላል መርሀ ግብር መሰረት 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እስኪደርስ ድረስ ውሀ ይይዛል። ከውሀው ዓመታዊ ፍሰት 77 ቢሊዮን ኪዩቡን የምታበረክተው አገር ከዚህ ውሀ ጥቂቱን መያዟ ምንም ክፋት የለውም።
ግብጽ እና ሱዳን ግድቡ ሲያልቅ ስለሚያገኙት ጥቅም ብዙ ማሳመን አያስፈልጋቸውም። ብልህ ሱዳናውያን ባለስልጣናት እንደሚሉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ የቀጠናዊ ትብብር ምንጭ ነው። አስዋን ግድብ ለግብጽ የሚሆነውን ያህል ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለሱዳናውያን እንደዚያ ነው። ግድቡ ማንንም እንደማይጎዳም እንዲሁ ማስረዳት እፈልጋለሁ።
ሁላችንም ከወንዙ የሚገኘውን ጥቅም ለመቋደስም ሆነ ችግሩን ለመጋፈጥ አብረን አለን። አንዳችን ስንረካ ሌላችን ልንጠማ ግን አይገባም። በህዳሴ ግድብ በኩልም ኢትዮጵያ ይህ ስሜት እንዲዳብር ጥሪ ታቀርባለች። ስለዚህም ይህ ምክር ቤት አገራት ውስጣዊ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት በሚያደርጉት ጥረት ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ተጎትቶ የሚገባበት ምክንያት የለም።
ክቡር ፕሬዚዳንት ምክር ቤቱ በሱዳን እና ግብጽ ጥሪ መሰረት ወደዚህ ድርድር ከገባ ራሱን በብዙ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አተካሮ ውስጥ ተጠምዶ ሊያገኘው ይችላል። በሚያስገርም ሁኔታ በዚህ ምክር ቤት ውስጥ ከአንዲት ደሴት አገር በቀር ሁሉም የምክር ቤቱ አገራት ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ አላቸው ። እኛ በሁለትዮሽ እና በተፋሰስ ሀገራት ምክክር መድረክ ልዩነቶቻችንን ልንፈታ ሞክረናል፤ እንቀጥላለንም።
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በግድቡ ዙሪያ ያካሄድነው ድርድር ብዙ ትምህርት ሰጥቶናል ። ይህ ሂደት ቀጠናዊ መፍትሔዎችን እንድናገኝ እንደሚረዳንም ተስፋ እናደርጋለን። ስለዚህም ምክር ቤቱ ወደዚህ ጉዳይ ከገባ ይህን ተስፋ ከማጨለሙም በላይ በበጎ ድርድር ሊፈታ የሚችለውን ነገር ሁሉ በጸጥታው ምክር ቤት እንዲፈታ ሊያደርገው ይችላል። ምክር ቤቱ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዙሪያ ጣልቃ ገብ እንዲሆን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት መቃወም አለበት።
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ቅኝ ግዛት እና የቅኝ ግዛት ውሎች አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷን ለሕዝቦቿ ጥቅም እንዳታውል አድርጓታል። የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ይህን ችግር በመረዳት መፍትሄ ለማበጀት ጥረናል። በ1999 እ.ኤ.አ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ምክክርን ያቋቋምን ሲሆን ከ13 ዓመታት ድርድር በኋላም በ2010 የትብብር ፍሬም ወርክን
ተፈራርመናል። በዚህ አብዛኞቻችሁ የምክር ቤቱ አባላት በፋይናንስ እና በቴክኒክ በደገፋችሁት ፍሬም ወርክ የተፋሰሱ አገራት የዓባይ ውሀን በፍትሐዊነት እንዲጠቀሙ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ብቸኛ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍነውን የቅን ግዛት ውል በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት ባለው ስምምነት ቀይረናል። ይህ ስምምነት ወደ ተግባር እንዲገባም እስኪጸድቅ እየተጠበቀ ነው።
በሱዳን እና በግብጽ የሚቀርበው ስሞታ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሳይሆን በቀጣይ በኢትዮጵያ እና ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ስለሚኖሩ ልማቶች ነው። ያለ ፍሬም ወርኩ እና ቀጠናዊ መፍትሄዎች ሁሉም ጉዳዮች ወደዚህ ምክር ቤት ይመጣሉ። ዛሬ ተረኛዋ ኢትዮጵያ ናት። ነገ ድግሞ ከተፋሰሱ አገራት አንዳቸው ሊሆኑ ይችላሉ ።
ዓባይ የሁሉም የተፋሰሱ አገራት እና በዚያ ውስጥ የሚኖር ግማሽ ቢሊዮን ሕዝብ ሀብት ነው። ደግሞም ውሀው ለሁላችንም ይበቃል ። በዚህም መሰረት የሱዳን እና የግብጽ ወንድም እና እህቶቻችን እንዲረዱ የምንፈልገው መፍትሔ ከጸጥታው ምክር ቤት እንደማይመጣ ነው። መፍትሄ የሚመጣው በበጎ መንፈስ ከሚደረግ ውይይት እንዲሁም እርስ በርስ በመተሳሰብ ነው። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄድ ድርድር ለመቀጠል ቁርጠኛ ናት።መፍትሄው በእጃችን አለ። በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ስምምነት በመፈረም ለአለም መልካም ዜና እንደምናበስርም ተስፋ አለን።
በመጨረሻም ክቡር ፕሬዚዳንት ይህን ጉዳይ አቅሙም ሆነ ሕጋዊነቱ ላለው የአፍሪካ ሕብረት እንዲመልሰው እንዲሁም ግብጽ እና ሱዳን በቀናነት እና በቁርጠኝነት እንዲደራደሩ እንዲያበረታታ እጠይቃለሁ። ምክር ቤቱ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ይህ የመጨረሻ ስብሰባው እንዲሆንም ጥሪ እናቀርባለን። ለጸጥታው ምክር ቤት ከዚህ የሚርቅ አጀንዳ የለም።
አመሰግናለሁ።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2013