ፀጉር በማንኛውም የሰውነታችን ቆዳ ላይ ከእጃችን መዳፍ እና ከእግራችን ሶል ውጪ ይበቅላል ነገር ግን አብዛኛዎቹ ፀጉሮች ስስ ስለሆኑ በአይናችን ላናያቸው እንችላለን። ፀጉር ኬራቲን ከሚባለው ፕሮቲን በውጨኛው የቆዳ ክፍል የፀጉር ፎሊክል ውስጥ ይሰራል። ፎሊክላችን አዲስ የፀጉር ሴል ሲሰራ/ሲያመርት አሮጌ ሴሎቻችን በአመት 6 ኢንች ወደ ውጪ ቆዳችን ተገፍተው ይወጣሉ የምናየው ፀጉር የሞተ ክር መሳይ ኬራቲን ሴል ነው።
በአማካይ የአንድ አዋቂ ሰው ጭንቅላት ከ 100 ሺህ እስከ 150 ሺህ የሚደርስ ፀጉር ሲይዝ በቀን 100 ፍሬ ፀጉር በራሳቸው ጊዜ ይነቀላሉ። እንደሚታወቀው አብዛኛው ጊዜ በማበጠሪያ ውስጥ ትንሽ የተነቀሉ ፀጉር ማግኘት የተለመደ እና ሊያስደነግጠን የማይገባ ጤናማ ሁኔታ ነው። ፀጉር አምራች የሆኑት እያንዳንዳቸው ፎሊክሎች የራሳቸው የሆነ የእድሜ ገደብ ሲኖራቸው በእድሜ፣ በበሽታ እና በተለያዩ በርካታ ምክንያቶች ተጽዕኖ ይወሰናሉ። ይህ አውደ ህይወት በሶስት የለውጥ ደረጃ ይከፈላሉ።
ሦስቱ ደረጃዎች
1.አናጅን ፦ ፀጉር በፍጥነት የሚያድግበት ጊዜ ሲሆን ከ2-6 ዓመት ያበቃል
2.ካታጂን፦ ይህ የፀጉር እድገት ጊዜ የሽግግር ደረጃ ሲሆን ከ2-3 ሳምንት ይፈጃል
3.ቴሎጂን፦ የእድገት ጊዜ የሚያርፍበት/የሚቆምበት ሲሆን ከ2-3 ወር ይፈጃል። በዚህ የለውጥ ደረጃ መጨረሻ ላይ ፀጉራችን ይረግፍና የዕድገት ሂደቱን እንደገና ከመጀመሪያ ይጀምራል። እድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ የፀጉር እድገት ፍጥነቱን ይቀንሳል።
የራስ በራነትን የሚያመጡ የችግር ዓይነቶች
አንድሮጀኒክ አሎፔሺያ፦ ወንድና ሴትን የሚያጠቃ በዘር ህዋስ ምክንያት የሚከሰት ነው። ወንዶች በወጣትነታቸው ወይም በሃያዎቹ መጀመሪያ ፀጉራቸው ያሳሳል። በመሃልና በፊት ጭንቅላታቸው ላይ ያሉ ፀጉሮች ቀስ በቀስ ያሳሳሉ። ሴቶች እድሜያቸው 40 እስከሚሆን የፀጉር መሳሳት አይታይባቸውም። ሴቶች አጠቃላይ በጭንቅላታቸው ላይ ያለ ፀጉር ይሳሳል በተለይ መሀል አካባቢ።
አሎፔሺያ አርያታ፦ በድንገት የሚጀምር ሲሆን በመጠንም ሆነ በአይነት ያልተስተካከለ ፀጉርን ማጣት በህፃናት እና ወጣቶች ላይ ያጋጥማል። ሙሉ ለሙሉ የፀጉር መመለጥ ሊያጋጥም ይችላል። በዚህ ሁኔታ ከተጠቁት 90 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች በጥቂት አመታት ውስጥ ፀጉራቸው ተመልሶ ይበቅላል።
አሎፔሺያ ዩኒቨርሳሊስ፦ሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች ፀጉር ቅንድብ፣ የአይን ሽፋሽፍትና የሀፍረተ ስጋ አካባቢ ፀጉሮች ሙሉ ለሙሉ ይረግፋሉ።
ስካሪንግ አሎፔሺያ፦ በቋሚነት የፀጉር መርገፍ ሲሆን በተለያዩ የቆዳ ችግሮች ይከሰታል።
መነሻ ምክንያቶች
የተለያዩ ብዙ ምክንያቶች ፀጉራችን እንዲረግፍ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ከነዚህም መካከል፡-
– ሆርሞን
– የተዛባ የአንድሮጂን ሆርሞን መጠን (የወንድ ሆርሞን ሲሆን በወንድና ሴቶች ይመረታል)
– ጂን (ዘረ መል)
– ከሁለቱም ወንድ እና ሴት ወላጆች ለወንድ ወይም ሴት ልጅ መመለጥ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
– ጭንቀት፣ ህመም እና ወሊድ ጊዜያዊ የሆነ የፀጉር መርገፍ ያስከትላል። የሆድ ትላትሎችና የፈንገስ ኢንፊክሽን ተጠቃሽ ናቸው።
የችግሩ መንስኤዎች
መድሃኒቶች፦ ለካንሰር ህክምና የሚውለው ኬሞቴራፒ፣ የደም መቅጠን፣ ለደም ግፊት የሚውሉ መድሃኒቶች፣ አንዳንድ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ጊዜያዊ የሆነ የፀጉር መርገፍ ሊዳርጉን ያችላሉ።
ቃጠሎ፦ አደጋና ራጅ ጠባሳ እስካልተከሰተ ድረስ አደጋው በሚድንበት ጊዜ መደበኛ ፀጉራችን መብቀል ይጀምራል።
የኮስሞቲክስ ውጤቶች፦ በብዛት ሻምፖ፣ ፐርም እና የተለያዩ ንጽህና መጠበቂያዎች ፀጉር በቀላሉ እንዲሰበር በማድረግ ለፀጉር መሳሳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ነገር ግን ለራሰ በራነት ላይዳርጉን ይችላሉ።
የጤና ችግሮች፦ የታይሮይድ በሽታ፣ የስኳር በሽታ፣ የብረት እጥረት፣ የአመጋገብ ችግርና የደም ማነስ የፀጉር መመለጥ እንዲከሰት ያደርጋሉ።
ምግብ፦የፕሮቲን መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምግቦችና የካሎሪ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምግቦች የፀጉር መመለጥ እንዲከሰት ያደርጋሉ።
የራሰ በራነት ህክምና
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት መድሃኒቶች በህክምና የተረጋገጡ በተሳካ ሁኔታ የራሰ በራነትን ይከላከላሉ ተብሎ ይታመንባቸዋል።
ሚኖክሲዲል(ሮጌይን)
ያለ ምንም መድሃኒት ማዘዣ ልንገዛው የምንችል መድሃኒት ሲሆን ሴቶችም ሆነ ወንዶች ሊጠቀሙበት ይችላሉ። በተለይ በመሃል አናት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ይሰራል። በፊት ለፊት የፀጉራችን ክፍል ላይ የመስራት እድላቸው ዝቅተኛ ነው። በ2%፣ 4% የተዘጋጀ ሲሆን በከባድ መጠን 5% ተዘጋጅተዋል።
ይህ መድሃኒት ትንሽ አዲስ ፀጉር ሊያበቅል ይችላል ዋናው ጥቅሙ ግን ፀጉራችን ባለበት ቦታ ላይ እንዲቆም(እንዳይመለጥ) ይረዳል። የዚህ መድሃኒት ችግር በቀን አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ስለምንጠቀመው ሊያሰለቸን ይችላል። በአንገት ወይም ፊት ላይ መድሃኒቱ የሚነካን ከሆነ ያልተፈለገ ፀጉር ሊበቅልብን ይችላል።
ፊናስቲራይድ
በአሜሪካ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የተረጋገጠ ሲሆን ለወንዶች ጥቅም ብቻ ይውላል። ተፈጥሮአዊ የጭንቅላት ፀጉር ፎሊክሎችን ሆርሞን በመዝጋት ፀጉር እንዳይበቅል ያደርጋል። ፕሮፔሺያ/ በዝቅተኛ መጠን የተዘጋጀ ፕሮስካር/ የተባለ መድሃኒት ዝርያ ነው። ይህ መድሃኒት ትልቅ ፕሮስቴቶችን በማጨማደድ በመካከለኛ እና ትልቅ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ወንዶች ይጠቅማል። ፕሮፔሺያ በ1 ሚ.ግ. የተዘጋጀ በመድሃኒት ማዘዣ በየቀኑ የሚወሰድ መድሃኒት ነው። ሙሉ ለሙሉ ፀጉራችንን ለመመለስ ከ6-12 ወራት መውሰድ ይኖርበታል።
ፕሮስታግላንዲን አናሎግ
እነዚህ መድሃኒቶች ፀጉር እንዲያድግ የሚያደርግ ሲሆን ገና በጥናት ላይ ይገኛል። ከነዚህ መካከል ቢማቶፕሮስት/ ለቅንድብና ለአይን ሽፋን ፀጉር የሚስተካከለው የለም።
ምንጭ፦ ከጠቃሚ የህክምና ምክሮች ማህበራዊ ገጽ
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2013