የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጽጥታው ምክር ቤት አርብ ምሽት በትግራይ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያውን ይፋዊ ውይይት አድርጓል። በዚህ ውይይት ላይም በተመድ የኢትዮጵያ ልኡክ የሆኑት አንጋፋው ዲፕሎማት ታዬ አጽቀስላሴ የመንግስታቸውን አቋም ያስረዱ ሲሆን 10 ደቂቃ የፈጀውን የአምባሳደሩን የእንግሊዝኛ ንግግር በዚህ መልኩ ወደ አማርኛ መልሰነዋል።
ክቡር ፕሬዚዳንት ፤ በመጀመሪያ የጸጥታው ምክር ቤት የፕሬዚዳንትነት ወንበርን ለወሩ ስለተረከቡ እንኳን ደስ አለዎት ለማለት እወዳለሁ። እኔና የምመራው የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ሙሉ ድጋፉን እንደሚሰጥዎትም ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ።
ክቡር ፕሬዚደንት ፤ ሀገሬ በአሁኑ ወቅት ውስጣዊ ጉዳዮቿን በጥንቃቄ እና አውድን ባገናዘበ መንገድ እየተቆጣጠረች የምታስኬደው ሽግግር እያከናወነች ይገኛል። ከጸጥታው ምክር ቤት አባላት ጋር ባደረግነው የሁለትዮሽ ውይይት እና ባለፈው ወር ከምክር ቤቱ ጋር ባደረግነው መደበኛ ያልሆነ ውይይት ምልከታዎችን እና ሃሳቦችን የተለዋወጥን ሲሆን እነዚህን ሃሳቦች የኢትዮጵያ መንግስት ገንቢ በሆነ መልኩ ወስዶ እየተገበረ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህን ይፋዊ ስብሰባ ለመጥራት በምክንያትነት በተጠቀሱት ጉዳዮች እንደተገረምኩ መግለጽ እወዳለሁ። እኛ ይህ ምክር ቤት ለዓለም ሰላም ያለበትን ሃላፊነት እንገነዘባለን። ይህን የተከበረ ሃላፊነት ለማሳካት ደግሞ ሁነኛው መንገድ በገንቢ ግንኙነት ውይይትን ማበረታታት እና ውጥረትን ማብረድ ነው። ይህ ስብሰባ የተጠራው የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት ለማስከበር እና በህግ ማስከበር ዘመቻው ጉዳት የደረሰባቸውን ለማገዝ ትልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔ በወሰደበት ወቅት ነው። እነዚህ እርምጃዎች ወዳጆቻችን ድጋፍ እንዲያደርጉ እና ጠቃሚ ያልሆነውን ጫና እንዲያቆሙ ሊያደርግ ይገባ ነበር። በዚሁ አጋጣሚ ለሰላም ላሳየነው ተነሳሽነት ድጋፍ ለሰጣችሁ ለሁላችሁም ምስጋና ልናቀርብ እንወዳለን።
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ምክር ቤቱ በሰብአዊ እርዳታ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ስብሰባ ካካሄደ በኋላ ብዙ እውቅና ሊሰጣቸው የሚገቡ ለውጦች ኢትዮጵያ እንዳካሄደች ሊታወቅ ይገባል። ሰኔ 21/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚያደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆም አድርጓል።
ይህ ለሰብአዊ ጉዳዮች ሲባል የተወሰነ ውሳኔ ሲወሰን ከብዙ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል። ይህ አስተዋይነት የተላበሰ ትልቅ ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግሰት ለትግራይ ህዝብ ሲል በታገሰው ነገር ግን ሃላፊነት በማይሰማው የህወሓት ቡድን ተግባር እንደማይበላሽም ተስፋ አለን። የወታደራዊው እንቅስቃሴ መቆም በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ስራ እንዲጠናከር እንደሚያግዝም ተስፋ አለን። ሁሉን አካታች ለሆነ ሀገራዊ ውይይት በር እንደሚከፍትም እምነታችን ነው።
ህገወጡ የህወሓት ቡድን አጀንዳውን ለማስቀጠል እና ጥቂት አመራሮቹን ለማዳን ሲል ህጻናት እና ወጣቶችን ከሰለጠነ ጦር ጋር እንዲዋጉ ለማድረግ እየመለመለ ነው። በዚህም መልኩ የትግራይ ህዝብ ላልተዘጋጀበት ጦርነት እንዲጋለጥ አድርጎታል። በተጨማሪም ይህ የግብርና ስራ የሚከናወንበት ወቅትም እንዲታወክ አድርጎታል።
የቡድኑ ብሄርን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ ብዙሃን ከገዛ ሀገራቸው ዜጎች ጋር እንዲጋጩ ምልልሶች አሁን ያለ ገደብ ለሚከናወን ሰብአዊ እርዳታ እና ለወቅታዊው የግብርና ስራ አመቺ ሁኔታ ፈጥረናል ብለን እናምናለን። በተጨማሪም በመላው ትግራይ ከሚገኙ የእርዳታ መጋዘኖቻችን ምግብ እና ምግብ ያልሆኑ እርዳታዎችን ማከፋፈል እንቀጥላለን። ብሄራዊ የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን እንዲሁም ሌሎች አምስት ኤጀንሲዎችም አገልግሎታቸውን በሁሉም ወረዳዎች ለመቀጠል ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከአዲሱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተገናዘበ መልኩ የሰብአዊ ስራዎች መመሪያ እና የቅንጅት አሰራሮችን ለማስተካከል በሂደት ላይ እንገኛለን። የህዝብ አገልግሎትን በተመለከተም የአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ እና የሰራተኞቻቸው ደህንነት እንደተረጋገጠ ስራ የሚቀጥሉ ይሆናል።
ክቡር ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያ አሁንም ባለፈው ህዳር ወር የመከላከያ ሰራዊታችን የደረሰበትን ጥቃት ተከትሎ የተፈጠሩ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ ክፍተቶች የማስተካከል ግዴታ ውስጥ ትገኛለች። አጣዳፊው የቤት ስራ ደግሞ በእጅጉ ተፈላጊ የሆነውን ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረግ ስራ ነው።
በዚህም በኩል መንግስት ያለውን እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ ያለውን የመጨረሻ አቅም በሙሉ ይጠቀማል። በፈሪው የህወሓት ቡድን ታክቲክ ምክንያት በተፈጠረው ችግር ተጎጂ የሆኑ የትግራይ ወገኖቻችንን አስመልክቶ ወዳጆቻችን ያሳዩትን መጨነቅ እናደንቃለን። ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስቃይ ተቀባይነት ያለው እንዳልሆነ ነው።
ይህን ለማስቀረት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ያለ እጥረትም መንግስት በቀላሉ የሚያየው አይደለም። በተመሳሳይ መልኩ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖርን ተጠያቂነት እና ችግሩን በማከም በኩል ያለብንን ሃላፊነት በቀላሉ አናየውም። የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፤ የመንግስቴን ይህን ሃላፊነት ለመወጣት ያለ ቁርጠኝነት ግልጽ ማድረግ እወዳለሁ።
አሁን በገጠመን የጸጥታ ችግር ውስጥ አስተዋጽኦ ያደረጉ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ጉዳዮች እንዳሉ እርግጥ ነው። ውጫዊው የደህንነት ስጋታችን እኛ ተጠያቂ ልንሆንበት በማንችለው ትንኮሳ ምክንያት የተፈጠረ እና ውስጣዊ ሰላማችንን እያወሳሰበ እና ከቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ እንዳናተኩር እያደረገ ያለ ጉዳይ ነው። ምክር ቤቱም ይህን ውጫዊ አደጋ ግንዛቤ ውስጥ እንዲያስገባ ጥሪ አቀርባለሁ።
ክቡር ፕሬዚዳንት በዚህ ወር እጅግ ስኬታማ ምርጫ ካደረግን በኋላ አሁን ትኩረታችን አንድነቷ የተጠበቀ ፤ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሀገር ወደመገንባት ዞሯል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ መንግስትም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚረዳ ብሄራዊ ውይይት ለማድረግ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ ይገኛል። መንግስቴ ለሰብአዊ መብት እና በትግራይ ክልል ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት ለማስፈን ያለውን ቁርጠኝነትም እንዲሁ ይፋ ማድረግ እወዳለሁ። ከተጠያቂነት ማምለጥንም እንደማንታገስ ላረጋግጥ እወዳለሁ።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ተግዳሮት ለመወጣት ከበቂም በላይ አቅም እንዳለው ግንዛቤ በመያዝ ከአጋሮቻችን ጋር ለመስራትም ቁርጠኛ ነን። የዚህ ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ መንግስት ለሚያደርገው የተኩስ አቁም ስምምነት ገንቢ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን። አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ላደረጉት ድጋፍም ላመሰግን እወዳለሁ።
በተቃራኒው ግልጽ ማድረግ የምወደው በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ፖለቲካዊ ጫና እና አደገኛ የሆነ ተጋፊ እርምጃዎች ተቀባይነት የሌላቸው እና ከዓለም አቅፍ ህጎች የወጡ መሆኑን ነው። ከልክ ያለፈ ጫና ይህቺን ጥንታዊት እና የ 110 ሚሊዮን ህዝቦች ሀገር መመለሻ ወደሌለው ጫፍ ይመራታል።
የኢትዮጵያ ህዝብ እያየ ነው። ለኢትዮጵያ ይህ ወቅት ወደ ውስጥ የምንመለከትበት እና እውነተኛ በሆነ መልኩ ስኬቶቻችንን እና ተግዳሮቶቻችንን የምንገመግምበት ወቅት ነው። ዋናው ጉዳይም ቁስሎቻችንን እንዴት እንጠግናለን የሚለው ነው። በህወሓት ወጣት ቡድን የተፈጸመው የማይካድራው ጭፍጨፋ ፤ባለፉት 30 ዓመታት ከቀደምቶቻቸው ምድር የተፈናቀሉት የወልቃይት እና ጠገዴ ህዝብ ስቃይ እና መሰል ያላለቁ ኀዘኖች አሉ። ስለዚህም ትክክለኛ መቋጫ ያስፈልጋል። ከቅጣት ነጻ የመሆን ፖለቲካው ባህሉ መቋጨትን ይፈልጋል።
እንደ ሀገር አንድ ያደረገን ነገር ተግዳሮቶቻችንን መጋፈጥ እና ማለፍ መቻላችን ነው። ከፍ የሚደርግንም ህዝባችነ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ነው። ድሃ ልንሆን እንችላለን ፤ ነገር ግን ተስፋ አለን። እኛ የምንወዳቸው የጋራ እሴቶች ያሉን ህዝብ ነን። የኢትዮጵያ ተስፋ አሁንም አለ።
ለማጠቃለል የምክር ቤቱ አባላት በሀገሬ ያለውን ሁኔታ በትክክለኛው መነጽር እንደሚያዩት፤ የገጠመንንም ተግዳሮት ግዝፈት እንደሚረዱት እና የወሰድናቸውን ጠቃሚ እርምጃዎች እውቅና እንደሚሰጡ ተስፋ አለን።
በአሁኑ ወቅት ከኣለም አቀፉ ማህበረሰብ የምንፈልገው ነገር ድጋፍ ፤ ትክክለኛ ግንዛቤ እና ወዳጃዊ ትብብር ነው። ለዚያም ነው ንግግሬን ዓለም አቀፍ ወዳጆቻችን በመላው ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ በማድረግ የማጠናቅቀው።
አመሰግናለሁ ክቡር ፕሬዚደንት!
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2013