ወ/ሮ መሰረት አብዲ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የዘወትር አንባቢ ናቸው።ደንበኛዋ ወደ አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ደውለው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን በስፋት እያስተዋቀ ስለሚገኘው የ4ጂ አገልግሎት ምንነትና ጠቀሜታ መረጃ እንድንሰጣቸው ጥያቄ አቅርበውልናል።በዚሁ መሰረትም ከኢትዮጰያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣንና ከተለያዩ የመረጃ ምንጮቾች ያገኘናቸውን ሃሳቦች ለሁሉም አንባቢ በሚስማማ መልኩ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።መልካም ንባብ ።
አዳዲስ የመገናኛና የመረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂዎች በየጊዜው የሰዎችን ህይወት እያቀለሉት ይገኛሉ።ዛሬ በዓለም ላይ በእጅ ስልክና በኮምፒዩተር አማካኝነት ሰዎች ቦታ ሳይወስናቸው የማይሰሩት ስራና የማይለዋወጡት መረጃ የለም።በዚሁ ዘመን በወለደው የመገናኛ ቴክኖሎጂ ገንዘብ ይለዋወጡበታል፣ንግድ ያቀላጥፉበታል፣መረጃ ይቀባበሉበታል፣ በጥቅሉ በአዳዲስ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችና አገልግሎቶች አማካኝነት የሰዎችን የአኗኗር ዘይቤ ሁሉም ነገር ቀላል እየሆነ መጥቷል።
ይህ የመገናኛ ቴክኖሎጂና አገልግሎት በየጊዜው እየተሻሻለና ብዙ አይነት ፈጠራዎች እየታከሉበት በመሄዱም ሰዎች በየትኛውም የዓለም ጫፍ ሆነው አስተማማኝ የመረጃ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፣ፈጣን የመረጃ ልውውጥ ተደራሽ እያደረገም ነው ፣የኔት ወርክ ሽፋኑም በእጅጉ እያደገ ይገኛል።
ዓለማችን ከመጀመሪያው ትውልድ 1ጂ ጀምሮ አሁን እስከተደረሰበት 5ጂ(5ኛ ትውልድ) የሞባይል የመረጃ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ድረስ ጥቅም ላይ ውለዋል። በተለይ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት መጀመሩን ተከትሎ 1ጂን ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ከጊዜ ሂደት በኋላ 2ጂ፣ 3ጂ፣4ጂ እያለ 5ጂ አገልግሎት መድረስ ተችሏል።1ጂ የመገናኛ ቴክኖሎጂ አገልግሎት የድምጽ ጥራት ጉድለት ያለበትና የሚሸፍናቸው አካባቢዎች ውስን ቢሆንም እነዚህ መሰረታዊ ችግሮችን በመፍታት 2ጂ፣3ጂ፣4ጂና 5ጂ የቴክኖሎጂ የኤተርኔት ዳታ አገልግሎት ሊፈጠሩ ችለዋል።
በቴክኖሎጂ ትውልዶች የዕድገት ሂደትም መረጃ የሚለዋወጡና የኤተርኔት አገልግሎት የሚጠቀሙ ሰዎች አስተማማኝ መረጃ የማግኘታቸው አቅም እየጠነከረ፣ፈጣን የመረጃ ልውውጡም እየጎለበተና የኔት ወርክ ተደራሽነት ሽፋኑም እየተስፋፋ ሊመጣ ችሏል።
እነዚህ በየጊዜው እየተሻሻሉ የመጡ የቴሌኮም አገልግሎቶች በአገራችን ጥቅም ላይ ከዋሉም ውለው አድረዋል።አገራችን ኢትዮጵያም አዳዲስ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችንና አገልግሎቶችን መጠቀም ከጀመረች ሁለት አስርት ዓመታትን ልትደፍን አራት ዓመታት ብቻ ነው የቀራት።ኢትዮጵያ የተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል)ና የኢንተርኔት አገልግሎትን መጠቀም ከጀመረች 16 ዓመታት ያህል ሁኗታል።በዚሁ ሂደትም አራተኛው ትውልድ(4ጂ) ኤልቲኢ አድቫንስድ የተሰኘውን አገልግሎት ጥቅም ላይ ከዋለ እንኳ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። አሁንም በአገራችን የተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋ ይገኛል።
እ.ኤ.አ 2020 ላይ ዕውን የሆነው የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ ቴክኖሎጂን ዛሬ ላይ እየተስፋፋ መጥቶ ኢትዮጵያን ሊያዳርስ ነው።በአዲስ አበባ በውስን አካባቢዎች የጀመረው አራተኛው ትውልድ የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ የተሰኘውን አገልግሎት እየተስፋፋ መጥቶ ዛሬ ላይ በ47 ከተሞች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። ይህ ቴክኖሎጂ አገልግሎት እስካሁን ከነበሩት ሁሉ ላቅ የሚልና በሁለቱ የትውልድ እርከኖች የተስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታ ነው።
ለአብነት ያህል በ3ጂ ሞባይል ኔትወርክ የዳታ ለውውጥ በሰከንድ ከአምስት እሰከ ሰባት ሜጋ ባይት አንድን ዳታ ለመጫን የሚያስችል ሲሆን፤ ዳታውን ለማውረድ ደግሞ ከ21 እስከ 42 ሰከንድ ይወስዳል። በአንጻሩ በ4ጂ ኤልቲኢ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ፍጥነቱ በብዙ እጥፎች ተሻሽሎ በሰከንድ ወደ 150 ሜጋ ባይት ከፍ ብሏል። ሂደቱ ወደ 4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ ሲያድግም ከ300 እስከ 600 ሜጋ ባይት በሰከንድ ፍጥነት ይኖረዋል። ይህ የዘመናችን ቴክኖሎጂ ዳታን የመጫንና ማውረድ ፍጥነትን በአማካይ ሲሰላ ስልሳ በመቶ ያሳድገዋል።
በ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ የሞባይል ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ጥራት የቪዲዮ ኮንፍረንሶችን ለማካሄድ ያግዛል። አገልግሎቱ በከፍተኛ ፍጥነትና ባንድዊድዝ የዳታ እና ኢንተርኔት አገልግሎትን ለመጠቀም ያስችላል። በቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ ታግዘው የሚከናወኑ ማናቸውም ተግባራትን በአስተማማኝ ሁኔታም የማቀላጠፍ አቅም አለው። ይህ በመሆኑም የደንበኞችን ምርታማነት ለማሳደግ የሚኖረውን ድርሻ የላቀ ያደርገዋል። በርቀት ሆኖ ስራዎችን ለማቀላጠፍ ይረዳል። በቀላሉ መረጃዎችን ለማግኘትና ለመለዋወጥ ያለው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው።
4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን የ4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ አገልግሎት መስፋፋቱም በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አውድ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው።የ4ጂ አድቫንስድ አገልግሎት ያለ ተጨማሪ ወጪ አሁን አገልግሎት እየሰጠ ካለው የ3ጂ አገልግሎት ቢያንስ በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ጥራት እና አስተማማኝነት ያለው የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት የሚያስችልና የጥራት ደረጃውም ከ3ጂ በ14 እጥፍ ከፍ ያለ መሆኑንም የኢትዮ ቴሌኮም መረጃዎች ያሳያሉ።
ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በብቃት ለመጠቀምና ኢኮኖሚውንና የሰዎችን መስተጋብር ለማሳለጥ በእጅጉ ያግዛል።የቴክኖሎጂ ለውጥ ለማህበራዊ እድገት፣ ምርታማነት ለማሻሻልና ሁሉን አቀፍ እድገት ለማምጣት ወሳኝ ሚና እንዳለው እሙን ነው። በየጊዜው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶች ለውጥ እውን በሚሆኑ ጊዜ በጥራት፣በፍጥነትና በጊዜ አጠቃቀም ከፍተኛ ልዩነት ያመጣሉ።።
ይህ ለውጥ በተለያየ የእድገት ደረጃ ላሉ ሀገራት የተለያየ ዓይነት ምቹ አጋጣሚን ይፈጥርላቸዋል።በተለይ በኢትዮጵያ 4ጂ ኤልቲኢ አድቫንስድ አገልግሎት እየተስፋፋ መምጣቱ በመንግስትና በግል ተቋማት የሚሰጡ ጅምር የዲጂታል አገልግሎቶችን በማስፋፋት ኢኮኖሚውን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ከ55 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉትና ከእነዚህ መሀከል ከ25 ሚሊዮን የሚልቁት የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ያመለክታል።
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2013