ትናንት
ኢትዮጵያ ጥንታዊና ታሪካዊ ሀገር ናት ። ለዚህም የአክሱም ሥልጣኔን፣ከመካከለኛው ዘመን የሐረር ግንብንና ከቅርቡ የአምስቱ ጊቤዎችን ለአብነት ማንሳት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ስልጣኔ ባለቤት አገር መሆኗን በቂ ይመስለኛል።
የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች መገኛ መሆን የጀመረችው ደግሞ ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደሆነም ድርሳናት ያሳያሉ።
ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የአድዋ ድል ደግሞ የነጭ የበላይነትን ያከተመና ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ፈር የቀደደ እንደነበርም በታሪክ ተመስክሮለታል።
የዘመናዊ ሥልጣኔ መገለጫ የሆኑት የመንግሥት መዋቅር ማለትም ካቢኔ የተዋቀረው፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑት ወፍጮ፣ ስልክ፣ተሽከርካሪዎችና ሲኒማ ወደ አገሪቱ የገቡት በዚህ አንድ ክፍለ ዘመንን በዘለለው ጊዜ ውስጥ ነበር።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ ገደማ በኢትዮጵያ የንጉሳውያን አገዛዝ እንዲያበቃ ከተቀሰቀሰው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ ኢትዮጵያ የተረጋጋ መንግሥትና አስተዳደር ያገኘችባቸው ዓመታት ነበሩ ማለት አይቻልም።
ይልቁንም የንጉሳውያኑ አገዛዝን ‘’ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት ናት’’ተብላ የተሰየመችበት ጊዜ መጣ ። “ብሔራዊ ጭቆና”የሚል ዜማ መቀንቀን የጀመረውም በዚህ የታሪክ ወቅት ነበር።
የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ 17 የሥልጣን ዘመናት ከእርስ በርስ ግጭቶችና ከሶማሊያ ጋር በተካሄደ ጦርነት ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ ሰላም እንደናፈቃት አልፏል ። ይልቁንም አንዳንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወገኖች የኤርትራ ሕዝብ ጥያቄ “የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው” ብለው ማንሳት ጀመሩ ። የአገር ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶች እየደገፉት አገር እስከማስገንጠል ማድረሳቸውን ታሪክ መዝግቦታል።
አገር ማፈራረስና ’’ያልተማከለ አስተዳደር ….’’
የኢህአዴግ መንግሥት ኤርትራ ነጻ እንድትወጣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር ደብዳቤ በመጻፍ ቀጥሎም ውሳኔ ሕዝቡ በነጻነትና በባርነት አማራጮች እንዲገደብ በማድረግ በአፍሪካ ቀንድ ሌላ አገር እንድትወለድ አድርጓል ። ዛሬም የመገነጣጠል አባዜው ሳይለቀው ሌላ “አገር” ለመፍጠር እየጣረ ነው ።
ከኢትዮጵያ ጋር አንድ ሆና እንድትቀጥል አማራጭ ማቅረብ ሲገባው፤ኤርትራ ራሷን ችላ እንድትወጣ ተባብሯል ። “ከጳጳሱ በላይ ቄስ” ሆኖ ኢትዮጵያ እንድትገነጣጠል በር ከፍቷል።ነጻዪቱ አገር ሰንደቅ ዓላማዋን ማውለብለብ ጀምራለች።
