እንደሚታወቀው ከአንድ አገራዊ ብቻም አይደለም ማህበራዊም ሆነ ግለሰባዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያንን ጉዳይ ጠቅለል አድርጎ የሚያስተላልፍ፣ በሰዎች ዘንድ በቀላሉ ሊያዝ የሚችልና ሊረሳ የማይችል፤ ድንበር (ዘመንንም) ተሻጋሪ የሆነ መልእክት የማስተላለፊያ ዘዴ ይቀረፃል፤ ወይ በፅሁፍ አልያም በንግግር፤ ወይም በሁለቱም የሚተላለፍ፤ ከእነዚህ አንዱ ደግሞ በሁለቱም እየተላለፈ ያለው ታሪካዊውና የእኛው – “ግድቡ የ’ኔ ነው” ነው።
“ግድቡ የ’ኔ ነው”ን ትንሽም ቢሆን ከለፋንና እውነቱ ጋር ለመድረስ ካልሰነፍን በስተቀር “እኔ”ን ይዘን በመንገዱ ብንጓዝ ከ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› (ዮሐ.፲፬፥፮) የማይገናኝበትና የማናገናኝበት ምክንያት የለምና “ግድቡ የ’ኔ ነው”ን ከዚሁ አንፃር (እዚህ ብዙም ባንገፋበት) መቃኘት ይቻላል።
“ግድቡ የ’ኔ ነው” ሲባል ባለቤቱ (“እኔ” ባዩ ተናጋሪ) ግድብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ለምን እንደሚሰራ፣ ከምን እንደሚሰራ፣ መቼና የት እንደሚሰራ፣ በማን እንደሚሰራ፣ መቼ ተጀምሮ መች እንደሚያልቅ ሁሉ አውቃለሁ እያለ ነውና “ግድቡ የ’ኔ ነው” መኪና ለማሳመር በመኪና ላይ የተለጠፈ የመኪና ጌጥ አይደለም ማለት ነው።
“ግድቡ የ’ኔ ነው” ባዩ እነዚህን ብቻ አይደለም እየተናገረ ያለው። እየተናገራቸው ያሉ በርካታ ቁም ነገሮች ያሉ ሲሆን፤ ግድቡን አቁም አትበሉኝ፣ የኛ ነው አትበሉኝ፣ በአባይ ጉዳይ ምን አገባህ ልባል አይገባም፣ በውሀዬ፣ በወንዜ፣ በሀብትና ንብረቴ ልጠቀም ይገባልና ተውኝ ወዘተርፈ እያለ መሆኑን መጥቀሱ ብቻ ይበቃል። አዎ – ግድቡ የ’ኔ ነው!!!
“ግድቡ የ’ኔ ነው” በቋንቋ (ንግግር) ክፍሉም ሰበነክ ሲሆን፣ አንደኛ መደብ ምድብ ተውላጠ ሥም ነው። ሲበዛ ደግሞ “እኛ” ይሆናልና “ግድቡ የ’ኔ ነው” ሲባል የእያንዳንዱ፤ በተራዛሚውም “ግድቡ የእኛ ነው” እያልን ነውና የግድቡ ጉዳይ የእኛ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን ከሩቁ ያውጃልና “ስማ በለው” እንዲል ስነ ቃሉ ሊሰሙ ላልሰማም ሊያሰማ ይገባልና ነው ሁላችንም “ግድቡ የ’ኔ ነው” እያልን ያለነው። ድምፃዊው “አንድ ላይ” እንዳለው ሁሉ – ግድቡ የ’ኛ ነው!!!
“ግድቡ የ’ኔ ነው” ለብዙ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ የሚሰጥ ሲሆን አንዱና ዋናውም “ግድቡ የ(እነ)ማን ነው?” የሚለው ነው። “ግድቡ የ(እነ)ማን ነው?” ብሎ የሚጠይቅ (እያወቀም ይሁን ሳይውቅ፤ ገብቶትም ይሁን ሳይገባው) ካለ እሩቅ ሳይሄድ፣ ምንም ሳይታክትና ሳይለፋ፣ ሳይወጣና ሳይወርድ፣ ላይ ታች ሳይል፣ ጦር ሳይመዝና ሳይሰብቅ . . . ያለ ምንም አይነት ወጪና ኪሳራ መልሱን ከ”ግድቡ የ’ኔ ነው” ያገኘዋልና ተገላገለ ማለት ነው።
“ግድቡ የ’ኔ ነው” ከኃላፊነትም አኳያ ለሚመለከተው ሁሉ የሚያስተላልፈው መልእክት ያለ ሲሆን እሱም አበሻ እማይነካውን ሲነኩበት፣ በማይመጣው ሲመጡበት . . . “በአይኔ የመጣ/ህ/ሽ” እንደሚለውና እንደሚባለው ሁሉ፤ “ግድቡ የ’ኔ ነው” ሲልም “በአባይ ግድብ የመጣ በአይኔ የመጣ ነው” እያለ ነውና ለመምጣት ያሰበ ካለ እንደማያዋጣ ከወዲሁ እቅጩን መልስ እየሰጠ ነው ማለት ነው።
የ”ግድቡ የ’ኔ ነው” ሌላው መልእክት የባለቤትነት ማረጋገጫ “ሌቼንሳ” መሆኑና ባለቤቱንም በግልፅ ማስቀመጡ ሲሆን፤ እሱም የባለቤትነት መብቱ፣ የተጠቃሚነት መብቱ፣ ድርሻን የማግኘት መብቱ፣ የተፈጥሮ ሀብትን የመጠቀም መብቱ . . . – መብቶች ሁሉ አሉኝ፤ እነሱን የመጠቀም መብቴንም ማንም ሊከለክለኝ አይገባም፤ አይችልምም የሚል ነውና “ግድቡ የ’ኔ ነው” የመልእክት ማስተላለፊያው ብልሀትም ሆነ ያስተላለፋቸው መልእክቶቹ ብዙ ናቸውና ልብ ያለው ልብ ይል ዘንድ የሚያሳስብ ነው።
“ግድቡ የ’ኔ ነው” አንድ ከድህነት የመውጣት እንጂ በድህነት ውስጥ ተዘፍቆ የመኖር ፍላጎት የሌለው ሰው ድምፅ፤ የማደግና መበልፀግ ጉጉቱ ከፍ ያለና ለዚህም ቆርጦ የተነሳ ሰው ድምፅ ነው፤ የአንድ ቢያስፈራሩት የማይፈራ ሰው ድምፅ ነው፤ በውሸት ሀይቅ ቢያጥለቀልቁት ተጠርጎ የማይወስድ ሰው ድምፅ ነው። ሲጠራቀም – የድሆች ድምፅ ነው!!!
ከጀርባው “አትንኩን፣ አትንኩን …” የሚል ድምፅ ያለው፣ “ተወኝ ጠላት ተወኝ … ተው ተወኝ …” የሚል ድምፅ ያለው “ግድቡ የ’ኔ ነው” መሪ ቃል ተናጋሪው (“እኔ” የሚለው) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ “ንክች ያያ ቢላዎ ልጅ” የሚል ፅኑ አቋም፤ ፈሪው “ዘጠኝ ሞት መጣ” ቢለው፣ ጀግናው “አንዱን ግባ በለው” እንዳለው ለነፍሱ የማይሳሳ መሆኑን ከመግለፁም በላይ ጠላት፤ “ግድቡ ያንተ አይደለም” የሚለው፣ አስቀድሞ ከራሱ የተጣላ ወንበዴም ይህንን በአግባቡ እንዲረዳ በአደባባይ የተሰጠ መልስ፤ ከመልስም የዘለለ የማንነት፣ የባለቤትነት፣ የእኩል ተጠቃሚነት አቋም ነው – “ግድቡ የ’ኔ ነው”። በመሆኑም በአንድ ላይ “ግድቡ የ’ኔ ነው” ማለት የሁሉም ፋንታ፤ የሁሉም ድርሻ፤ የእያንዳንዱ ባለቤት፣ ተጠቃሚ … ግዴታ ይሆናል ማለት ነውና – ግድቡ የ’ኛ ነው!!!
“ግድቡ የ’ኔ ነው”ን ከጊዜ አንፃር ከተመለከትነውም ተገቢው ሰዓት ላይ ከተፍ ያለ፤ ጫጫታው ከፍ ባለበት ወቅት በነፍስ የደረሰ መሪ ቃል – ምትሀታዊ አረፍተ ነገር – ነውና በጊዜ የደረሰልንን “ግድቡ የ’ኔ ነው” መልእክት ከወረቀት ባለፈም ወደ መሬት ልናወርደው የግድ ይላልና። በተለይ ኢትዮጵያ በታሪኳ ባንዳ፣ የእናት ጡት ነካሽ፣ የታሪክ አተላ፣ አምስተኛ ረድፈኞች ወዘተ ወዘተ አጥታ እንደማታወቀው ሁሉ አሁንም ከውጪዎቹ፣ በተለይም “ግድቡ የእናንተ አይደለም። ዋ ትነኩና …” ከሚሉን ጋር በማበር ከአላማችን ሊያደናቅፉን፣ ከግባችን ሊያሰናክሉን ባሰፈሰፉበት በዚህ ክፉ ጊዜ (ግን ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ 80 በመቶን ሊሻገር ሴኮንዶች በቀሩት) ወቅት “ግድቡ የ’ኔ ነው” መሪ ሀሳብ ደርሷልና ከጊዜ አንፃር መስፈርቱን በማለፉ ደግመን ደጋግመን፤ ሁላችንም እንላለን – ግድቡ የ’ኛ ነው!!!
“ሲጋልብ የመጣን አህያ ቀርቀብ አድርገህ ጫነው” እንደሚባለው ሳንነካው የሚነካንን አሳምሮ መቅጣት፤ ሲሰግርም ይሁን ሲቦርቅ የመጣን እያነከሰ እንዲመለስ የማድረግ አቅምና የዳበረ ልምድ ያለን ከመሆኑ አኳያ በዚህ ወቅት “ግድቡ የ’ኔ ነው” የሚለው አሰባሳቢ አረፍተ ነገር መከሰቱ ተገቢ መሆኑን፤ ከሳቾቹም ባለውለታ መሆናቸውን፤ መልእክቱን በአደባባይ ይዘው በመንቀሳቀስ (በተለይ ባለ መኪኖች) እያስተላለፉ ያሉትን ሁሉ እያመሰገንን “ግድቡ የ’ኔ ነው” የሚለውን መልእክታችንን እናስተላለፋለን። አዎ፣ ግድቡ የ’ኔ ነው!!!
“ግድቡ የ’ኔ ነው”ን ከሞራል፣ ከመንፈሳዊና ዜግነት አኳያም ከተመለከትነው የሚመጥን ሆኖ የምናገኘው ሲሆን፤ ለዚህም በመግቢያ አንቀፃችን ላይ የጠቀስነውን (ዮሐ.፲፬፥፮) “የሚያሟላ” ሆኖ መገኘቱ፤ ይህም የባለቤትነታችን ጉዳይ (“የ’ኔ ነው” ማለታችን) ፍፁም እውነት መሆኑ፣ የመልማትና ከድህነት የመውጫ መንገዱም ይሄው በሥራ (“ጥረህ ግረህ …” እንደተባለው) ሆኖ መገኘቱ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው።
(“ግድቡ የ’ኔ ነው”ን የእውነት አምላክ ከሆነው ከ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ›› ቃል ጋር ማገናኘታችን መሪ ሀሳቡ፣ አሰባሳቢው አረፍተ ነገርና ምትሃታዊው አባባል በውስጡ እውነትንም፣ መንገድንም፣ ህይወትንም ይዞ በመገኘቱ መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን – ግድቡ የ’ኔ ነው!!)
አዲስ ዘመን ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም