በቡና ንግድ ከ25 ዓመታት በላይ ቆይቷል። ሥራውን የጀመረው ቀደም ሲል ቡና አቅራቢ በነበሩ በሁለት ወንድማማቾች ሲዳማ ላይ ነው። በሂደት በስፋት፣ በመጠንና በጥራት መሻሻሎችን በማሳየቱ በዓለም አቀፍ ዙሪያ የቡና ገዢዎችን ትኩረት ለመሳብ ችሏል። በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ግዙፍ ቡና ላኪ ኩባንያዎች መካከልም ከቀዳሚዎቹ ተርታ ለመሰለፍ በቅቷል።
በየዓመቱ ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው የቡና መጠን እየጨመረ ከመምጣቱ ባሻገር የቡና መዳረሻ ሀገራቱም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። ስታርባክስን ጨምሮ ከሌሎች ታላላቅ የቡና ኩባንያዎች ጋርም አብሮ ይሠራል። ለበርካታ ዜጎችና አርሶ አደሮችም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል- ዳዬ ቤንሳ ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ።
አቶ ከንአን አሰፋ የዳዬ ቤንሳ ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የኤክስፖርት ማናጀር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ኩባንያው ቀደም ሲል ከሲዳማ ቡና በሚያቀርቡ አሰፋ እና ሙሉጌታ ዱከሞ በተባሉ ሁለት ወንድማማቾች በአንድ ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታልና በሦስት ሠራተኞች እ.ኤ.አ በ2006 ተመስርቶ ቡናን ወደ ውጭ ሀገር መላክ ጀመረ። ወንድማማቾቹ ወደዚህ የቡና ወጪ ንግድ የገቡበት ዋነኛ ምክንያትም ቡና በአካባቢያቸው ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆኑና ወላጆቻቸውም የቡና አምራች ገበሬዎች በመሆናቸው ነበር።
በመጀመሪያዎቹ የኩባንያው የምስረታ ዓመታትም ሁለቱ ወንድማማቾች የቡናን የወጪ ንግድ በተመለከተ ትምህርት ቀሰሙ። ወንድማማቾቹ በጊዜው ቡናን ወደ ውጭ ሀገር መላክ ሲጀምሩ የመላክ አቅማቸው በዓመት ከ19 ነጥብ 2 ቶን አይበልጥም ነበር። የቡና መፈልፈያ ቦታቸውም አንድ የነበረ ሲሆን፤ ለኤክስፖርት የሚቀርብ ቡና ማበጠሪያ ማሽን የሚገለገሉትም በኪራይ ነበር። ይሁንና በሂደት የቡናን የወጪ ንግድ ይበልጥ እየተለማመዱት መጡ። ወደውጭ ሀገራት የሚልኩት የቡና መጠንም እያደገ ሄደ። የኤክስፖርት መዳረሻ ሀገራትንም ማሳደግ ቻሉ።
በአሁኑ ጊዜም ኩባንያው በሀገሪቱ ካሉ አምስት ከፍተኛ ቡና ላኪ ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ለመሆን በቅቷል። ከአርባ በላይ የሚሆኑ ደምበኞችና ከሃያ አራት በላይ ለሚሆኑ ሀገራትም ቡናን ይልካል። በዓመት ስምንት ሺና ከዚያ በላይ ቶን ቡና የመላክ አቅም አለው። አንድ መቶ አንድ ቋሚ ሠራተኞችም ያሉት ሲሆን፤ በቡና ምርት መሰብሰቢያ ወቅት እስከ 10 ሺ ለሚጠጉ ሠራተኞች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
የኩባንያው የቡና መፈልፈያዎች ከአንድ ወደ ሃያ አምስት ያደጉ ሲሆን፤ 35 የሚሆኑ የቡና አቅራቢዎችና 2 ሺህ 500 ቡና አቅራቢ አባል አርሶ አደሮች አሉት። ኩባንያውም ለእነዚሁ አባል አርሶ አደሮች ቡናን በተሻለ ጥራት እንዲያመርቱ በልዩ ሁኔታ ስልጠናዎችን ይሰጣቸዋል። ማዳበሪያዎችንም ያቀርብላቸዋል። በዓመቱ መጨረሻም ኩባንያው ባገኘው ትርፍ ልክ ተጨማሪ ክፍያም ይፈፅምላቸዋል። በሠላሳ አምስቱ ቡና አቅራቢዎች ስር ያሉ ሌሎች አርሶ አደሮችም በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በዓለም ላይ ታዋቂ ለሆነው የስታርባክስ ኩባንያ በከፍተኛ ደረጃ ቡናን ያቀርባል። ለሌሎችም ተመሳሳይ ኩባንያዎች እንዲሁ። ቡና የሚልክባቸው ሀገራት መዳረሻዎችንም አሳድጓል። አሁንም አዳዲስ ሀገራትን ጨምሯል። የኩባንያው ዋነኛ ስትራቴጂም ተጨማሪ መዳረሻ ሀገራትን ማስፋት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት መዳረሻውን ወደ ተጨማሪ ሰባት ሀገራት አሳድጓል። ይህም የኩባንያውን ገበያ ከማስፋት በዘለለ በቡና ወጪ ንግድ ሊከሰት የሚችለውን ኪሳራ ለመቀነስ አስችሎታል። በተለመዱ ሀገራት ላይ ብቻ የመንጠልጠል ስጋትንም ቀንሶለታል።
የቡና መፈልፈያዎቹ በሲዳማ ክልል ሃያ አምስት የቡና መብቀያ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ሦስት የቡና ማበጠሪያዎች ደግሞ በተለያዩ የሲዳማ ዞኖች ውስጥ አሉ። ሁለት የኤክስፖርት ቡና ማጠሪያም በአዲስ አበባ ጃክሮስ አካባቢ አለው። የኤክስፖርት ቡና ማበጠሪያ ማሽኖቹም በሰዓት ስድስት ቶን ቡና የማበጠር አቅም አላቸው። ከሲዳማ ተፍልፍሎ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው ቡናም በእነዚሁ ማበጠሪያዎች ከተቀነባበረ በኋላ ለመቆላት ዝግጁ የሆነው ታሽጎ ወደ ውጭ ሀገራት ይላካል።
ኩባንያው ቡናን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ በየዓመቱ የሚያገኘው የውጭ ምንዛሬም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ይናገራሉ። በተያዘው በጀት ዓመት እስከ 30 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማገኘት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜም ይህንኑ አቅድ ለማሳካት ከጫፍ ደርሷል። አምና ከነበረው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ጋር ሲነፃፀርም የ13 ሚሊዮን ዶላር ልዩነት አለው። ከ2011 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ22 ሚሊዮን ዶላር ልዩነት እንዳለው ያሳያል። ይህም ኩባንያው ቡናን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ በየዓመቱ የሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ እያደገ መምጣቱን ይጠቁማል። በተለይ ደግሞ ኩባንያው ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ እድገት አሳይቷል። በአሁኑ ጊዜም አጠቃላይ ካፒታሉ 21 ሚሊዮን 290 ሺ ብር ደርሷል።
የነበረውን የማኔጅመንት ስርዓት መቀየሩ፣ የሽያጭ አሠራሩን ማስተካከሉ፣ ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎችንና ማህበራዊ ሚዲዎችን መጠቀሙ እንዲሁም የቡና ወጪ ንግድ ተደራሽነቱን ማስፋቱ ለኩባንያው እድገትና መሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለውን የማምረት አቅሙን መጨመሩና ከአርሶ አደሮች ጋር በጋራ መሥራቱ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ቡና ላይ አተኩረው ከሚሠሩ መገናኛ ብዙሃን ጋር መሥራቱ ለኩባንያው እድገት የራሱን አስተዋፅኦ አብርክቷል።
የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ እንደሚሉት፤ የቡና ኢንዱስትሪ የሀገሪቱ ትልቅ ኢኮኖሚ ከመሆኑ አኳያና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትም ጉልህ ድርሻ ያለው በመሆኑ በዚህ ረገድ ኩባንያው እንደ አንድ የቡና ላኪ የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል። ይሁንና በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ውጣውረዶች ያጋጠሙት ሲሆን፤ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የሎጀስቲክ ችግሮች በተለይ የኮንቴነርና መርከቦች ማጣት ችግር አጋጥሞታል። የቡና ፖሊሲዎች በየጊዜው መቀያየርም በተመሳሳይ ኩባንያውን ፈትኖታል።
በአሁኑ ወቅት ግን በመንግሥት በኩል ዘርፉን ለማሳድግ የተወሰዱ በርካታ ዕርምጃዎች አሉ። እነዚህ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ቢሆኑም ታዲያ በረጅም ጊዜ ያለውን የዘርፉን ሁኔታ ያገናዘበም መሆን ይኖርበታል። ዘርፉ ተጨባጭና ዳታ ላይ መሰረት ያደረገ መሆንም ይጠበቅበታል። ከዚህ አኳያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተቋማትም በዚህ ጉዳይ ላይ ሊሠሩ ይገባል። ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሠራበት አሁን ካለበት በበለጠ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ የጎላ መሆን ይችላል።
ኩባንያው ከሌሎች ተፎካካሪ ቡና ላኪ ኩባንያዎች ልቆ ለመገኘት በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ይጠቅሳሉ። በሀገር ውስጥ ያልተሞከሩ አዳዲስ ሃሳቦችንና የወጪ ንግድ ገበያ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል። ለአብነትም ውድ ቡናዎችን ወደ ውጭ ሀገር ሲልክ ታግ /መለያ/ በቡናው ማሸጊያ ላይ ያደርጋል። ይህም በችርቻሮ የሚገዛው አካል የቡናውን ታግ ስካን በማድረግ ምንጩንና ዓይነቱን በቀላሉ ለማግኘት ያስችለዋል። በአሠራር ደረጃም ፈጣንና ቀልጣፋ አሠራር እንዲኖር በየዕለቱ ከጥራት ቁጥጥር ክፍል ጋር በቅንጅት ይሠራል። በዚህም ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለመዋዠቅ ቡናን ከሚያቀርቡ ጥቂት የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ውስጥ አንዱ ለመሆን በቅቷል። በረጅም ጊዜ ሂደትም ያልተሞከሩ የቡና እርሻዎችን ለማከናወን እያቀደ ነው።
በቀጣይም ኩባንያው በቡና ላይ ይበልጥ አተኩሮ በመሥራት በአዳዲስ ሀገራት ላይ ተደራሽነቱን የማስፋት ፍላጎት አለው። ያለውን የቡና ጥራት ጠብቆ የማስቀጠልና የማስፋት ውጥንም አለው። የሠራተኞቹን ቁጥር ማሳደግ፤ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አዲስ የኤክስፖርት ፋሲሊቲ ጣቢያ የመክፈት እቅድም ይኖረዋል። በይርጋለም ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሼድ ተረክቦ ቡናን በማቀነባበር ለውጭ ገበያ የማቅረብ ራዕይ ይዟል። በሰዓት ስድስት ቶን የኤክስፖርት ቡና የማበጠር አቅሙን ወደ 15 ቶን የማሳደግም ሃሳብ አለው።
በሌላ በኩል ደግሞ ኩባንያው በረጅም ጊዜ ሂደት ቡናን በማቀነባበርና እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ ይዞ እየተንቀሰቃሰ ይገኛል። በቡናው ኢንዱስትሪ የሚታየውን የተማረ የሰው ኃይል ችግር ለመቅረፍም በዚህ የትምህርት ዘርፍ ውስጥ ገብቶ የመሥራትና የቡና ትምህርት ማዕከል የማቋቋም ፍላጎት አለው። ይህም በኩባንያው በኩል ከቡና እርሻ ጀምሮ አስከ መጨረሻው የቡና ምርት ውጤት ድረስ ያለውን ተሞክሮ ለሌላው ማጋራት ያስችለዋል። ይህም እንደተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፤ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎም ይታሰባል።
እአአ ከ2006 ጀምሮ ቡናን ወደ ውጭ ሀገር እየላከ የሚገኘው ዳዬ ቤንሳ በቆየባቸው አስራ አምስት ዓመታት ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል። አንዳንዴም ተስፋ አስቆራጭ ዓመታትን አሳልፏል። ሆኖም ተስፋ ሳይቆርጥ በጥንካሬ በመገስገሱ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ ችሏል። በጣት ከሚቆጠሩ ሠራተኞች ተነስቶ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩና ቡና የሚልክባቸውን ሀገራት መዳረሻ በማሳደግ የወጪ ንግድ አቅሙን ማሳደጉ የውጤታማነቱ ማሳያ ነው። ቡና አምራቾችን በፋይናንስ በመደገፍ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉና የባንክ ብድር እንዲያገኙ ማመቻቸቱ ብሎም ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገባቱም የውጤቱ ሌላኛው ማሳያዎች ናቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ የሁለቱ ወንድማማቾች የጋራ ጥረት ለኩባንያው ውጤት የአንበሳውን ድርሻ ወስዷል።
በዚህ አጋጣሚም የኤክስፖርት ማናጀሩ አቶ ከንአን አሰፋ የሁለቱ ወንድማማቾችን ጥረት በአርያነት በመውሰድ በተለይ ወጣቶች በዚህ የቡና ዘርፍ ላይ ገብተው እንዲሠሩና ውጤት እንዲያመጡ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ። በቡናው ንግድ ዘርፍ ረጅም ዓመታት የቆዩትም ለወጣቶች ያላቸውን ልምድና እውቀት ማካፈል እንዳለባቸውም ያሳስባሉ። በዚሁ ዘርፍ የሰለጠኑ ባለሞያዎችን አሰልጥኖ ማፍራት የሚችል ጠንካራ ተቋም ቢኖር ዘርፉን ይበልጥ ማዘመንና ማሳደግ እንደሚቻልም ይጠቁማሉ። ለዚህም መንግሥት የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ያመለክታሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2013