በምግብ ዘይት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል የሚታየውን ክፍተት ለማጥበብ በርካታ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። ባለፉት ሶስት ዓመታት በመንግስትና በግሉ ባለሀብቶች የጋራ ቅንጅት በርካታ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። በዚህም ግዙፍ ዘይት አምራች ፋብሪካዎች እንዲገነቡ እና የዘይት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ለመሸፈን አበረታች ስራ ተሰርቷል። ይሄም በአቅርቦቱ ዙሪያ መሻሻል አሳይቷል። ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ የህብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላትና የዘይትን ዋጋ ከተሰቀለበት ማውረድ አልተቻለም። በመሆኑን በመንግስት በኩል ትልቅ የቤት ስራ ሆኖ ቀጥሏል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ሰሞኑን የምግብ ዘይት አምራቾች ጋር ባጋጠሙ ችግሮች፣ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎችና የወደፊት አቅጣጫ ከማመላከት ጋር ተያይዞ ምክክር አድርገዋል። ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የምግብ ዘይት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው። ባለፉት ሶስት ዓመታት በማምረት ሂደት ላይ የሚገኙና ማጣሪያ ያላቸው የዘይት አምራች ፋብሪካዎች ብዛት ከ14 ወደ 30 ማሳደግ ተችሏል። የዘይት አምራች ፋብሪካዎች ዓመታዊ የማምረት አቅም ከ89 ሚሊዮን ሊትር ቶን ወደ አንድ ነጥብ 25 ቢሊዮን ሊትር እንዲያድግ ተደርጓል።
የአገሪቱ የዘይት ፍላጎት በሃገር ውስጥ ምርት ከአምስት በመቶ ወደ 40 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። ሆኖም ለዘይት ፋብሪካዎች አስፈላጊ የሆኑ የቅባት እህል አቅርቦት ችግር አልተፈታም። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ ድፍድፍ ዘይት ከውጭ ለማስገባት ተገዳለች። የምግብ ዘይት ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለው ልዩነት እንደሰፋ ቀጥሏል። በዚህም የተነሳ የዘይት ዋጋው በገበያ ማሻቀቡን ተከትሎ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የከተማ ነዋሪ ህይወቱን ለመግፋት እየተቸገረ ነው።
‹‹የዘይት ፋብሪካዎችን ማስፋፋትና ቁጥር ማብዛት ብቻውን እየተባባሰ የመጣውን የዘይት እጥረት እና የዋጋ መናር ለመቆጣጠር አያስችልም›› የሚሉት የምጣኔ ሀብት ምሁራን የፋብሪካዎችን ቁጥር በማብዛት ረገድ የተሰራው አመርቂ ስራ ግብዓት አምራች ኩባንያዎችን በማብዛት ረገድ ሊሰራበት ይገባል ይላሉ።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጣሰው ታደሰ እንደሚሉት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘይት ፋብሪካዎችን ቁጥር በማሳደግ ረገድ የተሰሩት ስራዎች አመርቂ ናቸው። አሁንም ሌሎች ፋብሪካዎችን ወደ ምርት ለማስገባት የሚደረገው ርብርብ ይበል የሚያሰኝ ነው። የፋብሪካዎች ቁጥር መብዛቱ ግብ በራሱ የዘይት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማመጣጠን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት አያስችልም።
የዘይት ፋብሪካዎች ቢቋቋሙም፤ ለፋብሪካዎቹ አስፈላጊ ጥሬ እቃዎችን የሚያቀርቡ ካምፓኒዎች በግብርናም ሆነ በሌሎች ዘርፎች እንዳልተስፋፉ የሚያብራሩት ዶክተር ጣሰው፤ ሰፋፊ የሰሊጥ እና የኑግ ማሳዎች በሌሉበት ከትናንሽ ገበሬዎች እየለቀሙ የዘይት ፋብሪካን ማቋቋምና ማንቀሳቀስ ብሎም የሀገሪቱን የዘይት ፍላጎትና አቅርቦት ማጣጣም አይቻልም ይላሉ።
ለፋብሪካዎቹ ግብዓት የሚሆን ሰሊጥ፣ ኑግ እና ሌሎች ሰብሎችን የሚያመርቱ የግል ኩባንያዎችን የማስፋፋት ስራ በአግባቡ ባለመሰራቱ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርት መግባት አልቻሉም። ዘይት አምራቾች ከፍተኛ መጠን ያለው ድፍድፍ የምግብ ዘይትን ጨምሮ አብዛኛውን ግብዓት ከውጭ ሀገር በማስገባት ለመጠቀም እየተገደዱ መሆናቸውን ያነሳሉ።
እንደ ዶክተር ጣሰው ማብራሪያ ግብዓትን ከውጭ በማስገባት የዘይት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም የሚደረገውን ጥረት ማሳካት የሚቻለው ለዘይት ፋብሪካ የሚያገለግሉ እንደ ሰሊጥ፣ ኑግ እና ሌሎችንም ምርቶች የሚያመርቱ ሰፋፊ ካምፓኒዎች በማስፋፋት ነው። በመሆኑም ሰፋፊ የሰሊጥ እና የኑግ የግብርና ማሳዎች ያስፈልጋሉ።
«ፋብሪካዎች ሲቋቋሙ ጎን ለጎን ጥሬ እቃ አምራችንም ማሰብ፣ ጥሬ እቃ የሚያመርቱ የግሉ ባለሀብቶችን ማበረታታት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም የዘይት ፋብሪካ ባለቤቶችን ከጥሬ እቃ አምራቾች ጋር ማስተሳሰር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። በቅባት እህል ምርት ላይ ለሚሰማሩ የግል ባለሃብቶች መሬት፣ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ በማቅረብ እንዲሁም አስፈላጊውን ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል »ይላሉ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ፤ የግብዓት እጥረት ችግርን መቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። በቀጣይ 10 ዓመታት በግብርና እና በአምራች ኢንዱስትሪው መካከል ጠንካራ የግብአት ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ ለምግብ ዘይት በግብአትነት የሚውሉ የቅባት እህሎችን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን የድፍድፍ ዘይት ለማስቀረት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራ በመስራትና ከግብርና ጋር ጠንካራ ትስስር መፍጠር ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ይህንን በዘርፉ የተሰማሩ ሀይሎችም ለሀገር ኢኮኖሚ ልዩ ትርጉም ያለውን ይህንኑ እቅድ እንደሚያሳኩት እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/ 2013