
አዲስ አበባ፡- በቀጣዩ አምስት ዓመት በዙሪያችን ባሉና ብልጽግና በሚቀላጠፍባቸው አራት ማዕዘኖች መሐል ቆመን ለአገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ፈር ጠራጊ እንሆናለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምርጫው ውጤት ይፋ መሆኑን በማስመልከት ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት እንደገለጹት፤ በቀጣዩ አምስት ዓመት ብልጽግና የሚመራባቸው አራት ማዕዘኖች አሉ።
የመጀመሪያው ማዕዘናችን የመሠረተ ልማት ግንባታ ሲሆን፥ አገራችን እንድትበለጽግ በኢኮኖሚውም ሆነ በማኅበራዊና ፖለቲካ ዘርፎች ዘላቂ መሠረት የሚሆኑ፣ በፍጥነት የሚጠናቀቁ፣ ጥራታቸው የተጠበቁ፣ ከብክነት ነጻ የሆኑ እና የምንፈጥራቸውን ተቋማት መሸከም የሚችሉ ትውልድ ተሻጋሪ መሠረተ ልማቶችን መገንባታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ጥቂትም ቢሆኑ ባለፉት 3 ዓመታት አመርቂ ሥራዎችን ለመሥራታችን ምስክሮቹ እናንተው ናችሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁለተኛው ማዕዘን የተቋማት ግንባታ ሲሆን፣ በጥቂት ግለሰቦችና ነጠላ ተቋማት ላይ ከማተኮር ባለፈ ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆሙ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጉናል ብለዋል።
ዘመን ተሻጋሪ ሥርዓት ለማጽናት የሚያስችሉ ገለልተኛና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚያገለግሉ ተቋማትን መገንባት ላይ ትኩረት ይደረጋል ። ይኼ ማዕቀፍ ከፌደራል እስከ ክልል የሚገኙ ተቋማትን እንደሚያካትት ገልጸዋል ።
በሦስተኛ ደረጃ እንደ አገር የሚያስተሳስሩን የጋራ አመለካከቶችና የጋራ ትርክቶች ላይ ትኩረት ሰጥተን ልንሠራባቸው ይገባል ። እርስ በእርስ የሚቃረኑና የሚጠፋፉ ትርክቶች ምን ያህል ለጠላቶቻችን ተመችቷቸው እኛን ደካማ እንዳደረገን ያሳለፍናቸው ዓመታት ሕያው ምስክሮች ናቸው ። ስለዚህ ክፍተቶቻችንን በሚደፍን መልኩ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር አጠንክረው በሚያቆሙን ዕሴቶች ላይ የተመሰረተ፣ ገዢና ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ ትርክት ለመገንባት ጠንክረን እንሠራለን ብለዋል ።
በአራተኛ ደረጃ የሞራል ልዕልናና ግብረገባዊነት ተመጣጣኝ ትኩረት አግኝተው እስካልተሠራባቸው ድረስ በአገራችን ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ፣ በተቃራኒው ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች እየተስፋፉ እንዲመጡ በር ይከፍታል ። ይኼንን ችግር የመቅረፍ ኃላፊነት መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ላይ ብቻ የሚጣል ሳይሆን፣ ከግልና ከቤተሰብ ጀምሮ የሚሠራ ሥራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል ።
ሁሉም አካላት ተረባርቦ ሀገርና ትውልዱን እያቆሸሹ ያሉ መጥፎ ተግባሮችን ጠርጎ ሊጥላቸው ይገባል። በቀጣይ ዓመታት በሞራል ንጽህና የተገነቡ ተቋማትንና መሪዎችን አንጥረን የምናወጣበት እንዲሆን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል ።
ጌትነት ተስፋማሪያም
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም