የበርካታ ወንዞች መገኛና የለም መሬት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በሀብቷ በሚገባት መጠን ሳትጠቀምበት ኖራለች።ሰፊ መሬትን የሚሰራ ጉልበትን ታቅፋም ለዓመታት በተረጅነት ቀጥላለች። ይሁን እንጂ አሁን በፀጋዎቿ ለመጠቀም አይኗን ከፍታ ጉልበቷን አጠናክራ እንቅስቃሴ ጀምራለች። ሰርታ ልትለወጥ የተረጂነት ታሪኳን ታሪክ ልታደርግ ተነስታለች።
በተለይም ካለፉት ሶስት የለውጥ ዓመታት ጀምሮ በግብርናው ዘርፍ ዜጎችን በምግብ ራስን የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከሥራዎቹ አንዱ አሁን እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የምግብ አቅርቦትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው። ለዚህም መንግስት በግብርናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ዘላቂ ልማት ውስጥ መግባት የምትችልበትና አርሶ አደሩ የምርቱ ተጠቃሚነትን የሚረጋገጥበት የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ነድፎ ወደ ተግባር ስራዎች መግባት ጀምሯል።
በ10 ዓመቱ የግብርና መሪ ዕቅድ ላይ ከተጠቀሱት አንዱ በሰብል ልማት ዘርፍ ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ነው ። የክረምቱ ዝናብ ብቻ ሳይጠበቅ በበጋ ወቅት ባሉት ሰፋፊ መሬቶች ላይ በመስኖ ስንዴን በማልማትና ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት በምግብ ራስን ለመቻል ጥረት ወደ ማድረግ ተግባርም በይፋ ተገብቷል።
ይሄ ስራ ለረጅም ዓመት የዘለቀውን የሀገሪቱን የተረጅነት ታሪክ ከመቀየር ባሻገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት። አርሶ አደሩ እጁን አጣጥፎ የክረምት ዝናብ ከመጠበቅ ተላቅቆ በበጋ ወቅት በመስኖ ስንዴን ወደ ማልማት እንዲገባ ያስችላል። ሀገራችን ከውጪ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የምታስገባውን ስንዴም ያስቀራል። አሁን ላይ ይሄንኑ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ ስንዴ በግማሽ የማስቀረት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚናገሩት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ዳንኤል ሙለታ ናቸው።
በጋን ተንተርሶ ብቅ ያለው የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት መነሻው በመካከለኛው አዋሽ በተለይም አፋር አካባቢ ነው። ተግባሩ አሀዱ የተባለውም የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አካል በሆነው በወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ነው። የቆላ ስንዴ በመባል በዚሁ ማዕከል በአንድ ሄክታር ላይ የተሞከረበት ሁኔታ መኖሩን አስተባባሪው ያስታውሳሉ። ሙከራው በ2011 ዓ.ም በሶስት ሺህ 500 ሄክታር ተጀመረ።በ2012 ዓ.ም ደግሞ ወደ 20 ሺህ ሄክታር ከፍ እንዲል ተደረገ። በዚህ ምርት ዘመን ሂደቱ ከፍ እንዲል የተደረገባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አፋር ሸበሌ ተፋሰስ፣ በሶማሌ ጎዴ አካባቢና ደቡብ ኦሞ ናቸው ።
እንዲሁም ልማቱ የላይኛው አዋሽ ተፋሰስን ይዞ እንደመከናወኑ እስኪ ደግሞ ከፍ ብሎ እስከ ወይና ደጋ አካባቢ ይውጣ በሚል እሳቤ በኦሮሚያ ክልል ከቱሉ ቦሎ እስከ ጊንጪ አካባቢ እንዲሰፋ የተደረገበትም ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ‹‹ፕሮጀክቱ ሲጀመር የቆላ ስንዴ ነበር የሚባለው›› የሚሉት አስተባባሪው አሁን ላይ በቆላማ ብቻ ሳይሆን በወይና ደጋ እና በደጋማ አካባቢ መመረት መቻሉ መረጋገጡን ያስረዳሉ። ከዚሁ ጋርም ተያይዞ የቆላ ስንዴ የሚለው ስያሜ የመስኖ ስንዴ በሚል ለመቀየር መብቃቱን ነው የጠቀሱት።
ምርቱ የተጀመረው በአንድ ሄክታር ቢሆንም ከዓመት ዓመት እየተስፋፋ በ2013 ዓ.ም በ300 ሺህ ሄክታር ላይ ለመስራት የታቀደበትና ለመከናወን የበቃበት ደረጃ ላይ መድረሱንም ይናገራሉ።
ዶክተር ዳንኤል እንዳሉት፤ከዚህ ውስጥ 172 ሺህ 515 ሄክታሩ በኦሮሚያ ክልል አካባቢ የተሰራ ነው።13 ሺህ 200 ሄክታር አካባቢ የሚጠጋው ደግሞ በአማራ ክልል ነው የለማው።በአፋር ክልል 1 ሺህ 230 ሄክታር የተሰራበት ሁኔታ አለ። በጎዴ አካባቢ ደግሞ በሰርቶ ማሳያነት 500 ሄክታር ለመስራት ተችሏል።እንደ አጠቃላይ በዘንድሮ በጀት ዓመት በመስኖ ብቻ ከ187 ሺህ ሄክታር በላይ ማሣን በመስኖ ስንዴ መሸፈን ተችሏል።ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል ከበጋ ወደ በልግ ተሸጋግሮ በ209 ሺህ 530 ሄክታር ላይ ተጨማሪ የመስኖ ስንዴ የለማበት ሁኔታ መኖሩንም አስተባባሪው ነግረውናል።
በዚህም በአጠቃላይ በበልግ የለማው ስንዴ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በበጋ ከለማው መስኖ ስንዴ ጋር ተዳምሮ ከ2013 የስንዴ መስኖ ልማት 300 ሺህ ሄክታር ዕቅድ በላይ ክንውን እንዲመዘገብ በማስቻል ዕቅዱን ለማሳካት አግዟል። ይሄ ከሰባት ሚሊዮን ኩንታል ጋር ሲደመር በበጀት ዓመቱ የተገኘውን የስንዴ ምርት ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ያደርሰዋል። መጠኑ በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን በየዓመቱ ከውጪ የሚገባውን 17 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ሊተካ የተቃረበ በመሆኑ እጅግ ይበረታታል። በአጠቃላይ ዘንድሮ የመስኖ በጋ ስንዴ ሥራ ከበልጉ ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡ ያስደስታል።
ሥራው በሀገር ደረጃ የራሱ መርሐ ግብር ወጥቶለት ለብቻው ቢከናወንም በተለይ ደግሞ እያንዳንዱ ክልል የራሱ አድርጎ በእኔነት ስሜት ቢይዘውና ቢያከናውነው ከዚህ የበለጠ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት እንደሚያስችል ነው የተናገሩት ። ክልሎች የመስኖ ስንዴ አምርቼ ከውጪ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ እተካለሁ ብለው እንደ አንድ ዕቅድ ቢይዙት መልካም መሆኑንም ያስረዳሉ። በዘንድሮ ምርት ዘመን እንደ ሀገር በዘርፉ ከተሰራው 90 በመቶውን የሰራው ኦሮሚያ ክልል ጥሩ አርአያ መሆን መቻሉንም ይጠቅሳሉ። ቁርጠኝነት ካለ በእርግጠኝነት በዚህ መልኩ ሰርቶ ከውጪ የሚመጣውን ስንዴ ማስቀረት ይቻላል የሚል እምነት አላቸው። ሆኖም ሰፋ ያለ በጀት የሚጠይቅ መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበትም ይናገራሉ።
መንግስት በዚህ መልኩ ከውጭ የሚመጣውን ስንዴ በሀገር ውስጥ አመርታለሁ፣ የውጪ ምንዛሪውን እቆጥብና ለሀገር ውስጥ ልማት ግንባታ አውላለሁ የሚል ከሆነ አሁን ላይ በስፋት እየተሰራበት የሚገኘውን የስንዴ ፕሮጀክት በሀገር ደረጃ ራሱን ችሎ የሚካሄድ መርሐ ግብር አድርጎ ማዋቀር እንደሚጠበቅበትም ያመለክታሉ።
እንደ አስተባባሪው ማብራሪያ ፣ኢንስቲትዩቱ በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ሀሳብ ያቀረበበት ሁኔታ አለ። ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓመት በአማካኝ 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ ታስገባለች። ዘንድሮ በመስኖ የተመረተው ስንዴ ደግሞ ወደ 15 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ በመሆኑ አሁንም ባይሆን ወደ ፊት ከውጪ የሚመጣውን ስንዴ በመተካቱ በኩል ተስፋ የሚጣልበት ነው። መንግስት ይሄን ያመረተውን ስንዴ ኪሎውን በ30 ብር እንኳን ቢሸጠው 21 ቢሊዮን ብር ሊያፈስበት እንደሚችልም ይገመታል።
በእርግጥ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ሙሉ በሙሉ ገበያ ላይ የሚቀርብ ከመሆኑ አንፃር አትራፊነቱ ዕሙን ነው። ሆኖም ይሄ ከውጪ የመጣ ስንዴ ለገበያ የሚቀርበው በሚያተርፍ መልኩ አይደለም። ሲጀመር ዓላማውም ዜጎችን በምግብ ራስን በማስቻል ሀገሪቱን ከተረጅነት ማውጣትና ለስንዴ የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ አድኖ ለሌሎች ጉዳዮች ማዋል እንጂ ትርፍ አይደለምና ነው።በመሆኑም ለገበያ የሚቀርበውም የዜጎችን የመግዛት አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው።
የውጪውን ተክቶ ሀገር ውስጥ የተመረተውን መንግስት ለገበያ ቢያቀርበው ሀገርን አትራፊ ያደርጋል።አሁን ላይ ሀገር ውስጥ ኩንታል ስንዴ እየተሸጠበት ካለው አራት ሺህ ብር እጅግ ባነሰ ዋጋ የተሰላውንም የ21 ቢሊዮኑንም ሲሳይ ለማዳን ይበቃል። ነገር ግን አሁን ሀገራችን ባለችበት በተለይም ዜጎች በኑሮ ውድነት ደቅቀው አቅም ባጡበት የኢኮኖሚ ሁኔታ መንግስት ደፍሮ ይሄን ስንዴ መሸጥ ቢፈልግ እንኳን ሀገር ውስጥ የሚመረተው ስንዴ በብዙ ሁኔታዎች የሚያልፍ በመሆኑ ለገበያ ለመቅረብም ብቃት አይኖረውም። ምክንያቱ ደግሞ አስተባባሪው እንደሚሉት በሀገር ውስጥ የሚመረተው ስንዴ ለአርሶ አደሩ ለዘር፣ ለቀለብ ፍጆታ፣ ለማዳበሪያና ለተለያዩ ክፍያዎች ወጪ ጭምር የሚውል በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ለገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ የለም። በመሆኑም ሙሉ ለሙሉ ለገበያ ለማቅረብ ዘንድሮ ከተመረተው በላይ መጠን ያለው ምን አልባትም እጥፍና ከእጥፍ በላይ የመስኖ ስንዴ በበጋና በበልግ ተጠቅሞ በቆላ ፣ በወይናደጋና በደጋ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሰፊው ማምረት ይጠይቃል።
በእርግጥ ክንውን ከወጪ አንፃር የሚጠይቀው ቀላል በጀት አይደለም።ለአብነት በዘንድሮ 2013 ምርት ዘመን በመንግስት ፕሮጀክት የለማው ስንዴ ሥራው የተካሄደው መንግስት በመደበው 418 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ነው ።ሆኖም ሥራው በዚህ በጀት ብቻ ሊሰራ ባለመቻሉ መንግስታዊ ካልሆኑ የተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች በተሰባሰበ ዳጎስ ያለ ገንዘብም የተደገፈ ነው።በተለይ ለተሳታፊ አርሶ አደሮች የቀረበው የስንዴ ዘር የተሸፈነው ከለጋሽ ድርጅቶች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።ከዚህ አኳያ ከውጪ የሚመጣውን ስንዴ በሀገር ውስጥ የመተካቱን ራዕይ ሊያሳኩት የሚችሉት የግል ባለሀብቶች ጭምር መሆናቸው አያጠራጥርም
ከዚህ አንፃር በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ኢንስቲትዩቱ የአስተራረስና የዘር አመራረት ዘዴ ቴክኖሎጂን ጨምሮ ሙያዊ ምክርና እገዛ በማድረግ እያበረታታ እንደሚገኝም አስተባባሪው ይናገራሉ።ኩንታል ስንዴ አራት ሺህ ብር ከመሆኑ አንፃር በርካታ ባለሀብቶች ገብተው ቢሳተፉበት የሚያዋጣቸው ከመሆኑ ባሻገር ሀገርንና ወገንን ከተረጅነት በማላቀቅ በተጨማሪም ስንዴ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ በማዳን የየራሳቸውን ሚና መወጣት የሚያስችልም መሆኑን ዶክተር ዳንኤል ያሳስባሉ። በዘንድሮ ምርት ዘመን ፕሮጀክቱ አንዳንድ ተግዳሮቶች ባይገጥሙት የበለጠ ባለሀብቱ በስፋት እንዲገባና እንዲሳተፍበት የሚጋብዝ አመርቂ ውጤት ያስመዘግብ እንደነበረም በቁጭት ይናገራሉ።
ለቁጭታቸው ምክንያት ያደረጉት አንዱ ተግዳሮት በበጋ የለማው የመስኖ ስንዴ ዕቅዱ 300 ሺህ ቢሆንም አፈፃፀሙ 187 ሺህ ሄክታር አካበቢ ብቻ ነው።እንዴት ቢባል የመስኖ ስንዴ ለማልማት ትልቅ አቅም ያለው የአፋር ክልል ነበር።ይሁንና በጋ ላይ የመስኖ ስንዴ ልማት በሚጀመርበት ጊዜ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ከፍተኛ መጥለቅለቅ አጋጠመ።ጎርፉ ሥራው እንዳይሰራ እንቅፋት በመሆኑ በአፋር ክልል ለመሥራት ከታቀደው ከ50 ሺህ ሄክታር በታች 1 ሺህ 230 ሄክታር የመስኖ ስንዴ ብቻ ማልማት ግድ ሆነ።
ሌላኛው ተግዳሮት ደግሞ በሶማሌ ክልል የመስኖ መሰረተ ልማቱ ባለመጠገኑ የታሰበው መሳካት ያልቻለበት ሁኔታ አለ ።ሦስተኛው የ2013 ምርት ዘመን የመስኖ ስንዴ ፕሮጀክት ተግዳሮት የሚሉት በደቡብ ኦሞ የበጋ ወቅት የመስኖ ስንዴ ልማቱ ከኮቪድና ከፍተኛ የአንበጣ ወረርሽኝ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ ዝግጁነቱ እጅግ አናሳ በመሆኑና ክልሎች ሥራውን የራሳቸው አድርገው ባለመያዛቸው ነበር። በበጋ የለማው ስንዴ በነዚህ ተግዳሮቶች ምክንያት ዕቅዱን ማሳካት ባይችልም፤ችግሮቹን ተቋቁሞ ከ187 ሺህ ሄክታር በላይ የመስኖ ስንዴ ማልማት መቻል ትልቅ ስኬት ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ።በእዚህ ላይ 187 ሺህ ሄክታር በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከበጋ ወደ በልግ ዞሮ በ209 ሺህ 530 ሄክታር ላይ ከለማው የመስኖ ስንዴ ጋር ሲዳመር በአጠቃላይ በ2013 ዓ.ም በበጋና በልግ የለማው ማሳ ከዕቅድ በላይ ስኬት ማስመዝገብ ችሏል። ይሄ አበረታችና ይበል የሚያስብ በመሆኑ ሊቀጥል ይገባል እያልን ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2013