
አዲስ አበባ፡- ተሰናባቹ ፓርላማ በችግር ወቅት የነበረበትን ጫና ተቋቁሞ ሀገርን ለማሻገር በጽናት የሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አስታወቁ። መጪው ፓርላማም በሌሊት ተሰልፎ የመረጠውን ህዝብ ለማገልገል ከወዲሁ ሊዘጋጅ እንደሚገባ አመለከቱ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በአምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ፓርላማው ከሌሎች ፓርላማዎች ለየት የሚያደርጉት በኮሮና ምክንያት ለስድስት ዓመት ያገለገለ መሆኑ እና በመንግስት ለውጥ ጊዜ ስራ ላይ የነበረ መሆኑ ነው።
ፓርላማው በለውጥ ጊዜ ሆነ ከዚያ በኋላ እንደሀገር የነበሩ ጫናዎችን ተቋቁሞ ሀገርን ለማሻገር በጽናት የሰራ መሆኑን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ህጎችን በማርቀቅ የነበረው ድርሻ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
ፓርላማው ሙስናን በመቀነስ ረገድ ያበረከተው ስራ አለው። ትልቅ ልምድ እና ዕውቀት ያለው በመሆኑ ልምዱን በወረዳዎች ድረስ ወስዶ መጠቀም ይገባል። የፓርላማ አባላቱም አብዛኛዎቹ በስድስተኛው ምርጫ ያልተሳተፉ ቢሆኑም ኢትዮጵያ አሸንፋለች በሚል ሰላማዊ ምርጫ በመካሄዱ ደስተኛ መሆናቸው የሚያስመሰግናቸው እንደሆነ አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ ምርጫዎች የምናውቀው ሂደት ነበረው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዛ ሂደት ያለፉት የፓርላማ አባላት ይህን ያክል ጥረት ለሀገራቸው ካደረጉ በሰላማዊነቱ ነጻ በነበረው ምርጫ የሚያልፉ የቀጣዩ ፓርላማ አባላት ደግሞ ከዚህ የበለጠ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በምርጫ ያልተወዳደራችሁ እድለኛ ናችሁ፤ እኔ የሚያስፈራኝ እና ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ድረስ ተሰልፎ የመረጠውን ህዝብ እንዴት ብንሰራ ነው ልንክሰውና ልናገለግል የምንችለው ብዬ ነው የማስበው። በዚህ ረገድ ቀጣዩ ምክር ቤት ትልቅ ሸክም ያለበት እንደሚሆን አመልክተዋል።
እኛም ከዚህ ቀደም የነበረው መንግስት አይነት እንዲኖረን አንፈልግም ያሉት ዶክተር ዐብይ፤ ልክ ምርጫ ቦርድ አሸንፋችኋል ባለን ማግስት በምርጫው የተሳተፉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት በካቢኔ እና በኤጀንሲዎች ውስጥ ገብተው የሚያገለግሉበትን መንገድ እንፈጥራለን ብለዋል።
እንደ ከዚህ ቀደሙ ተቃዋሚ ናችሁና በምርጫ ስለተሸነፋችሁ አታስፈልጉም የሚል አካሄድ አይኖርም። ከየፓርቲዎቹ ያሉ ሰዎች በልማቱ አብረው ይሰራሉ፤ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ሲሆን ደግሞ እየተከራከሩና እየተጨቃጨቁ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ መሄድ ይቻላል የሚል እምነት አለን ብለዋል።
በወዳጆቻቸው ግምገማና ምክር ተሳስተው በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ያልተሳተፉ ፓርቲዎች ግን ለዚህ እድል ለመብቃት ባለመቻላቸው እስከ ቀጣዩ ምርጫ አምስት ዓመት መጠበቅ እንደሚኖርባቸው አስታውቀዋል።
ዶክተር ዐብይ እንደገለጹት፤ በምርጫው ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ አደግን በሚሉና እንደነአሜሪካ ባሉ ሀገራት እንኳን ለምርጫ ከተመዘገበው ሰው የመረጠው ሲነጻጸር በኢትዮጵያ ያለው ቁጥር ይበልጣል። በምርጫው ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ህዝብ እና ለሰራዊቱ ክብር ይገባል። ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ አትሸነፍም። በቀላሉ የማንፈርስ እና የማንንበረከክ መሆናችንን ታሪካችንም ያሳያል።
በእለቱም የምክር ቤቱ አባላት በምርጫው ለተሳተፈው ህዝብ እና ለመከላከያ ሰራዊት በክብር ቆመው ምስጋና አቅርበዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2013