ኢትዮጵያ በዓለም ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታም ‘’የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች’’ መብት እስከ መገንጠል ድረስ እንደሚከበር በሕገ መንግሥት ጭምር በማረጋገጥ ሌላ ጉደኛ ታሪክ አስመዝግቧል። አንድነትን የማይፈልግ፤መለያየትን የሚናፍቅ ሕገ መንግሥት በመተግበር አገር አፍራሽነቱን ያሳየ ድርጅት መሆኑን በተግባር አሳይቷል ። ይሄ ጨዋና አንድነቱን የሚወድና የሚያከብር ሕዝብ አልተቀበለውም እንጂ።
በተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ሲነሱ የነበሩት የነጻነት እንቅስቃሴዎች ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተብለው በተከለሉት ዘጠኝ ክልሎች መልስ ለመስጠት ተሞክሯል ። ከ75 ያላነሱ ብሔረሰቦችን በክልል ደረጃ ማዋቀር ባይቻል እንኳ፤የአከላለል “ጭቆና”አድርሷል።
በዚህም “እስከ መገንጠል” የሚፈቅደው የፌዴራላዊቷ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ለአንዳንዶች በረከት የሆነውን የክልልነት መብት ሲሰጥ፣ሌሎች በዞን ደረጃ እንኳን የአስተዳደር መዋቅር የከለከለበት ሁኔታ ታይቷል ። በዚህም ራስን በራስ ማስተዳደርን ለውሱን ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብቻ በመቸር የ”ማንነት”ን ጉዳይ በከፊል አዳፍኗል።
የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ በተጣለበት ‘’ታሪካዊ አደራ’’ በመገንጠልና በመገነጣጠል አባዜ የተጠመደው ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት ለክልል የማይበቃውን ክልል አድርጎ፣ የክልልነት መብት ያገኙትን ደግሞ በመጨፍለቅ አገዛዙን ሲያሳምር ቆይቷል።
በዚህም በማንነት ላይ ባተኮረው የብሔርነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፤አነስተኛ የሕዝብ ብዛትና ጠበብ ያለ የመሬት ስፋት ያላቸው ክልሎች ሲሆኑ፤በተቃራኒው ማንነቱ ሊከበርለት የሚገባ ቁጥሩ ከፍ ያለ ሕዝብና ሰፊ መሬት የሚሸፍኑት ቢበዛ ዞን አልያም ልዩ ወረዳ እንዲሆኑ አድርጓል።
እንደ ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ አከላለል ቢሆንማ አገርም አገር ሆና ዛሬ እዚህ ባልደረስን ነበር? እዚህጋ ከሁለት ዓመታት በፊት ያነጋገረኳቸው የሰመራ ዩኒቨርሲቲ መምህር ያሉኝ ትዝ ይለኛል። ‘’ሕገ መንግሥቱ እንደሚለው ከሆነ፤ የአገራችን ክልሎች ዘጠኝ ብቻ ይሆኑ ነበር?’’ብለውኛል። ቢያንስ የ75 ክልሎች ባለቤት እንሆን ነበር ማለት ነው።
በሞግዚትነት በሉት በቀላጤ የሚተዳደሩት ክልሎች ራሳቸውን የማስተዳደር ነጻነት እንዳልነበራቸው ይታወቃል። ለአንዳንዶች ማንነትን አጡዞ፣ራስን የማስተዳደር መብትን መከልከል በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት አወቃቀር ሸፍጥ ታይቶበታል።
ከአንድ ትውልድ በላይ አገርን የማስተዳደር ኃላፊነትን የተረከበው ፓርቲ ከአሃዳዊ መንግሥት ባልተናነሰ መንገድ ሰጥ ለጥ አድርጎ እየገዛ ‘’ፌዴራል’’ አስተዳደርን እንደሚተገብር ሲሰብከን ነበር ። እኩልነት፣ፍትህ፣ዴሞክራሲ በራሱ ፍላጎት ብቻ እየተመጠነ ለክልሎች ሲሰጥ እንደነበርም ታሪክ ምስክር ሆኖን አልፏል።’’ ባልተማከለ አስተዳደር ስም የተማከለ አስተዳደር’’ አገር ይገዛ ነበር።
