
አዲስ አበባ፡- መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍልና ሀገር ወዳድ ዜጎች ሀገሪቱ ከገጠማት የብሔራዊ የደህንነት አደጋ ለመታደግ ግልፅ ግንዛቤ በመያዝ በአንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ አቀረበ። በስድስተኛው ሀገራዊ የመራጩ ድምጽ እንዲከበር ተገቢውን ሰላማዊና ህጋዊ ጥረት እንደሚያደርግም ገለፀ።
አብን ትናንት በህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጣሂር ሙሃመድ በኩል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፣ አብን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር ወዳድ ዜጎችና በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ሀገሪቱ ስለገጠማት የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያን ለመታደግ በአንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርቧል።
በወታደራዊ ኃይል የሚገኘው ድል በዲፕሎማሲው እንዳይነጠቅ መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን አምባሳደር በመሆን በአለም ዲፕሎማሲ ትግል መሰለፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
መንግስት ልዩ የደህንነት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ በተይም አሸባሪው የህወሓት ቡድን መልሶ በተቆጣጠረው በትግራይ ክልል የተማሪዎችንና የሲቪል ዜጎችን እና የትግራይ ህዝብ ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል።
በፀረ ኢትዮጵያዊው ጎራ በጠላትነት ተፈርጆ ዘርፈ ብዙ ጥቃት የተሰነዘረበት የአማራ ህዝብ የሚገኝበት ወቅታዊ የስጋት ደረጃ በውል ተገንዝቦ የበኩሉን ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ አለበት። የአማራ ዲያስፖራ በህዝባችንና በሀገራችን ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ ሁለገብ የሃሳብ፣ የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ ተሳትፎውን አጠንክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክቷል።
መላው አፍሪካውያን ወንድሞች፣ የኢትዮጵያ ወዳጆችና አጋሮች የጥንታዊ ስልጣኔ፣ አኩሪ የነጻነት ታሪክ ያላት ሀገር በእኩያን ኃይሎች የተከፈተባትን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቃት ለመመከት ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪ አቅርቧል።
በሀገሪቱ ላይ የተደቀነው ጽኑ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ለመመከትና ከምንም በላይ የቆመለትን የሀገር ሉዓላዊነትና የህዝብ ጥቅምና ክብር፣ እንዲሁም የሀገረ መንግስቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድርጅታዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዳለው አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረገው ከፍተኛ ተጋድሎ ከአፈናና ጭቆና መንበሩ የተባረረውና በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ህዝባዊ ሚሊሻ ድባቅ የተመታው አሸባሪው ህወሓት ተመልሶ በማንሰራራት በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ ተቀዳሚ አደጋ ሊሆን በቅቷል። ማዕከላዊ መንግስትና በየደረጃው ያሉ መንግስታዊ አካላት ሀገሪቱ ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ሚና በግልጽ ከመወሰን አንስቶ ሁሉን ባለ ድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ ደህንነት እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።
የመጀመሪያው የሆነውን አብይ የፖለቲካ ተሞክሮው በሆነው በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ ሲያቅድ ገና ከመነሻው ሀገሪቱ የምትገኝበትን የፖለቲካ አውድ በመገምገም በምርጫው የመሳተፉን ውሳኔ ያደረገው በዋነኝነት ከድርጅታዊ ፋይዳዎች ይልቅ ለሀገራዊ ፖለቲካው መረጋጋትና ለዲሞክራሲያዊ ተሞክሮ ከሚኖረው ፋይዳ አንጻር እንደሆነ ጠቁሟል። የመራጩ ድምጽ እንዲከበር ተገቢውን ሰላማዊና ህጋዊ ጥረት እንደሚያደርግም አስታውቋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2013