በቀድሞው አጠራር ራያና ቆቦ አሁን ደግሞ ራያ አላማጣ ከተማ በሚባለው አካባቢ ነው የተወለዱት። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አላማጣ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ታዳጊዋ ኢትዮጵያ በተባለ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ይሁንና 12ኛ ክፍል ሲደርሱ ወቅቱ የደርግ ሥርዓትን ለመጣል ትግሉ የተፋፋመበት ስለነበር ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ። ትግሉን ተቀላቅለውም የራሳቸውን አሻራ አሳረፉ። ከድል ማግስትም አቋርጠውት የነበረውን ትምህርት ተከታትለው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ወሰዱ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በጤና መኮንነት የማዕረግ ተመራቂ ሆነው አጠናቀቁ። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ ክፍለ ጦር ተመድበው ለሁለት ዓመታት አገለገሉ። በመቀጠልም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተወዳድረው የማስተርስ ዲግሪያቸውን በማህበረሰብ ጤና ሳይንስ ሰሩ።
ይህንን ተከትሎም በመከላከያ ሚኒስቴር ጤና መምሪያ ክፍል ተመድበው በመምህርነትና በጤና አገልግሎት መስራት ጀመሩ። በክፍለ ጦር ዳይሬክተርነት፣ በመስክ ቀዶ ጥገና ክፍል የክፍለጦር ህክምና ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገለገሉ። እንዲሁም በመከላከያ ጤና መምሪያ ውስጥ ማርች በተባለ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሆነው ለሶስት ዓመት ሰሩ። በሰላም ማስከበር ሥራም እግረኛ ሆነው የበኩላቸውን ኃላፊነት ሲወጡ ቆይተዋል። ይሁንና በተቋሙ ውስጥ ያለውን ኢ-ፍትሐዊነት በተለይም በአንድ ብሔር የበላይነት የሚሰራውን ግፍ በገሃድ በመቃወማቸው ምክንያት በነበሩት ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ጥላቻን አተረፉ። ከዚህም አልፎ ተርፎ ተደጋጋሚ በደልና መገፋት ደረሰባቸው። ደማቸውን ያፈሰሱለት እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲመጣ ሲሉም ትግላቸውን የቀጠሉት እኒሁ ሰው ‹‹አለቆችን ዘልፈሃል›› ተብለው ይቅርታ እንዲጠይቁ ቢጠየቁም ‹‹አሻፈረኝ›› አሉ። ይህም ያለ እድሜያቸውና ያለበቂ ምክንያት ከሠራዊቱ እንዲሰናበቱ አደረጋቸው።
በዚህ ሁኔታ ተስፋ ሳይቆርጡ በሙያቸው ሕዝባቸውን ለማገልገል ወሰኑ። ከመከላከያ ያለበቂ ምክንያት ከተባረሩበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የግል የጤና ኮሌጆች ተቀጥረው በመምህርነትና በዲፓርትመንት ኃላፊነት የሰሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሜድኮ ባዮ ሜዲካል፣ ኪያሜድ፣ ዩኒቨርሳል ሜዲካል ኮሌጆች ተጠቃሽ ናቸው። ለውጡ እንዲመጣ የግላቸውን ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት እኚሁ ሰው የህወሓትን መወገድ ተከትሎም ከተመሰረተው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አባል መሆን ችለዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ተካተው ላለፉት ሰባት ወራት የትግራይ ክልል የጤና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው በመስራት ላይ ነው የሚገኙት። ከዛሬው የዘመን እንግዳችን ከሌተናል ኮሎኔል ፍስሐ በርሔ ጋር በክልሉና በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ከህወሓት ከፍተኛ ጄኔራሎች ጋር በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ የገቡበት ምክንያት ምን እንደነበር ያነሱልንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– የህወሓት አመራሮች ከመጀመሪያውም አይወዱኝም ነበር። ከእነሱ ጋር በፍጹም አልስማማም ነበር። ምክንያቱም ሴራቸውንና ተንኮለኝነታቸውን ስለማልወደው በገሃድ እቃወማቸው ስለነበር ነው። እነሱ ስለኢትዮጵያዊነት የሚናገር ሰው በድፍረት ትሰርቃላችሁ እላቸዋለሁ። በትልልቅ አዳራሽ ሕዝብ በተሰበሰበበት የሕዝብ ንብረት እያጠፋችሁ ነው፤ በማለት ጄኔራሎቹን እናገራቸው ነበር። እዛ ተቋም ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አድሎ፤ ዝምድና ፣ ኔትወርክ አለ። ተቋሙ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ቢሆንም የአንድ ብሔር ከዚያም በላይ የአንድ አካባቢ ሰዎች የተሰገሰጉበትና እርስበርስ የሚጠቃቀሙበት ነበር። እነዚህ ሰዎች ምንም አይነት እፍረት አልነበራቸውም ነበር። ለሚፈልጉት ሰው ሁለትም፤ ሶስትም መሬት እንዲሁም ቤት ይሰጡታል።
የማይፈልጉትን ሰው ደግሞ እንዲለምን ነው የሚያደርጉት። የማይፈልጉት ሰው ሲንከራተትና ሲወድቅ ማየት የሚያስደስታቸው ሰዎች ነበሩ። ሰው ቤተሰቡን ይዞ ወድቆ ሲያዩት ያስደስታቸዋል። ርህራሄና ፍትሐዊነት የሚባል ነገር የላቸውም ነበር። ‹‹ጥቅም ለማግኘት ከፈለግህ የእኛ ሰው መሆን አለብህ›› የሚል አስተሳሰብ ነው ያላቸው። አይወዱም። መከላከያ ሲጀመርም የህወሓት ድርጅት ነበር። በተለይም ከሠራዊቱ በላይ ያለው አዛዥ ወይም ከጋንታ አመራር ጀምሮ ያሉት የእነሱ ሰዎች ብቻ ነበሩ። እርግጥ ነው ከሌላ ብሔር የመጡ ጥቂት ጄኔራሎች ነበሩ፤ ግን በተቋም ውስጥ ትርጉም አልነበራቸውም። ምክንያቱም የእነሱን ፍላጎት እንዲናገሩ አይፈቀድላቸውም ነበር።
ቢናገሩም ታፔላ ይለጠፍላቸው ነበር። ለኦሮሞው ጄኔራል ‹‹ኦነግ›› እያሉ ያስፈራሩታል። ለአማራው ጄኔራል ‹‹ነፍጠኛ›› እና ‹‹የተነቀልክ›› እያሉ ስም ይሰጡና ያሸማቅቋቸዋል። በዚያ ወቅት አንድ ህወሓት የሚባል ቡድን ሥራ አስፈፃሚ ብቻ ነበር የነበረው። እኔ የራያ ልጅ ነኝ። እኔ በተወለድኩበት ዘመን ሰሜን ወሎ ክፍለ ሃገር ነበር፤ ከህወሓት በኋላ ደግሞ ደቡብ ትግራይ ብለው ራያ አላማጣ ብለውታል። እርግጥ ለእኔ አንድ ሕዝብ ነው። ትግራይም ገባ አማራ ብዙ ትርጉም አይሰጠኝም። ምክንያቱም ለእኔ ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ይበልጥብኛልና ነው።
ከትምህርት ቤት ጀምሮ የአገር ፍቅር ስሜት ኖሮኝ ስላደኩኝ እነሱ በብሔር ሰዎችን ለመከፋፈል በሚያደርጉት ነገር አልስማማም ነበር። አሁንም ቢሆን የዚህ አካባቢ ሰው በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ እንደሆነ ነው የማውቀው። ደግሞ ምርጫውን ለሕዝቡ መተው ነው የሚገባን። ራሱን ችሎ ይተዳደር፣ ወደ አማራም ይሁን ትግራይ መግባት የሕዝቡ ምርጫ ነው መሆን ያለበት። ዴሞክራሲ በሆነ መንገድ ፍላጎቱ እንዲጠበቅለት ማድረግ ያስፈልጋል። ስለዚህ እኔ በዚያ ሰዓት አብዛኛው አማራ አንተ የአማራ ተቆርቋሪ ነህ ነው የሚሉኝ። ‹‹ትግሬ ሆነህ ግን ትግሬነትን የካድክ›› ይሉኛል።
እኔ ግን አልካድኩም። እውነቱን መናገር ኃጥያት አይደለም። አለማጣ ሰሜን ወሎ ነበር ብሎ መናገር ወንጀል አይደለም። ከማውቀው እውነታ ውጭ ልናገር የምችለው የለም። የግድ ግልብጥ ብዬ እንደነሱ ውሸታም ልሆን አልችልም። እነሱ እውነትን እንድክድና ሁሉም ነገር እንደሚደረግልኝ ነበር የሚነግሩኝ። ሰላም ማስከበር ውጭ እንላክህ ይሉኝ ነበር። ቃል በቃል ይቅርታ ጠይቅና መሬት እንሰጥሃለን ብለውኛል። በአጠቃላይ ሌሎች ያገኙትን ጥሩ እድሎችን እንዳላገኝ ተደርጌያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ምን ስለበደሉ ነው ይቅርታ እንዲጠይቁ የተፈለገው?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡- በድፍረት ጄኔራሎች እናገር ስለነበር ነው። በየመድረኩ ጄኔራሎቹን ወንጅያለሁና ይቅርታ በል ነበር የሚሉኝ። በተለይ ጄኔራል ተስፋዬ ግደይ የሚባል አለ፤ ይህ ሰውዬ መከላከያን በሙሉ የእሱና የቤተሰቦቹ የግል ሃብት ያደረገ፤ የመከላከያ ንብረት በሙሉ እንደፈለገ ይጠቀምበት ነበር። እንዳልኩሽ ‹‹ እሱን ይቅርታ ጠይቅና ሁሉንም ነገር እናድርግልህ›› ይሉኝ ነበር። ‹‹ እሺ የማትል ከሆነ ግን እናባርርሃለን፤ እንዳውም በዲሲፒሊን እናስርሃለን›› ነው ያሉኝ። እኔ ግን አሻፈረኝ በማለቴ በ37 ዓመቴ በ2004 ዓ.ም ላይ ከመከላከያ እንድቀነስ ተደርጌያለሁ። በነገራችን ላይ በዚህ እድሜ ከፍተኛ መኮንን በፍፁም አይወጣም ነበር። አንድ የሰራዊቱ አባል የሚሰናበተው የአቅም ክፍተት ከታየበት፣ እድሜው ለጡረታ የደረሰ ከሆነ ብቻ ነው። እኔ ብቻ ሳልሆን እነ ጄኔራል ባጫና ጄኔራል አበባውንም በተመሳሳይ ሁኔታ መባረራቸው የሚታወስ ነው። ሶስት ዙር አውጥተው የማይፈልጓቸውን ሰዎች እና ለእነሱ ፍላጎት የማይገዙ ሰዎችን ነው እንዲባረሩ ያደረጉት።
አዲስ ዘመን፡-ያለበቂ ምክንያት ሲባረሩ ይግባኝ የሚጠይቁበት እድል አልነበረም?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– እኔ በመስፈርት ደረጃ ሁሉንም አሟላ ነበር። እንዳውም ሁሉንም እበልጣቸው ነበር። የእኔ አለቆች እኮ 8ኛ ክፍልን ያላጠናቀቁ ነበሩ። አለቆቼ ማስተርስ አልነበራቸውም። እድሜዬም ለጡረታ አልደረሰም ነበር። አብዛኞቹ ለመማር ሄደው ሲፈተኑ እየወደቁ ነው የሚመለሱት። በውትድርና አቅምም ቢሆን እኔ ወጋገን ሻለቃ ውስጥ ኮማንዶ ነበርኩ። እውነቴን ነው የምልሽ በወቅቱ በውትድርና ከእኔ ጋር የሚደራረሱት ከሶስት አይበልጡም ነበር። ስለዚህ በምንም አይነት መስፈርት ልሰናበት አልችልም ነበር። በወቅቱ ጡረታ ሊወጡ ይገቡ የነበሩት እነጄኔራል ሳሞራ የኑስ ፣ ተስፋዬ ግደይ ነበሩ። ሶስትና አራት ጊዜ እድሜያቸውን እያራዘሙ እንዲጠቀሙ ተደርጓል። የሚገርምሽ ዘመዶቻቸውን ከገጠር አምጥተው ለሰላም ማስከበር ስራ ውጭ ይልኳቸዋል። በተለያየ ምክንያት ከመከላከያ የተባረሩ ሴቶችን ጠርተው ነው የሚልኳቸው። የእነሱ ተቃዋሚ ከሆንሽ ደግሞ ወድቀሽ እንድትለምኚ ነው የሚያደርጉሽ። በተለይ የኢህዴን ኮሎኔሎችንና አዛዦች የነበሩ አባረዋቸው አሁን ላይ የባንክ ዘበኛ ሆነው ነው እየሰሩ ያሉት።
ስለዚህ የነበረው ሥርዓት በሴራና በተንኮል የተሞላ ስለነበር ይግባኝ ብትዪም ሰሚ አታገኚም። ህወሓትን የማትደግፊ ከሆነ ቦታ የለሽም። እኔ ያኔም ቢሆን ይህች አገር የጋራ ነች ነበር የምላቸው። ቃል በቃል እናንተ ጄኔራሎች ዘላለም የምትኖሩ አይምሰላችሁ እላቸው ነበር። በአጠቃላይ የሚያሳፍር ተግባር ነበር በዚያ ተቋም ውስጥ ሲፈፀም የነበረው። አገሪቱን ብቻቸውን ሊበሏትና ሊዘርፏት የተዘጋጁ ነበሩ። ስለዚህ እኔ በድፍረት ፀያፍ ሥራቸውን አጋልጥ ስለነበር ነው ከመከላከያ የተባረርኩት። መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አስተምር ነበር። የፕሮጀክት ኃላፊ ነበርኩኝ። ግን እኔን አባረውኝ በዚያ ቦታ ላይ የራሳቸውን ዘመድ የሆነና ገና የተመረቀ ወጣት ነው ያስገቡት። ይህንንም ያደረጉት ለሌብነታቸው እንዲመቻቸው ሲሉ ነው።
በቡድን ተፈራርመው እንደፈለጉ ገንዘብ ይዘርፋሉ። በተለይ ኤች.አይ.ቪን ለመከላከል የተመደበውን በጀት በከፍተኛ መጠን ነበር ይዘርፉ የነበሩት። እናም ከማዘን ውጭ ይህች አገር የሁላችን አገር ናት የማትዪበት ሁኔታ ነበር። እንዳልኩሽ ከሌላ ብሔረሰብ የመጡ እና የመማር እድሉን ያላገኙት ትላልቅ መኮንኖች አሁንም የቴሌና የባንክ ዘበኛ ሆነው ነው የሚሰሩት። እኔ ግን በትግልና በስንት ክስ በመማሬ እነሱ እንዳሰቡት ወድቄ አልቀረሁም። የሚገርምሽ የመጀመሪያ ዲግሪዬንም ሆነ ማስተርሴን የተማርኩት ከስሼ ነው። እንደዚያም ሆኖ በመማሬ እነሱ ሲያባርሩኝ ብዙ አልተቸገርኩም። ብዙ ጓደኞቼ አግዘውኛል። ከመከላከያ ከወጣሁኝ በኋላ ብዙ ሳልቆይ ነው በግል የጤና ኮሌጆች ስራ ያገኘሁት።
የሚገርምሽ ከስራ ማባረራቸው አልበቃ ብሎ በደብዳቤ ያለምንም ዝግጅት በድንገት ከምኖርበት ቤት እንድወጣ አድርገውኛል። የሚያሳዝነው ደግሞ ደብዳቤውን የሰጡት ለህፃን ልጄ ነበር። ልጄ በህፃን አዕምሮዋ ደብዳቤውን ተቀብላ ስታነብ በጣም ነበር የደነገጠችውና ያለቀሰችው። ይህ የሚሳየው እነዚህ ሰዎች የህፃን ልጅ አዕምሮ ለመጉዳት ቅንጣት ታህል የማያቅማሙ ግፈኞች መሆናቸውን ነው። በዚህ ምክንያት አሁን ላይ የህወሓት ሰዎች ተራቸው ደርሶ በየበረሃው ሲሰቃዩ ስመለከት በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ግን እንደዚህ እንደማይባል አውቃለሁ፤ ሆኖም የበደሉኝ ህመም ዛሬም ድረስ ዘልቆ የሚሰማኝ በመሆኑ እነሱም እንደዚህ ሆነው ስመለከት የእጃቸውን እንዳገኙ አስባለሁ። ሰው አንጠልጥለው ገርፈዋል፤ አሰቃይተዋል፤ ግፍ ሰርተዋል። አሁን እነሱ እንዲህ አይነት ስቃይ ውስጥ ሲገቡ እግዚአብሔር የዘሩትን እንዳሳጨዳቸው ነው የማምነው። እነሱ እኮ ኢትዮጵያን ለመቶ ዓመት ለመያዝ ነበር እቅዳቸው። ግን እነሱ እንዳሰቡት ሳይሆን ጊዜ ፈራጅ ሆኖ በሰፈሩት ቁና እንዲሰፈሩ አድርጓቸዋል። አሁን በረሃ ለበረሃ እየተንከራተቱ ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ከሚደግፉ የትግራይ ተወላጆች አንዱ ነበሩ፤ ለውጡ በአገሪቱ ውስጥ ትክክለኛ ዲሞክራሲ እንዲመጣ ያበረከትኩት ውጤት ነው ብለው ያምናሉ?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– ልክ ነሽ፤ ቁጥር አንድ የለውጡ ደጋፊ ነበርኩኝ። ለውጡን ደግሞ የደገፍኩበት ምክንያት አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ እኔም የዚያ አስከፊ ሥርዓት ተጎጂ ስለነበርኩ ነው። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለውጡ እንደመጣ ያራምዱት የነበረው የዲሞክራሲ አስተሳሰብ፤ ፍትሕና እኩልነት እንዲሰፍን ያደርጉት የነበረው ጥረት ለውጡን በሙሉ ልቤ እንድደግፍ አድርጎኛል። እኔ ብቻ ሳልሆን ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው ነበር። በነገራችን ላይ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የትግራይ ሕዝብ የዶክተር ዐብይ ደጋፊ ነበር። ምክንያቱም ህወሓት ከሚገባው በላይ አፍኗቸው ስለነበረ ለውጡን ከማንም በላይ ይፈልጉታል። ዴሞክራሲ የሚባል ነገር አልነበረም፤ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሲመጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ደግፏቸዋል።
ጥሩ ዲሞክራት ሆነው ነበር የመጡት። በነገራችን ላይ አሁን ላይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል ብሆንም የኢዜማ አባል ነኝ። ነገር ግን አሁን ከአንቺ የምናገረው ነገር ሁሉ የግሌን አመለካከት እንጂ ፓርቲዬን ወይም ጊዜያዊ አስተዳደሩን ወክዬ አለመሆኑ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። አሁን ጊዜያዊ አስተዳደር ሲቋቋም ሕዝብ እንዳገለግል ከትግራይ ሕዝብ ጋር እንድሆን መንግሥትና የምሰራበት ድርጅት ፈቅዶ ለሰባት ወራት ያህል የትግራይ ክልል የጤና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆኜ እየሰራሁኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ክልል ኢዜማ አስተባባሪ ሆኜ ተመድቤ የነበረ ቢሆንም በዋናነት የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል ሆኜ ነው እየሰራሁ ያለሁት። የምሰራውም በሙያዬ እንጂ በፖለቲካ አይደለም። ኮሎኔል እንደመሆኔ ግን በወታደራዊ አቅም ብዙ ላግዛቸው ብችልም እነሱ እንዳግዛቸው አልፈቀዱልኝም።