አፈና በተሞላበት ዴሞክራሲ፣ባልተመጣጠነ የኢኮኖሚ ዕድገትና የኑሮ ሁኔታ እየተማረረ የመጣው ሕዝብ በስመ አንድነት የሚደርስበት በደል እያንገፈገፈው ሲመጣ ማንነቱን ለማስከበርና የተሻለ ነገር ለማምጣት መነሳሳት የጀመረው የ2007 አገራዊ ምርጫ ውጤት በታወቀ ጥቂት ወራት ውስጥ እንደነበር ህያው ምስክሮች ነን።
በምርጫው ኢህአዴግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን 547 ወንበሮች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ የዜጎችን ድምፅ የማይሰማበት ፓርላማ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ፤ዜጎች በድምጻቸው የመረጧቸው ወኪሎቻቸው ለማይገኙበት ምክር ቤት ያላቸውን ክብር ቀንሶታል ። በ2002ና በ2007 ዓ.ም ከተካሄዱት ምርጫዎች ውጤት የነበሩት ውስን የተቃዋሚዎች ወንበሮች በፓርቲው ተወስደው በዘመነ መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ አንድ ድምፅ ብቻ የሚሰማበት የአንድ ፓርቲ-አንድ መንግሥት ሥርዓትን አስፍኖባታል።
ከያለበት ውስጥ ውስጡን የተቀጣጠለው ቋያ መቀመጫ ያሳጣው ገዢው ፓርቲ ‘’በተሃድሶ’’ና በ”ጥልቅ ተሃድሶ” ስም ረጃጅም ስብሰባዎችን ቢያደርግም፤የአገዛዝ ዕድሜውን የሚያራዝምበት ስልት ከመሆን አላለፈም።
ለውጡ
በአገሪቱ የፖለቲካ ትግል ሁሌም ተደራጅቶ መንግሥትን ተክቶ የሚሰራ ፓርቲ ያለመኖሩ አንዱ ችግር በመሆኑ ይሄኛውን ትግል የሚመራ አካል ማግኘት በራሱ ፈተና ነበር። ’’ሳይደግስ አይጣላም’’ እንደሚባለው ከሩቅ ሳይሆን፤ ከዚያው ፓርቲ ውስጥ ለለውጥ የተዘጋጀ ኃይል ብቅ ማለቱ እፎይታ አመጣ። በተራማጅና በተጎታች የፓርቲው አባላት መካከል በተደረገው ትግልም ለውጥ አራማጁ ወገን ኃላፊነት ለመረከብ በቃ። ኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የተነሳው ቡድን ዶክተር ዐቢይ አሕመድን የድርጅቱን ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጡም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሆነው ተሾሙ።
ምርጫው ከአገር አልፎ በመላው ዓለም በሚገኙ ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአገሪቱን ዳግም ውልደትን ከተስፋ ጋር ወለደ ። የኢትዮጵያን ትንሳዔ ያበሰረ ታላቅ ታሪክም ተመዘገበ ። ለውጡ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ሾተላይ እየሆኑባት በመጡት ለውጦች ያጣችውን ሁሉ ለማሟላት በሩን በመክፈቱ ድጋፍ ያገኘው በትጥቅ ትግል ከሚሳተፉ ተዋጊዎች ጭምር ነበር።
የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር(ኦነግ)፣የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር(ኦብነግ)ና የአርበኞች ግንቦት ሰባት ታጣቂ ኃይሎች ጋር በተደረገ ስምምነት ከኤርትራ ወደ አገር ውስጥ ለመግባት እምብዛም አልተቸገሩም።
ለውጡን ከልብ የተቀበሉትና ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደ አገራቸው የገቡት ድርጅቶች ከሕዝብ ተደባልቀው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ፤ኦነግ ግን ታጣቂውን ኃይል ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ከ40 ዓመታት በላይ በጦርነት ያጣውን ድል በሰላማዊ መልኩ ገብቶ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀመረ።
