
ሩዋንዳ የሞዛምቢክ ግዛት ወደሆነችው ካቦ ዴልጋዶ አንድ ሺህ ወታደሮችን ልታሰማራ ነው:: የምታሰማራውም በሞዛምቢክ መንግስት ጥያቄ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል::
ካቦ ዴልጋዶ የተባለችው የሞዛምቢክ ግዛት ከፍተኛ የጋዝ ክምችት ያለባት ስትሆን ውጥረትና ወከባ የማይለያት ሆና ቆይታለች፤ እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት በወታደራዊ ኃይል ለማስቆም ሞዛምቢክ ሩዋንዳን የወታደር ጥያቄ ጠየቀች፤ በጠየቀችው መሰረትም ሩዋንዳ ጠንካራ የሚባሉ ወታደሮችን መድባለች ተብሏል::
በዚች ቦታ ላይ የነበረው ግጭትና ውጥረት ለአራት ዓመታት ያህል ቀጥሏል:: በእነዚህ አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከሦስት ሺህ በላይ ዜጎች ተገድለዋል፤ 800 ሺህ ያህሉ ተፈናቅለዋል፤ ለስደት ተዳርገዋል:: ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ (400 ሺህ አካባቢ ማለት ነው) ልጆች እና ሴቶች ናቸው ብሏል አልጀዚራ::
ይህን ውጥረት ለማርገብ 16 አባላት ያሉት የደቡብ አፍሪካ የልማት ማህበር ወታደር መሰማራት አለበት ብሎ ሀሳብ ማቅረቡንና ሀሳቡም ተቀባይነት ማግኘቱን አልጀዚራ አስታውሷል:: በዚህም መሰረት ሩዋንዳ ፈጣን ምላሽ በመስጠት አካባቢውን ለማረጋጋት 100 ሺህ ወታደር አሰማራለሁ ብላለች::
የሩዋንዳ መንግስት እንደገለጸው፤ የሩዋንዳ ወታደሮች የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበር አባል አይደሉም፤ የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር ከአማጽያኑ ጋር የሚዋጉት ግን ከደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበር አባል ወታደሮች እና ከሞዛምቢክ ወታደሮች ጋር በመሆን ነው::
የሩዋንዳ መንግስት የሞዛምቢክን ሰላም ለማስከበር፣ አካባቢውን ለማረጋጋት፣ የአገሪቱን ህግና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሚቻለውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብሏል የሩዋንዳ መንግስት:: ይህንንም በጻፈው ደብዳቤ አረጋግጧል::
የሩዋንዳ መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ለሮይተርስ እንደተናገሩት የተሰማራው ወታደራዊ ሃይል ትናንት ቅዳሜ ሙሉ በሙሉ ወደ ሞዛምቢክ ተሰማርቷል:: ይህም ሩዋንዳ ሽብርተኝነትንና አለመረጋጋትን ለማስቀረት ያላትን ቁርጠኝነትና አቋም የሚያሳይ ነው ተብሏል:: የሩዋንዳ የፀጥታ ኃይል የዳበረ ልምድ ያለውና ሰላምና ፀጥታን በማስከበር እውቅና ያለው ነው ተብሏል:: ይህ በሞዛምቢክ የሚደረገው ሰላምን የማስከበር ሥራ ግን ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ወታደራዊ ኃይል ጋር የሚሰራ ነው::
አንሳር አል ሱና የተባለው የሞዛምቢክ አማጺ ቡድን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ የሽብር ጥቃቶች አድርሷል:: በተለያየ ጊዜ ተጠያቂ የሆነ ሲሆን፤ ከፈረንጆቹ ጥቅምት 2017 ጀምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል::
ስለእርስ በርስ ጦርነት ሲነሳ እንደ ምሳሌ የምትጠቀሰው ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ በዚህ አስነዋሪ ጦርነት ብዙ ዜጎቿን ብታጣም ዛሬ ግን የሰላም ምሳሌ ከመሆን አልፋ የሌላ አገር ሰላም እያስከበረች ነው::
‹‹ጋቻቻ›› የተሰኘው እና በሩዋንዳው ዘር እልቂት ወቅት ጥፋት ፈፅመዋል በተባሉ ሰዎች ላይ ፍርድ እንዲበይን የሚተጋው አካል ሁለት ሚሊየን ያክል ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ አድርጓል። በዚህ ቆራጥ ውሳኔዋም ዛሬ ስሟ የሚነሳው በበጎ ሆኗል::
ሩዋንዳ ውስጥ አሁንም ድረስ ስለዘር ማውራት ያስነውራል፤ ስለ እልቂቱ ማውሳት ያስወቅሳል። ሬድዮ ጣብያዎች የእርስ በርስ ጦርነቱን አንስተው እንዲነጋገሩበት አይበረታቱም፤ ቴሌቪዥኖች ስለጉዳዩ አያወሩም:: ይህ የሰላም ፍላጎቷ ደግሞ ወደ ዕድገትና ብልጽግና እየወሰዳት መሆኑ ይነገርላታል::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም