የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኑሴፍ) እ.ኤ.አ በ2020 ሪፖርቱ በመላው ዓለም 152 ሚሊዮን ልጆች ለጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸውን ገልፇል። ይህ ቁጥር ካለፉት አራት ዓመታት ጋር ሲነፃጸር በ8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ጭማሪ አለው ።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ኮቪድ- 19 መቀስቀሱን ተከትሎ 9 ሚሊዮን ተጨማሪ ልጆች ለጉልበት ብዝበዛ ተጋልጠዋል። እንደ ዩኒሴፍ ሪፖርት እድሜያቸው ከ5-17 ባሉ ልጆች መካከል ግማሹ ለከባድ ስራ በመገደዳቸው የጤናቸው፣ የደህንነታቸው እና የአስተሳሰብ እድገታቸው አደጋ ላይ ወድቋል።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በአፍሪካ ከአምስት ልጆች አንዱ ለጉልበት ብዝበዛ ይጋለጣል። በተለይም በአህጉሩ የጦርነት እና የግጭት ቀጠናዎች ስለሚበዙ ችግሩም ይባባሳል።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ከዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት ጋር በጋራ ባቀረቡት የ2015 ሪፖርት በኢትዮጵያ የልጆች ጉልበት ብዝበዛ 42 ነጥብ 7 በመቶ ደርሷል።
ልጆች በአካልም ሆነ በአእምሮ ብስለት ያልዳበሩ በመሆናቸው ለጥቃት የተጋለጡ ናቸው። በተለይም የልጆች ጉልበት ብዝበዛ በስውርም ሊፈጸም ይችላል። የልጆች የጉልበት ብዝበዛ አይነቶችን በዋናነት በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን። የመጀመሪያው የቤት ውስጥ የጉልበት ብዝበዛ፣ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ባርነት ወይንም የግዴታ ስራ ነው።
በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ የልጆች ጉልበት ብዝበዛዎች በአብዛኛው ከማህበረሰቡም ሆነ ከመንግስታዊ አካላት እይታ የተሰወሩና በግልጽ የማይከናወኑ በመሆናቸው የልጆች ስቃይ በጣም የከፋ ነው። በዚህም የተነሳ በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች የችግሩ መኖር እንኳን ሳይታወቅ ታፍኖ ይኖራል።
ሁለተኛው አይነት የልጆች ጉልበት ብዝበዛ ደግሞ የባርነት ወይም የግዴታ ስራ ነው። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ልጆች በአስገዳጅ ሁኔታ የጉልበት ብዝበዛ ይካሄድባቸዋል። እነዚህ ልጆች በአብዛኛው ከብድር እዳ፣ ባርነት እና ከፆታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ ነው። ይህ የጉልበት ብዝበዛ ልጆች ሳያውቁት በገንዘብ ለስራ ይሸጣሉ።
በሌላ በኩል ልጆች የወላጆቻቸው እዳ መያዣ ሊሆኑ ይችላሉ። ይኸውም የልጆች ወላጆች ያለባቸውን እዳ መክፈል ሲያቅታቸው ልጃቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ። በዚህ ሁኔታ ልጆች ከአቅማቸው በላይ ምንም አይነት ትምህርትም ሆነ እንክብካቤ ሳያገኙ እንደ ባሪያ ይሰራሉ። በልጆች ጉልበት ብዝበዛ የተጋለጡት አብዛኛውን ጊዜ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ደላሎች አማካኝነት ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከገጠር ወደ ከተማ እንዲኮበልሉ የተደረጉ ናቸው።
የልጆች ጉልበት ብዝበዛ መንስኤ ከሚባሉት መካከል በዋናነት ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የትምህርት እድል እጦት፣ ጦርነት እና ግጭትና የመሳሰሉት ተረጠቃሽ ናቸው። የልጆች ጉልበት ብዝበዛ ለከፍተኛ አካላዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊ ወዘተ ጉዳቶች ያጋልጣል። ለብዝበዛ ሰለባ የሆኑ ልጆች ከቀላል የአካል ጉዳት እስከሞት ሊጋለጡ ይችላሉ።
ለአብነትም አካላዊ ቁስለት፣ መድማት፣ መቃጠል አልያም እድሜ ልክ ለማይሽር አካላዊ ጉዳት መዳረግና ሌሎችም ይገኝበታል።
እነዚህ ልጆች የፍርሃት፣ የብቸኝነት፣ ራስን የመጥላትና ተስፋ ቢስነት ስሜት ይሰማቸውል። በራስ የመተማመን ስሜታቸው ይሸረሸራል። በማህበራዊ መስተጋብራቸው ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። እነዚህ ተደራራቢ ችግሮች ደግሞ ለአደንዛዥ እፆችና ለተለያ ዩሱሶች እንዲያጋለጡ ያደርጋቸዋል።
በመሆኑም ልጆች ገና በጨቅላ እድሜያቸው የሚደርስባቸውን የጉልበት ብዝበዛ ለመከላከል ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል። በተለይም ቤተሰብ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በምንም እና በማንም የማይተኩ ልጆቻችንን ልንከባከባቸው፣ ልንጠብቃቸው እና ልናበረታታቸው ይገባል። በልጆች ጉልበት ብዝበዛ ዙርያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲኖሩም ይመከራል። ከመንግስት በኩል ጠንካራ ህግ ማጽደቅ እና ለተፈፃሚነቱ መትጋት ይጠበቃል። የሲቪክ ማህበረሰብ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና መገናኛ ብዙሃን በልጆች ጉልበት ብዝበዛ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል።
ሰላማችሁ ይብዛ ።
ብርሃኑ በላቸው አሰፋ
(birhanubasefa@gmail.com)
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2013