ዳግም ወደ ‘’አስታጥቁን አታስጨርሱን’’
ኢትዮጵያ በ1969 ዓ.ም በአገር ውስጥ የፖለቲካ ኃይሎችና የሶማሊያ ወረራ ገጥሟት ህልውናዋ ስጋት ላይ ወድቆ ነበር። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከአሜሪካ የገዛቸው የጦር መሳሪያዎች ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ‘’ህብረተሰባዊነት’’ን በማወጁ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ አልቻሉም። ይህም የውጭ ወራሪን በተለይ ሰርጎ ገብ የሚባለውን ኃይል ለመግታት አቅም አሳጣ።
በዚህ ጊዜ ደርግ ‘’አምስተኛ ረድፈኞች’’ ያላቸው የአገር ውስጥ የፖለቲካ ኃይሎችና ደርግ በራሱ ሕይወት እየቀጠፉ ነበር ። በዚህ የቀይና ነጭ ሽብር ትግል በመጧጧፉ ሰላምና አለመረጋጋት የታሪክ መዛግብት ይነግሩናል።
ታዲያ ባልተረጋጋ ወንበር የተቀመጠው ደርግ ሕዝቡን ከአደጋ ስላልታደገው አንድ ጥያቄ ይቀርብለት ነበር። “አስታጥቁን አታስጨርሱን” የሚል ። በዚህም መንግሥት አገርና ሕዝብን ለማዳን የህልውና ዘመቻ ጀመረ። 300ሺህ ሕዝባዊ ሰራዊት(ሚሊሺያ) ሰልጥኖ ወራሪውን የሶማሊያ ጦር በማስወጣት ሂደት ከመደበኛው ሰራዊት ጎን አሰልፎ ድንበር አስከበረ።
የደርግና የአምስተኞቹ ረድፈኞቹ ውስጣዊ ትግል በመንግሥት የበላይነት በመደምደሙና በመሄዱ አገር ህልውናዋን አስቀጥላለች። በሰሜን ኢትዮጵያና በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ለነጻነት የሚታገሉ ኃይሎች ትግል የራሱን መንገድ ይዞ እስከ 1983 ዓ.ም የቀጠለውን ትግል ሳንዘነጋ ማለት ነው።
ዛሬስ?
ዛሬ በአንዳንድ ክልሎች ማንነትን ተገን ባደረገው ጥቃት ዜጎች “አስታጥቁን አታስጨርሱን” ሲሉ ተደምጠዋል። “አስታጥቋቸው” ያሉም ወገኖች ድምፅ ተሰምቷል። የአንድ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ሌላው ገብቶ ተዋጊ ኃይሎችን እንዲያጠፋም ሐሳብ የቀረበበትን ሁኔታ ታዝበናል።”አገሬ” ባለው ክልል ‘’ወደ ዘር ማንዘርህ ተመለስ/ግባ” እየተባለ ጥቃትና ጥፋት ሲደርስ “አስታጥቁን አታስጨርሱን” የሚል ጥያቄ ቢቀርብ አይገርምም።
ሶስት ዓመታት ባስቆጠረው ለውጥ አገሪቱ በዜግነትና በብሔር ተኮር ዘውጎች ተከፍላለች ። ይህንን በተለይ በፖለቲካ ድርጅቶችና በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ማየት አያስቸግርም።
ኢትዮጵያን ማለት አሃዳዊነትና አንድ እምነት አራማጅነት ተደርጎ ተቀምጧል ። ሌላውን ትተነው ። አንዱ ወገን ማንነትን ሳይሆን ሰውነት አይቶ ከሌሎች መኖር ባያቅተውም፤ትምክህተኛ ተደርጎ ይወሰዳል ። በጋራ ተጠቃሚነት ቢያምንም፤የሌሎችን ማንነትን እንደማይቀበል ተደርጎ ይወሰዳል።
ብሔርተኛው ወገን ደግሞ ካለ የእሱ/ሷ ማንነት እንጂ፤የሌላው ጉዳይ ምኑም አይደለም። የሚያቀነቅነው፣ የሚያስበውና የሚያነበንበው የራሱ/ሷን ማንነትና ተበዳይነት ብቻ ነው ። ኢትዮጵያዊነት፣አንድነትና አብሮነት ምኑ/ኗም አይደለም።
የ21ኛው ክፍለ ዘመኗ ኢትዮጵያ እንዲህ ባለ አተካራ ውስጥ ገብታለች ። በሕዝቧ ብርታትና ጥንካሬ ወደ አንድነቱ እንደሚመለስ ባያጠራጥርም።
በትግራይ ክልል ከተካሄዱት የሕግ ማስከበርና የወንጀለኞች ማደን ዘመቻዎች ተከትሎ በአፍቃሪ ህወሓት ተከታዮች እየተከሰተ ያለው “ተጋዳላይነት”ም ሕይወት መቅጠፍና ንብረት ማውደሙን ቀጥሏል።
በሁሉም ሥፍራዎች እየተካሄዱ ያሉት ግጭቶች መነሻው ሴራ፣ደባ፣ተንኮል ወይም የፈለጋችሁትን ስያሜ ብትሰጡትም ወገን ወገኑን የሚያጠፋበት “ተልዕኮ” እንደሆነ በገሃድ አሳይቷል።
ታላቂቷንና ታሪካዊቷን አገር ሊያፈራርሷት በሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ተቀናጅተው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ሳይታለም የተፈታ ከሆነ ሰነባብቷል። ልክ የደርግ መንግሥት ባልተረጋጋበት ዘመን ሕዝብ “አስታጥቁን አታስጨርሱን” የሚል ድምፅ ያሰማበትን ወቅት ያስታውሳል ። ዛሬ ወደዚያ ጊዜ መመለሳችን በራሱ ያሳፍራል?
ያልዘመነ አስተሳሰብ በዘመነ ሉዓላዊነት(ግሎባላይዜሽን)
የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ማንነትን በመጠየቅና በማስከበር ላይ እንደተመሰረተ ይታወቃል። ማንነት ከራስና ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ብሔር/ብሔረሰብ ያድጋል ። ዜግነት ደግሞ መልክዓ ምድራዊ ይዞታ ጠብቆ በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ መኖርን ይጠይቃል።
ታዲያ ማንነትን ያከበረና ዜግነትን ብሔራዊ መለያው ያደረገ ትውልድ መፍጠር ተገቢ ይሆናል ። ማንነቱን አክብሮና በዜግነቱ ኮርቶ ሕይወትን መቀጠል ማንንም አያስከፋም።
ዛሬ በኢትዮጵያ በጦዘው ፖለቲካ ሁለት ጎራዎች ተደበላልቀው ወደ አደባባይ ወጥተዋል ። ሁለቱም የየራሳቸው አገር አጥፊ መለያ ባህርያት አላቸው። “አንድነት” የሚለው ወገን ፤የብሄርን ማንነት ያለመቀበል ገታራ አቋም ይይዛል። በ”ብሔር”ስም የተደራጀው ወገን ደግሞ ‘’አንድነት’’ የሚለውን ቡድን ጠላቱ አድርጎ ያቀርባል።
በዚህም አንድነት የሚለውን ወገን “አሐዳዊ”፣” ትምክህተኛ”ና “ወራሪ” አድርጎ መመልከት፣የብሔር ማንነት እንዲከበር የሚጠይቀውን ወገን ደግሞ “ጠባብ”፣ከፋፋይ”ና “አገር አጥፊ” አድርጎ መፈረጅ ይታያል።
በሕዝቦቿ አንድነትና መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ የኖረችውን አገር “ኢትዮጵያዊነት አይመቸንም” የሚሉ ዜጎችን ማየት ጀምረናል።በብሔር ማንነትና ፍቅር ያበዱ ዜጎች ዜግነታቸውን ትተው ለራሳቸው ብሔር መቆማቸውን ማሰብ ይከብዳል።
ኢትዮጵያዊነትን የማይመጥኑ፣ የመቻቻልና የመከባበር ባህልን የዘነጉ አመለካከቶች ከየአቅጣጫው ሲወረወሩ ስንሰማ ብሎም ሲተገበሩ ስናይ ይህቺን አገር አለማወቅ የሚመነጭ በመሆኑ ያሳዝናል።
ኢትዮጵያ እኮ ዓለም ስለ ሉዓላዊነት ሳያውቅ የሌሎችን አገሮችን ዜጎችና የተለያዩ እምነት ተከታዮች ተቀብላ እንዲኖሩ ያደረገች አገር ናት ። የአንዳንዶቻችን የዘር ሐረግ ቢቆጠር ምንጫችን ከየት እንደሆነ የምናውቅ ስንቶቻችን እንሆን? የእምነቶቻችን መነሻ ከየት እንደሆነ ለማወቅ ጥልቅ ምርምር አያሻውም? ለመሆኑ ዛሬ ኢትዮጵያ የስንት አገሮችን ስደተኞች ተቀብላ እንደምታስተዳድር ብናውቅ ዘር አንቆጥርም ነበር ። የውጭ ኃይሎችም ሊከፋፍሉን የሚሞክሩት ክፍተቶቻችን አይተው መሆኑንም ልብ ማለት ይገባል። “ባንዳዎችና ባዳዎች”እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ!!
እንደ መፍትሄ
ባለፉት ሶስት ዓመታት አገሪቱ የገጠሟትን ፈተናዎች ለመወጣት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል ። ኢትዮጵያዊነትን ከማንነት ጋር ባጣጣሙ መንገዶች እንድንቀጥል ውይይትን በየቦታው ማስቀጠል ይገባናል። ኩርፊያንና የዳር ተመልካችነትን ሳይሆን፤ አሳታፊና ባለቤት የሚያደርጉ መድረኮችን ማካሄድ ያስፈልጋል። አገር የምትገነባውና ሰላምና ደህንነቷ የሚረጋገጠው በዜጎቿ በመሆኑ። የውስጥ አንድነታችንንም ስለሚያጠናክር።
በግሌ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በዚህች አገር ምን በመሥራት ላይ እንደሆነ አላወቅኩም ። ኮሚሽኑ አገሪቱን ከችግሮቿ ለማውጣት ምን እየሰራ ይሆን?
ኢትዮጵያ በታሪኳ ያላጋጠሟት ችግሮች ዛሬ ገጥመዋታል። ምክንያቶቹን እንኳን ኢትዮጵያውያን ቀርቶ የቅርብ ወዳጆቿና ጠላቶቿ ጭምር ያውቋቸዋል። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሰበብ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ምን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አውቀናል። የውስጥ ችግሮቻችን በእኛው መወጣት እየቻልን የውጭ ኃይሎችን ሴራ ማክሸፍ እንጂ፤ለማን ይመቸው ብለን ነው በራችንን የምንከፍተው?
እንዲያውም በዚህ ዘመን በመኖራችን ዕድለኞች ነን። ቢያንስ የተጎዳችና የተጎሳቆለች አገር ለልጆቻችን ከማስተላለፍ ዕዳ ወጥተናል ። ነገ ታላቅ እንሆናለን። ከፍታው ላይ እየወጣን ነው። መወጣጫውን እንድንሰበርላቸው የሚፈልጉ ኃይሎች መሳሪያ መሆን የሚሹ ወገኖቻችንን “አይበጅም” እንበላቸው ።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ያረፈችበት መሰረት እንዳይናጋ፣ የተዋቀረችበትም ማገር እንዳይላላ መረባረብ ያለብን ዛሬ ነው። ያለ አገር ሁላችንም ባዶ ነን። በአገር ሁሉም አለ። በኢትዮጵያ ደግሞ ያጣነው ነገር የለም። ዋናው ተከባብሮ፣ ተግባብቶና አንድነትን አስጠብቆ መዝለቅ ነው።
ሞልቶን በተረፈ የአብሮነት፣የመቻቻልና የመከባበር ባህል ሌሎች እንዲያውቁትና እንዲከተሉት የምናደርገው ነውና እናስቀጥለው። መሰረቱ ያልፈረሰ፤ ማገሩም ያልላላባት አገር በመገንባት ትውልዶችን እናሻግር ።
የውስጥ ችግሮችን እየፈታንና የውጭ ኃይሎች ጫና ተቋቁመን ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ!!!
አዲስ ዘመን ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም