አንዳንዴም ፍልስፍናን የሆነ ቋጥኝ ነገር እናደርገውና አጠገባችን ያሉ፤ የራሳችን፣ የፍልስፍናዎቻችን መገለጫ የሆኑ ጥቃቅን ጉዳዮችን፤ የእኛነታችን መለያ፣ ማሳያ ወዘተርፈ የሆኑትን ልብ ሳንል እንቀራለን። ይህም ይጎዳናል፤ ጎድቶናልም።
ችግሩ ሰም እና ወርቅ (እዚህ ጋ ተሰማ እሸቴ ትዝ ካሉን ትክክል ነን)፣ ተረቱ፣ የሕግ ሥርዓታችን (በላ ልበልሀ፣ የሺበሺ ለማ “ተጠየቅ!” ይጠቀሳል) ወዘተርፈ እሴቶቻችንን ሁሉ የፍልስፍናችን መሰረት አድርጎ እስካለመውሰድ ድረስ አርቆ አሸፍቶናል ። በመሆኑም ከ3500 አመት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን፤ ከፈጣሪያችን ጋር (ከክሮቹ ጀምሮ) ጥብቅ ትስስር ያለውን፤ ለተቀረው ዓለም ሁሉ ያበረከትነውን … በገና የሙዚቃ መሳሪያችንን (ኦ አለሙ አጋ!!!) ማየት እንዳንችል ሁሉ አድርጎናል ። ይህም ወሰኑ እስከ ከማንነት መነቀል ድረስ ሁሉ እየዘለቀ ነውና “ሳይርቅ በቅርቡ፤ ሳይደርቅ በእርጥቡ” እንዲል የቅኔው ፍልስፍናችን፣ መፍጠንን የግድ እያለ ነው።
የቅኔ ነገር ከተነሳ በአንድ ወቅት “እየተዳከመ ያለው የአብነት ትምህርት” በሚል ርእስ ለንባብ ባበቃነው ጽሑፍ ላይ የተጠቀምንበትን አንጓ እዚህም እንድግመው፤ ስንደግመው ግን ምክንያታችን “የቤተክህነት ነው” ተብሎ ከትምህርት አለም የተሰረዘውን “የአብነት ትምህርት ቤት” (School of Thought?)ን እንዲያስታውስልን በማሰብ መሆኑን ማስገንዘብ ያስፈልጋል። (እዚህ ጋር “ቅኔ […] ምስጢር የተሞላ የረቀቀ ፍልስፍና የተከማቸበት ማለት [ሲሆን] ባለቅኔውም ሰሚውም በህሊና ርቀት የተራመዱ ናቸው።” እንዲሁም “የፍልስፍና ሕዝባዊ አቀራረብ ግጥም ይባላል።” የሚለውን የእጓለ ዮሀንስን ብያኔ (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ ገጽ 73) ሳይጠቅሱ ማለፍ ይህን ጽሑፍ ጎዶሎ ያደርገዋልና ጠቅሰነዋል።)
የየኔታ መቋሚያ የቆሎው ተማሪ
የሞተን ቀባሪ ለአምላኩ ዘማሪ፤
ከተማርከው ትምህርት ካጠናኸው ቅኔ
በኮፈዳህ ዋሻ ላክልኝ ለጎኔ።
እርግጥ ነው አንዳንድ ተራቃቂዎች ከፈላስፎቹ ስም ጀርባ በመደበቅ አጓጉል ሲራቀቁ፤ ሲመፃደቁ፤ ከዛም ባለፈ እጅ እግር በሌለውና ፋይዳ ያለው መልእክትን እንኳን ማስተላለፍ የማይችል ጽሑፍ በማቅረብ እራሳቸውን ከፈላስፎች ጎራ ለመመደብ ሲጥሩና ሲያጣጥሩ ይስተዋላሉ። ይህም ለየዋህ አንባቢና ገራገር አድማጭ “ፍልስፍና” ተደርጎ ይወሰድና ፀሐፊ/ተናጋሪውም “ፈላስፋ” ተብሎ የማይዘልቅ እውቅናን ይጎናፀፋል ። ይህም ጎድቶናል። የጉዳቱ መገለጫም “አትፈላሰፍ(ብኝ)” የሚለው ተዝወታሪ አገላለፅ ነው። (ይህ በ1776 በተመሰረተችው አሜሪካ “ተፈላሰፍ” የሚል ሆኖ መገኘቱና ከ3000 ዓመት በላይ የእድሜ ፀጋ ያላት ኢትዮጵያ ግኝቶቿን፣ ፈጠራዋን፣ እሴቶቿን ወደ ዘላቂ ፍልስፍናነት (“-ዊነት/-ism”) መቀየር አቅቷት፤ ከስንትና ስንት ጊዜ ታናሿ ከሆነችው አገር “ኢምፖርት” ማድረጓ ሲታሰብ ያናድዳል። የሚገርመው ሳሙኤል ጆንሰን ስለእኛ እስካሁን ድረስ በአነጋጋሪነቱና ጠቃሚነቱ የዘለቀውን The History of Rasselas, Prince of Abyssinia የፃፈው አሜሪካ ከመፈጠሯ በፊት በ1759 ነው።)
የራሳችን የባህላዊ አመጋገብና አለባበስ (የዶርዜ ጥበብ) ወዘተ እሴትና ሥርዓት እያለን አረቄ፣ ጠላ እና ጠጅን ንቀንና አናንቀን እንጦሮጦስ አስገብተናቸው የእነ ሩሲያን ቮድካ (እንደ’ኛው አበሻ አረቄ (ካቲካላ) ባህላዊ መጠጣቸው ነው)፣ የጀርመንን ቢራ (እንደኛው ጠላ ማለት ነው)፣ አስገብተን፤ ለእነሱም ተማርከን ቁጭ ። ርዝመት መለኪያ (ክንድ፣ ጋት፣ እርምጃ …)፤ ሰአት መለኪያ (ጥላ)፣ ኪሎ ግራም መለኪያ (እቅጩን 50 ኪሎ ግራም የሚይዘው እንቅብ፤ 10 ኪግ የሚይዘው ቁና፣ እንደየአስፈላጊነቱ (በፍየሉ መጠን ይወሰናልና ነው) የሚለፋው ስልቻ፤ በቻይና ሰራሽ ፕላስቲክና ሴራሚክስ እየተተኩ ያሉት እንስራ፣ ማዞሪያ፣ ጀበና … ባጠቃላይ እደ-ጥበቡ፣ ኪነ-ጥበቡ፣ ሥነ-ጥበቡ (ልዩነቱን እንዳትጠይቁኝ)፤ እስክስታው (የወንዱም የሴቱም) ወዘተርፈ ቀሪዎቹን አንባቢ ይቁጠራቸው እያልን ዝርዝሩን እዚሁ ላይ ስናቆም ሁሉም የእኛው የራሳችን ታሪካዊና ባህላዊ እሴት (ያጠኑት “ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች” ይሏቸዋል።) የሆኑ የፍልስፍናዎቻችን መሰረቶች ናቅናቸው።
(በነገራችን ላይ በጋና እንደኛው አበሻ አረቄ (Akpeteshie) በባህላዊ መጠጥነቱ የሚታወቀውን ባህላዊ መጠጥ ከማህበራዊ ኑሮና ህይወት፣ ከግጭት አፈታትና ይቅር ባይነት፤ ከፀረ አፓርታይድ ትግል ወዘተርፈ ጋር አያይዞ ጥልቅ ምርምር ያደረገበትን What’s in a Drink? Class Struggle, Popular Culture and the Politics of Akpeteshie (Local Gin) in Ghana, 1930–67 በሚል ርእስ EMMANUEL AKYEAMPONG በ “Journal of African History” አማካኝነት ለንባብ የበቃውን ጥናት ማየት ጉዳዩን ይበልጥ ግልፅ ስለሚያደርገው ማንበቡ ጠቃሚ ሲሆን፤ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስና ውርሶቻችንንም በቀላሉ ለማየት ያግዙናል።)
ኢትዮጵያ የተመሰከረለት የጀግኖች አገርና የጀግንነት ፍልስፍና (ከሽለላ/ፉከራ/ቀረርቶ ወዘተ) አለን። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የአቡነ ጴጥሮስን ገድል “ጴጥሮሳዊነት”፤ ሲሉና “ኢትዮጵያዊነት ጴጥሮሳዊነት” በማለት ሲያዘልቁት የጀግንነት ፍልስፍና ያለን መሆናችንን ለማመልከት ነው። ሎሬት ፀጋዬም ከጴጥሮስ “ገፀባህርይ” ጋር መከራውን ያየው በዚሁ ሁኔታና እምነት ነው።
አንድ የቅርብ ጊዜ የ”ግዮን” አምደኛ ያቀረበውን ጽሑፉን እንዳ’ለመታደል ሆኖ “የጋራ ጀግና የለንም” በሚል ነው ጀምሮ የደመደመው። ያ ጽሑፍ ከነበርካታ ስህተቶቹም ቢሆን (ከስህተቱ አንዱ “የጋራ ጀግና የለንም” ሲል “የጋራ ድል የለንም” እያለ መሆኑን አለማወቁና አውቆም ይሁን ሳያውቀው የ”አድዋ ድል” እና ሌሎችም ድሎች የጋራችን አይደሉም እያለ መሆኑን አለመረዳቱ ነው። የጋራ ድል ካለ የጋራ ጀግና አለና።) እዚህ ጋር እንጠቅሰውና ይህችን አንድ አንቀፅ ጣል እንድናደርግ ምክንያት ሆኖናልና እናመሰግነዋለን።
Alan I. Baily የተባሉ የLouisiana State University የሶስተኛ ዲግሪ (Dissertation) መመረቂያቸውን በ”Heroic Individualism: The Hero as Author in Democratic Culture” ርእስ የሰሩ ሲሆን፤ ከጀግና ቀረፃ፣ ገለፃና ትንተና አንፃር የእውቅ ሰዎችን (የሩሶ፣ ቶማስ ካርሌይ እና ኒችን) ስራዎች የመረመሩ ሲሆን ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ የአሁኑ ዘመን ዲሞክራቲክ ነን ባይ መንግስታት ለብሔራዊ ጀግንነት ተገቢውን ቦታ ይሰጣሉ ወይስ አይሰጡም? ብሔራዊ ጀግናስ እንዲፈጠር ይፈልጋሉ ወይስ አይፈልጉም? የሚል ሲሆን፤ ጉዳዩን ከእኛው አገር አኳያም መመልከት ይቻላል።
በእኛ ቤት በገና የፍልስፍናችን አንዱ መገለጫ አይደለምና ይሄው ሊጠፋ አንድ ሐሙስ እስኪቀረው ድረስ ተደላድለን ተቀምጠናል ። እንደ ጤፍና መጽሐፈ ሄኖክ ሁሉ “የእኛ ነው” እስኪሉን ድረስ እየጠበቅናቸው ነው። ዛሬ አለም “Reconciliation” እያለ ከሚያደርቀን በፊት እኛ የ”እርቅ” እና “ማስታረቅ” (ለምሳሌ ሀላባ ቆሊቶ ሄዶ የ”ሴራ ሥርዓት”ን መመልከት) ሥርዓቶች ያሉን መሆናችንን እንኳን ከመጤፍ የቆጠረው የለም። ከምንም አንቁጠረው እንጂ ቁልፍ የሆነ የፍልስፍናችን መገለጫ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይገባም።
የአገራችን ፍልስፍና እድሜ ጠገብ ሆኖ ሳለ አናውቀውም፤ ዘመናት እየተሻገረና እያሻገረ እዚህ ድረስ ስለ መዝለቁ እራሱን የቻለ የፍልስፍና ጥያቄ ሆኖ ሳለ ቁብ ያለው እንኳን ስለመኖሩ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም ። የኢትዮጵያ ማህበረሰብ እንደ አንድ የሉዓላዊነት አገር ሕዝብ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሲወራረስ የወረደ የዘመንና ርዝመቱ፤ የትውልድ መለዋወጥ ያልሻራቸው የታሪክ፣ የሕግ፣ የኑሮ ሥርዓት (ዘይቤ)፣ የአስተዳደርና ፖለቲካ፣ የልማድ፣ የወግ ቅርሶች ወዘተርፈ ሁሉ የፍልስፍናዎቻችን መገለጫ-ማሳያዎች መሆናቸውን “ስንቶቻችን ከቁብ ቆጥረናቸው ይሆን??” የሚል ቴስት ቢመጣ “የምናልፈው ስንቶቻችን እንሆን ይሆን?” የሚል ሌላ ጥያቄ ከማጫር ያለፈ ምንም ይዞ ሊመጣ አይችልም።
ስለ አክሱም ሐውልትና “እራሱ”ም ሆነ ስለ ሽመና ስራችን ፍልስፍናችንን ተሸካሚ፣ ገላጭና አመላካችነት እስኪ ልናገር ብለን እራሳችንን ብንጠይቅ፤ ለራሳችን እንመልሰዋለን? “የመጣንበት መንገድ” የሚለውንስ? የታሪክ ጉዟችንስ? የመጣንበት መንገድ ያሳዝናል፣ ያስደስታል፣ ያኮራል ወይስ …? ወይስ ዛሬ የነሸጠው ሁሉ ብድግ እያለ እንደሚለው ነው ነገሩ? ለመሆኑ “እኛ የራሳችን የሆነ ፍልስፍና አለን ወይስ የለንም?” ለሚለው dichotomy በጋራ ቋንቋ የምንሰጠው የጋራ መልስ አለን?? ጥንታዊው የአገራችን የትምህርት ሥርዓት ምን ይመስላል? የሀረሩ የቅርጫት ስራ ምን አይነት ፍልስፍናን ተሸክሟል? ከህይወትም ሆነ አኗኗር፤ ከሳይንስም ሆነ ፍልስፍና፤ ከማህበረሰብ እድገትም ሆነ የታሪክ ሂደት ወዘተ አኳያ አልፈተሽናቸውም።
እዚህ ላይ የራሳችንን ፍልስፍና እና አገር በቀል እውቀት “የቤተ ክህነት ነው” ብለንና “የሃይማኖት ስብከት” አድርገን ስንጥልና የሌላውን አለም ስናጠብቅ፤ አጥብቀንም ላለመርሳት ስንሸመድድ ሁሉ የእነማን እንደሆን እንኳን በቅጡ ሳናውቅ መሆኑ ነው። (ወይም እንደ ፍቃዱ ቀነኒሳ (በአዳማ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር) “ያልተጠናው የኢትዮጵያውያን ፍልስፍና” ጽሑፍ የአገራችን ፍልስፍና ገና አልተጠናም። ካልተጠና ደግሞ የጋን ውስጥ መብራት ማለት ነው።)
የዘመናትን አባጣ ጎርባጣና ውጣ ውረድ አልፈው እዚህ የደረሱ፤ ከመድረስም አልፈው ለአለም የተረፉ የኢኮኖሚክስ፣ የአስተዳደርን፣ የፖለቲካ፣ የወታደራዊ ሳይንስ፣ የተግባረ ዕድንና ሌሎችንም የጥበብ ቅርሶቻችን፣ ፍልስፍናዎቻችን (ጥበበ ቃላቱን ጨምሮ)ና አገር በቀል እውቀቶቻችን፤ ቋንቋችን (ዛሬ ግእዝን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ የሚሰጡ አገራት ከ12 በልጠዋል) ወዘተርፈ እንደ አልባሌ ቆጥረን ከተውን፤ ወደ ሚቀጥለው ትውልድ እንዳይሻገሩ ድልድዩን ከሰበርን “እነሆ…” እንደሚባለው ሁሉ እነሆ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይን አስቆጥረናል።
እንግሊዛዊው ፈላስፋ፣ በ1950 የሥነ ጽሑፍ ኖቤል ሽልማት አሸናፊው በርትራንድ ረስል ባለ 900 ገጹ “History of Western Philosophy” (1945)፣ («የምዕራባዊያን ፍልስፍናና ስልጣኔ ታሪክ» በቀለ ተገኘ መኮንን «የምዕራባውያን ፍልስፍናና ሥልጣኔ ታሪክ» በሚል ርዕስ ጥሩ አድርጎ እንደተረጎመው ይነገራል)፤ እና ሌሎችም የራሳቸውን ፍልስፍናና ፈላስፎቻቸውን “እንከን የለሽ” አድርገው ያንቆለጳጵሳሉ (ያብጠለጥላሉም)ና “አዲስ” ብለው ዓለም እንዲቀበለውና በእሱም እንዲመራ ሲያደርጉ፤ እኛ ግን እዚህ “ዘርአያእቆብ ኢትዮጵያዊ ነው/አይደለም”፤ “አክሱምን የሰሩት ኢትዮጵያውያን ናቸው/አይደሉም” እያልን በሚዲያ ሳይቀር የምንከራከር ጉዶች ነን (ዘርአያእቆብ የእናንተ ሳይሆን የእኛ ነው፤ አክሱምን የሰራነው እኛ እንጂ እናንተ አይደላችሁም ብሎ ሸንጎ (ICC) ያቆመን ያለ እስኪመስል ድረስ)፤ “የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ” በሚል ርዕስ ቃላት የምንደረድር ደርዳሪዎች ሆነን ነው በትውልዱ የምንታወቀው።
እነሱ “የምዕራብ ፍልስፍና አባት ሶቅራጥስ ነው።” በማለት ሲነግሩን “አዎ ነው” ከማለት ውጪ “የአፍሪካ ፍልስፍና አባት፣ የኢትዮጵያ ፍልስፍና አባት ዘርዓያዕቆብ ነው!!!” ለማለት ፍላጎትም ይሁን እውቀት፣ ትጥቅም ይሁን ስንቅ ስለሌለንም ይሁን እንጂ፣ ባንድ ላይ “ዘርዓያዕቆብ!!!” አንልም። “ለምን?” ጥያቄው ይሄ ነው። እነሱ ታሪክና ፍልስፍናቸውን በሶስቱ ምሰሶዎች ከፋፍለው (ancient era, medieval era, እና the modern era እያሉ) ሲያስተምሩን እኛ ገና የተረጋጋ የዘመን ክፍፍል እንኳን የለንምና “ኋላ ቀር” ብንባል ምኑ ይገዳል?
የቀድሞውን “የኢትዮጵያ ተማሪ ቤትና ትምህርት በግጥም፣ በጐዳና ድርሰት፣ በሙዚቃና በፍልስፍና ውበትና ረቂቅነት ያላቸው ብዙ ሥራዎች አበርክተዋል፡፡” በማለት ሀዲስ አለማየሁ ነግረውናል። በእጓለም ተደጋግሞ ተወስቷል። የአሁኑንስ የዛሬዎቹ ምን ብለው ነው የሚነግሩን? ብሎ የመጠየቅ መብት ካለን የምንጠይቃቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉን።
ዛሬ ሞራላችን የላሸቀ ማህበረሰብ መሆናችን በእነ “ማኃልየ መኃልይ ዘካሳንችስ” (እና በእሱ አምሳል የተፈጠሩና ከእሱ በኋላ የመጡ፤ …..ዘቺቺኒያ”ንና የመሳሰሉትን አካባቢዎች መሰረት ያደረጉ ስራዎች) አማካኝነት ልክ ልካችን ቢነገረንም፤ ባንዳነት (አምስተኛ ረድፈኝነት) እየገነነና አገርና ሕዝብን ለውጭ አካላት እየሸጠ መሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ሳይቀር እየተነገረ ቢሆንም፤ ፍልስፍና አለን፤ መገለጫዎቹም አሉንና ዝም ብሎ አገር፣ ዝም ብሎ ሕዝብ አለመሆናችንን ልናውቅ፤ አውቀንም ልናሳውቅ ይገባል። ለዚህ ደግሞ፣ እስካሁን ከጠቀስናቸው በተጨማሪ በወቅቱ “ጉድ” እና “በአይነቱ የመጀመሪያው …” የተባለለት የፍቅረ ድንግል በየነ “የሳይንስ ራእይ” ልቦለድና ዋና ገፀባህርይው ኤሊያስ፤ እንዲሁም ፍልስፍናው (ኤሊያሲዝም) ነውና መገለጫዎቹ ለምን ተግባራዊ አልሆኑም ካልሆነ በስተቀር በመገለጫዎቻችን ላይ ጠብ አይኖርም ። (ከኤሊያስ እና ፍልስፍናው (ዘላቂነቱ) ኤሊያሲዝም ጋር በተገናኘ ወደ ጎጃም ብቅ ብሎ ደብረ ኤሊያስን ያጠኗል።)
ምንም እንኳን ዛሬ ፖለቲካችን የዘር፣ አንድነታችን የክልል፣ ደረጃችን “ያ’ለም መጨረሻ” ቢሆንም “ትልቅ ነበርን፤ ትልቅም እንሆናለን” እንዳለው “አሁን”ን ፈሪ አባባል ተስፋ ልንቆርጥ አይገባምና “አይዞን!!!” ማለት ተገቢ ነው። አይዞን!!!
አጥኚዎቹ “በሀገራችን የመጀመሪያው ወርቃማ የፍልስፍና ዘመን 1947–1956″ በማለት ቢነግሩንም፤ ጌታቸው ኃይሌ በ”ደቂቀ እስጢፋኖስ” በኩል ግእዝ ለእኛ ለአሁኖቹ ትውልድም ሆነ መጪዎቹ አባላት “የባህልና የታሪክ ቅርስ” መሆኑን መሬት አስነክተው ቢነግሩንም፤ … ቢነገረንም፣ … ቢነግሩንም፤ … ቢነገረንም ምንም፤ … ንክች ያባ ቢላዎ ልጅ!!! ጭራሽ ግእዝ ለምኔ …፣ ታሪክ ለምኔ …፣ አገር ለምኔ … እያልን (በልባችን እስክስታ እየወረድንም ጭምር) ማዜሙን የቀጠልን እስኪመስልብን ድረስ መኝታው ቀልጧል።
ዛሬ፣ የፍልስፍናዎቻችን መገለጫዎችን መርሳት ብቻ አይደለም ቢያስታውሱንም እንኳን መስማት እማንፈልግ ሞልተናል ። እየተጠቀምንባቸው፤ ሰው የሆንባቸው ሁሉ እንጠየፋቸዋለን፤ እኛው እየተጠቀምንባቸው የእኛ አይደሉም፤ የእኔ አይደለም የምንል ለየት ያልን ልዩዎች ነን ። ደስ ይላል ¡¡¡ ደስ ከማለቱ በፊት ግን “በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታየው የማኅበረሰብ እሴት መሸርሸር ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፤ ስለዚህም የሲቪክ ማኅበራት ፊታቸውን ወደ እሴት ግንባታ ሊያዞሩ ይገባል” የሚለው የታዛቢዎች አስተያየት፤ የፕሮፌሰር ፓንክረስት በርካታ ጥናቶች ሊታወሱ እንጂ ሊረሱ አይገባቸውም ማለት ያስፈልጋል ። በተለይ በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ አምርረውና አጥብቀው ይዘውት የነበሩትና ጠልቀውም የገቡበት፤ በዚህም ምክንያት ዘርዓያዕቆብንና ስራዎቹን ለዓለም ያስተዋወቁት ፕ/ር ክላውድ ሰምነር “ትምህርትን የሚመሩት እውቀቶች ከሕዝቡ ፍልስፍና የሚፈልቁ ሊሆን ይገባል::” እንዲሁም “የኢትዮጵያን ትምህርት በኢትዮጵያ ፍልስፍና፣ ታሪክና እሴት ላይ” እንዲመሰረት ማድረግ የሚገባ መሆኑን በድርቡ ያሰመሩበት ምክረ ሀሳብም ሊታሰብበት የግድ ነው። ይህን ስንል የጥንቱ የኢትዮጵያ ስልጣኔና ፍልስፍና ወደ ተሻለ ደረጃ ማደግ ያለበት ሲሆን ለዚህም “በዘመናችን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምሁር ፊት የተደቀነው ሥራ ይህ ይመስለኛል። ሁለቱን ሥልጣኔዎች የኢትዮጵያንና የአውሮፓን በገዛ መንፈሳችን ድልድይነት ማገናኘት፤ በጥረታችን ግለትና ሙቀት እንዲዋሃዱ ለፍሬም እንዲበቁ ማድረስ። ዋናው ስራ ይህ ነው።” (ገጽ 78-79) ያሉትን በመዘንጋት ሳይሆን በማሰላሰልና ማስታወስ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2013