ዲያስፖራው ለኢትዮጵያ አገሩ የሚያደርገው አስተዋጽኦ በጉዳዮች የሚወሰን አይደለም። በአገር ቤት ለሚገኙ ቤተሰቦቹ ገንዘብ ከመላክ ጀምሮ የአገሪቱን መልካም ገጽታ ከመገንባት፣ በአገር ቤት ኢንቨስትመት ከማድረግ አንስቶ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን፣ ዲሞክራሲ እንዲጎለብትና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ሁለንተናዊ ጥረት ያደርጋል። ሌላው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ዘግናኝ ጥቃት ከማውገዝ ባሻገር የቡድኑ ርዝራዦች በውጭ አገራት የኢትዮጵያን ስም ጥላሸት ለመቀባት ሲሯሯጡ ጭምር የውሸት መረጃቸውን በማክሸፍና በመሞገት ረገድም ጉልህ ተሳትፎ አድርጓል።
በተለይ ሽብርተኛው ቡድን ሆን ብሎ የትግራይ ህዝብ ዕርዳታ እንዳያገኝና እንዲራብ በማድረግ ረሃብን ለቅስቀሳ ሲጠቀምበትና በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ በተከፋይ ሎቢስቶችና የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ሲወተውት ዲያስፖራው ይህንን የሀሰት መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመረጃ በማስረዳት ሞግቷል። የውጭ አገራት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ በመግባት የሚፈጥሩትን ጫና በመቃወም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ኢትዮጵያውያን በሉዓላዊነታችን አንደራደርም፣ የውስጥ ጉዳያችን ራሳችን እንፈታዋለን፤ በሀሰት መረጃዎች ኢትዮጵያ ላይ ጫና አትፍጠሩ፣እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ የሚሉ መልዕክቶችን በማስተላፍ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምዱት አቋም የተሳሳተ መሆኑን አደባባይ በመውጣት ሰልፍ በማድረግ ጭምር ገልጸዋል።
እንዲሁም ቴሌግራም፣ኒውስ ዊክ፣ አልጀዚራ፣ አሶሼትድ ፕሬስና ሌሎች የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት ከሚያሰራጩት ሚዛናዊነት የጎደለውና የሀሰት ዘገባዎች እንዲቆጠቡም ጭምር የሚያሳስቡ ተቃውሞዎች ተካሄደዋል። ዲያስፖራው አገሩን በሚመለከት የሚፈጠሩ ውጫዊ ጫናዎችን መቃወም ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም እውነታውን ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በቅርቡም መንግስት ሽብርተኛው ቡድን ለሚፈጽመው ወንጀልና የዕርዳታ ማስተጓጎል ተግባር ሰበብ ላለመሆን፣የትግራይ አርሶ አደር ያለ ስጋት እርሻውን እንዲያካሄድ፣ ህዝቡ የመንግስትን ሁለንተናዊ ጥረት በጥሞና እንዲገነዘበውና ኢትዮጵያ ውጫዊ የደህነት ስጋት ስላለባት መንግስት በቅርቡ በትግራይ ክልል በተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አስተላልፏል። በዚህ መሰረትም የአገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ መውጣቱንም ይፋ አድርጓል።
ይህ የተናጠል ተኩስ አቁምም ወታደራዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን መንግስት ገልጿል ሰሞኑንም በዚህ ጉዳይ ላይ ለዲያስፖራው ግንዛቤ ለማስረጽ ተሞክሯል ። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እንድሪስ እንደገለጹት፤ ኤጀንሲው ዲያስፖራው በአገሩ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ መረጃ እንዲኖረው የማስገንዘብ ስራ ሰርቷል። በተለይ መንግስት በቅርቡ በትግራይ ክልል የወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ኢትዮጵያን እንደ አገር የሚጠቅም፣ ውጫዊ ጫናን የሚቀንስና ለሰብዓዊ ዕርዳታ ትኩረት የሰጠ ነው ብለዋል።
የተናጠል የተኩስ አቁሙ ውሳኔ ይፋ ሲደረግ እንኳን በዲያስፖራው በአገር ቤትም በህዝቡ ዘንድ የፈጠራቸው ብዥታዎች መኖራቸውን አውስተው፤በአገር ውስጥ በተሰጡ መግለጫዎችና ማብራሪያዎች እንዲሁም በኤጀንሲው በኩል በተካሄዱ በቴክኖሎጂ የታገዙ በርካታ ውይይቶች ከዲያስፖራው ጋር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል። ዲያስፖራው በየትኛውም ጉዳይ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር፣ ብርታቷን ለመጨመርና ጉዳት ለመቀነስ በቋሚነት መስራት እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
የዲያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ተወካዮች መንግሥት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በበቂ ምክንያቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን የተብራራላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት መንግሥት ከወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ጋር በተያያዘ ለውሳኔው መነሻ የሆኑ ምክንያቶች ጠቅሰዋል።
ከእነዚህ ምክንያቶች መካከልም የሰብዓዊ ዕርዳታ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣አርሶ አደሩ ያለስጋት የእርሻ ስራው እንዲያከናውን፤ ሌላ ውጫዊ የደህንነት ስጋት መኖሩና ሽብርተኛ ቡድን አቅሙ ስለመከነ የአገር ስጋት አለመሆኑ የሚሏቸው እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
ዲያስፖራው ከውሳኔው ጋር በተያያዘ ያሉትን ጥያቄዎችና አስተያየቶች እንዲሁም ቀጣይ የዲያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አካሄድን በተመለከተ ሐሳቡን እንዲያጋራም ጠይቀዋል። የዲያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ተወካዮች የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ በበቂ ምክንያቶች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መረዳታቸውን ገልጸዋል።
በዲያስፖራው ዘንድ የሚከናወነው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን መረጃዎች ወቅታዊነታቸውን ጠብቀውና ተናበው እንዲቀርቡ፣ የዲያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት የሚያከናውኑትን ሥራ የሚደግፍና በባለሙያዎች የሚመራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንዲከናወን፣ በሀገር ውስጥ በመንግሥት የሚከናወኑ ተግባራትን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደራሽ ለማድረግና አመለካከትን ለመለወጥ ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አስተባባሪዎች በዕውቀታቸውም ሆነ በገንዘባቸው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራውን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አመላክተዋል። በየአካባቢያቸው በሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን በመቅረብ የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታ ለማስረዳት የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ባስተላለፉት መልዕክት መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር መሆኑን አስረድተዋል። መንግሥት የመረጃ ፍሰት ክፍተት እንዳለበት እንደሚረዳና ይህንንም ለማስተካከል አሠራሮችን ማበጀቱን ገልጸዋል። ዲያስፖራውም በአዲሱ አሠራር የሚመነጩ ወቅታዊ መረጃዎችን ከሚሲዮኖችና ከሚመለከታቸው ክፍሎች በማግኘት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያስረዳል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በኢንቨስትመንት በመሰማራት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የአገራቸውን የቱሪዝም መስህቦች እና ምርቶች ለዓለም በማስተዋወቅና የአገራቸውን ገጽታ ለመገንባት ጉልህ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው።እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዕውቀት፣ የሙያ እና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለኢትዮጵያ በማስተላፍ ረገድም የማይናቅ ሚና አላቸው። ለዚህም ነው መንግስት አልፎ አልፎ መዘናጋቶች ቢታዩም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዲያስፖራው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያደርገው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ግንባር ቀደሙን ሚና እየተወጣ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2013