ሰው ቀጥ ባለ የህይወት መስመር ላይ አይጓዝም። ኑሮውን ለማሸነፍ ሲል፤ አባጣና ጎርባጣውን፣ አቀበትና ቁልቁለቱን፣ ሜዳና ሸለቆውን፤ ይወጣል፤ ይወርዳል። አንዳንዴ ከፊት፤ አንዳንዴ ከመሃል፤ አንዳንዴም ከኋላ ሆኖ በከፍታና በዝቅታ መሃከል እየዋዠቀ ይኖራል። የዛሬዋ ባለታሪክም በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈች ነች። ከልጅነት እስከ እውቀት የገጠሟትን ችግሮች ተቋቁማ ለማለፍ ያልከፈለችው መስዋዕትነት የለም። አስቸጋሪውን የመከራ ጊዜ አልፋ በመምህርነት ስራ ላይ ተሰማርታ ህይወትን ማጣጣም ጀምራ ነበር። ብዙም ሳትቆይ የዓይኗ ብርሃን ይከዳታል። ብርሃኗን ለመታደግ ወጣች፤ ወረደች ግን የሚቻል አልሆነም። ብርቱዋ መምህር በስተኋላ ያጋጠማትን አይነ ስውርነት አሸንፋ ስራዋን እየሰራች ለመኖር በ42 ዓመቷ የብሬል ትምህርት መማር ጀምራለች። እድሏና ገጠመኟ የሚያስቀና ባይሆንም ከችግር ለመውጣት የምታደርገው ጥረት አስተማሪ ሆኖ ስላገኘሁት የዚህ አምድ እንግዳ ላደርጋት ወደድኩኝ።
መምህርት ዘውዴ ጎንፋ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ በድሮው ከፍተኛ 22 ቀበሌ 01 በአሁኑ ልደታ ክፍለ ከተማ ነው። ለቤተሰቦቿ ሁለተኛ ልጅ ነች። በልጅነቷ ምንም ዓይነት የጤና ችግር የለባትም። ከአብሮ አደግ ጓደኞቿ ጋር እየተጫወተች ማደጓንም ታስታውሳለች። ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ በአባይ ምንጭ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብታ ፊደል መቁጠር ትጀምራለች። ከዚያም ከስድስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በተስፋ ኮከብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ተምራለች።
ዘውዴ በችግርና በመከራ እንዳደገች ትናገራለች። ወላጆቿ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ናቸው። አባቷ በአንድ የዱቄት ፋብሪካ ውስጥ በአነስተኛ የወር ደመወዝ የሚሰሩ ነበሩ። እናቷ ሰው ቤት እንጀራ በመጋገርና ቅጠል በመሸጥ ይተዳደሩ ነበር። ወላጆቿ እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን እየሰሩ ስምንት ልጆችን ማሳደጋቸውን ትገልጻለች።
ዘውዴ ሁል ጊዜ ቤተሰቦቿ ያለባቸው የኑሮ ጫና እያስጨነቃት ራሷን ችላ የምትኖርበትን ጊዜ ታስብ ነበር። ገና ለአቅመ ሄዋን ሳትደርስ ፈጥና ወደ ትዳር እንድትገባ ያደረጋትም ይኼው ጉዳይ ነው። ልክ የ8ኛ ክፍል ተማሪ እያለች የቀረበላትን የትዳር ጥያቄ ሳንታገራግር ተቀብላ አግብታ መኖር ትጀምራለች። ትምህርቷንም አቋርጣ የቤት እመቤት ትሆናለች። ዘውዴና የምትወደው ባለቤቷ በፍቅር እየተሳሰቡ ህይወትን ቀጠሉ። እያደር ግን ያ በፍቅር የተሳሰረ ጥምረታቸው ንፋስ ይገባው ጀመር። በወቅቱ ዘውዴ እንዳገባች አለመውለዷ በባለቤቷ ዘንድ ጥሩ ስሜት ስላልፈጠረ ላለመግባባታቸው አንድ መንስኤ ነበር ትላለች። ከባለቤቷ በላይ የመውለድ ፍላጎት የነበራት እርሷ ብትሆንም ልጅ እምቢ ይላታል። ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳረገዘችም ያስወርዳታል። ኋላ ግን አንድ ወንድ ልጅ መውለዷን ትናገራለች። ያም ሆኖ በባልና በሚስት መካከል የነበረው አለመግባባት ልጅ ከተወለደ በኋላም ይቀጥላል። ዘውዴ በራሷ ሰዓት ቤቱን ለቃ ትወጣለች።
