የተወለዱትና ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ካቴድራል እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤቶች ነው የተከታተሉት። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ትምህርት ክፍል ገብተውም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ቢሾፍቱ በሚገኘው አየር ኃይል ውስጥ ተቀጥረው ለአራት ዓመታት በህክምና ሙያ አገለገሉ። ይሁንና በሀገሪቱ የመንግሥት ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ ሥራውን ለማቋረጥ ተገደዱ።
ለጥቂት ወራት ሥራአጥ ሆነው ከቆዩ በኋላ እቤት መቀመጣቸው ያሳሰባቸው እናታቸው የግላቸውን ሥራ የሚጀምሩበትን ሰባት ሺ ብር ይሰጧቸዋል። ያንን ብር ይዘውም ከጓደኞቻቸው ጋር በመተባበር ዩኒቲ የተባለ አነስተኛ የቋንቋ ትምህርት ቤት ከፈቱ። ከዚሁ ጎን ለጎንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ ጤና ትምህርት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠሩ። ውጤታቸው ጥሩ ስለነበረም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት የማህበረሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ውስጥ በመምህርት የሚያገለግሉበትን ዕድል አገኙ።
ለአራት አመት ካገለገሉ በኋላ የውጭ ሀገር ነፃ የትምህርት ዕድል አገኙ። ይሁንና ለትምህርት ዕድል ብለው ወደ ውጭ ከሄዱ እያበበና እየጎለበተ የመጣው የቋንቋ ትምህርት ቤታቸው ይፈርሳል የሚል ስጋት አደረባቸው። በሌላ በኩል የመንግሥት ተቀጣሪ ሆኖ የመቀጠሉ ነገር ስላላሳመናቸው እያደገ የመጣውን ሥራ ማስቀጠል እንደሚገባቸው ያምናሉ። ጭራሹንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥራቸውን ለቀው በሙሉ መንፈስና አቅም ዩኒቲን የማሳደጉ ሥራ ላይ ተጠመዱ። በሰባት ሺ ብር የተጠነሰሰችውን ይህችን አነስተኛ የትምህርት ተቋም እየዋለ ሲያድር ዘርፏን በማስፋት ወደ ኮሌጅነት ብሎም ወደ ዩኒቨርሲቲ ማሳደግ ቻሉ።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የግል ዩኒቨርሲቲ በመክፈት ፈርቀዳጅ የሆኑት እኚሁ ሰው ታዲያ በግል ቀርቶ በመንግሥት ደረጃ የማይደፈሩ የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት በርካታ ምሁራንና ተመራማሪዎችን ማፍራት ችለዋል። በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግባት ያልቻሉ ኢትዮጵያንን ተስፋ በመፈንጠቅ ረገድም ስማቸው ጎልቶ ይነሳል። ከመማር ማስተማር ሥራው ባሻገርም ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን እድገት የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ከመክፈት ጀምሮ ‹‹ዕለታዊ አዲስ›› ጋዜጣና እና ‹‹ማይ ፋሽን›› የተባለ መፅሔት በማዘጋጀት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል። እንዲህ እንደአሁኑ ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋበት ከ15 ዓመት በፊት የዲጂታል ገበያ ፅንሰ-ሃሳብን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ረገድም ፈርቀዳጅ ሆነዋል።
በተለይም የአፍሪካን አማዞንና አሊባባን የመሰለ የዲጂታል ኩባንያ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ለመክፈት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር ለማስገባት ከፍተኛ ሥራ የሠሩት እኚሁ ሰው ታዲያ ይህ ሃሳባቸው በነበረው መንግሥት ብዙም አልተወደደላቸውም። ለነበረው መንግሥት የማያጎበድዱና አድርባይ ባለመሆናቸውም በእሳቸው ስር ያሉ ተቋማት ስር ሁሉ በጥርጣሬ መታየት ጀመሩ። በአንዳንድ የመንግሥት አመራሮችና አስፈፃሚዎች በየነገሩ ሁሉ ጉቦ እንዲሰጡ የሚቀርብላቸውን ጥያቄ ‹‹አሻፈረኝ›› በማለታቸው ምክንያት በሰበብ ባስባቡ ተቋሞቻቸው በወንጀል የሚጠየቁበት ሁኔታ ተፈጠረ።
ክስና ማሳደዱ እየዋለ ሲያድር በመጠንም በስፋትም ጨምሮ ብዙ ዋጋ የከፈሉለትን የትምህርት ተቋም መሰረት ማናጋት ቻለ። አላፈናፍን ያላቸው ብልሹ አሠራር የነበረው መንግሥት እስካልተቀየረ ድረስ እንደማያሠራቸው ተገነዘቡ። እናም የልጅ ያህል ዋጋ ከፍለው ያሳደጉትን የትምህርት ተቋም ለማዳን ሲሉም ራዕያቸውን ለማስቀጠል አቅም አለው ብለው ላመኑት ሚድሮክ ኩባንያ አሸጋግረው አገራቸውን ጥለው ተሰደዱ።
በዱባይና አሜሪካ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ላለፉት አስር ዓመታት የቆዩት እንግዳችን በውጭ ሆነውም በሀገሪቱ የነበረውን ሥራ እንዲነሳና የሽግግር መንግሥት እንዲመጣ ታግለዋል። ዲያስፖራውን ያሳተፈ ምክር ቤት ከፍተውም የበኩላቸውን ጥረት ቢያደርጉም ውጭ ድረስ የዘለቀው በብሄርና በቋንቋ የመከፋፈል አድማስ ልፋታቸውን አመከነባቸው። በዚህ ግን ተስፋ አልቆረጡም፤ ዩኒቲ ውስጥ ተጠንስሶ የነበረውን የዲጂታል ቴክኖሊጂና ማርኬት ጉዳይ መላውን የጥቁር ህዝብ ሊጠቀም የሚችል ኩባንያ ከአንዳንድ በጎ አሳቢ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን አቋቋሙ።
በአሜሪካ የተመሰረተውን ”ብላክ ኢኮኖሚ ኤክሰለንስ” እና መሰረቱን ኢትዮጵያ ያደረገውን፤ ”ፐርፐዝ ብላክ” በመወከል ነው። በአሜሪካ በ135 ሰዎች የተመሰረተው ይህ ድርጅት፤ በአሜሪካ ህጋዊ መሰረት ያለውና በርካታ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሆነው የመሰረቱት የመጀመሪያው ትልቅ የንግድ ድርጅት ነው። ”ብላክ ኢኮኖሚ ኤክሰለንስ” የሥራ መሰረታቸውን አሜሪካ በማድረግ፤ በተለያዩ አገራት የጥቁር ህዝቦችን መዋዕለ ንዋይ ከፍ እንዲያደርጉ፤ የንግድ ግብይታቸውንም እርስ በርስ በማስተሳሰር፤ የጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚሠራ ተቋም ነው። ይህ ተቋም በቦርድ የሚተዳደር እና ከአርባ በላይ ዳይሬክተሮችን ያካተተ ሲሆን፤ ከምስረታው ጀምሮ ላለፈው አንድ ዓመት በዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር ፍስሃ እሸቱ
የሥራ መሪነት የውስጥ ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል። ይህ ተቋም ቀደም ሲል የተነሳበትን ዓላማ መሰረት በማድረግ፤ በተለያዩ አገራት ለመቋቋም ጥናት ካደረገ በኋላ፤ የመጀመሪያውን የጥቁር ህዝብ የኢኮኖሚ ትስስር ለመመስረት፤ መነሻውን አዲስ አበባ ኢትዮጵያ በማድረግ፤ ”ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ” የተባለውን የአክስዮን ማህበር፤ በኢትዮጵያ የንግድ ህግ መሰረት አስፈላጊውን ምዝገባ ፈጽሞ የሥራ እንቅስቃሴውን ጀምሯል። በዚህና በህይወት ገጠመኞቻቸው ዙሪያ ውይይት አድርገናል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ኮሌጅ መስራች እንደመሆንዎ በወቅቱ በመንግሥትና በህዝቡ በኩል የነበርዎ ተቀባይነት ምን ይመስል እንደነበር ያንሱልንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ዶክተር ፍስሃ፡– ኮሌጁን በሁለት እግሩ ለማቆም በነበረው ውጣ ውረድ ውስጥ ብዙ ተማሪዎቻችን ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ዩኒቲ በዚያ ደረጃ እንዲያድግ የተማሪዎቻችን ሚና ከእኛ ያልተናነሰ ነበር። ስለዚህ በዚህ አጋጣሚ ታማሪዎቻችንን ማመስገን እፈልጋለሁ። እንደሚታወቀው ዩኒቲ ከተጀመረ በኋላ ወደኮሌጅነት የማሳደጉ ሃሳብ ሲመጣ የግል ኮሌጅ እንዲቋቋም የሚፈቅድ ህግ ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም። ከዚያ በፊት የነበረው የደርግ መንግሥትም ኮሚኒስት ስለነበር የግል የትምህርት ተቋማት እንዲቋቋሙ አይፈቀድም ነበር። የመንግሥት ህግ መኖሩም ሆነ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡም ደረጃ ያልተለመደ በመሆኑ ቶሎ ተቀባይነት ማግኘቱ ትልቅ ፈተና ነበር። ምክንያቱም በዚያ ወቅት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ትምህርት ይሰጥ የነበረው በመንግሥት ነበር። ስለዚህ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የራሱ ችግር ነበረው። እናም ያንን ሁሉ ውጣ ውረድ ማለፍ ነበረብን።
በተለይም አዳዲስ ፕሮግራሞች ሲጀመሩ ፍቃድ ለማግኘት በመንግሥት በኩል የነበረው ቢሮክራሲ በጣም አታካች ነበር። ብዙውን ጊዜ እንዳውም እኛ ቀድመን እንጀምርና እነሱን መጎተት ሌላ ሥራ ሆኖብን ነበር። ለምሳሌ ቋንቋን ያየሽ እንደሆነ እኛ ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ፈረንሳይኛ አረብኛ እናስተምር ነበር። ከዚያ ቀጥለን የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት ጀመርን። በመቀጠልም መሰረታዊ ህግ ጀመርን። በነገርሽ ላይ መሰረታዊ ህግ ትምህርት የጀመርነው እኛ ፈልገንና አቅደን አልነበረም።
በህግ መማር የሚፈልግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በመኖሩ ጭምር ነው። እኛ በመሰረታዊ ደረጃ የህግ ትምህርት እንስጥ ብለን የሦስት ወር ስልጠና ስንሰጥ ተማሪዎቹ ጣማቸውና ‹‹አንወጣም›› አሉ። እሺ ብለን ለስድስት ወር ቀጠልን። ከዚያ ዘጠኝ ወር ደረሰ። በኋላ ግን በመንግሥት በኩል ጥያቄ ይነሳብናል ብለን ተማሪዎቹን በጉልበት አባረርናቸው። የሚገርምሽ የምክር ቤት አባላት የሆኑ በርካታ ተማሪዎች ስለነበሩን ትምህርቱ ቢያንስ በዲፕሎማ ደረጃ እንዲሰጥ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ብዙ ትግል አደረጉ። በመጨረሻ ላይ በዲፕሎማ ደረጃ እንድናስተምር ተፈቀደልን።
ከዚያ በኋላ አዋጆች መሻሻል ጀመሩ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራትና ምደባ የሚባለው ተቋም ተቋቋመና ነገሮች መለወጥ ጀመሩ። ያም ቢሆን ግን አዳዲስ ፕሮግራሞች መጀመራቸው ውጣ ውረዱ ብዙ ነው። በተመሳሳይ አራተኛው መንግሥት የሚባለውን የጋዜጠኝነት ሙያ ለማሳደግ ሚናችንን እንወጣ ብለን የጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ለመክፈት ስንነሳ ከፍተኛ ችግር አጋጥሞን ነበር። በነገራችን አዳዲስ ትምህርት ክፍል ስንከፍት መመዘኛችን ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን ጥቅም ከግምት ውስጥ አስገብተን ነው። ከዚህ አኳያ ፈር ቀዳጅ እንደመሆናችን አዳዲስ ፕሮግራሞችን ለመጀመርን በጣርን ቁጥር ብዙ ጦርነት በሚል ደረጃ ችግሮችን አሳልፈናል።
አዲስ ዘመን፡- ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን የህትመት ሥራዎችን ታከናውኑ ነበር። በተለይም ”ዕለታዊ አዲስ‘ እና ”ማይፋሽን‘ የተባለ ጋዜጣና መፅሔትንም በማሳተም ከፍተኛ እውቅና አግኝታችሁ ነበር። ይህንን ሥራ በድንገት ያቋረጣችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?
ዶክተር ፍስሃ፡- እንግዲህ እንደትምህርት ተቋም ሁሉንም ያከለለ ሥራ መሥራት እንዳለብን አምናለሁ። ከዚህ አኳያ ብዙዎች ፍስሃ አንድ ነገር ጀምሮ ያቋርጣል ይሉኛል። ግን እኔ የምጀምራቸው ብዙዎቹ ሥራዎች ዝም ብዬ ለመጀመር ብዬ አይደለም። እኔ የማምነው የትምህርት ተቋማት ከማስተማርና ምርምር ከማከናወን ባሻገር ህብረተሰቡን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል። ህብረተሰቡን ማገልገል ሲባል ደግሞ በብዙ መልኩ ነው። አንድም በበጎ ፍቃድ አልያም በገንዘብ እናገለግላለን።
አይተሽ እንደሆነ ብዙዎቹ የምንጀምራቸው ነገሮች ከማንም በፊት ህዝቡን ያነቁና ጥልቅ ዓላማ ያላቸው ናቸው። ለምሳሌ ካነሳሁልሽ የኦንላይ (በይነ መረብ) ትምህርት ማንም ሳይጀምር ነበር ከዛሬ 15 ዓመት በፊት የጀመርነው። ኢ-ኮሜርስ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ የሚባሉና በርካታ ፕሮጀክቶችን ጀምረን ነበር። እንዳልኩሽ የምንጀምረው ህብረተሰቡን ይጠቅማሉ በምንላቸው ዘርፎች ያሉትን ክፍተቶች በማየት ነው። ከዚህ አኳያ ሚዲያ ላይ ትልቅ እምነት ነበረኝ። ለዚህም ነው ‹‹እለታዊ አዲስ››ን ብቻ ሳይሆን ‹‹ማይፋሽን›› የተባለ በፋሽን ኢንዱስትሪው የመጀመሪያው ደረጃውን የጠበቀ መፅሔት ማሳተም የጀመርነው።
‹‹እለታዊ አዲስ›› ጋዜጣ ሥራውን ሲጀምርም እንዳው ሙገሳውን ለመውሰድ ሳይሆን ጋዜጠኛን ያስከበረ ተቋም ነበር ማለት እንችላለን። ከዚያ በፊት አንድ ጋዜጠኛ የሚከፈለው ከ800 ብር አይበልጥም ነበር። በመሰረቱ ጋዜጠኝነት እንደሙያም አይታይም ነበር። ከመንግሥት ተቋም ውጪ በግሉ ዘርፍ ጋዜጠኛው ዋጋ አይሰጠውም ነበር። እኛ ስንጀምር በአምስትና ስድስት ሺ ብር ጣሪያ ደሞዝ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነው እንከፍል የነበረው። ጋዜጣውም ደግሞ እኛ በጀመርንበት መጠንና ደረጃ የጀመረ አልነበረም። አብዛኞቹ አሁን ድረስ ታብሎይድ ናቸው።
እኛ ግን በብሮድ ሽት ደረጃ በየቀኑ የሚታተም 30 ገፅ የነበራት ጋዜጣ እናሳትም ነበር። እንደምረዳውም አሁንም ድረስ በግል በየቀኑ በዚህ ደረጃ የሚያሳትም የለም። ይህ ጋዜጣ መጀመሩ በራሱ ለዘርፉ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ባይ ነኝ። በሌላ በኩል የዚህ ጋዜጣ መከፈት ከጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል የሚወጡ ተማሪዎቻችን የሥራ ዕድል ይሰጣል። በመማር ማስተማር ሂደትም ተማሪዎች የተግባር ልምምድ እንዲደርጉ ዕድል ሰጥቷል።
ያም ቢሆን ግን አንዳንድ ጊዜ የጀመርሻቸው ነገሮች ሁሉ በጀመርሽበት ሁኔታ አይቀጥልም። በዚያ ጊዜ ታስታውሺ እንደነበረው ህወሓት በሁለት የመሰንጠቅ አደጋ አጋጥሞት ነበር። እናም ይህ በሚሆንት ጊዜ ጋዜጣው ብቻውን የተቋቋመ አልነበረም። ከዩኒቲ ጋር የተቆራኘ እና የሺዎችን ህይወት የያዘ ተቋም ነው። ጋዜጣው ደግሞ በከፊል ነፃ ሆኖ የተደራጀ ቢሆንም በዩኒቲ በጀት የሚንቀሳቀስ ነበር። የህወሓት መከፋፋል ሲፈጠር ጋዜጣው ሊዘግብበት የነበረበት አካሄድ በጋዜጣውና በተቋሙ አመራሮች መካከል ውዝግብ አስነስቶ ነበር።
የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች በጋዜጣው የሚወጡ ነገሮች ከጋዜጣው እይታ ብቻ መሆን እንደማይገባው አመነ። ምክንያቱም በጋዜጣው የሚወጡ ዜናዎች ዩኒቲንም ይጎዳል የሚል ስጋት ነበራቸው። በተለይም የትኛው ወገን እንደሚያሸንፍ በማይታወቅበት ሁኔታ ትንሽ እንኳን ስህተት ቢሠራ በቀጥታ ተቋሙ ላይ ነው ተፅዕኖ የሚፈጥረው። ስለዚህ በዚህ ጊዜ ሊወጣ አይገባም የሚል ነገር ሲወጣ ጋዜጣው ላይ የነበሩ አባላት ደግሞ ‹‹ከሙያው መርሆ ጣልቃ ገባችሁብን›› በሚል ትልቅ ውዝግብ ውስጥ ተገባ። ተቋማዊው ጦርነት እየተካራረ ሄዶ መጨረሻ ላይ ጋዜጣውን የማስቆም ውሳኔ መጣ።፡ እናም በአጠቃላይ የነበረው ሁኔታ ይህንን ይመስል ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቲን የአፍሪካ ሀርባርድ ወይም ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የማድረግ ራዕይ እንደነበሮት ይታወቃል። ሆኖም ልክ አንደጋዜጣው ሁሉ ዩኒቨርሲቲ ማበብና መስፋፋት በጀመረበት ወቅት ሁሉንም እርግፍ አድርገው በመተው ለሌላ አካል አሰልፈው ሰጥተዋል። ይህ የሆነበትስ ምክንያት ምንድን ነበር?
ዶክተር ፍስሃ፡- በጥቅሉ በመንግሥት በኩል በተቋሙ ላይ ይደረግበት የነበረው ጫና ከአቅሜ በላይ ስለሆነብኝ ነው ጥዬው ለመውጣት የተገደድኩት። እንዳልሽው ተቋሙ ያተርፍ ነበር። መንግሥት ቢደግፈው ኖሮ ደግሞ ማትረፍ ብቻ ሳይሆን ለመንግሥት በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገባ የሚችል በአፍሪካ ላይ ስመጥር የሆነ የትምህርት ማዕከል ሊሆን ይችል ነበር። አስቀድሜ እንደገለጽኩልሽ ከዛሬ 16 ዓመት በፊት እኛ የኦን ላይን(በይነ መረብ) ትምህርት ስንጀምር ማንም አያውቀውም ነበር።
ይህም እኛ ያለ ጊዜችን ፈጥነን መጥቀን መሄዳችንን ነው የሚያስረዳው። ተማሪዎች ከአውሮፓ ከአሜሪካ ሰብስበን ነበር ስናስተምር የነበረው። ወዲያውኑ ነበር ያስቆሙን። እኛን አስቁመው እነሱ ግን የደቡብ አፍሪካውን ዩኒሳን በመንግሥት ተቋም ውስጥ እንዲገባ አደረጉ። ይህ አካሄድ ግን ፈፅሞ ፍትሐዊ አልነበረም። እንዳውም ሀገርሽ ውስጥ እንዲህ አይነት ሃሳብ ሲመነጭ ማበረታታት ነበር የሚገባው።
በኦን ላይን (በይነ መረብ) ልናስተምራቸው የነበሩትን ተማሪዎች ብናስቀጥል ኖሮ ከቡና ያልተናነሰ የውጭ ምንዛሬ ያስገባ ነበር። ምክንያቱም ለሰው ርካሽ በሆነ ሁኔታ ከብዛት ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ ነበር ልናስገባ የምንችለው። በተመሳሳይ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ግዙፍ ፕሮጀክት አቅደን ነበር። ከ29 የአፍሪካ ሀገራት ጋር ተፈራርመን፤ በዓለም ላይ ያሉ ቀዳማዊ እመቤቶችን ለመጋበዝ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረን፤ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ጋርም ተስማምተን ውጭ ሀገር ጥሪ ለማድረግ ዝግጅት ለማድረግ ስንነሳም በድጋሚ አስቆሙን።
አዲስ ዘመን፡- ለዚህ ደግሞ ምን ነበር የተሰጣችሁ ምክንያት?
ዶክተር ፍስሃ፡– እዚህ አገር እኮ የፖለቲካው ደጋፊ ያልሆነ ሁሉ እንደተቃዋሚ ነው የሚቆጠረው። መሃል ላይ መሆን አትቺይም። በዚያ ላይ ገንዘብ ካለሽ በደረሽበት ሁሉ ጉቦ እንድትሰጪ ትጠየቂያለሽ። እኛን ከልክለውን ሲያበቁ ሌላው ደግሞ ዝም ብሎ ዲግሪ ሲያትም ዝም ይባላል። ምክንቱም በጉቦ ነበር ሁሉ ነገር የሚሠራው። ጉቦ ካልሰጠሸ ሁሉም ይጠምድሻል። እዚያው ትምህርት ሚኒስቴር ላይ የነበሩ ሰዎች ጉቦ አታመጣም ተብዬ በግሌ ብዙ ነገር ደርሶብኛል። አምስት ሳንቲም አልሰጥም ስትፈልጉ ዝጉት ነው ያልኳቸው። ከዚያ በኋላ ትኩረት ያደርጉብሽና የተለያዩ ክልከላዎች ይጥሉብሻል። መንቀሳቀስ እንዳትችይ ሽባ ያደርጉሻል። እኛ በርካታ ወጣት ቦዘኔ ሆኖ ለአገር እና ለወላጅ ሸክም ከሚሆን ትምህርት ቤት የሚገባበትን ዕድል ማመቻቸታችን እንደወንጀል ነበር የታየብን።
እንዳልሽው እኛ በጀመርንበት ፍጥነት ብንጓዝ ኖሮ አይደለም በኢትዮጵያ የአፍሪካ ሃርቫርድ እናደርገው ነበር። የምንጀምራቸው ፕሮጀክቶች መንግሥት ቢደግፋቸው ኖሮ ያለጊዚያቸው የተወለዱ ቢሆኑም እንኳን ዛሬ ሁሉም ተጠቃሚ በሆነ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱ ‹‹anything on ethiopia›› ዲጂታል ቢዝነስ ስርዓት ጀምረን ነበር። እኛ ስንጀምር አሁን ላይ ግዙፍ የሆነው አማዞን ገና ሥራ የጀመረበት ወቅት ነበር።
የእኛም ቶሎ ባያጨናግፉብን ኖሮ ዛሬ የት ሊደርስ እንደሚችል ማሰብ አይከብድም። ወደ ኋላ ሄደሽ ስታስቢ በጣም ነው የሚያንገበግበው። የተጀመሩ ፕሮግራሞችን ሲዘጉ፣ ሲዘጉ መጨረሻ ላይ መቀጠል ከባድ ነው የሆነብን። ደግሞስ ምንም እንኳ የትምህርት ተቋም ቢሆንም የንግድ ተቋም እንደመሆኑ ፕሮግራሞች ሁሉ ሲዘጉ ድርጅቱን ማስቀጠል የማይቻል ነው የሆነው።
እርግጥ ነው፤ በወቅቱ የነበረው መንግሥት ዓለማ የነበረው ዩኒቲን በሰበብ አስባቡ እንቀፋት በመፍጠር ከስሮ እንዲዘጋ ማድረግ ነው። ስለዚህ ችግሩ ከእኔ ጋር ከሆነ ለሌላ አቅም ላለው ሰው አስተላልፎ መሄዱ ግድ የሆነበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ያ ደግሞ ለእኔ በጊዜው በጣም የሚያም ውሳኔ ነበር። ስለሱ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ማውራትም አልፈልግም ነበር። ለመጠቃትትኩረት ከተደረገብሽ ተቋሙን አሳልፈሽ መስጠት ነው የሚጠብቅሽ። አለበለዚያ ደግሞ ከተቋሙ ጋር ተያይዘሽ ገደል መግባት ነው ዕጣፈንታሽ። እናም በዚያ ሰዓት እኔ ብልሃት የተሞላበት አካሄድ እንደተከተልኩ ነው የሚሰማኝ። ምክንያቱም ተቋሙ ከሚዘጋ እኔ ጥዬላቸው ብሄድ ነው የሚሻለው።
አዲስ ዘመን፡- አሁንም ድረስ በግል ኮሌጆች እንዳይሰጡ የተደረጉ የትምህርት ክፍሎች አሉ። ይህ ለዘርፉ እድገት የሚኖረው አሉታዊ ሚና ምንድን ነው? እንደምክንያት የሚነሳው የጥራት ጉዳይስ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችስ ምሉዕ ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ፍስሃ፡– አድሏዊነት ለየትኛውም የቢዝነስ ተቋም ጠቃሚ አይደለም። ጥራት መጠየቅ ያለበት በግል ተቋም ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችም ጭምር ነው። ምንያህሎቹ የመንግሥት ተቋማት ናቸው አስፈላጊውን ግብዓት አሟልተው እና በጥራት ትምህርቱን የሚሰጡት? የሚለው ነገር አሁንም አጠያያቂ ነው። ገና የተመረቁ ተማሪዎች መምህር በሚሆኑበት አገር ውስጥ ሌላው ከውጭ አገር ጥሮ ግሮ ከመጣ በኋላ አታስተምርም የሚባል ነገር አይገባኝም። ሁለተኛ አንድን ነገር ገድበሽ እንዳይሠራ ከማድረግ ይልቅ ያንን ነገር እንዲሠራ ድጋፍ ማድረጉ ነበር የበለጠ ለሁሉም ጠቃሚ ይሆን የነበረው።
በዓለም ላይ የህግ ትምህርት ቤቶች የት ነው ያሉት? አብዛኞቹ የግል ተቋማት ናቸው። አሜሪካ ውስጥ ምርጥ የሚባሉት የመንግሥት ኮሌጆች ሁለት ወይም ሦስት ቢሆኑ ነው። የተቀረው በሙሉ የግል ኮሌጅ ነው። ከዚህ አኳያ የመንግሥት ተቋም ስለሆነ ብቻ ጥራት ያለው ትምህርት ይሰጣል በሚለው አስተሳሰብ አልስማማም። ሌሎች አገልግሎቶችን በጥራት ከግሉ ዘርፍ ካገኘን ከትምህርት የማይገኝበት ወይም የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው። በእኔ እምነት አብዛኛው ነገር የራሱ ሌላ የፖለቲካ ተፅዕኖ አለው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ምሳሌ ልስጥሽ ፤ ፍርድ ቤት የሥራ ማስታወቂያ ወጣና የእኛ የህግ ተማሪዎች እንደማንኛውም ተመራቂ ተወዳዳደሩ። ከወጣው 23 ቦታ ውስጥ አንድ ተማሪ ብቻ ከሌላ ተቋም አለፈ፤ ሁሉም የዩኒቲ ተማሪዎች ነበሩ። ከዚያ ‹‹ ፍስሃ ጉቦ ሰጥቶ ፈተናውን አስወጥቶ ነው እንጂ ይህንን ያህል ተማሪ ሊያልፍ አይችልም›› ተባለና እንደገና ፈተናው እንዲሰጥ ተደረገ። እንደገና ሲፈተኑ ጭራሹኑ አንድ ተማሪ ተጨምሮ ሁሉም በጥሩ ውጤት አለፉ። ስለሆነም በወቅቱ የተቀጠሩት በሙሉ የዩኒቲ ተማሪዎች ነበሩ።
እናም ያ ነገር ነገ ፍርድ ቤት የሚዳኙት ዜጎች ነፃ አዕምሮ ያላቸው፣ ገልለተኞች ከሆኑ አደጋ ይሆኑብናል የሚል ስጋት ፈጠረ። ነፃና በሙያው ስነ-ምግባር የሚሠራ ዜጋ አይፈለግም ነበር። ለእነሱም ለእይታቸው ጥሩ አልነበረም። እንደዚህ ዓይነት ነገር አይወደድም። ሌላ አጋጣሚ ልንገርሽ፤ አየር መንገድ ከግል ኮሌጅ የመጡ ተማሪዎችን አንቀበልም አለ። እኛ ደግሞ ትልቅ ክርክር ፈጠርን። አሳማኝ የሆነ ምክንያት እንዲሰጡን ሞገትናቸው። እነሱም በትምህርቱ ጥራት እምነት እንደሌላቸው ሲነግሩን የማትተማመኑ ከሆነ እንደማንኛው ኢትዮጵያዊ ተማሪ ዕድሉን ስጧቸውና ይፈተኑና ይውደቁ፤ ስንላቸው ‹‹አሻፈረን›› አሉ። ከዚያ በኋላ እንከሳለን ስንል በመጨረሻ እንዲወዳደሩ ፈቀዱላቸው። በዚያ ጊዜም በሙሉ ተማሪዎቻችን አለፉ። ከዚያ በኋላ አየር መንገድ በቀጥታ ነው የእኛን ተማሪዎች መቀበል የጀመረው።
ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቲ የሥራ ላይ ልምምድ ማንኛውም ተቋም ሳይጀምር ነው የጀመረው። ከተቋማት ጋር ነፃ አገልግሎት እንዲሰጡ ተፈራርመን ነው ስንሠራ የነበረው። በዚያ ምክንያት ብዙ ተማሪዎቻችን ገና ሥራ ሳይጨርሱ ነው ይቀጠሩ የነበሩት። እንደዚህ ዓይነት ዳይናሚክ አስተሳሰቦች እዚህ አገር አይወደዱም። ከነበረው ስርዓት ወጣ ስትይ ‹‹አፈንጋጭ›› ነው የምትባይው እንጂ ‹‹አዲስ ሥራ ፈጣሪ›› ተብለሽ አትበረታቺም። በዚያ ላይ ደግሞ ሙስናው ሲጨመር ወደ ፊት አስበሽ ለመሥራት ትቸገሪያለሽ።
አዲስ ዘመን፡- ከትምህርቱ ባሻገር በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት የሚሻ አንድ ባለሀብትስ ምቹ ሁኔታ አልነበረም?
ዶክተር ፍስሃ፡– እውነት ለመናገር መጀመሪያ ላይ ጥሩ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ለሚደረጉልሽ መልካም መስተንግዶዎች እውቅና መስጠት አለብሽ። ሁሉም ነገር መጥፎ ነበር ማለት አትቺይም። ለምሳሌ ጥሩ ከነበሩት ነገሮች አንዱ ለዩኒቲ ከሌላው በተለየ መልኩ ቦታ ተሰጥቶታል። ሌሎች ተቋማት ያላገኙትን ሰፊ መሬት አግኝተናል። እርግጥ ነው፤ የዚህ መሬት ጉዳይ ሦስት ዓመት ፍርድ ቤት አከራክሮናል።
ሆኖም ግን መሬቱ ታስቦ መሰጠቱ መንግሥትን የሚያስመሰግነው ጉዳይ ነው። አንድአንድ ጊዜ ደስ ሲላቸው ከቀረጥ ውጪ እቃ እንድናስገባ ይፈቅዱልናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይከለክሉናል። በተለይም ወደ መጀመሪያ አካባቢ ያው መንግሥትም ጀማሪ ስለነበር ኢንቨስትመንት ከማበረታታት አኳያ ትልቅ ነገር ነው። በዚያው ልክ ደግሞ ሙስናው አያፈናፍንም። ያም ደግሞ ጥሩ የሚሠሩትን ተስፋ ያስቆርጣል። መዋቅሩ በሙስና ስለተያዘ ዲግሪ የሚሸጡ ተቋማትን የፈጠረበት ሁኔታ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- እርሶዎ ከነበርዎት ሰፊ ራዕይ አኳያ ዩኒቲን የተረከቡት አካላት አስቀጥለውታል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ፍስሃ፡– እግዚአብሄር ይመስገን ሰዎቹ ዩኒቲን ከነስሙ አስቀጥለውታል። እርግጥ ነው፤ በርክክቡ ወቅት አንድ ቃል የገቡልኝ ነገር ቢኖር ስሙን ይዘው እንደሚቀጥሉ ነው። ያን ቃላቸውን በመጠበቃቸው በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። ከዚያ ባሻገር አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲውን ሳየው ብዙ ነገር ነው የሚሰማኝ። እኔ ብይዘው ኖሮ ትልቅ ደረጃ መድረስና መስፋት ይችል ነበር ብዬ አስባለሁ። ምንክንያቱም አንደነገርኩሽ ራዕዩ ብዙ ነበር። በእነዚያ ፕሮጀክቶች ትልቅ ከተማ ነው ለመገንባት የታሰበው። እነዚያን ነገሮች ስታያቸው ብዙ መሥራት እየተቻለ ያ ሳይሆን በመቅረቱ ቅር ይላል። ከውጭ ሳልፍ ሳየው ሕንፃ መሠራቱን ለማየት ችያለሁ። ግን ካላቸው ሀብት አንፃር ከዚህ በላይ ሊያደርሱት እንደሚችሉ አምናለሁ። ምንአልባት ወደፊት ሊያደርጉት ይችሉ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- አንድ ወቅት ወደ ፖለቲካ ተቃውሞ ገብተው ነበር። ወደዚህ የገቡበት ምክንያት ከዚህ ተገፍተው በመሄድዎት ብሶት የወለደው ነው ማለት ይቻላል?
ዶክተር ፍስሃ፡- እንዳልሽው ነው፤ የተገፋ ሰው ሁልጊዜ ሁለት ምርጫ ነው ያለው። አንደኛው መገፋቱን አምኖ እና ተቀብሎ ኢትዮጵያ ስለምትባለው አገር መስማትም፤ ማየትም አልፈልግም ብሎ ብዙ ሰው ፊቱን አዙሮ የሚኖርበት ሁኔታ አለ። እንደእኔ ያለው ደግሞ ቁጭት ያለበትና እስከመቼ ነው ይህች ሀገር በዚህ ሁኔታ የምትቀጥለው? ብሎ ቁጭት አድሮበት የሚችለውን አስተዋፅኦ ለማርከት የሚጣጣር አለ። ከዚህ አኳያ እኔ የማምንበት ነገር ለማድረግ ሞክሪያለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ብዙ ለሀገራቸው አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉ ዜጎች ከሀገራቸው እየተገፉ፤ እየታሰሩ፤ እየተሰደዱ መቀጠል የለባቸውም የሚል ነው።
እኔ ከዚህ እንደሄድኩ ያደረኩት ነገር ብዙዎች እንደሚውቁት የኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ምክር ቤትን ማቋቋም ነው። ዓላማው የነበረው ከዚህ በኋላ የዚህችን ሀገር ዕጣ ፈንታ መወሰን የሚኖርብን በጋራ ስንቆም ነው የሚል እምነት ነበረኝ። በእርግጥ በወቅቱ ምክር ቤት ሲባል አንዳንዶች ‹‹የመንግሥት ነው›› እያሉ ሲቀልዱ ነበር። ግን እውነታው ዝም ብሎ በደመነፍስ ከመሄድ ይልቅ ተመካክረን በግብታዊነት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ነው።
ለውጥ መምጣት የሚችለው ደግሞ ህዝብ ስላመፀ ሳይሆን በታቀደ መልኩ ሽግግር ሲፈጠር ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ሁሉንም ያካተተ ስርዓት እና ሂደት እንዲፈጠር አድርገን ነበር ለሦስት ዓመት ሙሉ ጊዜዬን እዚያ ላይ ነበር አሳልፍ የነበረው። ከዚያ በኋላ ደግሞ የነበረው ሁኔታ ባሰብኩት ልክ ሊያራምደኝ አልቻለም። በሌላ በኩል አገሪቷ ውስጥ ያልጠበቅናቸው ነገሮች መፈጠር ጀመሩ። የእኛ ባህል የነበረው መከባበር፣ መቻቻል አንድነት እየተሸረሸረ መጣ ፤ ፈሪሃ እግዚአብሄር ጠፍቶ መተራረድና መጨፋጨፍ ብሎም ሬሳ እያቃጠሉ መጨፈር ተጀመረ። ኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ሁኔታ ሰቅጣጭ ሁኔታ መታየት ጀመረ። የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ ደግ ህዝብ ነበር፤ ይህ ነገር እንዴት ሊመጣ እንደቻለ አይገባኝም። ለእኛ ይህ የልዩነት አካሄድ አያዋጣንም። ይልቅ ለእኛ ዳቦ የሚሆነንን፤
ከችግር፣ ከመናቅ፣ ከመዋረድ፣ ከስደት የሚያወጣን ነገር አንድነታችን ነው ብለን እንቅስቃሴ ጀመርን። እርግጥ እኔ በግሌ እንደማንኛው ሰው ይህችን ሀገር ዓይኗን አልይ የማለት ምርጫው ነበረኝ። ያለው ተጨባጭ ሁኔታም ያንን እንድታደርጊ ነው የሚያስገድድሽ። እንደምታውቂው ለኑሮ የሚያስፈልግሽን ለመግዛትና እዳዎችሽን ለመክፈል ሁለትና ከዚያ በላይ ሥራ መሥራት ይጠበቅብሻል። ከዚያ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ጊዜ ቆጥቤ ወገኔና አገሬን ልርዳ ማለቴ ለዚህች ሀገር ያለኝን ፍቅር ነው የሚያሳየው። በግሌ ቁጭት ነበረብኝ። ለውጥ ማምጣት እንችላለን ብዬ ነበር ወደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የገባሁት። ነገር ግን ሂደቱ ቀላል አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡-ከአንዳንድ ዲያስፖራዎች ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው የነበረበት ሁኔታ ነበር። ይህ አለመግባባት ቀደም ብለው ካነሱት ጉዳይ ጋር ምን ግንኙነት ነበረው?
ዶክተር ፍስሃ፡- ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ ምንአልባት ሰው አይገዳደል እንጂ ውጭ ሀገር ያለው መከፋፈልም የዚያኑ ያህል ነው። እኔ ለአገር ከመቆርቆር የመነጨ እንጂ የትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ስለነበርኩበት አይደለም ያንን ምክርቤት ለማቋቋም የሞከርኩት። የሚገርምሽ እንኳን እንደዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ ገብተሸ ይቅርና በሃይማኖት ውስጥ እንኳን በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ መከፋፋል ይፈጠራል። ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የቤተክርስቲያን ግንባታ ተጀምሮ፣ ጉድጓዱ ተቆፍሮ እንደገና ተጣልተው፣ ተደባድበው ሲያበቁ አባቶች ሲሰደቡ አይቻለሁ። አሁን ያ ግንባታ ሊከናወንበት የነበረው ሰፍራ ጉድጓዱ ተደፍኖ የመኪና ማቆሚያ የሆነበት ሁኔታ አለ። እናም ማህበረሰባችን እዚህ ብቻ ሳይሆን በሰው ሃገርም ሆኖ በሃይማኖት በዘር ተከፋፍሏል። ተመካክሮና ተወያይቶ ነገሮችን ከመፍታት ይልቅ ሁሉም በየአቅጣጫው የራሱን አጀንዳ ብቻ ለማራመድ ሲጥር ታይዋለሽ።
እርግጥ የነበረውን ስርዓት የሚደግፉ በርካታ ሰዎች ነበሩ፤ እነሱ ራሱ ስለሀገር በጋራ እንዳንሠራ ጠላት የሆኑበት ሁኔታ ነበር። ከዚያ ባሻገር ደግሞ የተሻለ ሃሳብ ይዘሽ ስትመጪ በዚያ የሚናደድ ሰው አለ። የእኛ መጥፎ ባህሪ ደግሞ ከመሬት ተነስቶ በማታውቂው ሰው ጭምር መቅናት ነው። ግን ይህ አልነበረም የቀድሞው ባህላችን። በዚያ የተነሳ ብዙ ችግር ነበር። እንዳውም ከዚያ በኋላ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጌ ነው የተውኩት። ምክንያቱም ስድስት ዓመት ሞከርኩት፤ ግን አልተሳካም። ስለዚህ መተው እንዳለብኝ አመንኩኝ። እንደሚባለው ደግሞ ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም። ሞከርኩ፤ ሞከርኩ ግን የሚሰማኝ ካላገኘሁ እንደእብድ ከግንብ ጋር መላተም የለብኝም ብዬ ተውኩት። እናም ላለፉት ሁለት ዓመታት ምንም ነገር ውስጥ አልገባሁም። በዚህ አጋጣሚ ቤተሰቦቼን በጣም ስለጎዳሁኝ ወደ ራሴ ኑሮ መመለስ አለብኝ ብዬም ነው ወደዚህ ዓይነት ውሳኔ ላይ የደረስኩት።
አዲስ ዘመን፡- ልክ እንደእርስዎ ለሀገር የሚጠቅም ሃሳብ እና ራዕይ ይዘው የሚመጡ ሰዎችን ማበረታትና መደገፍ ያለመቻሉ እንደሀገር ምን አስቀርቶብናል ይላሉ? ካለፈውስ ስህተታችን እንዴት ነው መማር የምንችለው?
ዶክተር ፍስሃ፡- ጥያቄው ካለፈው ስህተታችን እንማራለን ወይ? የሚለው ነው። እርግጥ ነው፤ ብዙ ማሰብና መመራመርን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም። ፍላጎት ብቻ ነው ሊኖረን የሚገባን። ግን ሁሉም ሰው እኩል ሊያስብ አይችልም። ብዙ ሰው ወጣ ብሎ የማየት ፍላጎት የለውም። አንዳንዱ ደግሞ የዕለት ኑሮ ለመወጣት ብቻ ነው የሚሮጠው። ሌላው ሰው አሳቢና መንፈሳዊ ቅንዓት ያለበትና አገሩን ለመለወጥ የሚጥር ነው። በእኔ በኩል አዳዲስ ነገሮችን የማምጣቱ ነገር ከፈጣሪ የተሰጠኝ ፀጋ ነው ብዬ ነው የማምነው።
በነገራችን ላይ ዓለም የተቀየረው ሁሉም ሰው ተሰብስቦ ስለተወያየ አይደለም። ጥቂጥ ሰዎች ናቸው ተነስተው ዓለምን የቀየረ ታሪክ መሥራት የቻሉት። እነዚህ ሰዎች ሌላው ዓለም ላይ ሀብት ወይም እንቁ ናቸው። ይከበራሉ፤ ይደገፋሉ። በአንፃሩ ግን እንደእኛ ዓይነት ሀገር ውስጥ እንደጠላት ነው የሚቆጠሩት። አዲስ ሃሳብ ይዘሽ ስትመጪ ትጠያለሽ፤ ትሰደጂያለሽ። በዚህ ረገድ እኛ ዩኒቲን ስንጀምር ያልተባልነው ነገር የለም። ይሄ ነው ወደኋላ የሚያስቀረን።
በአጠቃላይ ለእኔ ይሄ ነገር እንደበሽታ ነው። ይህንን በሽታ ልናክም ካልቻልን አገራችንን መለወጥም ማሳደግም አንችልም። ቀና የሚስቡ አዲስ ፈጠራዎችን የሚመጡ ሰዎችን ከመግፋት ይልቅ ተንከባክበን ልንደግፋቸው ይገባል። ነገር ግን ያሰቡት ነገር ግቡን እንዲመታላቸው ልናግዛቸው ካልቻልን ወደኋላ እየሄድን እንመጣለን። ሰው የሚያድገው አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ፤ ዓለም የሰለጠነችበትን መንገድ በሚያሳዩ ሰዎች ነው። በዚህ አገር ግን እድገት የሚታሰበው በመስረቅ፣ በማጭበርበር በጉቦኝነት ነው። የሚያስለፋ ነገር በሰዎች ዘንድ አይመረጥም። ይልቁንም አቋራጩን ነው የሚፈልገው። ግን ይህ መንገድ የትም አያደርስም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- አንድአንድ ሰዎች ‹‹ዶክተር ፍስሃ የጀመረውን ነገር አይጨርስም›› በማለት ያነሳሉ፤ ይህ የመጣው ቶሎ ተስፋ የመቁረጥ ሥነልቦና ስላልዎት ነው?
ዶክተር ፍስሃ፡– ምክንያቱ ሁለት ነገር ነው። አንድም በራሴ፤ ሁለትም በውጭ በሚደረግብኝ ግፊት ነው። እንደ እኔ ዓይነት ሰዎች ቅብጥብጦች ናቸው። ሁልጊዜ አዲስ ነገር ማየት ይፈልጋሉ። እንደሌላው ሰው አንድ ነገር ላይ ተረጋግቶ መቆየት አልችልም። ይህ የተፈጥሮ ባህሪ ነው። አዳዲስ ሃሳቦች እንዳመነጭ አድርጎ ነው ፈጣሪ የፈጠረኝ ብዬ አምናለሁ። ግን ደግሞ የጀመርኩትን ነገር እንዳላስቀጥል ከውጭ ኃይል ተፅዕኖ የሚደረግብኝ ነገር አለ። መሰናከል ሲፈጠርብኛና ምንም ማድረግ የማልችልበት ሁኔታ ሲፈጠር እኔም እንደ ማንኛውም ሰው ተስፋ የምቆርጥበት ሁኔታ አለ። ያንን ትቼ ግን ዝም ብዬ አልቀመጥም። አዳዲስ ሃሳብ ይመጣልኛል። አዲስ ነገር እጀምራለሁ። እንዳልሽው ግን ይህንን ሁኔታ ከውጭ ሆኖ ለሚያየው ሰው ጀምሮ የማቆም አባዜ ያለብኝ ነው የምመስለው። ግን የማቆመው ያለምክንያት አልነበረም።
እንደነገርኩ ከመጀመሪያው ጀምሮ የምጀምራቸው ነገሮች ለሀገር ይጠቅማሉ ብዬ የማስባቸው ጉዳዮችን ነው። ለምሳሌ ‹‹ናሽናል ፔይመንት›› ብለን የጀመርነውፕሮጀክት ነበር። ይህ ፕሮጀክት እንደ መብራት ውሃና ቴሌ የመሳሰሉትን ክፍያዎች በአንድ ላይ በማጣመር ታስቦ የታቀደ ነበር። ይህም በቴክኖሎጂ አማካኝነት የሚከፍል ስርዓት ለማምጣት የሚያስችል ነበር። ሆኖም ስንት መዋለንዋይ ካፈሰስንበትና ተፈራርመን መጨረሻ ደረጃ ከደረስን በኋላ ተከለከልን።
ሌላ ምሳሌ ላክልልሽ፤ አሁን ላይ በመላው ሀገሪቱ የተንሰራፋው ሞባይል ባንኪንግ ስርዓት እኛ ከ16 ዓመት በፊት ነው ሃሳቡን ያመነጨነው። ግን ይህም በመንግሥት ይቁም ተባለ። ታዲያ ፍስሃ ከዚህ በላይ ምን ማድረግ ይችላል? የሚገርምሽ ለማይፋሽን መፅሔት ብቻ ሁለት ዓመት ነው ፍርድ ቤት የተመላለስኩት። ፍርድቤት ከፈረደልኝ በኋላ ደግሞ በሌላ ወንጀል ከሰውኝ ፍርድ ቤት ያመላልሱኝ ነበር። አንቺ በእኔ ቦታ ብትሆኚ ምን ልታደርጊ ትቺይ ነበር? እንደ ወንጀለኛ ቀን ተቀን ፍርድ ቤት መመላለሱ በራሱ በጣም አታካች ጉዳይ ነበር። ይህ በራሱ ህሊና ላይ የሚፈጥረው ነገር አለ። እናም ብዙ የጀመርኳቻው ነገሮች በዚህም፤ በዚያም እንዲቆሙ ይደረጋል። አብዛኞቹ ነገሮች ብታይው እኔ ፈልጌ ያቆምኳቸው ነገሮች አይደሉም። ሁሉም ነገሮች በነበሩበት ፍጥነት ቢቀጥሉ ኖሮ የት በደረሱ ነበር።
እኛ የሚቻለንን ያህል ከመንግሥት ጋር ተጋፍጠናል፤ ማንም ግን ከጎናችን ከመቆም ይልቅ መተቸት ላይ ነበር የተጠመደው። እኔ ግን ፈጣሪ አዲስ ሃሳብ እስከቸረኝ ድረስ መሞከሬን አላቆምም። ደግሞም በዓለም ገናና የሆኑ ሰዎች አንድ ሺ ጊዜ ሞክረው ነው የሚሳካላቸው። አንቺ አንድ ሺ ነገር ሞክረሽ የሚያማሽ ሰው ግን ግማሽ ነገር አልጀመረም። ያ ነው ችግሩ። የነበረውን ሁኔታ እንዲህ የሚሉ ሰዎች ቢረዱልኝ ደስ ይለኛል። እኔስ ብሆን የምጀምረውን ነገር ችግር ካላጋጠመኝ በስተቀር ለምንድን ነው የማቆመው? እናም ተጀምረው የቆሙት ነገሮች ሁሉ እኛ ፈልገን ሳይሆን እኛ ተገደን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በሌላ ሚዲያ ላይ ቤተሰቦትን ሳያዩ ለረጅም ዓመታት መቆየቶትን ገልጸዋል። ለመሆኑ ወደሀገርዎት ተመልሰው ለመምጣት ያልቻሉበት ምክንያት ምንድን ነው?
ዶክተር ፍስሃ፡– እኔ እኮ ወደ ሀገሬ መግባት አልችልም ነበር። አንደኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክር ቤት እንዲቋቋምና የነበረው መንግሥት እንዲወርድ ስሟገት ቆይቼ በምንም አግባብ ወደ ሀገሬ እንድገባ ይፈቀደልኛል ተብሎ አይታሰብም። የነበረው ስርዓት ትክክል አልነበረም፤ ሁሉንም አቀፍ የሆነ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ብለሽ መንግሥት ሊወደው አይችልም። እሱ ብቻ አይደለም፤ ፓስፖርቴን ቀምተውኝ አምስት ዓመት ሙሉ አልሰጡኝም። አሁን ዶክተር ዐብይ ከመጣ በኋላ ነው የተሰጠኝ። እናም ልምጣ ብል እንኳን መምጣት የምችልበት ሁኔታ አልነበረም።
አባቴን በዚህ ጊዜ ውስጥ ነው ያጣሁት ፤ አልቀበርኩትም። አንቺ በእኔ ቦታ ብትሆኚ ምን ይሰማሻል? እኔ እስከአሁን ድረስ የማይወጣልኝ ነገር ነው። ምንም ቢሆን አባትን ያህል ነገር ሳላስታምምና ምርቃቱን ሳላገኝ መሞቱ ከልብ የሚወጣ አይደለም። ይህንን ሁኔታ ያለፈበት ሰው ነው ሊውቀው የሚችለው። ትንሹን ልጄን አሁን ነው ያየሁት። እናም ለእኔ ከባድ ነገር ነው። ብመጣ ኖሮ የሚያጋጥመኝ እስር ቤት መግባት እንደሆነ የታወቀ ነገር ነው። ያ ደግሞ ለማንም አይጠቅምም።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ የዚህ ለውጥ መምጣት የልፋቶት ውጤት ነው ማለት እንችላለን?
ዶክተር ፍስሃ፡- ለለውጡ የራሴን ትንሽ አስተዋፅኦ አድርጊያለሁ ብዬ ነው የማምነው። የሚቆጨኝ ነገር የለም። እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚቻለኝን ያህል ሞክሪያለሁ። አሁን ላይ ከምንም በላይ ተስፋ አለ፤ ይሄ ተስፋ ደግሞ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል። እርግጥ ነው ብዙ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ። አሁን በሄድንባቸው ሁለትና ሦስት ዓመታት ባይደረግ ብዬ የማምንባቸው ጉዳዮች አሉ። ከዚህ አኳያ ደግሞ መተቸት አልፈልግም ብዬ ላለፉት ሦስት ዓመታት ዝም ብዬ ነው የተቀመጥኩት። በመሰረቱ እኔ ከዚህ በኋላ ፖለቲካ ውስጥም መግባት አልፈልግም።
እኔ በፊትም ቢሆን ትግል አደርግ የነበረው እንደአንድ ዜጋ እንጂ የፖለቲካ አባል ሆኜ አይደለም። የማንም የፖለቲካ ድርጅት ርዕዮተ-ዓለም አቀንቃኝ አልነበርኩም። ስለሽግግር ሂደት ስታነሺና የነበረው ስርዓት ይቀየር ብለሽ ስትናገሪ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብለሽ ነው። ይህ ደግሞ አንድ ዜጋ ያለው መብት ነው። ዶክተር ዐብይ ጥሩ የማይሠራ ከሆነ ያንን መናገር እንደጠላት የሚያስወስድሽ ከሆነ ችግሩ እንደዚህ ከሚያስበው እንጂ ከአንቺ ሊሆን አይችልም። እርግጥ ነው፤ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን ማንም አልከለከለኝም። በፊትም አልነበርኩም፤ አሁንም አይደለሁም።
አሁን ላይ የለውጡን መምጣት ተከትሎ ጥሩ የቢዝነስ ከባቢ አየር ተፈጥሯል። በዚህ በተፈጠረው ሂደት ውስጥ ደግሞ እኛ አዲስ ፕሮጀክት ይዘን መምጣት ችለናል። ብላክ ኢኮኖሚክ ቢዝነስን ወደ ኢትዮጵያ ይዘን የመጣነው ብዙ ፍጭት አድርገን ነው። ይሄ ሥራ ትልቅ ሃሳብ ያለው ነው። የጥቁር ህዝቦችን ማንነት፤ ህልውና ክብር ለማስመለስ ታቅዶ የገባንበት ነው። ለእኛ ከቢዝነስም በላይ ተልዕኮ ያለው ነው። ይሄ ታሪካዊ ሂደት ነው። በነገራችን ላይ ይህንን ፕሮጀክት ሩዋንዳ ላይ ለማምጣት ተሞክሮ ነበር።
ለነገሩ ከኢትዮጵያ በተሻለ ቢዝነስ ለመሥራት በሚያስችሉ አገራት ይዘን መሄድ እንችልም ነበር። እኛ ግን ይህንን የታሪክ አጋጣሚ ለማንም አሳልፈን አንሰጥም ብለን ሀገሪቱ ውስጥ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም ሞክረን እንየውና ካልተሳካልን እና ህዝቡ አልቀበልም ካለ ወደ ሌላ አፍሪካ አገሮች ይዘን እንሄዳለን ብለን ነው አምንን የመጣነው። ለዚህ ደግሞ በለውጡ የተፈጠረው ሁኔታ አበረታቶናል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ፕሮጀክት ምን ምን ዓይነት ሥራዎች ነው ለመሥራት የታቀደው? የትኛውንስ የህብረተሰብ ክፍል ነው ተጠቃሚ የሚያደርገው?
ዶክተር ፍስሃ፡- በነገራችን ላይ ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋመው ዝም ብሎ ግንጥል ጌጥ ሆኖ አይደለም። ትልልቅ ራዕዮች ያሉት ግዙፍ ድርጅት ነው። ይህንን ራዕይ የወለደውም ብላክ ኢኮኖሚ ኤክሰለንሲ ነው። ይህም ማለት ጥቁር ሆኖ በነጩ ዓለም መኖር ባመጣው ቁጭት ነው የፈጠረው። ሁላችንም ጥቁሮች እንደመሆናችን አሜሪካ ውስጥ ስንኖር ብዙ ችግር ይደርስብናል። በተለይ ዶናልድ ትራምፕ ከተመረጠ በኋላ ጥቁሮች ላይ የሚደርሰው በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው የመጣው። አሜሪካ በጥቁሮች ላይ የሚፈፀምን በደል ካልኖርሽበት አትረጂውም።
እኛ ኢትዮጵውያን ደግሞ የቀኝ መገዛት ጣዕምን ስለማናውቀው እዛ የሚፈፀመውን ነገር ስንመለከት አዲስ ነገር ነው የሚሆንብን። በየሜዳው ጥቁሮች ላይ ያለው እንግልት፣ ኋላቀርነት በጣም ነው የምታዝኚው። በኮቪድ 19 እንኳን በብዛት የተጠቃው ጥቁሩ ማህበረሰብ ነው። በሌላም ዓለም የሚሰደደውም ጥቁሩ ማህበረሰብ ነው። እናም ፐርፐዝ ብላክ ይሄ በጥቁሮች ላይ የሚደርሰው ንቀትና ውርደት እስከመቼ ድረስ ነው የሚቀጥለው? ለምን አንድ ነገር አንሠራም? በሚል ትልቅ ሃሳብን ሰንቆ የተነሳ ድርጅት ነው። እናም ሃሳቡ የሚያጠነጥነው ጥቁሮች እስከዛሬ ድረስ የተበዳይነት አስተሳሰብ ይዘው፤ሌላው እኛን መካስ አለበት የሚለው አስተሳሰብ ምንም አልጠቀመም። ምክንያቱም እስከአሁን የካሳቸው የለም። ይህንን ሃሳብ ይዘው ወደፊትም ቢቀጥሉ የትም አይደርሱም። በሌላ በኩል ድህነታችንን በፀጋ እንድንቀበለው ተደርገናል። አጠቃቀሙን አላወቅንበትም እንጂ ደሃ አይደለንም። በመሆኑም አሁን ላይ ድህነትን ከአቀፍንበት አባዜ መላቀቅ አለብን።
አሜሪካ ውስጥ ብቻ ጥቁሮች 1 ነጥብ 1 ትሪሊየን ዶላር ወጪ ያደርጋሉ። ላባቸውን አንጠፍጥፈው ይለፉና ለሌሎች ያስረክባሉ። ይሄ ሁኔታ መቀጠል የለበትም። እኛ ጥቁሮች ድሃ አይደለንም። በዓለም ላይ ላለው የጥቁር ሀብት አንድ ላይ ቢሰባሰብ የኢኮኖሚው መሪ እንሆናለን። አንቺ ‹‹ደሃ ነኝ›› ብለሽ ቁጭ ካልሽ ደሃ ሆነሽ ትቀሪያለሽ። በዓለም ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይሄ ነው። የእኛ ድርጅት ይህንን ነባራዊ ሁኔታ እንለውጥ ብሎ ነው የተነሳው። ደግሞም ወደድንም፤ ጠላንም በዓለም ላይ ገንዘብ ከሌለሽ አትከበሪም።
ማንም ዞር ብሎ አያይሽም። ስለዚህ እኛ ለመሥረት የተነሳነው ስርነቀል የሆነ ኢኮኖሚያው ለውጥ ለማምጣት ነው። በነገራችን ላይ ችግሩ ገንዘብ የማጣት፤ ያለማጣት ጉዳይ ሳይሆን አጠቃቀሙን ያለማወቃችን። ስለዚህ ለዚያ የሚሆን ሞዴል ቀይሶ ነው ብላክ ኢኮኖሚክስ የተነሳው። ግቦቹ አራት ናቸው። በመላው ዓለም አንድ ቢሊዮን የሚሆን የጥቁር ህዝብን የሚለውጥ ሥራ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ለመፍጠር ነው። የጥቁር ህዝብ ብዙ እንደመሆኑ በትንሽ ጠጠር ልታፈርሺያት አትቺዬም።
በመሆኑም በዚህ ድርጅት አማካኝነት የጥቁር ህዝቦች የጋራ ሀብት የሆነውን በዓለም ዙሪያ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር የጋራ ሀብት እንዲፈጠር እንጥራለን። ያ የጋራ ሀብት ማለት አቅም ማለት ነው። አቅም በኖረን ቁጥር ግዙፍ ኮርፖሬሽኖች መፍጠር እንችላለን። ይህንን ስናደርግ ደግሞ ከሌሎቹ ጋር እኩል ሆነን የጥቁሩን ህዝብ መጥቀም ብቻ ሳይሆን ከሌላውም ዓለም ተጠቃሚ እንሆናለን። ከዚያ የሚፈጠረው ሀብት መልሰን እዚያው በማስገባት ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ሀብት እንፈጠራለን የሚል ነው ሦስተኛው ግባችን።
የመጨረሻው ደግሞ በዓለም ላይ የተበላሸን የጥቁሩ ገፅታ መቀየር ነው። ያበላሻው ደግሞ ስለጥቁር የሚያወራ ሚዲያ አለመኖሩ ነው። የጥቁሩን ማህበረሰብ መብት እና ማንነት የሚያስከበር ሚዲያ ያስፈልጋል ብለን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። እነዚህን ነገሮች ስናነሳ ደግሞ በቅድሚያ አሁን ላይ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ እንደመሆናችን ጥቁሩ የዚህ ተጠቃሚ አይደለም። ወደዚህ ስርዓት ጥቁሩን አስቀድመን ለማምጣት ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ገዢና ሻጭን ለማገናኘት የሚያስችል አሠራር መዘርጋት አለብን ብለን ነው የተነሳነው። ከዚህ ሃሳብ መነሻ ነው ፕርፐዝ ብላክ የተፈጠረው። ይህም የብላክ ኢኮኖሚ የመጀመሪያ ልጅ ሆነ ማለት ነው።
የፐርፐዝ ብላክ ኢኮኖሚ ዋና ዓለማው ኢ-ኮሜርስ ዘዴን ተጠቅሞ በአጠቃላይ ጥቁሩን ማህበረሰብ በጋራ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ነው። በተመሳሳይ ለነጩ ማህበረሰብ አማዞን አለ፤ ለቢጫው ማህበረሰብ አሊባባ አለ፤ ለጥቁሩ ማህበረሰብ ግን ምንም የለም። እኛ ያንን ክፍተት መሙላት አለብን በሚል ያንን ሥራ ለመሥራት ነው ያሰብነው። ይህንን ሃሳብ ይዘን የምንቀሳቀሰው እስከአሁን ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያውያን ነን። ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ሃሳቡን ደግፈውት መነሻ ገንዘብ አስተዋፅኦ ስላበረከቱ በዚያ ገንዘብ ነው ሥራው የተጀመረው። በነገራችን ላይ ይህንን ሥራ በተጨባጭ ተግባራዊ ማድረግ ያለብን አርሶአደሩ ላይ ነው ብለን ግብርናው ላይ ትኩረት አድርገናል።
ገበሬውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ከቻልን በርካታ ሚሊኒየር ገበሬዎችን እንፈጥራለን የሚል ትልም ነው ያለን። ለዚህ ደግሞ አርሶአደሩን በቀጥታ ለምንም ደላላ ማገናኘት የሚያስችል ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ገበሬ የልፋቱን ዋጋ እያገኘ አይደለም። ዓመቱን ሙሉ ለፍቶ ለደላላ ነው የሚያስረክበው። ተጠቃሚው ደላላው ነው። ማርኬት ፕሌስ ደግሞ እነዚህን ደላሎች ነው ከገበያው የሚያስወጣው። በአጠቃላይ የገበያ ሰንሰለቱንም ሙሉ ለሙሉ ያሳጥረዋል።
ከገበሬው ጋር ሠርተን ደግሞ ገበሬው ጥሬ አቅራቢ ብቻ መሆን የለበትም። እኛ ለገበሬው ኮንትራት ሰጥተነው የአቅራቢነት ሚና እንዲጫወት ነው የሚፈለገው። አቅራቢ ሲሆን ሁሌም ሥራ ይኖረዋል። እና ደግሞ ምርታማ የሚያደርጉትን ግብዓቶች ብናሟላለት የተሻለ ውጤታማ እናደርገዋለን። አይተሽ ከሆነ ደግሞ ገበሬው ሰሊጡን ሽጦ ዘይት ለመግዛት ፍዳውን ነው የሚያየው። ስለዚህ ይህንን ለማስቀረት ገበሬው ራሱ ሰሊጡንም ዘይቱንም የሚያመርትበት ሁኔታ ነው ለማመቻቸት የታሰበው። ከምርቱ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚ ድረስ ስርዓቱን ምቹ መደላደል መፍጠር ነው ዋና ዓላማችን። ከዚያ አግሮ ፕሮሰሲንግ እንሄዳለን። ወደ 50 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች ይኖሩናል። በኢንዱስተሪ የሚመረቱትንም በቀጥታ የምናስተላልፈው ራሳችን ነው የምንሆነው። አምስት ግዙፍ ሱፐር ማርኬቶች፣ አስር መካከለኛ ደረጃ ያሉ ሱፐር ማርኬቶች ፤ አንድ ሺ የማሰራጫ ጣቢያዎች ይኖሩናል።
በዚህ መሰረት እስከአሁን ድረስ 135 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ እየሠራን ነው ያለነው። ይሄ ታሪክ ለማንም አሳልፈን ይዘን መምጣት የለብንም ብለን ነው አገራችን ይዘን የገባነው። ከገበሬው ጀምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የዚህ አካል እንዲሆን እንቅስቃሴዎች ጀምረናል። በሚፈጠሩ ሥራዎች ገበሬው ብቻ ሳይሆን ወጣቱ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ይሆናል። ይህን ሞዴል ፕሮጀክት መሬት ላይ ለማውረድ የሚያስችል መዋለንዋይ ለማሰባሰብ የአክሲዮን ሽያጭ በቅርቡ ይፋ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ አርሶአደሩ ከቴክኖሎጂ ሩቅ ሆኖ ሳለ የኢ-ኮሜርስ እቅዳችሁ እንዴት ነው ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው?
ዶክተር ፍስሃ፡- ይሄ የኢ-ኮሜርስ ሥራ የፕሮጀክታችን አንዷ ክፍል ነው። እኛ ከዚያ በላይ ፋብሪካ ገንብተን ስንዴውን ወደ ፓስታ የመቀየር እቅድ ነው ያለን። አንቺ ያነሳሽው የቴክኖሎጂ ጉዳይ ብዙም የሚሳስብ አይደለም። አሁን ላይ ስልክ የማይጠቀም ገበሬ የለም። ደውሎ እቃ ማዘዝ ይችላል። መረጃ መለዋጥ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ብቻ ነው ከእኛ የሚጠበቀው። ደግሞም ከኢ-ኮሜርሱ ጎን ለጎን ምርቱን የሚያከፋፍልበት ግዙፍ ገበያ በአቅራቢያው ይከፈታል። በመሆኑም በተጨባጭ ገበሬው ተጠቃሚ ይሆናል። ቴክኖሎጂ ስንል ኢንተርኔት ላይ የተመሰረተ አይደለም፤ ስልክ የቴክኖሎጂ አንዱ አካል ነው። ስለዚህ በስልክ በቀላሉ መረጃ የሚለዋወጥበት፣ የሚገበያይበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ደረጃ እናንተ ተዘጋጅታችሁ ስትመጡ ከመንግሥት አካል ምን ዓይነት ተቀባይነት አገኛችሁ?
ዶክተር ፍስሃ፡- እንግዲህ ጫጉላ ላይ ፍቅር እንዳይሆንብን እንጂ በሚገርም ሁኔታ ነው የተቀበሉን። እኔ በጣም ነው የተደነቅሁት። አስቀድሜ የነገርኩሽን ነገሮች በሙሉ ለመሥራት ከአንድ ወር በላይ አልፈጀብንም። ፍቃዳችንን አግኝተናል። የተባለውን መስፈርት አሟልተናል። የሄድንባቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሁሉ በእሺታ ነው ቢሯቸውን ከፍተው የተቀበሉን። ባለፈው ሳምንት ፕሮጀክታችንን ስናስተዋውቅ ከ10 ድርጅቶች ጋር ነው የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረምነው። ሰሞኑንም በጋራ ለመሥራት ምክር ቤት እናቋቁማለን። በአጠቃላይ በመንግሥት ደረጃ እኔ በህይወት ዘመኔ እንደዚህ ዓይነት አቀባበል አላየሁም። አሁን የተደረገልን መልካም አቀባበል ወደፊትም አይቀየርብንም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ልክ አንደእርሶ ሁሉ በርካታ ኢትዮጵዊና ኢትዮጵውያን እውቀቱና አቅሙ ኖሯቸው ግን ደግሞ ዘዴውን ላላወቁ የዲያስፖራ አባላት ምንድን ነው የሚያስተላልፉት?
ዶክተር ፍስሃ፡– ዲያስፖራ አቅምና እውቀት እንዳለው ይታወቃል። ከዚያ አኳያ ለሀገሩ ሊጠቅም የሚችልበት ብዙ መንገድ አለ። እኛ ‹‹ዞሮ ዞሮ ለሃገር›› የሚል ዘመቻ ጀምረናል። ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ዲያስፖራው ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር በሪሚታንስ ይልካል። አብዛኛው ገንዘብ ግን ለእለታዊ ፍጆታ ይባክናል። እኛ አምስት በመቶውን እንኳን ወደ ኢንቨስትመንት ለማስገባት ነው ጥረታችን። በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ጋር በመሆን 250 ሚሊዮን ዶላር ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ነው ጥረት እያደረግን ያለነው። አንቺ እንዳልሽው መንገዱ ለጠፋውና ብቻውን መሥራት የማይችለው ሰው እኛ ተግባራዊ ልናደርገው ያሰብነው ፕሮጀክት ጥሩ ዕድል ነው የሚፈጥርለት። በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን መላው የአፍሪካ ህዝብ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ራሱንም ወገኖቹንም ይጠቅማል።
ሌላው መታሰብ ያለበት ጉዳይ ግን እንኳንስ ኢትዮጵያ ውስጥ አሜሪካም ቢሆን ቢዝነስ ስትጀምሪ ተግዳሮት ማጋጠሙ አይቀሬ መሆኑን ነው። ብዙ ሰው አሜሪካ አልጋ ባልጋ ይመስለዋል። ግን እውነታው ይህ አይደለም። ሁሉም ቦታ እንቅፋት ያጋጥማል። ስለዚህ በግሉ መጥቶም ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልግ ሰው አሁን ባለበት ሁኔታ በመጀመሪያ ታጋሽ ለመሆን መዘጋጀት አለበት። በተለይም ውጭ ያለነው ማህበረሰብ ኢትዮጵያን በመሰረተ ልማትም፤ በቴክኖሎጂም ቀድመው ከሄዱ ሀገራት ጋር ማወዳደር አይገባቸውም። ሌላው ይቅርና ከአንዱ አገር ሌላው ጋር ያለው ችግር ፈፅሞ የተለያየ ነው።
ስለዚህ ውጭ ያለው ዲያስፖራ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመጣ ተግዳሮት እንደሚያጋጥመው አስቀድሞ ሊገነዘብና ትዕግስት ሊኖረው ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ። በዚህ ረገድ እኛ ወደዚህ ስንመጣ ከሙስናው ጀምሮ ወደ 11 የሚጠጉ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙን አምነን ነው ቀድመን የተዘጋጀነው። ዛሬ ላይ በፈገግታ የተቀበለን የመንግሥት አካል ነገም በዚያው መልኩ ይቀጥላል ማለት ላይሆን ይችላል። ስለዚህ ዲያስፖራው ለሁሉም ነገር ልቡን አስፍቶ ነው መምጣት ያለበት። በአጠቃላይ እኔ የማምነው መጪው ጊዜ የአፍሪካ ነው። አሜሪካ ላይ ዛሬ ከስድስት በመቶ በላይ ትርፍ ማግኘት ብርቅ ነው። አፍሪካ ውስጥ ግን 100 በ100 ትርፍ የሚገኝበት ሁኔታ ሰፊ ነው። ስለዚህ ስጋቱንም ተቀብሎት ነው መምጣት ያለበት የሚል መልዕክት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ በአገሪቱ ላይ ያለው አጠቃላይ ፖለቲካ ሁኔታ በእርሶ እይታ ምን እንደሚመስል ይንገሩን እና ውይይታችንን እንብቃ?
ዶክተር ፍስሃ፡- እኔ ገና ከመጣሁ ጥቂት ቀናት በመሆኑ ብዙ መናገር አልችለም። ነገር ግን ውጭ ሆኜ እንደተረዳሁት ሀገራችን በጣም ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንዳለች ነው የምገነዘበው። በአሁኑ ሰዓት ምርጫ ተከናውኗል። የተመረጡት ሰዎች ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት አለባቸው። ህዝቡ ከእነሱ የሚጠብቅባቸው ሆኖ መገኘት ይገባቸዋል። እኛ ኢትዮጵያውያን ካለፈው ተሞክሯችን ልናማር ይገባል። ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመምጣት ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል። አሁን እዚህም እዚያም የሚታየው ግጭት መመለሻ ወደሌለው ችግር ውስጥ እንዳይከተን ሁላችንም ለሰላማችን መትጋትና ሰላማችንን መጠበቅ ይገባናል። በአጠቃላይ አገራችንን የምንወድ ከሆነ አሁን ያለንበት ሁኔታ ከምንም በላይ ወሳኝ መሆኑን ተረድተን ዋጋ ልንከፍል ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎችና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ፍስሃ፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2013