ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተጠናቆ በተወሰኑ አካባቢዎች የምርጫው ውጤት እየተነገረ ይገኛል። በምርጫው ሂደትም ብዛት ያላቸው ሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ይጠቀሳል። ማህበሩ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ወጣቶችን በማሰማራት የመታዘብና ፀጥታውን የማስከበር ስራ አከናውኗል። ማህበሩ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ዙሪያ ያከናወናቸው ተግባራትና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከማህበሩ ዋና ፀሐፊ ወጣት ይሁነኝ መሀመድ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ማህበሩ በምን ሁኔታዎች ላይ ተሳትፎ አደረገ? ምንስ ታዘበ?
ወጣት ይሁነኝ፡- የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ከምስረታው ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን ነበር። ከዚህም ውስጥ የወጣቶችን ጉዳይ አንዳንዴም አገራዊ ጉዳዮች ውስጥ እየገባ የሚንቀሳቀስ ማህበር ነው። ማህበሩ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይንቀሳቀሳል። እነዚህን ስራዎች በረጅም ጊዜ እቅድና በአዳዲስ ነገሮችና ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ይሰራል። በአገራዊ ጉዳዮች ላይም እጁን በማስገባት ተሳትፎ ያደርጋል። ከዚህ በመነሳት በቅርቡ በአገሪቱ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ይከናወናል ከተባለበት ጊዜ አንስቶ እንደ ማህበር ምን ምን ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ውይይት ተደርጓል።
በተደረገው ውይይት ቀደም ብለው የተካሄዱት ምርጫዎች ምን ይመስሉ እንደነበር፣ በምርጫዎቹ ውስጥ የሲቪክ ማህበረሰቡ የነበረው ሚና ምን እንደሚመስል እንዲሁም የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ምን ምን ስራዎችን ሲያከናውን ነበር። ምን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ነበሩት የሚሉትን በመለየት ጠንካራ ጎኖችን ለማጎልበትና ከወቅታዊ ጉዳዮች አንፃር ቃኝቶ እንዴት መስራት እንደሚቻል በእቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገባ። በተጨማሪም ምርጫውን ለመታዘብ የሚያስችል ፈቃድ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጠየቅም ስራ ተከናውኗል። ከዛም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅድመ ምርጫ ትምህርት መስጠትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፈቃድና የመታዘብ ፈቃድ ለማህበሩ ተሰጥቶታል።
ማህበሩ በታዛቢነትና በአስተማሪነት ስራዎችን ሲሰራ ሌሎች ሲቪክ ማህበራት በአጋጣሚ ይሁን በሌሎች ምክንያቶች ስፖንሰር ያገኙ ሲሆን ማህበሩ ግን በበጎ ፈቃድ በወጣቱ አቅም ስራዎችን አከናውኗል። የቅድመ ምርጫ ስራዎች እንዳሉ ሆነው በምርጫው ወቅት የተከናወኑ ስራዎች ምን ይመስላሉ? ምንስ ተከናወነ? የሚለውን ስንመለከት ማህበሩ በታዛቢነት፣ በምርጫው ወቅት ከኮሮና ወረርሽኝ ህብረተሰቡ እራሱን እንዲጠብቅ ግንዛቤ በመስጠትና የአካባቢን ሰላም በማስጠበቅ ዙሪያ ተሳትፏል። በታዛቢነት ስራ ላይ የተሰማሩት ወጣቶች ከየትኛውም ፓርቲ አባል ያልሆኑ ሲሆን አንድ ሺህ 285 ወጣቶች ተሳትፈዋል። በፀጥታ ስራ ወጣቶች የተሰማሩ ሲሆን በሚኖሩበት አካባቢ የፀጥታ ስጋቶችን እንዲቆጣጠሩ አንድ ሺህ አንድ መቶ ወጣቶች ተሰማርተዋል። ሌላው በኮሮና ወረርሽኝ ጥንቃቄ ማሳወቅና ግንዛቤ መስጠት ስራዎች ተሰርተዋል። በዚህ ስራ 780 ወጣቶች እንዲሰማሩ ተደርጓል። በአጠቃላይ ሶስት ሺህ 165 ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። ይህን ስራ የሚያስተባብሩ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተማ አንድ ሺህ 700 ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል።
ማህበሩ በምርጫው ወቅት የታዘባቸውን ነገሮች በሪፖርት መልክ ያዘጋጀ ሲሆን ሪፖርቱን በአራት ዘርፍ ከፍሎ አስቀምጧል። መራጩ የህብረተሰብ ክፍል፣ የፀጥታው ኃይል የነበረበት ሁኔታ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሚል የተቀመጠ ነው። መራጩ ህብረተሰብ ክፍል ላይ የተስተዋሉ ነገሮች ያሉ ሲሆን ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ ዝናብ፣ አካባቢ ምቹ አለመሆን፣ የምርጫ ወረቀት እጥረት እንዲሁም ሌሎች ችግሮች ቢኖርም ታግሶ ምርጫው እንዲከናወን አድርጓል። እስከ ማታም ድረስ በመቆየት ድምፁን ሰጥቷል። የሚፈጠሩ ትንንሽ ክፍተቶችን ከሚመለከተው ክፍል ጋር በመሆን ለመፍታት ያደረገው ሙከራ በመልካም ጎኑ የሚወሰድ ነው። የነበሩ ችግሮችን የኔ በማለት የሚፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ ችሏል።
የፀጥታ አካላት ከዚህ ቀደም ይፈጠራሉ ተብለው የተቀመጡ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንዳለባቸው አቅጣጫ የተቀመጠላቸው ሲሆን ይህን ስራ ለማገዝ ማህበሩ አባላቱን አሰማርቶ ነበር። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከተደረጉ ምርጫዎች በተለየ ሁኔታ በአዲስ አበባ የፀጥታ አካላት በአግባቡ ስራቸውን ያከናወኑ ሲሆን ከምርጫ ማስፈፀሚያው ቦታ የነበራቸው ርቀት፣ ምርጫው ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል ነፃ በሆነ መንገድ መስራታቸው የሚደነቅ ተግባር ነው። እጥረቶች የነበሩት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ ሲሆን የአስፈፃሚዎችን ግንዛቤ ክፍተት የነበረ ሲሆን በምርጫ አስፈፃሚዎች መካከል የነበረው የግንዛቤ ክፍተት ከፍተኛ ነበር። በየምርጫ ጣቢያው በቂ የሰው ኃይል አለመመደብ የተስተዋለ ሲሆን ጥቂት ሰው የተመዘገበበትና አንድ ሺህ አምስት መቶ ሰው የተመዘገበበት ጣቢያ እኩል አስፈፃሚ ተመድቦባቸዋል። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ሰልፎች እንዲፈጠሩ አድርጓል። የምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ አለመከፈታቸው በእጥረት የተወሰዱ ናቸው።
ብዛት ያላቸው ሰልፎች የነበሩት በምስጢራዊ ድምፅ መስጫ ሳጥኖች አካባቢ ሲሆን በየምርጫ ጣቢያው የተቀመጡት ሶስት ሚስጥራዊ ድምፅ መስጫዎች በመሆናቸው ለመራጩ ሕዝብ ሊበቁ አልቻሉም ነበር። አንድ ሰው የሚፈልገውን ፓርቲ ፈልጎ እስኪመርጥ ብዙ ደቂቃዎችን የሚፈጅ በመሆኑ መስተጓጎሎችን ፈጥሮ ነበር። ጉለሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ ማህበሩ ያሰማራቸውን ታዛቢዎች አናስገባም የሚል ምርጫ አስፈፃሚዎች አጋጥመው ነበር ። በምርጫው የተሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች በመልካም ጎን የሚነሱ ሲሆን በየምርጫው ጣቢያ የቻሉትን ያክል ታዛቢዎችን ለመወከል ሙከራ አድርገዋል ። ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ያላቸውን ጥያቄ በመገናኛ ብዙኃን በኩል ማቅረባቸው የሚያበረታታ ተግባር ነበር። በክፍተት ደግሞ በምርጫው ተወዳዳሪ ሆነው ምንም አይነት ታዛቢ ያላስቀመጡ ፓርቲዎች ነበሩ። አንዳንድ የፓርቲ ታዛቢዎች የተለያዩ እንከኖችን በመፈለግ የምርጫ ስራውን ለማስተጓጎል ሲጥሩ የነበሩ ሰዎች ተስተውለዋል።
ዋናው ነገር የነበሩ ችግሮችን በመቋቋም ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ያደረገው የህብረተሰቡ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነው። የፓርቲ ታዛቢዎች የድምፅ መስጫው ተጀምሮ የድምፅ ቆጠራ እስኪካሄድ ድረስ ቆይተው ያለመታዘብ ክፍተቶች ነበሩ። በምርጫው ወቅት የተከሰቱ ችግሮች ሆነው በአስተዳደራዊ ደረጃ የሚፈቱ ጉዳዮችን እንደ ነፃ ማህበር ለሚመለከተው ሪፖርት ተደርጓል። አሁን የተጠቃለለ ውጤት እየተጠበቀ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ባየነው ግን እንደተፈራው ምንም አይነት የፀጥታ ችግር ሳይፈጠር በሰላም ተጠናቋል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁን ወቅት የምርጫው ውጤት የሚነገርበት ወቅት ነው ። ነገር ግን አብዛኛው የምርጫ ክልሎች ላይ ቅሬታዎች እየቀረቡ ይገኛሉ። በማህበሩ በመታዘብ ስራው ለቅሬታ የሚዳርጉ ጉዳዮች አስተውሏል?
ወጣት ይሁነኝ፡- ማህበሩ አላማውና እንደ ውጤት የተመለከተው ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቱን ድምፅ ይዘን መንቀሳቀስ ነው። ማህበሩ በምርጫው ወቅት የነበረውን ሚና በአግባቡ ተወጥቷል የሚል ግምገማ አለን። በየምርጫ ጣቢያዎች የሚነሱ ጥያቄዎች በቃለ ጉባኤ እንዲሰፍሩ ተደርጓል። የተነሱትም ጥያቄዎች ወደ ምርጫ ቦርድ እንዲሄዱ፣ እንዲሁም ምርጫ ቦርድ የማይፈታቸውን ወደ ሕግ እንዲሄዱ የሚደረግበት አካሄድ ስላለ በዛ የሚታይ ነው። እንደ ምርጫ ቦርድ አባባል አብዛኛው ቦታ ላይ ቅሬታዎች ቀርበዋል። በተለይ የግል ታዛቢዎችና ፓርቲዎች አቅርበዋል። ማህበሩ የምርጫ ውጤቶች በፍጥነት የሚገለፁበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ነው ብሎ ያምናል። በምርጫው አሸናፊ ማን መሆኑ ቶሎ አለመታወቁ ህብረተሰቡ ላይ የሚፈጥረው ቅሬታ አለ። በጉዳዮቹ መብዛት ምርጫ ቦርድ የሚያዘገይበት ሁኔታ ስለሚኖር አስተያየት ለመስጠት ይከብዳል። በተቻለ ፍጥነት ቆጠራው ተጠናቆና ቅሬታዎች ተፈትተው ወደ ተግባር መገባት አለበት።
አዲስ ዘመን፡-የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ተጀምሯል ወጣቱ በግድቡ ዙሪያ በማህበራዊ ሚዲያው በምን አይነት መንገድ የአገሪቱን አቋም ማንፀባረቅ አለበት?