የልጇ አባት ለልጁ ማሳደጊያ የሚሆን ገንዘብ ከደመወዙ ላይ እየቆረጠላት ትንሽ ቤት ተከራይታ ልጇን እያሳደገች መኖር ትጀምራለች። ምንም እንኳን በሀሳብ አለመግባባት የተለያዩ ቢሆንም አንዳቸው ለአንዳቸው ማሰባቸውን አልተውም ነበር። ዘውዴ ዛሬም ድረስ ባለቤቷን እንደምትወደው ትናገራለች። የልጅነት ዕድሜ ሆኖባት ጥሩ ያልሆነ ውሳኔ መወሰኗ ይቆጫታል። ባለቤቷ ሲበዛ ቅን እና መልካም ሰው መሆኑን ከተለያዩ በኋላ በነበሩት ሁኔታዎች እንደተረዳች ትናገራለች።
ቤት ተከራይታ ልጅ እያሳደገች በምትኖር ሰዓት ያቋረጠችውን ትምህርት እንድትቀጥል ግፊት ያደርግባት እንደነበር ትናገራለች። በወር ለልጁ ከሚቆርጠው በተጨማሪ ለእርሷም የትምህርት ቤት ክፍያ እየከፈለ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አስተምሯታል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላም ፒያሳ ፓስፊክ የአፀደ ህጻናት መምህራን ማሰልጠኛ ገብታ እንደትማር የጎተጎታትና ገንዘብ እየከፈለ ያስተማራት ይኼው የልጇ አባት መሆኑን ትናገራለች።
ዘውዴ ነገሮችን በትዕግስት ማየት ሲገባት ስሜታዊ ሆና ከቤት የወጣችበትንና ከልጇ አባት ጋር የተለያየችበትን ሁኔታ እያስታወሰች ሁሌም ታለቅሳለች። በዚህ የተነሳም ዓይኗን ያማት ነበር።
የአፀደ ህጻናት መምህር ሆና ከተመረቀች በኋላ እንዳሰበችው ስራ ማግኘት አልቻለችም ነበር። ለበርካታ ጊዜ ያለስራ እቤት ተቀምጣለች። በየጊዜው እየተባባሰ የሚሄደውን የኑሮ ውድነት ተከትሎ ባለቤቷ የሚቆርጥላት ገንዘብም አልበቃት ይላል። በዚህን ጊዜ ዘውዴ የጉልበት ስራዎችን እየሰራች ኑሮን ለማሸነፍ ትጥር ጀመር። በዋናነትም በየሰው ቤት እየተዟዟረች ልብስ ማጠብን ተያያዘችው። ጠዋት አንድ ሰው ቤት አጥባ ከሆነ፤ ከሰዓት ሌላ ሰው ቤት እያጠበች አንዳንዴም ጥጥ እየፈተለች ልቃቂት በመሸጥ፤ ዳንቴልና አልጋ ልብስ እየሰራች በመሸጥ ገቢዋን ለማሳደግ ሞከረች። ግን ያሰበችው ላይ መድረስ አልቻለችም። ኑሮ ‹‹ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ›› ይሆንባታል። ልጇ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ አባትየው ይወስደውና ትምህርት ቤት ያስገባዋል። ዘውዴ አሁን እንደ ልቧ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስና ስራ የማፈላለግ እድል ታገኛለች።
አንድ ቀን የተማረችበት ተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት የአፀደ ህጻናት መምህር ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቶ ታይና ትመዘገባለች። ፈተናውን ከወሰደች በኋላ ማለፏ ይነገራትና የቅጥር ፎርም ትሞላለች። አዲስ የህይወት ምዕራፍ ላይ በመድረሷ ደስ ብሏት ስራዋን ትጀምራለች። ትንሽ ቆይታም የኮንዶሚኒየም ቤት ዕድለኛ ትሆናለች። ቤተሰቦቿና የልጇ አባት ባደረጉላት የገንዘብ ድጋፍ የመጀመሪውን ክፍያ ፈጽማ ከኪራይ ቤት ወጥታ መኖር ትጀምራለች። በሰው ቤት እየተዟዟረች ልብስ እያጠበች ተከራይታ የምትኖረው ሴት በአንድ ጊዜ የመንግስት ሰራተኛ ሆና በኮንዶሚኒም ቤት መኖር ስትጀምር ድርብርብ ደስታ ይሰማታል።
ዘውዴ በተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት የአፀደ ህጻናት ተማሪዎችን እያስተማረች ህይወትን በማጣጣም ላይ እያለች ድንገት ዓይኗ መታመም ይጀምራል። በሁኔታው ትደነጋገጣለች። ከስንት የህይወት ውጣ ውረድ በኋላ ስራ አግኝታ መኖር በጀመረችበት ሰዓት የገጠማት የዓይን ህመም በስራዋ ላይ ችግር ሲፈጥርባት ክፉኛ ታዝናለች። አሉ በተባሉ የዓይን ህክምና ማዕከሎች ክትትልና ምርመራ ብታደርግም ሳይሻላት ይቀራል። እንዲያውም ዓይኗ መጥፎ ደረጃ ላይ እንደደረሰና በህክምና ሊድን እንደማይችል ይነገራታል። ግን ዓይን ነውና ተስፋ አልቆረጠችም። የዓይን ስፔሻሊስቶችን በር እያንኳኳች ብርሃኗን ለመታደግ ጣረች። በሁኔታው ያዘኑት የተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት ሠራተኞችም ገንዘብ በማዋጣት የዘውዴን ዓይን ለመታደግ ርብርብ ማድረጋቸው አልቀረም።
የልጇ አባትም በግሉ ሊያሳክማት ሞክሯል። እስከ 40 ሺህ ብር አውጥታ ለመታከም ሞከረች፤ ግን የሚቻል አልሆነም። ዘውዴ ተስፋ ቆረጠች። ዓይኗ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማየት አቅሙ እየደከመ መጣ። እንደበፊቱ ወጥታ መግባት አቃታት። ግን እቤት ላለመቀመጥ ስትል በጭላንጭል እይታ ውስጥ ሆና ስራዋን እየሰራች ለመግባት ትጥር ጀመር። ዘውዴ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያጣችውን ብርሃኗን አምኖ መቀበል ስላዳገታት ሁልጊዜ ራሷን በበፊቱ ማንነቷ ውስጥ እያደረገች ቀደም ሲል የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ማድረግ አልተወችም። ነገር ግን የሚደርስባት አደጋ እየበዛ ይመጣል። እየወደቁ መነሳት የዘወትር ተግባሯ ሆኗል።
ከአንድም ሁለት ጊዜ የመኪና ግጭት ደርሶባታል። የመጀመሪያው አደጋ ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም። አለርት ሆስፒታል በተደረገላት ህክምና ምንም ሳትተኛ ወደ ስራዋ ተመልሳለች። ከሶስት ወር በኋላ ደግሞ ሁለተኛ አደጋ ይገጥማታል። ሁለተኛው አደጋ ግን ትንሽ የከፋ ነበር። ስትገጭ ተስፈንጥራ የወደቀች በመሆኑ የሰውነት መላላጥና መጋጋጥ እንዲሁም መጠነኛ የእግር ጉዳት ደርሶባታል። ከመኪና አደጋ ውጭም ሶስት ጊዜ ጉድጓድ ውስጥ ገብታ ተርፋለች። በተለይም በአንድ ወቅት ለቡ መብራት ሃይል አካባቢ ከባስ ወርዳ ወደ እህቷ ቤት ለመሄድ ስትሞክር ጉድጓድ ውስጥ ገብታ እግሯን ብረት ሰንጥቋት እስከመሰፋት የደረሰችበትን መጥፎ አጋጣሚ አትረሳውም።
ዘውዴ እንዳሁኑ መነጽር ከማድረጓና ዘንግ ከመያዟ በፊት አታይም ተብላ አትገመትም። አንድ ቀን የከተማ አውቶቡስ ውስጥ ስትገባ ደረጃው ያደናቅፋትና ትወድቃለች። የማየት ችግር እንዳለባት ማንም አልተረዳትም። ከዚያም ሰዎች ያነሷትና ወንበር ይሰጧታል። በሁኔታው የተደነጋገጠችው ዘውዴ ቁጭ ከማለቷ ዓይኗ የደረሰበትን የመጨረሻ ደረጃ እና እንዴት ብላ ስራዋን እየሰራች መኖር እንደምትችል እያሰበች ታለቅስ ጀመር።
አንድ አጠገቧ የተቀመጠ የማታውቀው ሰው ታዲያ ምን እንደሚያስለቅሳት ይጠይቃትና ሁኔታውን ታስረዳዋለች። መምህር እንደሆነች፤ ከጊዜ በኋላ ዓይኗ ማየት እንዳልቻለ፤ ስራዋን ከለቀቀች ለችግር እንደምትዳረግ፤ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ገብታ መማር እንደምትፈልግ፤ ግን የት ብላ መሄድ እንዳለባት አለማወቋን ትነግረዋለች። ሰውየው በጣም አዝኖ ወደሚያውቀው ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ሊያደርሳት ስልክ ተቀያይረው ይለያያሉ። በሌላ ቀን አጠያይቆ ባገኘው መረጃ መሰረት አራት ኪሎ ምስራች ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ይዟት ይሄድና እየሰራች ለመማር ያሰበች መሆኗን አስረድቶ የስራ ጊዜዋን በማይነካ መንገድ ፕሮግራም እንዲያመቻቹላት ያሳምናቸዋል። ዘውዴ የብሬል ትምህርት መማር ትጀምራለች።
የወደፊቱን ህይወቷን የተሻለ ለማድረግ የብሬል ትምህርት መማር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተረድታለች። ትምህርቷን ከጀመረች አንድ ዓመት ሆኗታል። ሦስት ዓመት ያልቃል የተባለውን የመጀመሪያ ኮርስ / አማርኛ መጻፍና ማንበብ/ን በአንድ ዓመት ለመጨረስ እየተጋች መሆኑን ትናገራለች። ከሰኞ እስከ ዓርብ ከሦስት ሰዓት እስከ ሰባት ሰዓት አራት ኪሎ ምሥራች የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ከተማረች በኋላ ከሰዓት በኋላ ወደ ትምህርት ቤት እየሄደች ተማሪዎቿን ታስተምራለች።
ትምህርቱንም በሚገባ እየተከታተለች ነው። ነገር ግን ቀደም ሲልዓይናማ ሆና የምታውቃቸውን ፊደሎች እና ቁጥሮች ከውስጧ አውጥታ በአዲስ ምልክቶች መተካት ፈተና እንደሆነባት ትናገራለች። ከዓይን ንባብ ወደ ጣት ንባብ የሚደረገው ሽግግር ከባድ ቢሆንባትም ትኩረት ሰጥታ በመማር ተጨባጭ ለውጥ እያመጣች ነው። አሁን እየተማረች ያለችው ኮርስ አምስት መጽሐፎች ያሉት ሲሆን፤ እርሷ አራተኛውን መጽሐፍ በመጨረስ ላይ ትገኛለች። እስከመጪው ነሐሴ ወር ማብቂያ አማርኛ ኮርስን ታጠናቅቃለች። በቀጣይ ዓመት ደግሞ አንግሊዝኛ ኮርስ በመጀመር የብሬል ትምህርቷን አጠናቃ ህይወቷን በአዲስ ጎዳና ለመምራት መዘጋጀቷን ትናገራለች።
ዘውዴ በየመንገዱ ዳርና ዳር የሚቆፈሩ ጉድጓዶች አደጋ ከፈጠሩባት በኋላ ዘንግ ይዛም ቢሆን እንቅስቃሴ ስታደርግ ሥጋት እንደሚፈጥርባት ትናገራለች። በተለይም ዓይናማ እያለች አንድ ሰው እንዲሁ መንገድ ዳር ባለ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው መሞታቸውን በዓይኗ አይታለች። የመንገድ ግንባታዎች ሲደረጉ ዓይነ ስውራንን እና አካል ጉዳተኞችን ታሰቢ ሊያደርጉ ይገባል ትላለች።
የትምህርት ቤቷ አስተዳደር የወረዳና ከፍለ ከተማ ትምህርት አመራሮች ችግሯን ተረድተው ስለዳረጉላት ትብብር ታመሰግናለች። በተለይም ርዕሰ መምራኖቿ የሰው ሃብት ሠራተኞችና መምህራን ግማሽ ቀን እያስተማረች ግማሽ ቀን እንድትማር ባደረጉላት ትብብር የመንፈስ ጥንካሬ አግኝታ እየተማረች መሆኗን ትገልጻለች። ለዛሬ የዘውዴን ጥንካሬ እያደነቅን እንሰነባበት። ሣምንት ከሌላ ባለታሪክ ጋር እንገናኛለን። ቸር ይግጠመን።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2013