አዲስ ዘመን፡- ለምንድን ነው ያልተፈቀደልዎት?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡- ተጋብዘን ከሄድን በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በራሱ ፍላጎት ብቻ ነበር ሰዎችን ሲመድብ የነበረው። በተለይም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በወቅቱ ብዙ ደስ የማይሉ ነገሮች ነበር ሲናገሩ የነበሩት። ‹‹ ኢዜማ ግንቦት 7 ነው፤ እኔ ዝም ብዬ ነው የመድብኳችሁ›› የሚልና ከአንድ ክልልን እንዲያስተዳድር ኃላፊነት ከተሰጠው መሪ የማይጠበቅ ንግግር ነበር ይናገሩ የነበሩት። ግን እኔ ባለሙያ ስለነበርኩኝ የክልሉ የጤና ምርምር ዋና ዳይሬክተር ሆኜ እየሰራሁ ነበር። በዚህ ግጭት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ እንድንመጣ ሆነናል።
በዚህ አጋጣሚ እኔ የህወሓት አባልም ደጋፊ አልነበርኩም። እኔ የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝ ነበርኩ፤ በዚህም ምክንያት ብዙ ተጎድቻለሁ። ድሮም ቢሆን ወደ ብሔር ማንነትና ውግንና ካልተጠጋሁ እንደማያልፍልኝ አውቀዋለሁ። ግን እንደእነሱ ከመሆን ባያልፍልኝ ነው የምመርጠው። እርግጥ ነው ጓደኞቼ ሶስትና አራት ህንፃ አላቸው። ከእነሱ ጋር ብለጠፍ የት ልደርስ እንደምችል አውቀዋለሁኝ። ለእኔ ያ ምንም አይደለም፤ ውስጤ ሰላም እስካገኘ ድረስ። 1981 ዓም ወደ ትግል ስወጣ ኢህዴን የሚባል ድርጅት አባል ሆኜ ነው የወጣሁት። ስወጣም በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ነው።
ወደ መከላከያ እስከምገባ ድረስ በኢህዴን ውስጥ ነበርኩኝ። መከላከያ ከገባሁ በኋላም የፖለቲካ አባል አልነበርኩም። ምከንያቱም መከላከያ የኢትዮጵያ ድርጅት ነው። ስለዚህ እኔ ከኢትዮጵያዊነቴ ወርጄ አላውቅም። አብዛኛው ሰው ግን የህወሓት አባል እንደነበርኩኝ ነው የሚያስበው፤ ይሁንና እኔ ሲጀመርም የህወሓት አባል አልነበርኩም። እሱ ነው እንዲጠሉኝ ያደረገው። ትግሬ ነኝ ብዬ ወደ ዘር ፖለቲካ ውስጥ የመግባት ሃሳቡም አልነበረኝም። በቃ እኔ በኢትዮጵያዊነቴ ነው የማምነው። ደግሞም አብዛኛው የራያ ተወላጅ ኢትዮጵያዊነቱን ነው የሚያስቀድመው።
አዲስ ዘመን፡- የህወሓት ተንኮለኝነትና ሴረኝነት ባህሪ ከትግል ጊዜ ጀምሮ የነበረ እንደሆነ ይነሳል። ከዚህ አንፃር የነበረውን ሁኔታ ትንሽ ያስታውሱን?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– እኔ ከህወሓት አመራሮችና አባላት ጋር የማልስማማበት አንዱ ጉዳይ ህወሓት ከጊዜ በኋላ እየተበላሸ ስለመምጣቱ ነው። አብዛኛው ሰው ስለህወሓት የሚናገረው ከግሉ ፍላጎት አንፃር እንጂ ትክክለኛ የህወሓትን ባህሪ አውቆት አይደለም። ለእኔ ህወሓት ገና ወደ በረሃ ሲወጣ ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ አማራ አቋም አንግቶ ነው የወጣው። የህወሓት ማኒፌስቶ ብታይው እኮ ሲጀምርም ፀረ አማራ አቋም እንደነበረው ትረጃለሽ። ስለዚህ ከመነሻው ጀምሮ በዚህ መልኩ ጥላቻን ሰንቆ የወጣ ድርጅት ‹‹ከዚህና ከዚያ ጊዜ በኋላ ነው›› የተበላሸው የሚለው ነገር የሚመጥነው አይደለም። በአጠቃላይ ሲጀመርም ፀረ- ሕዝብና ኢትዮጵያ አቋም ይዞ የመጣ እንዲሁም ትግራይ ገንጥሎ ለመኖር አቅዶ የተነሳ ድርጅት ነው። ለዚህም ነው ህወሓት በሴራ የተጎነጎነ ድርጅት ነው የምንለው። ህወሓት ውስጥ ዘልቀሽ ስትወርጂ እኮ የቤተሰብ ድርጅት ሆኖ ነው የምታገኚው።
በአድዋ አካባቢ ያሉ ሰዎች ስብስብ ነው። እነሱ ይውደዱም፤ ይጥሉም ይህ እውነት ነው። ይህንን ስል የአድዋ ሕዝብን ማለቴ አይደለም። በሥልጣንም ቤተሰባዊ መዋቅር ነው የያዙት። በቤተሰባዊ ካልሆነ እንኳን በጋብቻ ነው የተሳሰሩት። እሱ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ የፊውዳል ቤተሰቦችን ጨፍጭፈዋል፤ አሰቃይተዋል። እምቢ ያላቸውን ከመሬት በታች ጉድጓድ ውስጥ ነው ከተው ሲገርፉትና ሲያሰቃዩት የነበረው። ተቃዋሚ ድርጅት አባል የነበሩትን ‹‹እንታረቅ›› ብለው ጠርተው ሲያበቁ በተኛበት የሚገሉ አውሬዎች ናቸው። ስለዚህ ህወሓት ምኑ ነው ጥሩ?። እኔ ይሄ ነው ብዬ የምጠቅሰው ጥሩነት የላቸውም። ያንን ደግሞ ማንኛውም ሰው ያውቀዋል። በተለይ ነባር ታጋይ የነበሩ በግልፅ ነው የሚናገሩት። በትግል ወቅትም ቢሆን የነበራቸው ተንኮል፤ ሴራና ግድያ ቀላል አልነበረም። ስለዚህ ፀረ-ሕዝብ ሆኖ ያደገ ድርጅት የሚጠብቀው ምንም መልካም ነገር የለም።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም አለ ማለት አይቻልም። በየቦታው ያልተፈፀመ ግፍና ግድያ የለም። ፀረ አማራ እንቅስቃሴዎች በስፋት ነው የምታዪው። የዚህ ሁሉ መንስኤ ምንነትን ማንሳት ይገባናል። ለዚህ ደግሞ ህወሓት ለ47 ዓመታት ሲከተለው የነበረው ፖሊሲ ነው። ዘርን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ነው አሁን ለገባንበት ችግር የዳረገን። በተለይ አማራና ኦሮሞ እንዳይፋቀር፤ አማራና ትግሬ እንዳይፋቀር፤ እርስ በርስ እንዳይዋሃዱ ፤ የየራሳቸው በጎጥ ላይ የተመሰረተ ቡድን እንዲፈጥሩ ነው ያደረገው። ኢትዮጵያዊነትን ማዳከም የህወሓት አንዱ ስልቱና ትልቁ ሴራው ነው። ያ ሴራ ደግሞ እስከአሁን ድረስ እየሰራለት ነው።
የለውጡ ኃይል ከመጣ በኋላም ቢሆን ህወሓት የዘራው የዘር ፖለቲካ አስተሳሰብ በየቤቱ ከተሰቀለበት ማማ አልወረደም። ስለዚህ ይሄ አስተሳሰብ ከመሐላችን መነቀልና መውጣት አለበት። ህወሓት ክፉ ከመሆኑ የተነሳ ከማንኛውም ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር ይወግናል። ሱዳን ድንበር ደፍራ ስትገባ ለህወሓቶች ደስታ ነው። ግብፅ ኢትዮጵያን ብትወር፣ ዓባይን ብትጎዳ ለህወሓቶች ታላቅ ሃሴት ነው። ምክንያቱም ደግሞ ፈፅሞ የኢትዮጵያዊነት ሥነልቦና የሌላቸው በመሆኑ ነው።
አላማቸው አገር ማፍረስ ብቻ ነው። እነሱ ባይጠቀሙም እንኳን ኢትዮጵያ ፈረሰች፤ አልፈረሰችም ጉዳያቸው አይደለም። ምክንያቱም ክፉ በመሆናቸው ነው። ስለዚህ አሁን የሚያደርጉት ሴራ የዚህ ባሕሪያቸው አንዱ ማሳያ ነው። አሁን ላይ በሁመራ በኩል ከሱዳን የሚያዋስነን መንገድ መዘጋቱ እንጂ ቢከፈት የሱዳን ኃይሎች ሊገቡና ኢትዮጵያን ሊጎዱ ይችላሉ። ስለዚህ የህወሓት ሴራ ዝም ብሎ በትንሽ ነገር የምትመዝኚው አይደለም። በጣም ውስብስብና ኢትዮጵያ ውስጥ የዘራው በሽታ በቀላሉ የሚፈወስ አይደለም። በተለይም አማራ ጠል እንቅስቃሴያቸው እንዲህ ነው ብለሽ የምትገልጪው አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ድርጅት ሕዝብና ረሃብን እንደ አንድ የትግል ስልት የመጠቀም ባሕሪው ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡- ልክ ነሽ፤ ይህ አይነቱ ፀያፍ ተግባር የህወሓት የኖረ ባህሪ ነው። አስታውሳለሁ ህወሓት በረሃ እያለ ሕዝብ እንዲራብ ያደርጋል። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ ፖለቲካዊ ጥቅም ስለሚያገኝበት ነው። ለሕዝብ ተብሎ የሚመጣውን ቀለብ ቀምቶ መሳሪያ ይገዛበታል። ስለዚህ ይሄ የህወሓት ነባር መሰሪ ተግባሩ ነው። እሱ ብቻ አይደለም፤ ሕዝብን እንደጋሻና መከታ የመጠቀም ክፉ ልምድ አለው። በተለይ የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት ረገድ ህወሓትን የሚያክለው የለም። በቅርቡ ትግራይ አስተዳደር አካል ከሆንኩ በኋላ ሕዝቡን ምን ያክል በሃሰተኛ መረጃ የመቀየር አቅም እንዳላቸው አይቻለሁ። በዚህ ረገድ የእኛ መንግሥት ምንም አልሰራም። ቢሰራ ኖሮ የህወሓትን መሰሪ ተግባር ማክሸፍ ይችል ነበር። እነሱ ግን በፕሮፖጋንዳ በልጠውናል።
ሕዝብ እንዲሞት ያደርጋሉ ፤ በሕዝቡ ይነግዱበታል። ሕዝብ ጋር ገብተው እንዲጨፈጨፍ ያደርጋሉና ይጠቀሙበታል። ያንን ስልሽ የትግራይ ሕዝብ አልተጎዳም ማለቴ አይደለም። በሥነ-አዕምሮም ተጎድቷል። በኢኮኖሚም፤ በማህበራዊ ህይወቱ ተጎድቷል። ህወሓቶች የትግራይን ሕዝብ ጉዳት ግን አመፅ ማነሳሻና የፖለቲካ ጥቅም ማትረፊያ ነው ያደረጉት። ይህንን ነገር ግን መንግሥት በልጦ መገኘት ነው ያለበት። ለምሳሌ ዋሽተው ሲገኙ የሚያጋልጥ የኢትዮጵያ አልነበረም። ቲ.ኤም. ኤች የተባው ሚዲያ በሁለትና ሶስት ሰዎች እንዴት አይነት ፕሮፖጋንዳ ሲሰራ እንደነበር አይተናል። የሌለ ነገር ፈጥረው የዓለም ሕዝብ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ችለዋል። ትንሽዋን ነገር ሰማይ ያደርስና ሕዝቡን ያነቃቃል።
በእኔ እምነት ህወሓት እንደገና እንዲያንሰራራ ያደረገው በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንድም መንግሥታችን ከመታቸው በኋላ እስከመጨረሻ አልቀጠለም። ግን መቀጠል ነበረበት። ፀረ- ሽምቅ ማድረግ መቻል ነበረበት። በሶስት ሳምንት ውስጥ ህወሓት ስለፈረሰለት ብቻ መርካትና መተው አይገባውም። ከዚህ በተጨማሪ የተሳሳተ መረጃም ነበረው። በሁለተኛ ደረጃ ሕዝቡ ጋር መቅረብ ነበረበት። ምክንያቱም ህወሓት ስራ ሰርቷል። ገና ለውጊያ ሲዘጋጅ ጀምሮ አስቀድሞ ‹‹የኤርትራ ሰራዊት መጥቶ ይወርሃል ፣ ይገድልሃል›› አለው። የአማራ ልዩ ኃይል መጥቶ ይጨፈጭፍሃል፤ ያፈናቅልሃል›› ይለው ነበር። ያንን ያደረገው ደግሞ ሳይሆን በፊት ተሸንፎ እንደሚባረር አውቆ ስለነበር ነው። በተጨማሪም የዐብይ ሰራዊት መጥቶ ይጨቁንሃል እያለ ሕዝቡን ሲቀሰቅሰው ከረመ። እኛ ከዚያ በልጠን መስራት አልቻልንም። ውሸቱን ማጋለጥና የትግራይ ሕዝብ ሕዝባችና ዜጋችን መሆኑን ማሳመን አልቻልንም።
ምንም አያመጣም ብሎ ዝም ነው ያለው። ስለዚህ አጋጣሚ ተሸንፈው ሲሄዱ አንዳንድ ስህተቶች ሰርቷል። አላስፈላጊ የሆነ የሥነ-ምግባር ጉድለት ነበር። መከላከያም በንዴት ስለመጣ አንዳንድ ወጣ ያሉ ወታደሮች ግፍ ሰርተዋል። በእርግጥ እነዚህ አካላት አሁን ላይ በሕግ እየተጠየቁ ነው ያሉት። ከአማራ ክልል የመጣው ልዩ ኃይልም በስሜት ውጊያ ውስጥ ነው ያለው። እነሱም በተወሰነ ሰውን ማፈናቀል ፣ ህወሓት የመሰላቸውን የመግደል ሁኔታ ታይቶባቸዋል። ይህም ሕዝቡ ‹‹እዚህ ቁጭ ብለን ከምንሞትና በረሃ እንውጣ›› የሚል ነገር ተፈጠረበት። በተለይም የወጣቱ ስሜት ፈነዳ። በህወሓት ፕሮፖጋንዳ ተጠቀመ። ወጣቱን በጊዜያዊ ስሜት ወደ በረሃ እንዲገባ አደረገው። በዚህ ረገድ መንግሥት አስቀድሞ የህወሓትን ተንኮል ማጋለጥ ነበረበት። ሚዲያዎች ትግራይ ቢገቡ ኖሮ በየጊዜው መረጃዎችን እየቀመሩ ሕዝቡን ሊያረጋጉት ይችሉ ነበር። ይህ ባለመሆኑ ምክንያት የታጠረች ትግራይ ሆና ቆየች። በአጠቃላይ ህወሓት አደገኛ የሆነ ፕሮፖጋንዳ ሰርቷል፤ ተሳክቶለታል።
አዲስ ዘመን፡- ግን ከ40 ዓመት በላይ ሕዝብ ላይ የተሰራ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ መቀየር ይቻላል ተብሎ ይታመናል?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– ልክ ነሽ እኮ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ 47 ዓመት የነበረው የዘር ፖለቲካ በእያንዳንዱ ሕዝብ ውስጥ ሰርጿል። ይህ ችግር ደግሞ ህወሓት ጋር ብቻ ሳይሆን ኦህዴድ ላይ አለ። የህወሓት መንፈስ ያለቀቃቸው አመራሮች አሁንም አሉ። ታፍኖ ነው እንጂ አስተሳሰቡ አሁንም አለ። እንዳልሽው ለዓመታት ቆይቷል። በተለይም ትግራይ ውስጥ ህወሓትን ከእኛ የወጡ የእኛ ልጆች ናቸው ብሎ በዘር የማሰብ ነገር አለ። ግን ለውጡ ከመጣ በኋላ ያ በስህተት ፖለቲካ ታፍኖ የነበረው ሕዝብ መነቃቃት ተፈጥሮበት ነበር። 95 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ ዐብይን ደግፏል።
ትግራይም እንደዚሁ ነበር። ግን ደግሞ እንደምታስታውሽው ህወሓት ንብረቱን ሰብስቦ ነው ትግራይ የገባው። እዛ ከገባ በኋላ እንደገና ሕዝቡ ላይ ሰራ። የዶክተር ዐብይ ምስል ያለበትን ልብስ ለብሰው የሄዱ ሰዎች እኮ ታስረዋል፤ ተገርፈዋል፤ ተመተዋል። ይህም የሚያሳይሽ የለውጥ ፍላጎት ስለነበረ ነው። ስለዚህ ከዚያ በኋላ በዚህ ግርግር ህወሓት በውሸት በሰራው ፕሮፖጋንዳ ምክንያት ሳታውቂው ትቀበይዋለሽ። በተለይ የዘረኝነት አስተሳሰብ ካለ ‹‹ሌላው ከሚገለን የራሳችን ሰዎች ይግደሉን›› ወደሚል የተሳሳተና ጊዜያዊ ስሜት ውስጥ ትገቢያለሽ። ከዚያ በኋላ የመጡ ነገሮች በተለይም በውጊያ ወቅት የታዩ የዲሲፒሊን ስህተቶች ወጣቱ ህወሓት ጋር እንዲወግን አድርጎታል። መንግሥት ያንን ነበር ማየት የነበረበት። ቀድሞ እንዳውም እነዚያ ችግሮች እንዳይመጡ ትልቅ ሚና መጫወት ነበረበት። ግልፀኝነትም አልነበረውም። ለምሳሌ ስህተት ሲኖር ማመን ነበረበት።
እኔ ብሆን ‹‹ትግራይ ውስጥ ቤተክርስቲያን ተመታ፤ ትምህርት ቤት ፈረሰ›› ሲባል እውነት ነው፤ በውጊያ ውስጥ የሚፈጠር ችግር ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም አለም የሚያጋጥም ነው በማለት ውጊያ አውዳሚ መሆኑን አስረዳ ነበር። ከዚህ ባሻገርም ለለተፈጠረው ነገር ይቅርታ በይፋ እጠይቃለሁ። በዚህ መልኩ ለችግሩ ሁሉ በኃላፊነት መንፈስ እውቅና እየሰጠ ቢሄድ ሰው አያኮርፍም ነበር። ሰው እየተጎዳ ‹‹አልተጎዳም›› ከተባለ ይናደዳል። ምክንያቱም ስሜታዊነት የሰው ልጅ ባህሪ በመሆኑ ነው። ይህ ስሜታዊነት ደግሞ በተለይ ወጣቱን ወደ ስህተት እንዲገቡ አድርጎታል።
አሁን ቢሆን ወጣቱን ለመመለስ ቀላል ነው የሚል እምነት አለኝ። ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ፣ የህወሓትን ሴራ ደጋግሞ ማሳየት፣ ጠንካራ አመራሮች ማሰማራት ይገባ ነበር። አሁን ትግራይ ክልል ብትሄጂ ጊዜያዊ አስተዳደር ተብሎ የተመደበው ግማሹ እኮ ህወሓት ነው። እኛ ቀድመን እንናገር ነበር። አንድ እግር ህወሓት አንድ እግር ኢትዮጵያዊነትን ይዘው የሚሰሩ በርካታ ነበሩ። ምንአይነት ሃሳብ እንደሚያቀነቅኑ ያስታውቃሉ። መንግሥት ግን አያውቃቸውም። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንኳን አያውቃቸውም።
እውነት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ቢኖራቸው ኖሮ፤ ትግራይንና አገራቸውን ማዳን የሚፈልጉ ቢሆኑ ኖሮ አሁን ላይ በተፈጠረው ነገር መውጣት ነበረባቸው። ወደ 78 የሚሆኑ ከፍተኛ አመራሮች እዛው ቀርተዋል። ይህንን ስታዪ እኔ ከእነማን ጋር ነበርኩኝ ብዬ እንድሰጋና እንድቆጭ ነው ያደረገኝ። ከእነዚህ ሰዎች ጋር መስራቴ ለእኔም ትልቅ አደጋ ነበር። ስለዚህ መንግሥት ወይም ጊዜያዊ አስተዳደሩ እነዚህን ሁኔታዎች ማየት ያልቻለበት ሁኔታ ነበር። ለዚህ ውድቀትም ሁላችንም ተጠያቂ እንደሆንን ማወቅ አለብን ነው የምለው።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ተቆርቋሪ ነኝ ባይ ነው። በእርግጥ መሬት ላይ የነበሩት ነገሮች የሚያሳዩ ነበሩ? አሁንስ ወደ ጦርነት የገባው ለሕዝቡ አስቦ ነው?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– እንደእኔ እምነት ህወሓት ከሕዝብ ጋር የሚያገናኘው አስተሳሰብም ዓላማም የለውም። ለ27 ዓመታት መንግስት ሆኖ ሲሰራና አገርን ሲመራ ስለትግራይ ሕዝብ አንድ ቀን አስቦ አያውቅም ፤ ያደረገውም ነገር የለም። እውነቴን ነው የምልሽ ስለራሱ እንጂ የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ ተጨንቆ አያውቅም። ያንን ሁሉ ዓመታት ተጠቅሞ ከሥልጣኑ ሲነሳ ግን የሕዝቡን ትኩረት ለማግኘት የሞት ሽረት እንቅስቃሴ ነው ያደረገው። ምክንያቱም ህወሓት ሥልጣንና ዘረፋ ነው የሚያውቀው። ህወሓት የራሱን የበላይነት ለማንገስና ብቻውን ለማስተዳደር ነበር ሲሰራ የነበረው። ስለዚህ ያንን እድል ሲያጣ መመሸጊያ ያደረገው ሕዝቡን ነው። እኔ እዚህ ጋር ብዙ ስህተቶች ይታዩኛል።
እኔ በዶክተር ዐብይ ቦታ ብሆን ገና ከዚህ ሳይሄዱ ሰብስቤ እስር ቤት ነበር የማስገባቸው። ከሄዱም በኋላ ቢሆን ሳይደራጁ ሰብስቦ ማምጣት የሚችልበት እድል ነበረው። ምክንያቱም ያንን የማድረግ አቅም ነበረው። በነገራችን ላይ የመንግሥት መዘናጋት ብዙ ጊዜ ነው የሚታየኝ። ምንአልባት ለሰላም፣ አገር ለማረጋጋት ብሎ ይሆናል። እያወቀ ችላ ያላቸውም በድርድር አገርን ለማስቀጠልም ከማሰብ ሊሆን ይችላል። ግን ደግሞ ህወሓቶች መሰሪዎች መሆናቸውን አውቆ እርምጃ መውሰድ ነበረበት። ከሄዱ በኋላም ለራሱ መጠቀሚያ ነው ያደረጋቸው። ስለትግራይ ሕዝብ ቆርቁሮት አያውቅም። እንዳውም ሲጨፈጭፈው፣ ሲያስረው፣ ሲያንገላታው የነበረ ሕዝብ ነው።
ትግራይ ያለው ባለሃብት እኮ አዲስ አበባ መጥቶ መስራት ነው የሚፈልገው። ትግራይ ውስጥ ነፃነት የለም። ስለዚህ ህወሓት ወደመቀሌ ሄዶ መመሸጊያ ነው ያደረገው። ወዲያውኑ ነው ‹‹አማራ ጠላህ፤ ኤርትራ ከበበ›› እያለ ሕዝቡን ወደ መቀስቀስ የገባው። ስለዚህ ምንም ሰው ‹‹ተከበብክ›› ሲባል ከከበባ ለመውጣት ነው ጥረት የሚያደርገው። እናም በስህተት ፕሮፖጋንዳ ሰውን እያሳመኑ ሰዎን ወደ ራሱ ማድረግ ጀመረ። በመሰረቱ ግን ህወሓት ሕዝባዊነት የለውም፤ ለትግራይ ሕዝብም አስቦ አያውቅም። አሁንም ከሄደ በኋላ 27 ዓመት የትግራይን ሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሲል ብቻ ‹‹እስከዛሬ በድያለሁ ከዚህ በኋላ እክስሃለው›› ብሎ መሬትና ቤት ሲሰጥ ነበር። እስከዛሬ ሰርቶ የማያውቀውን ነገር ሲሰራ በተለይም ወጣቱ ህወሓትን ወደማመን መጣ።
ህወሓት በባህሪው ሕዝብን መከፋፈል ነው የሚታወቀው። ለምሳሌ የራያ ትግሬዎችን እነዚህ ሞኞች ይላል፤ ተንቤን ደግሞ ያሉትን ጉረኞች ይላቸዋል። አዲግራት ደግሞ ያሉትን ዜጎች ነጋዴዎች፣ ትግል የማያውቁ እያለ ቅፅል ስም እየሰጠ ሲያንቋሽሽ ነው የሚውለው። ለእሱ ጀግና አድዋ አካባቢ ያሉ ሊሃቃንና በተለይ የአቦይ ስብሃት ኔትወርክ አድርጎ ነው የሚወስደው። ስለዚህ ይህ ባህሪው ሕዝባዊ አለመሆኑን ያሳይሻል። ከመጀመሪያውም ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ለትግራይ ሕዝብ ቢያስቡ ኖሮ ዲሞክራሲን ለማስፈን ጥረት ያደርጉ ነበር። ትግራይ ብቻ ሳትሆን ይህች አገር የት በደረሰች ነበር። 1997 ዓም ምርጫም አልተጠቀሙበትም።
ሕዝቡ እንደጠላቸው ያውቃሉ፣ ሳይመረጡ ሲቀሩ እስቲ ለዲሞክራሲ ሲባል ሥልጣናቸውን መልቀቅ አልፈለጉም። ህወሓት ሕዝባዊ ድርጅት ቢሆን ኖሮ እኔም በደገፍኩትና በተቀላቀልኩ ነበር። እነሱ ፀረ ሕዝብ ናቸው። አብዛኞቹ አመራሮችም ‹‹እኔ ብቻ ልምራ›› የሚልና ‹‹እኔ ከሌለሁ ይህች አገር ትፍረስ›› የሚል አቋም ነው ያላቸው። ፈፅሞ ለትግራይ ሕዝብ የሚጠቅም አላማም፤ ራዕይም የላቸውም። አሁን የትግራይ ሕዝብ እየተሰቃየ ያለው እኮ በማንም ምክንያት አይደለም። በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ ትግራይ ውስጥ ያለው ስቃይ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ባሻገር የሥነ-አዕምሮ ችግር ደርሶበታል። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂ የሚሆነው ህወሓት ነው። ምንአልባት ሌላው አካል የየራሱን ድርሻ ሊወስድ ይችላል፤ ግን መሰረቱ የዘር ፖለቲካ ያደረገ የህወሓት ሴረኛ አካሄድ ነው ለዚህ የዳረገን ብዬ ነው የምደመድመው።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት አሁን ባለው ቁመና እድሉ ቢሰጠው ትግራይን የመምራት አቅም አለው?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡- ለእኔ ህወሓት እድል ቢሰጠውም ፈፅሞ የማይስተካከል ድርጅት ነው። እንደእኔ እምነት ህወሓት ከነጭራሹ መጥፋት ነው ያለበት። በእርግጥ ሰላማዊ ድርድር ጥሩ ነው፣ ወደ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ መምጣት ጥሩ ነው። ግን አንድ አውሬ እንዴት አድርገሽ ነው ልታላምጂው የምትችይው? እንዴትስ ነው ስለ ሰላም ዋጋ ነግረሽው የሚረዳሽ?። ለእኔ ፈፅሞ የማይታሰብና ረብ የለሽ ነው። ትግራይን እንዲመራ እድሉን ብትሰጪውም በትክክል አይመራትም። መለወጥ ቢችሉ እኮ መቀሌ ከከተሙ በኋላ ሕዝቡን በዚያ ደረጃ ባልጨቆኑት ነበር። አሁን እንኳን ስንዴ ለሕዝቡ ሲያድሉ የነበሩና ሕዝቡን ሲያግዙ የነበሩ ወጣቶችን ‹‹የዐብይ ደጋፊዎች ናችሁ›› በሚል እየጫኑ ወደተንቤን ነው ይዘዋቸው የሄዱት። ንፁሃንን እየወሰደ መግረፍ ጀምሯል። ማሰር ጀምሯል። እንዴት ብሎ ታዲያ ትግራይን የሚያስተዳድረው? ስለዚህ ውስጡ የሰላም አስተሳሰብ እስከሌለው ድረስ ህወሓት መጥፋት ነው ያለበት።
መንግስት ለውይይት ከመጡ እንደሚቀበላቸው ተናግሯል። በተለይም ከመካከለኛ እና ታችኛው አመራር ጋር ለመደራደር እንደሚፈልግ ገልጿል። በነገራችን ላይ በህወሓት ውስጥ መካከለኛ እና ታችኛው አመራር የሚባል ነገር የለም። እኔም አይገባኝም። ሁሉም አንድ ወጥ አስተሳሰብ ነው ያላቸው። አቋማቸውን ቀይረው እስካልመጡ ድረስ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም። እንዳውም ከላይኛው አመራር በላይ ይብሳሉ። ያገኙትን ሰው የመግደል፣ የመቁረጥ፣ የማሰቃየት ስራ የሚሰሩት እነሱ ናቸው። እኔ እንደዚህ አይነት ነገር አልቀበለውም። ህወሓትን ለድርድር መጥራት በራሱ የዋህነት ነው።
ይልቁኑ ከነጭራሹ እንዲጠፋ ነው መስራት ያለብን። በመሰረቱ ህወሓት ወደ ድርድር አይመጣም፤ ጊዜ ማባከን ነው የሚሆነው። አሁን እኮ ይህችን ሲሰማ ፈፅሞ ሊሆን የማይችል ቅድመ ሁኔታ ዘርዝሯል። መሣሪያ ከውጭ ጭኖ ለማምጣት ሲል አውሮፕላን በቀጥታ እንዲመጣለት ነው የጠየቀው። ስለዚህ የሞኝ ቅድመ ሁኔታ ነው ለእኔ። ህወሓትን ማሸነፍ የሚቻለው በኃይል ብቻ ነው። በረሃ ውስጥ እኮ እንደራደር ብለው ያልጮሁት ጩኸት የለም እኮ። አሁን እድሉ ሲሰጣቸውና ፋታ ሲያገኙ ደግሞ የምንደራደር ከሆነ መንግሥት ከእኛ በታች ይሁን ነው ያሉት። የማይሆን መስፈርት ነው እያወጡ ያሉት።
ስለዚህ ለእኔ የዚህ የድርድር ሃሳቡ ይሆናል ብዬ አላስብም። እንዳውም ከተቻለ መንግሥት ብዙ ሳይጠናከሩና ኃይል ሳይፈጥሩ ቶሎ ተመልሶ ገብቶ ማጥፋት መቻል አለበት። መከላከያ ተመልሶ ትግራይን መቆጣጠር አለበት ባይ ነኝ። መንግስት ቅድሚያ ለትግራይ ጉዳይ ቢሰጥ ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ። አገር ውስጥ ሆኖ የሚቦረቡረንን አካል ማጥፋት መቻል አለብን። እኔ እንዳውም አሁን ትልቁ ስጋቴ እንደራደር ካልን ለህወሓት እድልና ጊዜ ሰጥተነው የበለጠ ተጠናክሮ እንዳይመጣ ነው። በመሆኑም አሁን ቶሎ አቅም ሳይኖራቸው ቶሎ ማጥፋት መቻል አለበት። ሠራዊቱ ወደ ትግራይ መግባት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች ሠራዊቱ ከመሰረቱም ቢሆን መውጣት አልነበረበትም ሲሉ ይሞግታሉ፤ እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ? መንግስት የሠራዊቱን መውጣት አስመልክቶ ያቀረበውስ ምክንያት ምን ያህል አሳማኝ ነው ይላሉ?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– መንግሥት የተናጠል ስምምነት ማድረጉን እስማማበታለሁ፤ ትክክልም ነው ብዬ አምናለሁ። እንኳን እኛ በጦር አቅማቸው የበለፀጉ አገራትም የሚቀበሉት ነው። ነገር ግን የተናጠል ተኩስ አቁም ለማድረግ ከትግራይ መውጣት ይገባ ነበር ብዬ አላምንም። በሁለት ምክንያት ነው የሠራዊቱ ከትግራይ መውጣት ስህተት ነው ብዬ ነው የማምነው። አንድ ለህወሓቶች እድል መስጠት ነው። ለህወሓት እድል መስጠትና እንዲጠናከሩ ማድረግ ወጣቱን እንዲያስታጥቁ ማድረግ ማለት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ሲወጣ ተማሪዎችን፣ የብልፅግና ደጋፊዎችን ፣ የተቃዋሚ ድርጅት ደጋፊዎችን ይዞ መውጣት አልቻለም። እንደእኔ እምነት መውጣት አልነበረበትም ነበር። ባይወጣ ኖሮ ግን የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነቱ የሚደገፍ ነው። እዛው ሆኖ ማድረግ ይችል ነበር። አሁን ላይ የሚሰጡ ምክንያቶች ለእኔ አሳማኝ አይደሉም። አልያ ደግሞ ‹‹የውጭ ኃይሎች እየመጡብን ስለሆነ ለዚያ እንዘጋጅ›› ማለት አንድ ነገር ነው። በነገራችን ላይ አጠቃላይ ሁኔታው ግልፅ አይደለም። ብዙ ሰው ግራ ገብቶታል፤ እኔም ግራ ከገባቸው ሰዎች አንዱ ነኝ። ምክንያቱም ግልፅ የሆነ ሕዝብን የሚያሳምን አቋም በመንግሥት በኩል መደረግ ነበረበት።
ከትግራይ ሳይወጣ ሰራዊቱን በትላልቅ ካምፖችና ከተሞች ቢደረግ ህወሓት አቅም ኖሮት ከመከላከያ ጋር የሚዋጋበት ሁኔታ አይኖርም። እየተበታተንሽ ከሄድሽ ግን መከላከያችን ሊጎዳ ይችላል። ግን በካምፕና በዋና በዋና ከተሞች ቢሆን ማንም አይነካውም ነበር። ሕዝቡንም ይጠብቃል፤ የህወሓትንም እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል፤ አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት ደግሞ እርምጃ ይወስዳል። ከዚህ አንፃር ግን ድንገት ለቆ መውጣት ትክክል አይደለም። እንደእኔ የትግራይን ሕዝብ ለጅብ ሰጥቶ እንደመምጣት ነው የምቆጥረው። ምከንያቱም ህወሓት ማለት አራዊት ማለት ነው። ስለዚህ እኔ በዚህ ውሳኔ ቅር ብሎኛል።
አዲስ ዘመን፡- የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል የነበሩ በርካታ አመራሮች መገደላቸውን ተከትሎ የነበረው ሁኔታ ከመከላከያ ሰራዊቱ አቅም በላይ ሆኖ ነው ብለው የሚያነሱ ሰዎች አሉ። እርሶ ይህ ሃሳብ ምን ያህል አሳማኝ ነው?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– በወታደራዊ አይን ሳየው ከመከላከያ አቅም በላይ ስለሆነ ነው ብዬ አላምንም። በእርግጥ የጦርነት አንዱ ባህሪ አውዳሚነቱ ነው። በውጊያ ትማርኪያለሽ፤ ትማረኪያለሽ። ይሄ የውጊያ ባህሪ ነው። ከተማረከ ምንም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ሁኔታዎች በአካባቢ መልክዓ ምድር የሚወሰኑ በመሆናቸው ነው። በእነዚህ ምክንያቶች የኃይል አለመመጣጠን ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ የመከላከያ አንድ ጋንታ ሄዳ የህወሓት አራትና አምስት ኃይሎች ቢኖሩ የውጊያ አለመመጣጠን ይኖራል። ገምተሽው የሄድሽው ከገመትሽው በላይ ሲሆን ልትማረኪ ትቺያለሽ። ምንም አዲስ ነገር አይደለም። እንደከባድ ነገርም አልወስደውም። ከህወሓት አባላትና ሚሊሻዎች እኮ በብዛት ተማርከዋል። ስለዚህ የምርኮ ነገር እኔ እንደትልቅ ጉዳይ ሊታይ አይገባም። በመሰረቱ ልደብቀውም ብትይ አትደብቂውም። ውጊያ ገብተሽ ‹‹አልማረክም›› አትዪም። ምክንያቱም ሁኔታዎች ናቸው የሚያስገድዱሽ። በአካባቢው የአቅም የበላይነት ነው የሚወስነው።
ሌላው ትግራይ ውስጥ ከሶስት ሳምንቱ ውጊያና የህወሓት ሰራዊት ከፈረሰ በኋላ ህወሓትና መከላከያ ፊት ለፊት አይዋጉም ነበር። አቅምም አልነበራቸውም። የህወሓት ልዩ ኃይል ፈርሷል፤ ተበታትኗል። መሸሸጊያ ሲፈልጉ ነው የቆዩት። በኋላ ላይ ከዚያም ከዚያም ኃይል ፈጥረው ውጊያቸውን ቀይረው የሽምቅ እንቅስቃሴ ነው የጀመሩት። መከላከያ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ሲሄድ ካገኙት መንገድ ላይ ይጠብቁትና ባልታሰበ ሁኔታ ይመቱታል። በተለይም ደግሞ የዲሲፒሊን ችግር ያለበት ወጣት ወደእነሱ ሲቀላቀል አቅም አገኙ። ይህችን ተጠቅመው በየቦታው ይዋጉ ነበር።
መከላከያም እየሄደ ያጠቃቸው ነበር። እኛ ጋር ምን ይጎድለን ነበር? ብትዬኝ፣ መንግሥታችን ከደመሰሳቸው በኋላ መዘናጋቱ ነው። ይህ መሆን አልነበረበትም። የፀረ-ሽምቅ እንቅስቃሴ በሰፊው ማድረግ ነበረበት። የኦሮሚያ ፣ አማራ የአፋር የሱማሌ ልዩ ኃይል አለ። ለምን አላዘመተውም ኢትዮጵያዊ አይደለም እንዴ? ለምን ፖሊስ ሆኖ ትግራይ ውስጥ አይሰራም? ያንን ማድረግ ይቻል ነበር። በአጠቃላይ የመንግሥት አሸንፌያቸዋለሁ ብሎ መዘናጋት ለሌላ ስህተት ዳርጎናል ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- የሕዝብ ድጋፍ ካልታከለበትና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ያለመጠናከሩ ሠራዊቱ በሚገባው ልክ ውጤት እንዳያመጣ አያደርገውም? በተለይ ደግሞ የንፁሃን እና የአስተዳደሩ አካላት ግድያ እየተበራከተ መምጣቱ የመንግሥትንስ ቅቡልነት አያሳጣም?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– እውነት ነው፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት በየቦታው ይመታሉ፤ ታፍነው ይሄዳሉ። ሠራዊቱ በአብዛኛው በረሃ ላይ በአብዛኛው የሚያሳልፈው። ከተሞች አካባቢ ብዙ የተጠናከረ ጥበቃ አልነበረም። ከተማ ገብተው ሰው ይዘው ገለው እስኪሄዱ ድረስ በቂ ሠራዊት ቢኖር ይይዛቸው ነበር። ግን ክፍተቶች አሉ። እሱ ብቻ አይደለም ፣ ከ10ሺ በላይ እስረኛ ተበትኗል። በተጨማሪም ልዩ ኃይሉ የሲቪል ልብሱን ቀይሮ ከተማ ውስጥ አለ። ያንን የማፅዳት ስራ አልተሰራም። ያም ባለመሆኑ ባገኙት አጋጣሚ የሚፈልጉትን ሰው መጥተው የመውሰድ ነገር አለ። በነገራችን ላይ ወስዶ መግደል ጥሩ ነው።
የወሰዱትን ሰው ያሰቃዩታል፤ ከገደሉ በኋላ ያርዳሉ፤ ይቆራርጣሉ። ይህንን የሚደርጉት ሌላ ሰው እንዲፈራና እንዲማርበት ነው። ከውጭ ሆኖ ለሚያየው ሰው የትግራይ ሕዝብ ለምንድነው ከህወሓት ጋር የሚወግኑት? ብሎ ይጠይቃል። ግን ወዶ አይደለም የሚደግፈው። ብልፅግና ወይም ኢዜማ ጥሩ ነው ብለሽ መናገር አትችዪም። እንደዚያ ብትይ ልክ እንደእንስሳ ትታረጂያለሽ። እያሳዩ ነው የሚያርዱት። እንደሰው ይህንን ስታይ ትፈሪያለሽ። እንዳውም የሥነ-አዕምሮ ቀውስ ነው የሚፈጥርባቸው። ስለዚህ ያ ሁሉ መታሰብ አለበት። ያ ሁሉ ግምት ውስጥ መግባት አለበት። ይሁን እንጂ ሰው ስለተገደለ ብቻ ወይም ህወሓት ስለቀሰቀሳቸው ብቻ አይደለም። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ህወሓት የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ይጠቀማል፤ በማስፈራራትና ሰው በመግደል ሰዎችን ለማሳመንና ሰው በመቅጣት ሌላው እንዲማርበት ያደርጋል። ያ ግን ጊዜያዊ ነው። የትግራይ ወጣት አሁን ላይ የወገነ የሚመስለው ተደራራቢ የስነ ልቦና ጉዳት ስለደረሰበት ነው። ስሜታዊ ያደረገው ደግሞ ቀድሞ ግንዛቤ ስላልተሰጠው ነው። እውነታውን መሸፈን ነገሩን ያባብሰዋል እንጂ አይጠቅምም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ትግራይ ያሉ የኤርትራ ስደተኞችን የመግደል ሁኔታ እየተጠናከረ መጥቷል። እነዚህና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሕይወት ከመታደግ አኳያ ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– እነዚህን አካላት በሚመለከት ከፍተኛ የሆነ ስጋት ነው ያለኝ። እንደ እኔ እምነት ለመልቀቅ መከላከያ ሲዘጋጅ እነዚህ አካላት ይዞ መውጣት ይገባው ነበር። ከቻለ አለመውጣት ነበረበት። ከወጣ ደግሞ በህወሓቶች ሊጎዱ የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማሰብ መቻል ነበረበት። ይሄ ውሳኔ እንዴት ሊመጣ እንደቻለ ለእኔ ዛሬም ድረስ ግራ የሚያጋባ ነው። ህፃናት ተማሪዎች፤ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ ተማሪዎችን ትቶ መምጣት ፍትሐዊ አይደለም። ለምን እንደተደረገ መጠየቅ አለበት። ስህተት ነው። መቀበልም አለበት። ቸኩሎ ወጥቶ ከሆነም ይህንኑ ማስረዳት አለበት። አልያም ከህወሓት ጋር ተነጋግሮ ከሆነ ማስረዳት አለበት። ከዚያ ውጭ ግን ራሳቸውን በኃላፊነት መምራት የማይችሉ ተማሪዎችን ትቶ መውጣት አልነበረበትም። ስህተት ነው። መንግሥት ይህንን ማመን አለበት። ጠቅላይ ሚኒስትራችን ገና እንደመጡ እኮ በኢህአዴግ ስም ለተፈፀሙ በደሎች ሁሉ እኮ ይቅርታ ለሕዝቡ ጠይቀዋል። ስለዚህ አሁንም ይህ ነበር ሊደረግ ይገባል።
እሱ ብቻ አይደለም፤ የብልፅግና አባላትና ደጋፊዎች ፤ በተለይ የልማት ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን እኮ አልተነገራቸውም። አሁንም ድረስ ጠፍተው በየሰው ቤት እያደሩ በእግራቸው የገቡ አሉ። ይህ ሁኔታ ነገ ከመንግሥት ጎን ሕዝቡ ለመሰለፍ ጥያቄ የሚፈጥርበት ነው። መንግሥትን አምኖ እያለ የማያድነው ከሆነ አደጋ ነው። በመንግሥት ላይ የሚኖረን እምነት እየቀነሰ ነው የሚሄደው። የትግራይን ሕዝብ እኮ ለበላተኛ ነው ሰጥቶ የመጣው። በጥቂት ሰዎች በጊዜያዊ ስሜት ተገፋፍተው ከህወሓት ጋር ወግኗል ተብሎ ጥሎ አይወጣም። የጀርመን ሕዝብ እኮ በጊዜያዊ ስሜት ናዚን ደግፏል። ግን ናዚን የደገፈው የሌላውን ጭቆናን ውጊያን ደግፎ አይደለም። ጊዜያዊ ስሜቶች ካለፉ በኋላ ሕዝቡ ራሱ ጠላት ነው የሆነበት። ስለዚህ ጊዜያዊ ስሜቶች እንደሚቀዘቅዙ አስቦ እዛው ሆኖ መታገል ነበረበት። የህወሓት ሴራ ደግሞ እስከመገንጠል የሚደርስ ነው። የትግራይ ሕዝብ ስለኢትዮጵያ ዋጋ የከፈለ ነው፤ በምንም መልኩ ከሌላው ሕዝብ ጋር ሊነጠል አይገባውም። ዛሬ ትግራይ ብትገነጠል ነገ ኦሮሚያ ይገነጠላል። ምንም አትጠራጠሪ የዘር ፖለቲካ እስካለ ድረስ ይሄ አይቀሬ ነው። ከስሜታዊነት በመውጣት ቁጭ ብለን መመካከር አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ በህወሓት የተታለውም ሆነ ውዥንብር ውስጥ የገባው ሕዝብ የጥሞና ጊዜ ወስዶ እንዲያስብ እድል አይሰጠውም ብለው ያምናሉ?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– በእኔ እምነት መንግስት ከምንም በላይ ግዴታውንና ኃላፊነቱን ማወቅ አለበት። ወደደም፤ ጠላም ሕዝቡን የመጠበቅ ግዴታ አለበት። ነገ የአማራ ሕዝብ አልቀበልም ቢለው ከአማራ ክልል ሊወጣ ነው? የኦሮሞ ሕዝብ አልቀበልም ቢለው ከኦሮሚያ ሊለቅ ነው። አይደለም። ስህተት ነው። ስለዚህ ሕዝቡ ተቀበለውም አልተቀበለውም ፤ ደገፈውም አልደገፈውም ዜጋ ነው መጠበቅ አለበት። የደገፈሽኝ እሺ፤ ያልደገፈሽን እምቢ አይባልም። ከዚህ አኳያ ከደርግ ስህተት ብንማር ጥሩ ነው ባይ ነኝ። ደርግ ጠንካራ ሠራዊት ነበረው። ግን በሚሳሳታቸው ስህተቶች ነው እየወደቀ የመጣው። ራሱ ነው የወደቀው። ዓሳን ለማጥፋት ባሕሩን መጥረግ የሚባል ነገር ምንአልባት ስሜታዊ ለሆነ ሰው ትክክል ሊመስለው ይችላል። ግን ያ ስህተት ነው። እንደዚህ አይነት መርህ ሀገር እንድትቀጥል አያደርግም። ስለዚህ ሊሆን የሚገባው ሁሉንም በእኩል መንገድ መቻል ነው። ወዳጅም አለው፤ ጠላትም አለው። ሌላው ይቅርና የትግራይ ሕዝብ ችግር ምንድን ነው? ከየት መጣ? ብሎ ቢያስብ እኮ ምክንያቱን ያውቀው ነበር። በእኔ እምነት በፕሮፖጋንዳ ስለተበለጠ ነው። የህወሓት ፕሮፖጋንዳ በጣም ትልቅ ደረጃ ደርሷል። ለዚያውም በሃሰት ላይ ተመስርቶ።
በመሆኑም ሰዎች በውሸትና በስሜት ሊያኮርፉ ይችላል፤ ግን ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ ዝም ተብሎ ጥሎ አይወጣም። ‹‹ክፉዎች፣ ካንሰሮች አሉ›› እየተባለ ለእነዚህ አካላት የትግራይን ሕዝብ ጥሎ መውጣት በምንም መልኩ አሳማኝ አይደለም። ሌላ ድርጅት ቢሆን ኖሮ ምንአልባት እስኪ ይዩት የጥሞና ጊዜ ልስጣቸው ይባላል ፤ ለህወሓት ግን ሕዝብ ታምኖ አይሰጥም። ይህ ሁኔታ የትግራይን ሕዝብ ስቃይ ይጨምረዋል። ስለዚህ ረጋ ብለን አስበን ከስሜት ወጥተን መንቀሳቀስ ነው የሚገባን። የትግራይ ሕዝብ በስህተት የሚያደርጋቸው ስህተቱ እንዲመለስ ማድረግ ያስፈልጋል። ስህተትን በስህተት መመለስ አይቻልም። በመሰረቱ መንግሥት ከትግራይ በወጡ ሰዎች ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሞ እንዲመራ አደረገ። የላካቸውን ሰዎች ግን በትክክል አያውቃቸውም። ስለዚህ አስተውለሽ ካልሰራሽ ከባድ ነው የሚሆነው። ግማሹ የህወሓት ተላላኪ ስለነበር እርስበርሱ ይፈራራል፤ አንድነት አልነበራቸውም።
ሌላው የራሱን ኑሮ ማሯሯጥ ነው የተያያዘው። ሕዝብ ጋር ወርዶ የሰራው ነገር የለም። ስለዚህ ጥሩ አድርጌያለሁ የሚላቸውን ነገሮች መፈተሸ ነው ያለበት። ዝም ብሎ በስሜት ሹመት ይሰጣል፤ ግን አገር ሲመራ ሳይሆን ሲያፈርስ ነው የታየው። አንዳንዱ እኮ ለህወሓት መረጃ ሲያቀብል እኮ ነው የነበረው። ለሕዝብ ተብሎ የሚሄደው እህል እና መድኃኒት ህወሓት ጋር ነው የሚደርሰው። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ትክክለኛ የሕዝብ ተቆርቋሪ አለመሆናቸውን ነው የሚሳይሽ። ከዘር ፖለቲካ የፀዱ አለመሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። በነገራችን ላይ ህወሓት ተንኮለኛ በመሆኑ አንድ ሺ የራሱን ሰዎች ብልፅግና አድርጎ ሊያስገባ ይችላል። ስለዚህ አባል ናቸው ብሎ ማመን አያስፈልግም፤ እንዳውም ትክክለኛ ማንነታቸውን መፈተሸ ይገባል። ስለዚህ መንግሥት ከመሾሙ በፊት የኋላ ታሪካቸውን መፈተሸ አለበት።
በሌላ በኩል ደግሞ በተጋሩ ወይም ትግርኛ ተናጋሪዎች ላይ ዝም ብሎ በጅምላ የሚደረግ ማወከብ አለ። ሳያጣሩ ማሰርና ከሥልጣን ማውረድ ነገር ይታያል። ይህ በራሱ ሌላው ችግር ነው። ጊዜ ያልፋል፤ የማያልፍ ቅሬታ ግን በሕዝብ ላይ መፍጠር አያስፈልግም። እርግጥ ነው ወንጀለኛ በሕግ መጠየቅ አለበት፤ እኔ በዚህ አልደራደርም። ንፁህ ሰው ደግሞ ዝም ብሎ ስለተጠረጠረ ብቻ መንገላታት የለበትም። ስለዚህ ይህ በጣም ጥንቃቄ ያስፈልጋል። እኔ ዶክተር ዐብይ የራሳቸውን አመለካከትና ስሜት ብቻ ተከትለው ቢሄዱ ደስ ይለኛል። እኔ እሳቸው ቀና እና ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንዳላቸው ነው የማምነው። ለዚህ ደግሞ ማሳያ አድርጌ የማቀርብልሽ መጀመሪያ ተሹመው ሲመጡ ተናግረው ሲመጡ የተናገሩት ንግግር የራሳቸው ሃሳብ መሆኑ ነው።
ያንን አስተሳሰብ ማስቀጠልና ከጎናቸው ያሉ አሳሳች አማካሪዎችን ማስወገድ ነው የሚገባቸው። አንዳንዶቹ ወደ ብሔር ፖለቲካ ሊጎትቷቸው ይችላል።
አዲስ ዘመን፡-ህወሓት ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ለመፍጠር እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ምን ያህል አስጊ ነው ተብሎ ይታሰባል?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– ልክ ነው፤ መንግሥታችንም የተቸገረበት ጉዳይ ነው። ምንአልባት ለሕዝብ ላይናገር ቢችልም ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ እንዳለበት ግልፅ ነው። ምክንያቱም ደሃዎች ስለሆንን ከእነሱ የምናገኘው ብዙ ነገር አለ። ግንኙነቱን መዝጋት የለብንም። ህወሓት እንዳልሽው አለማቀፍ ተፅዕኖ ለመፍጠር የማያደርገው ነገር ዓለም አቀፍ ትኩረት ለማግኘት ሲል አንዳንድ ጊዜ እኮ ራሱ ገሎ ተገደሉብኝ ነው የሚለው። ራሱ የመከላከያ ዩኒፎርም ለብሶ እርምጃ ከወሰደ በኋላ ለውጭ አገራት ያሳያል። ፈረንጆች የሞተ ሰው ሲያዩ ደግሞ እውነት ነው የሚመስላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የእርዳታ እህል ወደ ሕዝቡ ሲሄድ መንገድ ላይ ያቆሙትና ወይም ይወስዱታል አልያ ደግሞ ይመልሱታል።
ሲመልሱ እኔ ብዙ ጊዜ አይቻለሁ። ይህንን የሚያደርጉት ሕዝቡ እንዲራብና እንዲማረር ነው። ከዚያ የረሃብ ስሜት ሕዝቡ ላይ ሲታይ ፈረንጆች መጥተው ያዩትና ረሃብ አለ ይላሉ። ያ የሴራ ፖለቲካ ነው። እነዚያ ፈረንጆች ደግሞ ያዩት ነገር እውነት ነው የሚመስላቸው። እነሱ ማን ገደለው? ማን አስራበው? አይሉም። መንግስት ይብለጣቸው የምለው ለዚህ ነው። ሚዲያ መግባት አለበት ያልኩትም ለዚህ ነው። ይህ የህወሓት ሴራ የኖረ ታሪኩ ወይም ልምዱ ነው። ህወሓት ድሮም ለተራበ ሕዝብ የመጣ እህል ሽጦ መሳሪያ የሚገዛ ድርጅት ነው። ስለዚህ ህወሓት ሆን ብሎ ሕዝብ እያስራበ ነው ያለው። በሌብነትና በብልጠት መንግሥትን በልጦታል። መንግሥት ደግሞ ይህንን ቀድሞ ብዙ መስራት አለበት። ይህንን የሴራ ፖለቲካ በዓለም ሕዝብ ፊት ሊያጋልጠው ይገባል። ራሱ ደፍሮ ተደፈረችብኝ ይላል። ስለዚህ ያንን ተከታትሎ ማጋለጥ የመንግሥት ስራ ሊሆን ነው የሚገባው።
የአዲስ ዘመን፡- በተመሳሳይ ህወሓት ውጭ የሚኖሩ የዲያስፖራ አባላቱን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ለመፍጠር ጥረት ያደርጋል። በዚያው ልክ ግን ሌላው ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ በህብረትና በአንድ መንፈስ የህወሓትን ሴራ ከማጋለጥ ረገድ የሚቀሩት ነገሮች መኖራቸው ይነሳል። ከዚህ አኳያስ ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– ትክክል ነሽ፤ አገር ውስጥ የምታይውን ስዕል እኮ ነው ዲያስፖራው ላይ የምታይው። እዚህ ሸምተውት ሄደው ነው። እዚህ በዘር ከተከፋፈልን እዛም ስንሄድ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ነው እየተከፋፈልን ያለነው። ይህ ደግሞ ህወሓት ለ47 ዓመት የሰራው የሴራ ፖለቲካ ውጤት ነው። ይህ የሴራ ፖለቲካ እኔና አንቺ በኢትዮጵያዊ አንድነታችን ፀንተን እንድንቆይና እንድንተባበር ከማድረግ ይልቅ በጎጥ አስበን ተለያይተን እንድንኖር ነው ያደረገን። እርስበርሳችን እንድንጠራጠር ያደረገ ድርጅት ነው። አሁን እኮ የመከላከያ ሰራዊት ሲጎዳ እልል ብሎ የህወሓት ባንዲራ ይዞ የሚጨፍር ዲያስፖራ አለ።
ስለዚህ ይህ የዘር ፖለቲካ የፈጠረው ውስብስብ ችግር ነው። እኔ አንዱ ከዶክተር ዐብይ የምጠብቀው የዘር ፖለቲካን ከነጭራሹ ያጠፋዋል ብዬ ነው። ከቀጠለ ግን አገሪቱ ከዚህ የባሰ ችግር ውስጥ ትገባለች። በሌላ በኩል ግን ቅድም እንዳነሳሁት ንፁሃን ከወንጀለኞች ሳይለዩ በብሔራቸው ብቻ የማግለሉ ነገር ዲያስፖራውን የሚያስቆጣበትና የሚከፋፍልበት ሁኔታ አለ። ይህ ደግሞ የተረኝነት መንፈስ እንዲጎለብት ያደርጋል። እርግጥ ነው ሆን ተብሎ ተደርጓል ብዬ ባላምንም እንደዚህ አይነት ነገሮችን መፈተሽ ይገባል ባይ ነኝ። ወንጀለኛ ያልሆነውን ትግራዋይ መንግስት አጠገቡ ሊያሰልፈው ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 100 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለህብረተሰቡ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል። ይህ ግን ብዙም ትኩረት አይሰጠውም። ይህ ከምን የመነጨ ነው ብለው ያምናሉ?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሃ፡- መጠኑን በሚመለከት ትክክለኛ መረጃ ባይኖርም እርዳታ ይገባል። ቢያንስ 70 በመቶ የሚሆነው እርዳታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ነው። ይሄ ግልፅ ነው። በውጭ የሚንጫጫው ድርጅት ከመንግሥት በላይ እርዳታ አላደረገም። ግን የሚላከው እርዳታ በትክክል ሕዝቡ ጋር ስለመድረሱ ግን ጥርጣሬ አለኝ። ይሄ ነው ትልቁ ጥያቄ መሆን ያለበት። እርዳታውን የሚቀበሉትና የሚያደርሱት እነማን ናቸው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል? ማጣራት ያስፈልጋል።
እኔ መቀሌ በነበርኩበት ሰዓት በእርግጠኝነት የተራበው ሰው እንዳልደረሰው ተመልክቻለሁ። አንዳንዶቹንም አግኝቼ ይህንን ማረጋገጥ ችያለሁ። በተቃራኒው የከተማው ነዋሪና ብዙም ያልተቸገረው እርዳታ ተሰጥቶት ታያለሽ። ስለዚህ በትክክል እርዳታ የሚያስፈልገውን ሰው መለየቱ ላይም ችግር እንዳለ ነው የምረዳው። ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው የመጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ስታዬ ደግሞ ታዝኚያለሽ። እዛ ያሉ አመራሮች ለተቸገሩት ቅድሚያ ለምን እንደማይሰጡ መጠየቅ ያስፈልጋል። ይህንን የሚደርጉት የህወሓት ተወካዮች መሆናቸውን አምናለሁ።
እነሱ ደግሞ ይህንን የሚያደርጉት ሰው እንዲማረርና እንዲያኮርፍ ነው። በአጠቃላይ መንግሥት የሚልከው እህልና መድኃኒት ለሕዝቡ የማይደርሰው በመሐል ላይ ያሉት የህወሓት ሴረኞች መኖራቸው ነው። መንግሥት የሚመድባቸው ሰዎች ሥራው እንዳይሰራ እንቅፋት እየፈጠሩ እና ሕዝቡ ስሜት ውስጥ እንዲገባ እያደረጉት ነው። ያንን መንግሥትም ተረድቶ መፈተሽ አለበት። በዚህ አጋጣሚ ሰላም ሚኒስትሯን ማድነቅ እፈልጋለሁ። ከልባቸው ነው ለሕዝቡ እየሰሩ ያሉት። የትግራይ የካቢኔ አባል ሆኖ በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሾመ ሰው ‹‹በአላማ ፅናት እኮ ህወሓትን የሚያክል የለም›› ሲል ትሰሚያለሽ። መንግሥት ሕዝብ እንዲያረጋጉ ልኳቸው አገር ሲያፈርሱ ነው የሚውሉት። ስለዚህ እንዲህ አይነቱን መንጥሮ ማውጣት ነው የሚገባው። ይህንን ሳያስተካክል ከላይ ብቻ ሆኖ የሚታየውን ሴራ መመዘን አይገባውም።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው የህወሓት ቡድን የመከላከያ ሰራዊት መውጣቱን ተከትሎ በሕዝቡ ላይ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ እየወሰደ ነው። ለመሆኑ ከዚህ ችግር ለመውጣት የትግራይ ሕዝብ ምን ማድረግ አለበት ? ከሕዝቡ ምን ይጠበቃል ?
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡– ጥሩ ጥያቄ ነው፤ እኔም ብዙ ጊዜ የሚስጨንቀኝ ጉዳይ ይህ ነው። በነገራችን ላይ ሁሉም ሕዝብ ሕወሓትን ይደግፋል ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። አብዛኛው ሕዝብ የኢትዮጵያዊነት ስሜቱ ታፍኖ የተቀመጠ ነው። ይህንን ታፍኖ ያለ ሕዝብ ቦታ ልንሰጠው ይገባል። ከህወሓት ጋር እየወገነ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ግን ሊያስተውል ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ነገሮችን በጥሞና መፈተሸ አለበት። በጊዜያዊ ስሜት ተነድቶ ክልሉንም ሆነ ሕዝቡን ወደአልሆነ መስመር መክተት የለበትም። እርግጥ ነው፤ እዛ ያለው ህብረተሰብ በኢኮኖሚ ተዳክሟል፤ በውጊያው ተጎድቷል፤ የሥነ አዕምሮ ችግር ደርሶበታል። ማህበራዊ ጫና ተፈጥሮበታል።
ያ ስቃይ ጊዜያዊ ነው ያልፋል። በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ፣ በጀግንነት ታሪኩና ባህሉ ሊደራደር አይገባም። ለሚያልፍ ጊዜ ብለው ከሰይጣናዊ ድርጅት ጋር ሊወግኑ አይገባም የሚል እምነት ነው ያለኝ። አሁን ላሉት ችግሮች በሙሉ ተጠያቂው ህወሓት መሆኑን የትግራይ ሕዝብ መገንዘብ አለበት። ስለዚህ የህወሓት ሴራ ነቅቶ በማጋለጥ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር በሰላምና በፍቅር ሊኖር ይገባዋል። ህወሓት ሕዝባዊ አስተሳሰብ የሌለው በመሆኑ ሕዝቡን አብሮ ይዞ ለመጥፋት የተዘጋጀ ድርጅት መሆኑን መረዳት ይገባናል። ሕዝቡ በቻለው መጠን ህወሓትን መቃወም ይገባዋል። ልጆቹ ታፍነው ሲወሰዱበት፤ ሲገደሉበት፣ ሲራብና ሲዘረፍ ለምን ብሎ ህወሓትን መጠየቅና መጋፈጥ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ሌ/ል ኮሎኔል ፍስሐ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2013