• ስር ነቀል የንባብ አብዮት ያስፈልገናል
ኢትዮጵያ ከፀሀፍት፣ መፃህፍት፣ ንባብ ቤት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የታሪክ ደሀ አይደለችም። የህትመት ታሪካችን ወደኋላ 100 ድህረ ክርስቶስ (AD) ይወስደናል። የፅህፈታችንም ቢሆን ከዚህ ብዙም አይተናነስም። የቤተ-መፃህፍት ታሪካችንም ከየት እንደሚነሳ የታወቀ ነው፤ ከአፄ ቴዎድሮስ መንደር – ከመቅደላ፤ የንባብ ባህላችንም፤ ከፍና ዝቅ እያለም ቢሆን “ወርቃማው ዘመን” በሚል እስከሚታወቀው 1960፣ 70 እና 80ዎቹ ድረስ ከነግርማ ሞገሱ ነበር ያለው።
ኢትዮጵያ ዓለም አይኑን ሳይገልጥ የስልጣኔ እጇን የዘረጋች፤ በመፃፍና በማንበብ (ከድንጋይ ላይ ፅሁፍ ጀምሮ) ችሎታዋ የተመሰከረላት፣ በግእዝ፣ አክሱም፣ አባይ . . . ስልጣኔዋ ያለተወዳዳሪ እስካሁን ያለች (በአሁኑ አያያዝ የወደፊቱ ቢያሰጋም)፣ ገና ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከትርጉም ስራዎች ጋር የተዋወቀች፣ የፀሀፊና ተርጓሚው ዘርአያቆብ አገር . . .(ነበረ)ች።
የዛሬይቱን ኢትዮጵያ በተመለከተ “ከአንባቢው ቁጥር የደራሲው ቁጥር የሚበልጥባት” አገር ይሉ አገላለፅ ከየት መጣ ሲል የሚጠይቅ ካለ መልሱ እዛው ውስጥ ነውና እሱኑ መመርመር ነው። ይህ ሽንቆጣ በኛ ብቻ አይቆምም፤ ድንበሩን ያሰፋና አፍሪካንም የሚጠቀልል ነው። እሱም “ከአፍሪካውያን እይታ ልትደብቀው የምትፈልገው ነገር ካለ መጽሐፍ ውስጥ አስቀምጠው” የሚለው ነው።
የመፃህፍት ነገር ሲነሳ አብረው የሚታሰቡ/ የሚጠራሩ ርእሰ-ጉዳዮች በርካታ ናቸው። አታሚና አሳታሚ፣ የወረቀት ዋጋ ንረት፣ የማሳተሚያው ወጪ ከአቅም በላይ እየሆነ መሄድ፣. . . የመሳሰሉት ተወደደም ተጠላ ተያይዘው የሚመጡ ጉዳዮች ናቸው። የመፃህፍት መደብር፣ ቤተ-መፃህፍት፣ ማከፋፈያዎች፣ የንባብ ማዘወተሪያ ስፍራዎች፣ የንባብ ክበባት. . . ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም። በተለይ በተለይ ስለመፃህፍት ሲነሳ በፍጥነት ወደ አእምሯችን ከተፍ የሚለው አንባቢ፣ የማንበብ ክሂልና የንባብ ባህላችን ነው።
እነዚህን ሁሉ እዚህ ጋ መደርደራችን ያለምክንያት አይደለም፤ እኛ አገር ሁሉም ስር የሰደዱ፣ ፈጣን መፍትሄ የሚጠባበቁ ችግሮች በመሆናቸውና ማስታወሱ ተገቢ ስለሆነ ነው።
ወደርእሰ-ጉዳያችን እንመለስ። ርእሰ-ጉዳያችን ከላይ ከዘረዘርናቸው መካከል አንዱ የሆነው አሳሳቢው የ“ንባብና የንባብ ባህላችን” ጉዳይ ነው።
በመጀመሪያ “የንባብ ባህል” የሚለውን ባጭሩ እንይ። የንባብ ባህል የሚለውን እጅግ ተቆጥበን ስንገልፀው “ልክ እንደማንኛውም ለህይወት አስፈላጊ እንደሆነ መሰረታዊ ጉዳይ ሁሉ ማንበብንም ያለማቋረጥ ልምድ እና ተግባራዊ ማድረግ” ማለት ነው። ይህ ለኛ ለምን አስፈለገ?
ማንበብ ልበ ቀና፤ አንደበተ-ርቱእ ያደርጋል። ማንበብ ሰብአዊ ርህራሄን ያጎናፅፋል፤ ማንበብ ያወያያል፣ ያነጋግራል፣ ያመራምራል። ውስብስቡን ሲፈታ ከባዱን ያቀልላል። ማንበብ “ያስከብራል፤ አገርን ያኮራል”። በንባብ የጎበጠ ይቀናል. . . የሚሉ ምክር አዘል ሃሳቦችን በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናት ገፆችን ገልበጥ ስናደርግ የምናገኛቸው ናቸው።
“እያወቁ በሄዱ መጠን አለማወቅዎን ይረዳሉ” እንዲል ፍልስፍናው፤ ማንበብ የእውቀትን ክፍተት ከመሙላት ባለፈ ተጨማሪ ክፍተት እየፈጠረ መሄዱም ሌላው የንባብ ጥቅም ሲሆን፤ መፍትሄው ክፍተቱን እየደፈኑ መቀጠል ብቻ ነው። እውነት እውነት እላችኋለሁ ማንበብ፣ ማንበብ ዘወትር ማንበብ።
እውቀት ሂደቱ ልክ እንደሰው ልጅ አካላዊ እድገት ነው። እያደግን በሄድን ቁጥር ከጫማ ቁጥራችን ጀምሮ ሁሉ ነገራችን እየጨመረ ይሄዳል። የሚጠይቀንን እያሟላን ካልሄድን በድሮው ጫማ መሄድ አንችልም። በአንድ ጊዜ ንባብ “ሁሉን አወቅ” መሆን አይቻልም እያልን ነው። (ይህንን በውል ለመረዳትና ንባብ ምን ያህል ሙሉ ሰው እንደሚያደርግ ለመገንዘብ በብዙዎቻችን የሚታወቀውንና ከአገራችን ታሪክ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያለውን የእስራኤሉን ንጉስ ሰለሞንን ማስታወስ ይቻላል።)
የተመሰከረላቸው አንባቢያን ካካፈሉን የህይወት ልምድ እንደተረዳነው በንባብ ህይወት ውስጥ ብቸኝነት የለም። ድንቁርና የለም፤ ባይተዋርነት የለም። ባጭሩ እኩይ ተግባራት ሁሉ ተገቢ ቦታቸው ያለማንበብ ህይወት ውስጥ ነው ማለት ነው። ምክንያታዊነት፣ ፍትሀዊነት፣ ተመራማሪነት፣ አሰላሳይነት. . . ሁሉ እዚያ ንባብ መንደር አሉ። የጥሩ ፀሀፊነት መነሻው ጥሩ አንባቢነት እንጂ ሌላ ሆኖ አልተገኘም።
ጥንታውያን ፈላስፎች እንደሚሉት “የሰዎች ክፋት የሚወገደው በትምህርት ነው”። ትምህርት ማለት እውቀት ማለት ነው። ትምህርትም ሆነ እውቀት ደሞ ያለንባብ አይታሰብምና የንባብ ሚናው ቁልፍ መሆኑን በቀላሉ እንረዳለን። በንባብ ሂደት ዓለምን ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ በምናብ መዞሩ ሌላው ሚስጥር ሲሆን፤ ወጥቶ መውረድ፤ ወርዶ መውጣት ሁሉ በሂደቱ ውስጥ መኖሩ በእነዚሁ ጥንታውያን ዘንድ የፀደቀ ነው።
ንባብን ከስነልቦና ጋር በማያያዝ ያጠኑ ምሁራን የሚስማሙበት ዋና ነገር ቢኖር፤ ማህበራዊነትን ያደረጃል፣ አብሮነትን ያጠናክራል ልዩነትን ያከብራል፣ የመዋቅራዊ አደረጃጀትን ምንነት ያስገነዝባል የሚለው ነው፤(ዝርዝሩ በ“The Psychology Of Reading” ውስጥ በስፋት ይገኛል)። የቋንቋ ምሁራን በበኩላቸው ማንበብ አእምሮአዊ ችሎታን – የመገንዘብ፣ የመረዳት፣ የመተርጎም፣ የመተንተን፣ አስተያየት የመስጠት፣ የማብራራት፣ ስነ-ፅሁፋዊ ስራዎችን የማጣጣም – ለማዳበር ፍቱን መድሀኒት ነው ሲሉ ያዳብሩታል። ንባብ ተግባቦትን ማዳበሩና ያለፉ ዘመናትን ሁነቶች በቀላሉ ለመረዳት ማስቻሉ ሌላው ከንባብ የሚገኝ ግዙፍ ትርፍ መሆኑ በፈላስፋው ማክስ ዌበር እና ሌሎችም ዘንድ ተገቢ ቦታ አለው።
መፃህፍት በሮች ናቸው። መውጣት መግባት ይቻላል፤ መፃህፍት መስኮቶች ናቸው ማያ – መመልከቻዎች፤ መፃህፍት ጥሩ ጓደኛ፣ ብልህ መካሪ ናቸው። በመፃህፍት ታሪክ አለ፤ በመፃህፍት ፍልስፍና አለ፤ በመፃህፍት እምነት አለ፤ ሀሳብ አለ፤ የካበተ ልምድ አለ። ሀቁ ይህ ከሆነ በአገራችን ያለውን የመፃህፍትና የአንባቢ ቁርኝት በተመለከተ የሚመለከታቸው ምን እንደሚሉ እንከታተል።
ከማንበብ ይህ ሁሉ ከተገኘ ካለማንበብስ ምን ይቀራል? ይህ በራስ ለራስ የሚቀርብ ጥያቄ ነው።
እዚህ ላይ ከሁሉም ቀዳሚ በማድረግ “ለኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ ትርጉም ያበረከተው አስተዋፅኦ” (2013) በሚል ርእስ በPEN ኢትዮጵያ የተዘጋጀውንና የበርካታ ምሁራንን የምርምር ስራዎች የያዘውን ጥራዝ እንመልከት። በጥራዙ በርካታ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ስነፅሁፋዊ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን አንዱ ንባብና የንባብ ባህላችን ነው።
በዚሁ ህትመት ላይ ባሉት ጥናታዊ ፅሁፎች ውስጥ ከሰፈሩት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፤ “የአንባቢ ቁጥር እየቀነሰ ነውና መፍትሄ ሊፈለግበት ይገባል፤ የአሁኑ ትውልድ ለመፃፍም ሆነ ለማንበብ ፈቃደኛ አይደለምና ልንወያይበት ይገባል፤ የአሁን ጊዜ መምህራን ተማሪዎቻቸውን ለንባብ አያበረታቱም፤ ዘመኑ የግሎባላይዜሽን እንደመሆኑ መጠን ማንበብ ግድ ሆኖ ሳለ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው። በ70ዎቹ እና በ80ዎቹ ከፍተኛ አንባቢ ስለነበር ብዙ መፃህፍት ይሸጡ ነበር። ይህም ደራሲያንን ስለሚያበረታታ ብዙዎች ይፅፉ ነበር። ኢንተርኔትና ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ንባብን እየተገዳደሩት ነው። አንድ አባት ለልጆቹ መፅሀፍ ገዝቶ ከሚገባ በሀያ ብር ሙዝ ገዝቶ ቢገባ ይመርጣልና ልጆቹ እንደምን አንባቢ ይሁኑ?. . . “ እና ሌሎችም በርካታ አስተያየቶች የሚገኙ ሲሆን ከሁሉም የጠነከረው ግን የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ አስተያየት ነው። “በታሪክ የንባብ ባህል እንዳሁኑ የወደቀበትን ጊዜ አይቼ አላውቅም” የሚለው።
ከእነዚህ በጥናት ከተደገፉ የበርካታ ምሁራን አስተያየቶች የምንረዳው አቢይ ጉዳይ ቢኖር በሀገራችን “የንባብ አብዮት” ማስፈለጉን ነው።
በዚህ ብቻም አያበቃም፤ የንባብ መሰረቱ ይጣልባቸዋል ተብለው የሚጠበቁት ትምህርት ቤቶች በተገላቢጦሽ ሲታሙ እየሰማን ነው። በተለይ “ከ67 በመቶ በላይ ከ1 – 4ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ማንበብና መፃፍ አይችሉም” ከሚሉት ከመንግስት የወጡ ጥናቶች ጀምረን ዋናውን ጉዳይ ጥለን ፊደል እያስቆጠርን ነው እስከሚሉት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ድረስ ስንሄድ፤ የችግሩ አሳሳቢነት “የንባብ አብዮት ያስፈልጋል” ወደሚለው ጥግ በጋራ እንድንሄድ ያስገድደናል።
ሌላው ብዙዎቻችንን የሚያስገርም ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥሩ ሃምሳ ሚሊዮን ባልሞላበት፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሁለት ብቻ ናቸው በተባለበት፣ ማተሚያ ቤቶቻችን (ስንት ነበሩ?)፣ ሳንሱር ፀሀፍትን ቀፍድዶ በያዘበት . . . በዚያ ዘመን ከነበረው የበሳል ፀሀፍትና የአንባቢ ቁጥር፤ ዛሬ – የህዝብ ቁጥራችን ከመቶ ሚሊዮን በዘለለባት፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችን (የመንግስትን ብቻ ወስደን ማለት ነው) ከሃምሳ በላይ በሆኑባት፣ በየአመቱ መቶ ሺህዎች በሚመረቁባት፣ ሰላሳ ሚሊዮን አካባቢ ወጣቶች ትምህርት ቤት በሚገኙባት . . . ኢትዮጵያ “ከአንባቢው ቁጥር የደራሲው የበለጠባት” መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ የመፃህፍት ህትመት ቁጥር ወርዶ፤ ወርዶ ወርዶ ከሁለት እስከ ሶስት ሺህ መድረሱ ነው። እውነትም ለሰሚው ግራ።
ይህ የንባብ አብዮት በቻይና (ባታውጀውም) ተግባራዊ ተደርጓል። ለዚህም ማስረጃው ይጠቅሙኛል፤ ለተያያዝኩት እቅድና ፕሮግራም ይበጁኛል ያለቻቸውን መፃህፍት ሁሉ ከዓለም ዙሪያ በመሰብሰብና በመተርጎም ለዜጎቿ የማንበብ እድል መፍጠሯና ዜጎች አእምሮታዊ ለውጥ እንዲያመጡ ማድረጓ ነው። (በነገራችን ላይ ቻይና የጀርመናዊው ፈላስፋ ዊልሄልም ፍሬደሪክ ሄግልን (1770-1831) ስራዎች/ቅፆች ወደ ማንድሪን በመተርጎም ላይ መሆኗን ያለፈው አመት “China Daily” ጋዜጣ እትም አስነብቧል።)
“የንባብ አብዮት”ን ፅንሰ-ሀሳብ የበለጠ ለመረዳት በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶችን፤ በተለይም ብዙዎች የፅንሰ-ሀሳቡ ባለቤት ነው የሚሉትን የ“Steven Lagerfeld”ን THE READING REVOLUTION ማንበብ (በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በስልጣኔ ቀደምት ለሆኑ አገራት) ጠቃሚ ነው እንላለን።
በእርግጥ በእኛ አገር የንባብ ባህላችንን ለማስቀጠል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ይታወቃል። ዓመት ጠብቀውም ቢሆን “ኢትዮጵያ ታንብብ”ን የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች አሉ። እዚህም እዚያም እንደ “ፖይቲክ ጃዝ” (በስያሜና ትርጉሙ ሁላችንም ስለመስማማታችን እርግጠኛ አይደለሁም) የምሽት የንባብ ስብስቦች ይደመጣሉ። “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል”ን በኤፍኤም ሬዲዮኖችና ሌሎችም አካባቢዎች ይሰማል። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኩልም “እየጣርኩ ነው” የሚል አልፎ አልፎ የሚሰማ ቀጭን ድምፅ አለ። እነሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ፣ ጎተ ኢንስቲትዩት እና የመሳሰሉትም እንቅስቃሴያቸው አልተቋረጠም። ይሁን እንጂ፤ እንኳን ባልዋሉባቸው በክልሎች ይቅርና በተቀመጡበት በአዲስ አበባም ለውጥ ስለማምጣታቸው እርግጠኞች አይደለንም። እነሱም አይደሉም።
ማጠቃለያ
የተጠቀሱትም ሆኑ ሌሎች እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው። ይህን እንጂ አብዛኞቻችን መስማት የምንፈልገውና እየጠበቅንም ያለነው አንድ ወፍራም ድምፅ አለ – የትምህርት ሚኒስቴር ድምፅ። በየትኛውም አገር፣ ተቋም፣ አካል፣ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም ሆነ እኛም እንደምናውቀው የንባብ መሰረቱ የሚጣለው በት/ቤት ነው። ከመዋእለ-ህፃናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ደረጃ ድረስ ያሉ የትምህርት ተቋማት የንባብ ባህልን ከማስረፅ አኳያ የመጀመሪያውን ከባድ ኃላፊነት የሚወስዱት እነሱ ናቸው። እውነታው ግን እሱን አያሳይም። ከፖሊሲው ጀምሮ እስከመምህራን ድረስ እየተወቀሱበት ነው። በመሆኑም፤ ሁኔታው የንባብ አብዮት ማስነሳትን ግድ እያለ ነው። ለዚህም ነው በሌሎች፤ ጉዳዩ እንደኛ አሳሳቢ በሆነባቸው አገራት ኃላፊነቱ እስከግለሰብ ደረጃ ወርዶ ተቆርቋሪዎች በዜጎች ላይ የንባብ ፍቅር እንዲያድርባቸው ማድረግ የሚያስችል ፕሮፖዛል (Love of Reading Project; Love of Reading Legacy Project (የነበራቸውን የንባብ ባህል ለማስቀጠል); Developing Student Reading Skills Proposal; Project Proposal for Non Readers እና የመሳሰሉትን) ቀርፀው የገንዘብ ድጋፍ ፍለጋ ሲንከራተቱ የሚስተዋለው፤ ባለሀብቶቹም ድጋፋቸው አልተቋረጠም። እኛም ዘንድ ከድጡ ወደ ማጡም እንበለው ከእሳቱ ወደ ረመጡ የዚሁ አይነት ስራ ሊሰራ ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
ግርማ መንግሥቴ