ወጣት ይሁነኝ፡- እንደሚታወቀው እንደ ሕዝብ ወይም እንደ ቤተሰብ የሚያለያዩ ጉዳዮች ቢኖሩም አንድ ከሚያደርጉን ነጥቦች መካከል የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ነው። ይህ የህዳሴው ግድብ ተጠናቆ ውጤት ላይ መድረስ ሳይሆን በሂደቱም ተጠቃሚዎች ነን። በራሳችን አቅም የትኛውንም ዓለም ለእርዳታ እጃችንን ሳንዘረጋ የምንገነባው ግድባችን ነው። በሌላ በኩልም የተለያዩ ጥያቄዎች ቢኖሩንም በግድቡ ግንባታ አንድነታችንንና ማንነታችንን የምናሳይበት ነው። አሸናፊነትና ድል አድራጊነትን የሚያጎናፅፍ ሲሆን ማቀድና መተግበር አገሪቱ እንደምትችል የታየበት ነው።
ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት እየተከናወነ ሲሆን በዚህ ዙሪያ የወጣቱ ሚና ብዙ ነው። እንደ ማህበር የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በመደበኛ እቅድነት ተይዞ የሚሰራ ነው። ምን ያክል ቦንድ እንደተገዛ፣ ምን ያክል በስጦታ መልክ እንደተሰበሰበና ምን ያክል ገቢ እንደገባ ይገመገማል። ሁለተኛው ዙር ሙሌት መጀመሩ ለስኬት እየተቃረበ መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው። በዚህ ጉዳይ ወጣቱ በሌሎች ጉዳዮች ሳይዋጥ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ማስተዋወቅና መስራት አለበት። በተጨማሪም የማህበራዊ ሚድያ እንቅስቃሴን በማጎልበት በግድቡ ግንባታና ውሃ ሙሌት ዙሪያ የኢትዮጵያን አቋም ማንፀባረቅና ለተቀሩት አለማት ማስተዋወቅ ይገባል። እያንዳንዱ ሰው የሚያስተላልፈው እያንዳንዱ መልዕክት ተርጉመው የሚመለከቱ ሰዎች ስለሚኖሩ በጥንቃቄ የኢትዮጵያን አቋም ማንፀባረቅ ያስፈልጋል። የግድቡ ግንባታ እንደተጀመረው ይጠናቀቃል። ሌሎችንም ስራዎች በዚህ ወኔ ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማሳየትም ይገባል። በግድቡ ዙሪያ ተቃውሞ ለሚያሰሙ አገራት ቅድሚያ በቃላት ጦርነት ማሸነፍ ያስፈልጋል። ከዛም በአስተሳሰብ በመብለጥ የራስን ሀሳብና አቋም ማሳየት ይቻላል። በተግባር የታየውን አሸናፊነት በሌሎች መንገዶችም መድገም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ ለማረጋጋት መንግስት ከክልሉ መውጣቱ ይታወሳል። ነገር ግን ወጣቱ ብሔርን መሰረት አድርጎ ወደ ግጭት እንዳይገባ በምን አይነት መንገድ ችግሮችን መፍታት አለበት?
ወጣት ይሁነኝ፡- መንግስት ለትግራይ ሕዝብ የፅሞና ጊዜ ለመስጠት ወታደሮቹን አስወጥቷል። ፅሞና ሲባል መረጋጋት እራስን ማድመጥ መስከንና ማገናዘብን ያመለክታል። ሁኔታዎችን በተረጋጋ ሁኔታ ማየት እንጂ የውሳኔ ጊዜ ላይ አይደለንም። ስለዚህ በዚህ በፅሞና ጊዜ ውስጥ የትግራይ ነዋሪ የሆኑ አርሷደሮች፣ ድሀውና ታማሚው ብቻ ሳይሆን ከትግራይ ክልል ውጪ ያለው ነዋሪም የፅሞና ጊዜ መውሰድ አለበት። የተከሰተውን ጉዳይ በአግባቡ ለማጤን በሰከነ መንገድ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። በዚህ የፅሞና ጊዜ ውስጥ ይህን ችግር በማየት አላስፈላጊ የሆኑ የቃላት ጦርነቶች ይነሳሉ። ከቃላት የተነሱት ናቸው ወደ ተግባር ጦርነት የሚያስገቡት። ተገቢ ያልሆኑ የቃላት ጦርነቶች በትግራይ ውስጥ የሚገኘውን ሕዝብ በሰከነ መንገድ ገምግሞ መካሄድ አለበት። ስለ ትግራይ ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያው በኩል እንደሚተላለፉት ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ወጣቱ ሊረዳው ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጠኸን ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡
ወጣት ይሁነኝ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2013