
የዶክተር አበበች ጎበና የቀብር ሥነሥርዓት ተፈጸመአዲስ አበባ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ዶክተር አበበች ጎበና የጀመሯቸውን በጎ ስራዎች እንደሚያስቀጥል አስታውቀዋል። ለወገን ደራሽነታቸው በቃልም በተግባርም የታየ መሆኑን አመለከቱ።
ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና (እዳዬ) የቀብር ስነስርአት ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ፣ እኚህ ታላቅ እናት ለአርባ አንድ አመታት ሲያከናውኑ የኖሩትን በጎ ተግባር የከተማ አስተዳደሩ ያስቀጥላል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማዕከሉ የተሟላ አገልግሎቱን እንዲቀጥል እና የዶ/ር አበበች ጎበና ታላቅ ስራ እንዳይደበዝዝ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ላለፉት አራት አስርት ዓመታት ላከናወኑት የበጎነት ስራ ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ከንቲባዋ፤ ̋እናታችን ስላደረጉልን በጎነት ባለ እዳዎች ነን፤ ወሮታም አለብን። በመሆኑም ይህ የሚሊዮኖችን ህይወት ያለመለመ የበጎ አድራጎት ማዕከል ቀጣይ ምእራፍ ምን ይሁን? የሚለው ላይ በጋራ እንስራ። ያን ማድረግ ስንችል ነው የእናታችን ነፍስ ሰላም የምታገኘው።” ብለዋል።
̋እናታችን የችግሮቻችን መፍቻው ቁልፍ አንድነትና መተባበር መሆኑን ያስተማሩን እናት ናቸው። ይህንን አስመልክቶ አንድ አባባል አላቸው። ችግሮቻችንን የምንቀርፈው “በግለሰብ ደረጃ ለምፅዋት በሚወረወሩ ሽርፍራፊ ሳንቲሞች ሳይሆን በአንድነት፣ በማበር እና በመተባበር በችግር ላይ ያሉ ወገኖቻችንን በተለይም ሴቶችን በማብቃት ነው።” የሚል በተግባር ያዋሉት አባባል እንደነበራቸውም አስታውሰዋል።
ይሄ የግዙፍ ስብእና እሳቤ ውጤት ነው ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ የወገን ደራሽነታቸውን በቃልም በተግባርም ፈጽመውታል። የተለየ ሀብትና ትምህርት ሳይኖራቸው ፍቅር፣ ርህራሄ፣ ቆራጥነት እና ጥንካሬን ተላብሰው ለሰው መኖር የሰው ልጆች የመጨረሻው የብቃት ደረጃ ሚዛን መሆኑን ማሳያ ሆነዋል ብለዋል።
ለዶክተር አበበች ጎበና ለሀገር ባለውለታዎች በሚደረግ የክብር አሸኛኘት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ 5 ሰዓት በመኖሪያ ቤታቸው፣ በመስቀል አደባባይ የተደረገላቸው ሲሆን ፤በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ስነ ስርዓታቸው ተፈፅሟል።
በመርሀ ግብሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክስርስትያን ፓትርያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።
ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና በኮሮና በሽታ ምክንያት በጳውሎስ ሆስፒታል በጽኑ ህሙማን ክፍል ሲረዱ ቆይተው ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም በተወለዱ በ85 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም