አብዛኛውን ዕድሜያቸውን ያሳለፉት በፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ረዘም ላሉ ዓመታት በማገልገል ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ፖለቲከኞችም አንዱ ናቸው። ከአርባ ዓመታት በፊት ኦነግን ከመመስረት እስከ መምራት ድረስ ያገለገሉም ናቸው። ከዚህ ባሻገር በመሬት ስርዓቱ ዙሪያ ለአገር ብርቱ ሥራ የሠሩና የመሬት አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆን ካደረጉ መካከል ይጠቀሳሉ።
በተመሳሳይ በሽግግሩ ወቅት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትርም ነበሩ። ከአገር ባሻገር ደግሞ በውጭው ዓለም እንደ ኦክስፎርድ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ላይም ቢሆን በምርምር ከተሳተፉ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው። ይሁን እንጂ አብዛኛው ህይወታቸው የሚያጠነጥነው የፖለቲካና ማህበራዊ ፍትህ ላይ በሠሩት ሥራቸው ነው። እናም በእነዚህ ዓመታት የነበራቸውን የህይወት ጉዞ ያስቃኙንና ልምዳቸውን ያጋሩን ዘንድ ለዛሬ የ‹‹ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል። መልካም ቆይታ።
ታሪክ አፍቃሪው ልጅ
የተወለዱት ልምላሜን ከክረምት እስከ በጋ በያዘችው፣ ነፋሻማው አየር ምግብ በሆነባት ጫካዋ ምድር ኢሉአባቡራ ውስጥ ከጎሬ ከተማ ወደ 18 ኪሎሜትር ተጉዘን በምናገኛት ጉመሮ በተባለች ልዩ ስፋራ ነው። በዚህች ስፍራ ዕድሜያቸው ለትምህርት እስኪደርስ ማለትም እስከ ሰባት ዓመታቸው ድረስ የልጅነት ጊዜያቸውን አጣጥመውባታል። በተለይም ቤተሰባቸው በግብርና ሙያ ላይ ኑሯቸውን መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው በዚያ ልምላሜ ላይ ከከብቶቹ እኩል እየቦረቁ ከብት በመጠበቅ አሳልፈዋል። መላላክና ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችንም በማከናወን ቤተሰብ ያግዙ ነበር።
እንግዳችን በልጅነታቸው በጣም የሚወዱት ነገር ታሪክና ተረቶችን ከአባታቸው እግር ሥር ቁጭ ብሎ መስማት ነው። እርሳቸው ባይኖሩ እንኳን ሌሎች ትልልቅ ሰዎች ሳይነግሯቸው አይውሉምና ይህንን ጊዜ በጉጉት ይጠብቁት እንደነበር ያስታውሳሉ። ምኔ በመሸም የሚሉበት ጊዜ ብዙ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚያ ውጪ ትምህርትቤት ሲሆኑ ኳስ መጫወት፤ በሰፈር አካባቢ ከሆኑ ደግሞ ባህላዊ ጨዋታዎችን መጫወት ያዘወትራሉ። በጣም ወደውትም እንደሚጫወቱት ያወሳሉ። በተለይም የገና ጨዋታና ጌንቦን የመሳሰሉትን በብዛት እንደሚጫወቱም ነግረውናል።
እንግዳችን ትምህርትቤት ከገቡ በኋላም ቢሆን የተለያዩ ግልጋሎቶችን ለሚኖሩባቸው ሰዎች ይሰጡ ነበር። በእርግጥ መጀመሪያ የገቡበት ዘመዳቸው የባንክ ሠራተኛ በመሆናቸው ለትምህርታቸው ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ያውቃሉና ጫና አይፈጥሩባቸውም። እንደውም ማረፍ ሲፈልጉ ብቻ አንዳንድ ነገሮችን እንዲያደርጉ ያበረታቷቸዋል። በማስጠናቱም ቢሆን በደንብ ነበር የሚያግዟቸው። ይሁን እንጂ ይህ ተንከባካቢያቸው ሰው እስከ አራተኛ ክፍል ካስተማራቸው በኋላ በሥራ ሌላ ቦታ ተቀይሮ ሄደ። በዚህን ጊዜ ሌላ ቤት ገብተው መማር ስላለባቸው ዘመድ ባይሆንም ያግዛቸዋል ተብሎ በሚታሰብ ሰው ቤት ውስጥ ገቡ። በዚህ ቤት ግን ከእስከዛሬው የተለየ ነገር ገጠማቸው። ይህም ያለዕረፍት የሚሠሩበት እንደነበር አይረሱትም።
ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለው የልጅነት ጊዜያቸው ተማሪ ሳይሆን ሠራተኛ ሆነው ያለፉበት እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር ዲማ፤ ቤተሰባቸውን ከሚያገለግሉት በላይ በአልጠነከረ የልጅነት ጉልበታቸው የማይሠሩት ሥራ አልነበረም። ይህ ሳይበቃቸው የተሰጣቸውን ሥራ ሳይጨርሱ እንኳን ትምህርትቤት እንዳይሄዱ ያደርጋቸው ነበር። ትምህርት ቤትም ብዙ ጊዜ አርፍደው ነው የሚገቡት። በተለይ የሚቆጫቸው ደግሞ ቤተሰብ ልጄን እያስተማረልኝ ነው በማለት ሁልጊዜ ማሩ፣ ቅቤው ፣ በግና ፍየሉ ለሰውዬው መጉረፉ ነው። ስለዚህም ጉልበታቸውም የቤተሰብ ሀብትም ዋጋ ሳይኖረው መጥፋቱ ከቤት እስኪወጡና በራሳቸው ተከራይተው እስኪኖሩ ድረስ ያናድዳቸው እንደነበርም አይረሱትም። ከዚያ ውጪ ልጅነት ወርቅ የነበረበትና ለዛሬ ማንነቴ መሰረት የጣልኩበት ስለነበር መቼም የማልረሳውና ዛሬም ተመልሶ ቢመጣ የምለው ጊዜ ነው ይላሉ።
ከጎሬ እስከ አሜሪካ በትምህርት
ዶክተር ዲማ ከዘመናዊ ትምህርት ጋር የተዋወቁት በጎሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት ሲሆን፤ በትምህርት ቤቱ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለውበታል። በእርግጥ ይህም ቢሆን በዕድላቸው ምክንያት ያገኙት ነው። ምክንያቱም መጀመሪያ እነርሱ በገቡበት ጊዜ በአካባቢው የነበረው ትምህርትቤት እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ የሚያስተምር ነው። እናም ለቀጣዩ ትምህርት ሌላ ቦታ ይሄዱ ነበር። ሆኖም ዕድል ቀናቸውና ቀጣዮቹ ትምህርትቤቶች ደረጃ በደረጃ መሠራትና ትምህርት መስጠት ጀመሩ። እነርሱም በዚያው ቀርተው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ ሆኑ። 12ኛ ክፍልን በ10 ዓመት ውስጥ ያጠናቀቁት ባለታሪካችን፤ ሁለቱን ክፍሎች ማለትም ሦስተኛንና አምስተኛ ክፍልን ብዙም ሳይማሩ ደብል በመምታታቸው የተነሳ ሁለት ዓመት ቆጥበው ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል።
ዶክተር ዲማ በትምህርትቤት ቆይታቸው በተለይም ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በሚማሩበት ጊዜ የሥራ ጫና ነበረባቸውና ያረፍዳሉ፤ ይቀራሉም። ነገር ግን በትምህርታቸው ጎበዝ ነበሩ። ለዚህ ያገዛቸው ደግሞ የእርሳቸው ትጋት እንዳለ ሆኖ መምህራኑ በሁሉም ነገር ማገዛቸው ነው። ፈተና ሳይቀር ዳግም የሚፈተኑበትን ዕድል ይሰጧቸዋል፣ ያለፋቸውን ትምህርትም ያስጠኗቸዋል። ይህ ደግሞ በከባድ ፈተና ውስጥ ቢሆኑ እንኳን ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ያበረታቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ሌላው ከተማሪነት ህይወታቸው ጋር ተያይዞ የማይረሷቸው ለማጥናት ከመብራት ጋር የሚያደርጉት ግብ ግብ ነው። በአካባቢው መብራት አገልግሎት የሚሰጠው በዛ ሲባል ለስድስት ሰዓት ነው። መብራት ያላስገባውም ብዙ ነው። እናም የመንገዱ መብራት እስኪጠፋ ድረስ ውጪ ሆነው የሚያነቡበትን ጊዜ መቼም አይረሱትም። ከዚያ የተረፈውን ደግሞ ኩራዛቸውን ለኩሰው የቻሉትን ያህል ማንበባቸው ለዛሬ እንዳበቃቸውም ያነሳሉ።
ብዙ ተማሪ መምህር መሆንን ይመኝ ነበር። እኔ ግን ይህንን አልፈለኩም ያሉን ዶክተር ዲማ፤ ከ10ኛ ክፍል በኋላ ብዙዎቹ ተማሪዎች ተግባረዕድና መምህራን ኮሌጆች ሲገቡ 11ኛ ክፍል ላይ ደግሞ ምንም እንኳን በዕደ ማርያም ትምህርትቤት የሚገቡት ጎበዞች ቢሆኑም ከትምህርት በኋላ መምህር የመሆን ዕድል እዳላቸው ስለገመቱ ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውን አላስተጓጎሉም ነበር። እንደውም የተለየ የትምህርት መስክ ለማጥናት ፍላጎታቸውን አጠነከሩ። ሳያቆራርጡም የ12ኛ ክፍል ትምህርቱንም ጨረሱ። ይሁን እንጂ እንዳሰቡት በቀጥታ ዩኒቨርሲቲ መግባት አልቻሉም ነበር። በአማርኛ ትምህርት በመውደቃቸው ዩኒቨርሲቲ መግባት አልቻሉም ነበር። እናም ከዓመት በኋላ ዳግም ተፈትነው በ1960 ዓ.ም በአገሪቱ ብቸኛ በነበረው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በአሁኑ አጠራር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ።
ዩኒቨርሲቲ በሚገባበት ጊዜ መጀመሪያ ዓመትን ዓርት፣ ቢዝነስ፣ ሳይንስ ወዘተ ተብለው በሚጠሩ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ገብተው አንዱን በመምረጥ የሚማሩ ሲሆን፤ እርሳቸውም ዓርትን የመጀመሪያ ዓመት የትምህርት መስካቸው አድርገው ቆይተዋል። ከዚያ ሁለተኛ ዓመት ላይ ሲደርሱ ዐብይና ንዑስ ወይም ሜጀርና ማይነር ብለው የትምህርት መስክ ይመርጡ ነበርና አብያቸውን የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት መስክ አድርገው መማር ጀመሩ። በእርግጥ የትምህርት ምርጫቸው ላይ ሌሎች አማራጮችም ነበራቸው። ነገር ግን በዓመት ብዛታቸው ሊመርጧቸው የሚችሉ የትምህርት መስኮች ከአምስት ዓመት በላይ በመሆናቸው ጊዜ ላለመፍጀት ሲሉ ይህንንም መስክ ስለወደዱት ምርጫቸው አድርገውታል። የማዕረግ ተመራቂ በመሆንም ነበር ትምህርቱን ያጠናቀቁት።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ዓመታትን በሥራ ካሳለፉ በኋላ ዳግም ወደ ትምህርት የተመለሱት ባለታሪካችን፤ የሁለተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሴኔጋል ዩናይትድ ኔሽን አፍሪካን ኢኒስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክ ዴቨሎፕመንት ኤንድ ፕላኒግ ውስጥ ነው። የትምህርት መስካቸውም ኢኮኖሚክ ፕላኒንግ ነበር። እናም ትምህርቱን የሚከታተሉት ከሁሉም አፍሪካ አገራት የመጡ ሲሆኑ፤ አብዛኞቹ በመንግሥት ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ናቸውና እርሳቸውም በዚህ ዕድል ነበር ያገኙት። እንደውም ከኢትዮጵያ የተላኩት ሦስት እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ከምረቃ በኋላ አንዱ ወደ አገሩ ሲመለስ ሁለቱ ግን በአገሪቱ ላይ ቀይ ሽብር በመግባቱ ወደ አገራቸው መመለስ አልቻሉም።
ሦስተኛ ድግሪያቸውን በአሜሪካ አገር የተማሩ ሲሆን፤ የማስተማር ዕድል ተሰጥቷቸው እያስተማሩ ጎንለጎን ነው ትምህርታቸውን የተከታተሉት። ይህም በቴኔሲ ዩኒቨርስቲ ሲሆን፤ በሶሾሎጂ ትምህርት መስክ ተመርቀዋል። በእርግጥ ይህም ቢሆን ዐብይ የትምህርት መስካቸው ፖለቲካ ኢኮኖሚ እንደነበር ያስታውሳሉ። በእንግሊዝ አገርም እንዲሁ በግጭትና የሰላም ግንባታ ዙሪያ የስድስት ወር ስልጠና ወስደዋል። በተመሳሳይ ጀርመንኛ ቋንቋ የተማሩ ሲሆን፤ ብዙ ስልጠናዎችን ለመውሰድ እንዳገዛቸው ይናገራሉ።
የዓለም ታሪክን የሚያውቁበት አጋጣሚ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት ጀምሮ የሰፋ በመሆኑም በማንበብ ብዙ እውቀት መቅሰም የቻሉ ናቸውም። ይህም በተለይ የፖለቲካ ትምህርቱንም በሚገባ አውቀው እንዲማሩና እንዲኖሩበት እንዳገዛቸውም አጫውተውናል።
በአገር ብቻ ያልተወሰነው ሥራ
የሥራ ጅማሮዋቸው የነበረው ለመመረቅ አንድ ዓመት ሲቀራቸው የዓመት አገልግሎት መስጠት ግዴታ ነበርና በተወለዱባት ጎሬ አካባቢ በመሄድ የታሪክና እንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር በመሆን ያገለገሉበት ነው። ከዚያ ከምረቃ በኋላ ለረጅም ጊዜ ሥራ ሳያገኙ ቢቆዩም ወለጋ የህዝባዊ ኑሮ እድገትና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚባል መስሪያቤት ነበርና ለህብረት ሥራ ኮፕሬቲቭ ለወለጋ ክፍለአገር ጠቅላይ ግዛት ሱፐርቫይዘር በመሆን እንዲሠሩ ሆኑ።
እንግዳችን የማዕረግ ተመራቂ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲ ቀርተው የማስተማር ዕድሉ ነበራቸው። ሆኖም የመመረቂያ ጽሑፍ በመሬት ሥርዓቱ ላይ ያጠነጠነ ስለነበር ለፖለቲካው አይመችምና ሦስት ጊዜ ቢወዳደሩም ሊቀጠሩ አልቻሉም። ከዩኒቨርሲቲ ወጥተው በብዙ መስሪያቤቶች ላይ ቢወዳደሩ ሊሳካላቸው አልቻለም። ሙያቸውም ሆነ የትምህርት መስካቸው መሬት አስተዳደርም ሆነ ውጭ ጉዳይ ሊቀጥራቸው ቢችልም እነርሱም እንዳይቀበሏቸው ሆኗል። ስለዚህም ለዓመት ያህል ያለሥራ ቆይተዋል።
ሳይደግስ አይጣላ እንዲሉ አበው በስተመጨረሻ ኦሮምኛ ቋንቋ የሚችል ሰው በመፈለጉ ብቸኛ ተወዳዳሪ በመሆንም ወለጋ ላይ ማገልገላቸውን ቀጠሉ። የተለያዩ የህብረት ሥራ ማህበራትን በማደራጀትና እነርሱን በማገዝ ለዘጠኝ ወር ያህል ተገቢ ግልጋሎትም መስጠት ችለዋልም። ቀጣዩ የሥራ ጉዟቸው ሐዋሳ ላይ የሚያደርሰን ሲሆን፤ የህዝባዊ ኑሮ እድገትና ህብረት ሥራ ማህበራት ስልጠና ኢንስቲትዩት/ ኮሚኒቲ ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኮፕሬቲቭ ትሬኒንግ ኢንስቲቲውት/ አሰልጣኝ በመሆን ነው ያገለገሉት። በተጨማሪ የጭላሎ እርሻ ልማት ድርጅት ውስጥ የነበሩ ወጣቶችን አስተምረዋል።
ሌላው የሠሩበት ቦታ መሬት ይዞታና አስተዳደር ሚኒስቴር ሲሆን፤ ሦስት ዓመታትን በሱፐርቫይዘርነት አሳልፈዋል። ይህንን ጊዜ ከሁሉም ለየት አድርገው ይወዱታል፤ ያስታውሱታልም። ምክንያቱም የመሬት አዋጁን ለማስፈጸም ገበሬዎችን ሲያደራጁ የአገሪቱ ክፍል በሙሉ የማየት ዕድል ገጥሟቸዋል። አገራቸውን በደንብ እንዲያውቁም አድርጓቸዋል። ዩናይትድ ኔሽን ኢንቫይሮመንት ፕሮግራምና ካውንስል ፎር ዘዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክ ኤንድ ሶሻል ሪሰርች ኢን አፍሪካ ውስጥም በተመራማሪነት መሥራት ችለዋል። ስድስት ወር በዚህ ከሠሩ በኋላ ደግሞ ወደ አውሮፓ አቅንተው ጀርመን ውስጥ የኦሮሞ ተማሪዎች ማህበርን በማጠናከር ለሦስት ወር ያህል ሠርተዋል።
ወደ ሱዳን ሄደው የትጥቅ ትግሉን ተቀላቅለውም 13 ዓመታትን ለማህበራዊ ፍትህ ነፃነት ታግለዋል። ይህ የሆነው ደግሞ በዋናነት የፖለቲካ ሥራውን ከውጪ ግንኙነቱ ጋር በማጣመር በመሥራትና የኦነግ ድርጅትን ከመመስረት እስከ መምራት በመድረስም ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የሱማሊያ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሮ ከፍቶ ሲሰጣቸው እርሳቸው ነበሩ በኃላፊነት የሠሩት። ይህም ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ ነበር።
የሱማሊያን መንግሥት የዌስተርን ሶማሊያ ሊበሬሽን ፍሮንትና ሶማሊያ ሊበሬሽን ፍሮንት ድርጅቶችን መስርተው በዚያም ውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸው ኦሮሞዎችን አደራጅተው ከእነርሱ በአስተሳሰብ አልስማማ ሲሉ መንግሥቱ የሶማሊያን ጥቅም የሚጻረር ሥራ ሠርተሃል በሚል አሠራቸው። ያም ሳይበቃው ከአገር እንዲወጡ አስገደዳቸው። በዚህም ጉዟቸው ወደ ሱዳን ሆነ። ጫካም ገቡ። ከ13 ዓመት የትጥቅ ትግል በኋላ በአገራቸው የሽግግር መንግሥቱ አባል በመሆን ወደ መሥራቱ ተመለሱ። ይህም የሚኒስትሮች ምክርቤት አባልና የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር በመሆን ነበር።
ይሁንና ይህም ቢሆን ከአስር ወር በላይ የቆዩበት አልነበረም። ምክንያቱም የመንግሥት ለውጥ በመምጣቱ ከአገር ወጡ። ኬኒያ ገብተውም በወለጋና በሀረርጌ ያለውን የነፃነት ሰራዊት እየደገፉና ቦረና አካባቢ ያለውን ደጋፊ እያደራጁ ቆይተዋል። ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላም ወደ እንግሊዝ አገር በመሄድ ከቤተሰባቸው ጋር ተቀላቀሉ። ከዚያ ወደ ጀርመን አቅንተውም ለድርጅቱ የሚሆኑ እንቅስቃሴዎችን ያደርጉ ነበር። ሦስተኛ ድግሪያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ሥራ ለሁለት ዓመት ያገለገሉት እንግዳችን፤ በአሜሪካ ፕሪዚስተር ዩኒቨርሲቲም ሁለት ዓመት ሠርተዋል።
አብዛኛው የሥራ ጊዜያቸው ያለፈው ግን የኢትዮጵያን የመንግሥት ሥርዓት መለወጥ ላይ ነበር። ወደ አገር እስኪገቡ ድረስም በዚህ ዙሪያ ሲሠሩ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ለውጡ በፈጠረው ዕድል መጥተው አገራቸውን በሙያቸው እያገለገሉ ይገኛሉ። በተለይም አገራዊ መረጋጋትን በሚፈጥሩ ውይይቶች ላይ ቋሚ ተሰላፊ ሲሆኑ፤ ለአብነት የኦሮሞና አማራ ፓርቲዎች ውይይት፣ የኦሮሞ ማህበረሰብ ውይይቶች ላይና የኢትዮጵያ ኢንክሉሲፍ ዲያሎግ የሚል ቡድን ውስጥ በመሳተፍና ሃሳባቸውን በማጋራት ከቻሉባቸው መድረኮች ተጠቃሽ ናቸው። በተመሳሳይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ጉዳዮችን ያማክራሉ። የውጭ ጉዳይ አማካሪ ጉባኤ የሚባለው ውስጥም አባል በመሆን ይሠራሉ። ከዚህ በተጨማሪም አዲሱ የኢትዮጵያ ገለልተኛ የብሄራዊ የኢኮኖሚ ምክር ቤት አባልም በመሆን እያገለገሉ ናቸው። አሁን ደግሞ አገራቸውን በፖለቲካው እንቅስቃሴ ዙሪያ የተቻላቸውን ለማበርከት በግል ተወዳድረው የምክርቤት መግቢያ ጊዜያቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ማህበራዊ ፍትህን ፍለጋ
ማህበራዊ ፍትህን የማስከበሩን ትግል የጀመሩት ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉ ነበር። ለዚህ ደግሞ መሰረት የሆናቸው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲሆን፤ በወቅቱ ባላባትና ጭሰኛ የሚለው አስተሳሰብ መስፋቱ እንዲሁም ብዙዎች በብሔራቸውና በሃይማኖታቸው ምክንያት መድሎ እየደረሰባቸው መሆኑ ትግሉን እንዲቀላቀሉት አድርጓቸዋል። በተለይ የመሬት ጉዳይ ለእርሳቸው ልዩ ትኩረት የነበረው ሲሆን፤ በህግ ጭምር ለመሬቱ ባለቤት የሚሸጠው ከሠራው በላይ መሆኑ ዕረፍት ይነሳቸው ነበር። እናም ማህበረሰቡ ከጭቆና እንዲወጣ መታገል ጀመሩ። የተማሪዎች አስተባባሪ በመሆንም ኦነግን የሚያራምደውን አስተሳሰብም የተቀላቀሉት ለዚህ እንደነበር ይናገራሉ።
መሬት የተፈጥሮ ሀብት ነች። ማንም የግሌ ነው ሊላት አይገባም። ምክንያቱም በአስተሳሰብ ለውጥ ምክንያት ይህ መጣ እንጂ ማንኛውም ፍጥረት እግዚአብሔር ሲፈጥረው ለሁሉም መገልገያ ብሎ ነው። እናም መሆን የነበረበት ሁሉም በእኩል ለመጠቀሚያነት የተፈጠረለትን መጠቀም ነበረበት የሚሉት ዶክተር ዲማ፤ የበላይ ነኝ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አራሹን ገበሬ ገባሪ ማድረጋቸው፣ ወደጎተራው የሚከተውን መቀነሳቸው ዝም ብለው እንዳይጓዙ አድርጓቸዋል። እንደውም ወደ ትግል ያስገባቸው ይህ እንደሆነም ያስታውሳሉ።
የኦሮሞ ህዝብ በተለይ የጥቃቱ ሰለባ መሆኑ እንዳይታገሱ እንዳደረጋቸው የሚያወሱት ባለታሪካችን፤ በሥራ እርሳቸው የደረሰባቸውን ስቃይ ስለሚያውቁ መሰሎቻቸውም በዚህ ስቃይ ውስጥ እንዳያልፉ ለማድረግም ብዙ ሠርተዋል። እንደውም ኦነግ እንዲመሰረት ከተንቀሳቀሱና ለውጥ ካመጡ መካከል በዋናነት የመጠቀስ ዕድሉን ያገኙት በዚህ ጉዟቸው እንደነበርም አጫውተውናል።
የኦሮሞ ህዝብ በአገሪቱ ብዙ የህዝብ ቁጥር የያዘና ለአገርም ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ሆኖ ሳለ መገፋቱ እጅግ ያማቸው እንደነበር ያነሳሉ። በፖለቲካ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ዙሪያም ቢሆን ድርሻው የለም በሚባል ደረጃ ላይ መሆናቸው ቁጭት ይፈጥርባቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ። እናም በትግል ኦነግ በይፋ እስኪመሰረት ድረስ ዋጋ ከፍለዋል። መስርተውም በመጠኑም ቢሆን ለውጦች እንዲመጡ አስችለዋል። በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ።
ኦነግን ሲመሰርቱ በዘፈቀደ ሳይሆን የኦሮሞው ጭቆና እስከምን ድረስ ነው በሚል ጥናት ተደርጎ ነው። የተለያዩ ችግሮች በሁሉም መስክ ከተለዩ በኋላም ከትጥቅ ትግል ውጪ ስርዓቱን መገርሰስ እንደማይቻል ከተረዱ በኋላ እርሳቸው ለ13 ዓመታት ሌሎች ከዚያ በላይ ታግለው ድርጅቱ እውን እንዲሆን አድርገዋል። መጀመሪያ ግን የተለያዩ ማህበራትን በመመስረት ነበር እንቅስቃሴውን የጀመሩት። ለዚህ ያገዛቸው ደግሞ መንግሥትን በመቃወም ሰልፍ ያልወጣ የማህበረሰብ ክፍል ባለመኖሩ ነው።
ሁሉም የፍትህ ጥማት ነበረበትና ፍትህን ፍለጋ ጮኸ። በዚህም መንግሥት ነገሮችን አላልቶ ብዙ የመብት መከበር ዕድሎች ሰጠ። ይህ ደግሞ ተሰጥተው ነበርና እንደ አሊቢራ ኦኬስትራ ዓይነት በመቋቋም የማህበረሰቡን ሙዚቃ እንዲያስተዋውቁ፣ የግል ጋዜጣ በመጀመር ቋንቋው የሚያድግበትን ዕድል እንዲፈጥሩ መንገድ ጠረገላቸው። ከሁሉም በላይ ድርጅቱን በህቡዕ እንዲንቀሳቀስ አድርገው የተለያዩ የማጠናከሪያ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ አገዛቸው። ከዚያ አስተሳሰቡን የሚደግፉ ሰዎችን በህቡዕ በማደራጀትና ስልጠና በመስጠት ቋሚ አባል ማድረግ ቻሉ። ዛሬ ድረስ አስተሳሰቡ እንዳይጠፋ የሆነውም በዚህ ሥራቸው እንደሆነም ያወሳሉ።
የፖለቲካ ምህዳሩ ዳግም ወደነበረበት በመመለሱ ከአገር እንደወጡ ያጫወቱን ዶክተር ዲማ፤ ጊዜው አይደለም የድርጅት ሥራ ለመንቀሳቀስም ፈታኝ ነበር። በዚህም አብዛኞቹ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ አካላት ወደ ትጥቅ ትግል ገቡ። ኦነግም ይህንን ካደረጉት መካከል ሆነ። ጫካ ገብቶ ለማህበራዊ ፍትህ መታገል ጀመረ። ተሳክቶለትም ብዙ ለውጥ በአገር ደረጃ አመጣ። ሆኖም የአመራር ለውጥና ሰዎች በሚያስቡት ልክ መሥራት መጀመራቸው ብዙ ነገሮችን ቀየራቸው። የግል አሠራርም ሰፈነበትና ዛሬ እንዲበታተን ሆነ ይላሉ።
በኦነግ የትጥቅ ትግል ውስጥ እንደ ሌሎቹ መሳሪያ ታጥቀው ሳይሆን ትምህርትና ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም የማደራጀት ሥራ በመሥራት እንደነበር የሚያስታውሱት እንግዳችን፤ ሱዳንን በሚያጎራብቱ የአገሪቱ ክፍሎች ሳይቀር ብዙ ሥራም ሠርተውበታል። በተለይም ከዜሮ ተነስቶ ማደራጀት ላይ ብዙ ለፍተዋል። በሌላ በኩል የትጥቅ ትግሉ ጅማሬ ኤርትራ በመሆኑ በዚያም ብዙ ሥራ ሠርተዋል። ወታደራዊ ትምህርቱን ሌሎች ሲሰጡ እነርሱ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ተገቢውን ትምህርትና ስልጠና በመስጠት ያግዛሉ። አብዛኛው ድርጅቱን የሚቀላቀለው የገበሬ ልጅ በመሆኑ እነርሱን የቀለም ትምህርት ማስተማርም የእነርሱ ሥራ እንደነበር ያስታውሳሉ። ታጋዩ እየበዛ ሲሄድ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እስከመስጠት እንደደረሱም አይረሱትም።
ትምህርቱን ሲሰጡ በአጭር ጊዜ ይገባቸው እንደነበርና ነፃነት ምን ያህል የመማር ዕድልን እንደሚሰጥ ያዩበት መሆኑንም ይህንን በሚሠሩበት ወቅት እንደተረዱት ይናገራሉ። እናም ለማህበራዊ ፍትህ መታገላቸው ትክክለኛ መስመር ላይ እንዳሉ እንዳረጋገጠላቸውም ያወሳሉ።
የ66ቱ አቢዮት ዋነኛ ዓላማ የብሔሮችን እኩልነት ማስከበር ነው። በተለይም የመብት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙና ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን ብዙ የተለፋበት ነበር። ደርግ መጀመሪያ አካባቢ መሬት ለአራሹ አለ። ቀጠለናም የብሔሮች እኩልነት እንደሚከበር ገለጸ። የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አቢዮትም የሚል ነገር አወጀ። ሆኖም የብሔሮችን እኩልነት ለማስከበር በጣም ተቸገረ። ምክንያቱም የደርግን ስርዓት የማይፈልጉ ብዙ አመራሮች በውስጡ ተሰግስገዋል። እናም በዘላቂነት አስቀጥሎ መተግበር አልቻለም። በዚህም የትጥቅ ትግሉ በየፊናው መስፋፋቱ በዛ።
ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን መስርቶም አምስት ራስ ገዝና 24 አስተዳደራዊ ክልሎችን ፈጠረ። ይሁንና ዴሞክራሲው ላይ ጥያቄ መነሳት ጀመረ። ክልሎቹ ራሳቸው በመረጡት ሰው መተዳደር ነበረባቸውና ምርጫ ሲካሄድ ራሳቸው የሾሙትን ማስቀመጥ በመቻላቸው በመካከል ጸብ ተፈጠረ። ችግሩን ሊፈታ የሚችልም የሽግግር መንግሥት ተመስርቶ ከቆየ በኋላ መልሶ ችግር በመፍጠሩ ጉልበት የነበረው ወያኔ አሸንፎ ቦታውን ያዘ። ይህ ደግሞ ለኦነግ እጅግ ፈታኝ ነበር።
የለፋበት የትግል ውጤት ለምልሞ እያለ ከአገር እንዲወጣ ተገደደ። በዚህም በውጪ ሆኖ ተበታትኖ ሳይቀር በግሉ አገሩን ሳይረሳ ላለፉት 29 ዓመታት እየታገለ ዘለቀ። እርሳቸውም ከ23 ዓመት በፊት ከድርጅቱ በአስተሳሰብ ልዩነት ቢወጡም ስለአገራቸው ያስባሉና ይህንኑ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በተለይም በማህበራዊ ፍትህ ዙሪያ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩም ነበር። ለውጡ ወደ አገር እንዲገቡ ባደረገው መሰረትም ከድርጅት አባልነት ይልቅ በግል ተወዳድሮ አሻራን ማሳረፍ እንደሚያስፈልግም በማመናቸው በግል በመወዳደር አሸንፈው ለመሥራትም ቆርጠው ተነስተዋል።
በፖለቲካ ጉዟቸው ከዚህ በኋላ የተሻለ ነገር ለአገራቸው እንደሚያበረክቱም በወጋችን መካከል አንስተውልናል። እንደርሳቸው ሃሳብ ዛሬ በምንም መልኩ የትጥቅ ትግል አስፈላጊ አይደለም። ምክንያቱም ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል። ዓለም ጭምር በውይይት እንጂ በመሳሪያ ማሸነፍ እንደማይቻል እየተረዳ ነው። እናም በአገር ውስጥ ሆኜ አገርን ላገለግል ነው የመጣሁት የሚል አካል ሁሉ ከትጥቅ አስተሳሰብ ራሱን ሊያላቅቅ ይገባል ባይ ናቸው። የትጥቅ ትግል ጊዜው ያለፈበት ፋሽን እንደሆነም ያነሳሉ። እናም ከዘመኑ ጋር ዘምኖ በነፃ ውይይት ራስን መሥራት አስፈላጊ እንደሆነም ያስገነዝባሉ።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ረጅም የትጥቅ ትግል የተማርነው በትጥቅ ትግል የመጣ ስልጣን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት እንደማይችል ነው። ስለሆነም ዴሞክራሲ ያስፈልገናል የምንል ሁሉ በአዲስ አስተሳሰብ መመራትን ተግባራችን ልናደርገው ይገባል ይላሉ። በቃል ብቻ ዴሞክራሲ ማለት የትም አያደርስም። ተግባር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መዋጋትን ትቶ በሃሳብ መሸናነፍን ማንገብ አስፈላጊ ነው ባይም ናቸው።
በጊዜ ብዛት ኦነግ የመበታተኑ ምስጢርም በሃሳብ አለመስማማትና በአንድ ዓላማ መቆም አለመቻላቸው ነው። ለማስታረቅና የምስረታውን ዓላማ ለማስገንዘብ ጥረት ብናደርግም የሚሰማን እንኳን አጥተናል። ስለሆነም ሃሳብ ከትጥቅ ካልበለጠ ዴሞክራሲም ሆነ ማሸነፍ እንደማይኖር በየውጤቶቹ እያየን መጥተናል። እናም አሁንም ጊዜው አረፈደምና ይህ ይበጀናል ይላሉ።
ወያኔን ዋናው አንጃው ደህንነት እየሸረሸረ የራሱን መሳሪያና አቅም መፍጠር ነው። እናም መጀመሪያ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ከዚያ የተወሰነው የኦነግ መስራች አባላትና የድርጅቱ አባላት በመሆን የመሰረትነው የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቅ ብዙ ሥራዎችን ቢሠራም ከመበታተን አልቀረም ነበር። የቀረው እንኳን በለውጡ ምክንያት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለት በነፃነት ገብቶ እንዲንቀሳቀስ ከሆነ በኋላ ከኦዲፒ ጋር ተቀላቀለ። ይህ ደግሞ አስተሳሰቡ እንዲሸረሸርና ሰዎቹ እንዲበታተኑ አደረጋቸው። እናም የአስተሳሰብ ልዩነት ምንጩ በጉልበት ለማሸነፍ መሞከር እንደሆነ ያስረዳሉ።
በግሌ ለመወዳደር የፈለኩት በሁለት ምክንያት ነው የሚሉት ዶክተር ዲማ፤ የመጀመሪያው የለውጥ ሂደቱ እንዲቀጥል ስለምፈልግ ሲሆን፤ ሁለተኛው የተረሱ አካባቢዎችን እንዲታወሱ ለመሥራት ነው። ለአብነት እኔ የተወዳደርኩበት ከተማ ለችግሮቹ መፍትሔ እንዲያገኝ የበኩሌን ማድረግ ስላለብኝ ፈጽሜዋለሁ ይላሉ። ለዚህ ደግሞ ምክርቤቱ ውስጥ መግባታቸው ብዙ እድሎችን እንደሚሰጣቸው ያምናሉ።
የትጥቅ ትግሉ ገጠመኞች
ትግል የመኖርም የመሞትም ውሳኔ ያለበት ነው። በዚህም በርካታ ገጠመኞች ኖረውኝ አልፈዋል። ከእነዚህ መካከልም አንዱ በሶማሊያ በኩል አቋርጠን ወደ ሀረርጌ ጉባኤ ለማካሄድ በመጓዝ ጊዜ የገጠመን በሁለት አካላት የተደረገ የመንገድ ላይ ጦርነት አንዱ ነው። ጦርነቱ የተከፈተብን በሱማሌ መንግሥት ተቃዋሚ ኃይልና በደርግ መንግሥት ሲሆን፤ ሁለቱንም ለማለፍ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ገብተን እንደነበር አረሳውም ይላሉ። ይሁንና ሰብሮ መውጣት እንዳለባቸው በማመናቸው በጦርነቱ ውስጥ ገብተው ብዙዎች ሲሞቱ እነርሱ መትረፍ ችለዋል።
በወቅቱ ህይወታቸውን ለማትረፍ ሰባት ቀን ሙሉ ያለምንም ምግብ ወተት እየጠጡ በእግራቸው የተጓዙ ሲሆን፤ በወተት ብቻ እንደሚያኖር ያዩበት ጊዜ እንደነበር አይረሱትም። ከዚህ በተጨማሪ የአገራቸው አርብቶ አደር ምን ያህል ደግ እንደነበርም የተመለከቱበት ጊዜ ስለነበርና ከጉዞው በላይ አለመብላቱ ለአደጋ ያጋልጠናል የሚለውን ስጋታቸውን ስላጠፋላቸው የበለጠ ለዚህ ህዝብ ነፃነት መታገል እንዳለባቸው ያስገነዘባቸው እንደነበርም አይዘነጉትም።
የመጀመሪያው ጉዟችን ቢጠናቀቅም መመለሻው ላይም ከዚህ ያልተናነሰ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር የሚያነሱት እንግዳችን፤ ጉዟቸው ሌሊት በመሆኑ ድሬዳዋ አካባቢ ሊደርሱ ሲሉ ጉም የሠራቸውን ነገር መቼም አይረሱትም። አቅጣጫቸውንም ሆነ መንገዳቸውን ዘጋና ወዴት እንደሚሄዱ ግራ አጋባቸው። ሆኖም እንቅስቃሴያቸውን በቴክኖሎጂ የሚያግዙት እንግዳችን ኮንፓስ ነበራቸውና ወዲያው ወደመፍትሔው ገቡ። ግን ይህም ቢሆን በቀላሉ ያሰቡት ላይ መድረስ አላስቻላቸውም ነበር። እናም ድንበሩን ሳይሻገሩ በመንጋቱ በጊዜው ጭር ያለ ቦታ ላይ አረፉ።
ቦታው ሰው ዝር የማይልበት ግን ብዙ ቤቶች ያሉበት ቦታ እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር ዲማ፤ አንዱ ቤት ገብተውም መጠለላቸውን ይሁን እንጂ እኩለ ቀን ሊቃረብ ሲሆን የሰዎችን እንቅስቃሴ በብዛት መስማታቸውን ከዚያም ከየት መጡ የማይባሉ ሰዎች ባረፉበት ስፈር ቤታችን ነው እያሉ መምጣታቸውን ይናገራሉ። በወቅቱ አማራጭ አልነበራቸውምና የቤቱ ባለቤት ነኝ ብሎ የመጣውን አፍነው እንዳስቀሩት፤ ድንበሩን ሲሻገሩም እንደለቀቁት አይረሱትም። በዚያ ላይ የእርሳቸው በጠና መታመም ተጨምሮበት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ከቷቸው እንደነበርም መቼም የሚረሳቸው ጉዳይ አይደለም። ይሁን እንጂ ይህ የትግሉ አካል በመሆኑ ለፍትህ የተከፈለ መስዋዕትነት ነው ብለው እንደሚያምኑና አሁንም ቢሆን ስለፍትህ እስከሞት ድረስ የሚታገሉ መሆኑን በጭውውታችን መሀል አንስተውልናል።
መልዕክት
በ50 ዓመታት የፖለቲካ ጊዜ ውስጥ ሁለት ነገሮች የኢትየጵያን ፖለቲካ ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት እንዳይሸጋገር አድርገውታል። ቀዳሚው የፓርቲዎች ምስረታ በትጥቅ ትግል እና በስውር የጠመንጃ ፖለቲካ መሆኑ ከዴሞክራሲ ጋር መላተሙ ሲሆን፤ ሁለተኛው ገዥው ፓርቲ እና የመንግሥት ተቋማት የማይለያዩ ሆነው መቀጠላቸው ነው። በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር እየተበራከተ የመራጮችን ድምፅ እንዲበታተን እና መሃል ላይ እንዲዋልል አድርጎታል። ስለዚህም ይህንን መፍታት የመጀመሪያ ሥራ መሆን አለበት ይላሉ። አሁን ተስፋ የተጣለበት የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ በመሆናችን ዕድሉ በክሽፈት እንዳይመለስ መጠንቀቅ ያሻል የሚለው የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
ሁለተኛ መልዕክታቸው ደግሞ የበለፀገች ሀገር ለመመስረት ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የሆኑ የደህንነት እና የመከላከያ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግ ያነሱት ነው። ነፃ ተቋም አገርን ከማሳደግም በላይ አገር ወዳድ ትውልድን ይፈጥራል። ለነፃነት የሚቆሙ ዜጎችንም ያበራክታል። እውነት እንድታብብም ያግዛል። ስለሆነም መንግሥት መጀመሪያ ሊያደርገው የሚገባው ይህንን ነው ይላሉ።
ሌላው ሃሳባቸው ደግሞ ሰው በተረዳው ልክ ሲሠራ ከመቃረን ይልቅ ደግፎ ስህተቱን ማረም ይገባል የሚለው ነው። ሃሳቡን ከከለከልነው የበለጠ ወደማድረጉ ይገባል። ይህ ደግሞ ጉልበት እንጂ ሃሳብ ዋጋ እንዳይሰጠው በር ይከፍታል። እናም የሃሳብ ነፃነት ከምንም በላ አስፈላጊ እንደሆነ በማመን አዳዲስ ሃሳቦችን ወደ መድረክ በማምጣት መማማሪያ ማድረግ ይገባል። ሃሳብ ከሁሉም ነገር በላይ እንደሆነች ማሳየትም ያስፈልጋል። ሃሳብ የበላይነት ሲያገኝ ዜጋውን በአዲስ ለውጥ ያሻግራል። መጠላላትን ሳይሆን መፋቀርን ያጎለብታል። ከሁሉም በላይ አገር ዘመን ተሸጋሪ ሥራ እንድትሠራና በሁሉም ነገር እድገቷን እንድታሳይ ያግዛል። ስለሆነም ዛሬ ይህ እንደሚያስፈልግ በማመን ሁሉም ለሃሳብ የበላይነት መሥራት አለበት መልዕክታቸው ነው።
ለትውልዱ የሃሳብ ተከታይ ሳይሆን ሃሳብ አመንጪ መሆን ዕድል መሰጠትም አለበት ይላሉ። ለዚህ ደግሞ ማንበብ ወሳኝ ነውና ማንበብን የሚያበረቱ ተግባራት ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ያላነበበ ሰው ዘወትር ተግባሩም ኑሮውም የሰው ሃሳብ ተከታይ መሆን ነው። ለእርሱ አዲስ ነገር እሩቁ ይሆናል። ኑሮውም ሥራውም የሰው እንጂ የራሱን ፍላጎት ያነገበ አይደለም። ስለሆነም ይህ ባህል ከቤተሰብ የጀመረ ሥራ ያስፈልገዋልና ይታሰብበት የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2013