
አስናቀ ፀጋዬ
በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለያዩ ክልሎች ሲገነቡ ዋነኛ ዓላማቸው ለአካባቢው ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር በዘለለ በኢንዱስትሪዎቹ የሚመረቱ ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትና በሀገር ውስጥ የቴኬሎጂ ሽግግር እንዲኖር ማስቻል እንደሆነ ይታመናል። በዚሁ እሳቤ መሰረትም የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ወደ ስራ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ከ 76 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የተለያዩ የስራ አድሎችን መፍጠር እንደቻሉና ከ 610 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንዳስገኙ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
እስካሁን ድረስ በአዳዲሶቹና በነባሮቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለበርካታ ዜጎች የስራ እድሎችን መፍጠር ቢቻልም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በዘንድሮው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ሀገር ከተላኩ ምርቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሬ በተለያዩ ምክንያቶች ዝቅተኛ መሆኑ ተነግሯል።
የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ትንሳኤ ይማም እንደሚናገሩት በተያዘው በጀት ዓመት በፓርኩ ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ 44 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል። በፓርኩ ውስጥ የተሰማሩ ባለሀብቶችም በዋናነት በጨርቃ ጨርቅና በቆዳ ጓንት ምርት ላይ የተሰማሩ ሲሆን የተገኘው የውጭ ምንዛሬም እነዚህ የጨርቃጨርቅና የቆዳ ጓንት ምርቶችን ለአሜሪካና አውሮፓ ገበያ በማቅረብ ነው። ይህ ግኝት ከአምናው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በስምንት ከመቶ ያንሳል። ለዚህ አፈፃፀም ዝቀተኛ መሆንም የኮሮና ወረርሽኝ መባባስና ቀደም ሲል በፓርኩ ውስጥ የነበረና ነግር ግን በአሁኑ ጊዜ ወደ ሞጆ ሄዶ በራሱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የቆዳ ምርቶችን እያመረተ ለአሜሪካን ኩባንያ የሚያቀርብ ፋብሪካ መኖሩ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል።
ይሁንና ኩባንያው ይዞት የነበረውን ፋብሪካ ሌሎች ኩባንያዎች ገብተውበት የኢንስታሌሽን ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ። ይህም በቀጣይ ዓመት የኢንዱስትሪ ፓርኩን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል። ኩባንያው ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ባይለቅ ኖሮ የዝንድሮው አፈፃፀም ከአምናው ጋር ሲታይ ከፍተኛ የመሆን እድል ይኖረው ነበር።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባለፈ ፓርኩ አስካሁን ባለው ሂደት ከ18 ሺህ 69 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል። ይህም ከአምናው የሀምሌ ወር ወዲህ ከነበረው የ 16 ሺ ሰራተኛ የ 2 ሺ ጭማሬ ያሳየ ነው። ከነዚህ ውስጥም 17 ሺህ የሚሆኑት ሠራተኞች ቋሚ ቅጥር ፈጽመዋል። ፓርኩ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል።
በቀጣይም ባለሀብቶች በፓርኩ ውስጥ ገብተው ተጨማሪ ማሽነሪ ተከላ አከናውነው ያለውን ቦታ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ንግግር እየተካሄደ ነው። በአሁኑ ጊዜም የሶስተኛው ዙር የኮሮና ወረርሽኝ ካልጀመረ የውጭ ገበያውም እየተረጋጋና ገበያዎችም እየተከፈቱ በመምጣታቸው የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።
የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ በበኩላቸው እንደሚሉት ፓርኩ ሁሉንም በመንግሥት ወጪ የተገነቡ ሼዶች ለባለሀብቶች አስተላልፏል። ተጨማሪ ሼዶች ደግሞ በግል ባለሀብቶች እየተገነቡ ይገኛሉ። አስካሁንም በመንግስት ከተገነቡ አስራ ዘጠኝ ሼዶች መካከል ስምንቱ ሥራ ጀምረዋል። በሼዶቹ የማምረት ሥራ የጀመሩት ባለሀብቶች ቁጥርም አራት ደርሷል።
ከዘጠኝ ባለሀብቶች ውስጥ በወጪ ንግድ ውስጥ ያሉት ሁለት ሲሆኑ ሌሎቹ ግን የማሽን ተከላና የኢንስታሌሽን ስራ ላይ ይገኛሉ። በሀምሌ ወር መጀመሪያ አካባቢ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ሀገራት ይልካሉ ተብለውም ይጠበቃል።
በዚሁ በጀት ዓመትም በፓርኩ ውስጥ ባሉ ፋብሪካዎች የተመረቱ የጨርቃጨርቅ ምርቶችን ለአውሮፓና ለአሜሪካ ገበያ በማቅረብ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል። ይህም ከአምናው በጀት ዓመት ጋር ሲወዳደር መጠነኛ ቅናሽ አሳይቷል። ለዚህም የኮሮና ወረርሽኝና የውጭ ገበያ መቀዛቀዝና የግዢ ፍላጎት ማጣት ለወጪ ንግድ መቀዛቀዝ የራሱን ሚና ተጫውቷል።
በቀጣይ ቀሪዎቹ ባለሀብቶች ምርቶቻቸውን ወደውጭ ሀገር መላክ ሲጀምሩ እስከ 50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት በእቅድ ተይዟል። በፓርኩ ውስጥ ለመስራት ሼዶችን ተረክበው የስራ ፈቃድ ከወሰዱት መካከልም በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ ቢያንስ 80 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሥራ እንዲገቡ እቅድ ተይዟል።
ፓርኩ እስካሁን ድረስ ለሰባት ሺህ ሠራተኞች የስራ እድል የተፈጠረ ሲሆን፤ አስራ ዘጠኙም ሼዶች ሥራ ሲጀምሩ ከ20 እስከ 25 ሺህ ሠራተኞችን የመቅጠር አቅም ይኖረዋል።
በቀጣይም ከወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ በተለይ ጥሬ እቃዎች በሀገር ውስጥ የሚቀርቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከመንግስትና የግል ሴክተሮች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ.ም