
ሃዋሳ፡- ኢትዮ ቴሌኮም በደቡብ ሪጅን በ12 ከተሞች የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ አገልግሎትን ማስጀመሩን አስታወቀ። በተቋም ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርን በሀዋሳ ከተማ አስጀመረ።
ኩባንያው አገልግሎቱን ትናንት በሀዋሳ ከተማ ሲያስጀምር የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እንደገለጹት፤ ኩባንያው ከፍተኛ የአገልግሎት ማሻሻያ እያደረገ ነው።
ኩባንያው በደቡብ ሪጅን ያስጀመረው የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ አገልግሎት 12 ከተሞችን የሚሸፍን መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሪት ፍሬህይወት፣ በአገልግሎቱ 952 ሺ 225 ደንበኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት ሀዋሳ ፣ ሻሸመኔ ፣ አርሲ ነገሌ ፣ ቡሌ ሆራ ፣ዲላ ፣ ያቤሎ ፣ይርጋለም ፣ አለታወንዶ ፣ ሞያሌ ፣ ሻኪሶ ፣አዶላ እና ነገሌ ከተሞች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የአገልግሎት ማሻሻያው አላማ የደንበኞችን እርካታ ከፍ ለማድረግ እንደሆነ የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ 4ጂ አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአገልግሎት ማስፋፊያውም በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አውድ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ለውጥ እንደሚያስከትል የጠቆሙት ወይዘሪት ፍሬህይወት፣ የ4ጂ አድቫንስድ አገልግሎት ያለ ተጨማሪ ወጪ አሁን አገልግሎት እየሰጠ ካለው የ3ጂ አገልግሎት ቢያንስ በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ጥራት እና አስተማማኝነት ያለው የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል።
ስራ አስፈጻሚዋ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ ያስጀመረው የቴሌ ብር አገልግሎትም ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ስድስት ሚሊዮን ደንበኞች ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ፤ በአንድ አመት ውስጥ የቴሌ ብር ተጠቃሚዎችን ቁጥር 21 ሚሊዮን ለማድረስ እና ከ69 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ በዚሁ ስርአት ለማንቀሳቀስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ከ55 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉትና ከእነዚህ መካከል ከ25 ሚሊየን የሚበልጡት የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ስራ አስፈጻሚዋ በእለቱ በተቋም ደረጃ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በሀዋሳ ከተማ አስጀምረዋል። ለሶስተኛ ጊዜ በተቋም ደረጃ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር እስከ ሀምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በስድስት የኢትዮ ቴሌኮም ዞኖች እና በ17 ሪጅኖች አንድ ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን አስታውቀዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ሁለት አመታት ከሁለት ሚሊየን በላይ ችግኝ መትከሉን ያስታወቁት ወይዘሪት ፍሬህይወት፣ ለዚህም ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አመልክተዋል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም