‹‹ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ›› ይሉት ብሂል ሆኖ በወርሃ ጥቅምት 2012 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ሀገር ሰላም ብሎ በተኛበት ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት ተፈጽሞበታል። ታዲያ የከሃዲዎች ድርጊት ያስቆጣው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አፀፋው ቀላል አልነበረም። በአጭር ጊዜም ከሃዲዎችን በመደምሰስ ከውስጥና እና ከውጭ ያለውን ጫና ተቋቁሞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስከበር ችሏል።
በወቅቱ የአሸባሪው ህወሓት ትንኮሳ ነገሩ ያላማረው የኤርትራ ሰራዊትም ወደ ድንብር መጠጋቱ የሚታወስ ነው። ሆኖም ጦርነቱ ፍፃሜ አግኝቷል። ያም ሆኖ ግን ከመከላከያ ሃይሉ ምት የተረፉት ጥቂት የአሸባሪው ቡድን አባላት በገደላገደል እየተሽሎኮሎኩ እዚህም እዚያም ጥቃት መሰንዘራቸውና ጥፋት ማድረሳቸው አልቀረም። ያም ሆኖ ግን በአሁኑ ወቅት እዚህም እዚያም ከተበታተነው ርዝራዥ ውጭ አቅም ያለው ሃይል በአካባቢው አለመኖሩን መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። በዚህም መሰረት ሰሞኑን የኢትዮጵያ ጦር ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በቀረበው ጥሪ መሰረት የክልሉ አርሶ አደር እርሻውን በሰላም እንዲያከናውን የእፎይታ ጊዜ ለመስጠት የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉ ይታወሳል።
ይህን የመንግስትን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ቻይና፣ አሜሪካ እና የአፍሪካ ህብረት በአዎንታ እንደሚመለከቱት ገልጸዋል። ሆኖም ግን አሸባሪው ህወሓት ተኩስ አቁም ብሎ ስምምነት የለም፤ እስከ ፍፃሜው ተያይዘን እንጥፋ እያለ ሲዝት ይሰማል። መንግስት ግን ነገሩን አስፈላጊ አይደለም ብሎ ሰራዊቱን ለሀገሪቱ አስፈላጊ ነው ብሎ ወደሚያምነው ስትራቴጂክ ቦታ አስቀምጧል።
ውሸት የለመደው አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ግን ግብአተመሬቱ ሙሉ ለሙሉ ካልተፈጸመ ውሸት ያደገበት ነውና ዛሬም ከተደበቀበት ዋሻ ሆኖ የውሸት ፕሮፓጋንዳውን አላቆመም። በአንድ በኩል መንግስት ተሸንፎ እንደወጣ ለማስመሰል ጥረት ሲያደርግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራንም ተከትሎ እንደሚወጋ እየዛተ ነው። ከዚህ ጸብ ዳቦው የሆነው ከዘመኑ እውነታ ጋር የተፋታው ይህ ቡድን አካሄዱ ሁሉ ወታደራዊም ፖለቲካዊም ያልሆነ የፈሪዎች በትር መሆኑ ታውቋል።
በጉዳዩ ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ‹‹ከስምንት ወር በፊት መቀሌ ስንሄድ የምናውቀውና የማናውቀው የሀብት ማዕከል ነበር፣ ዛሬ ላይ በተለየ መንገድ የሚታይ አይደለም ፣ በአሁን ላይ መቀሌ በወታደራዊ ዕይታ ምንም ነው፤›› ብለዋል። መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የገባው ህግን ለማስከበር ነው፤ የህግ ማስከበር ዘመቻው ዓላማ ትጥቃችንን ማስመለስና የሽብር ቡድኑ በሀገር ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ማምከን ነበር ሲሉም ተደምጠዋል። የአሸባሪው ህወሓት ዓላማ ማሸነፍ ሳይሆን አመድ ሆኛለሁና አብረን ተያይዘን አመድ እንሁን ነው ሲሉም አክለዋል።
መሰረተ ልማቶችን እየሰሩ ሰዎች ሞተዋል፣ እርዳታ እየሰጡ ተገድለዋል፣ አንድም ሰው ጥሩ ሰርታችኋል አላለም የሚሉት ዶክተር አብይ፤ ክሶች ነበሩ፤ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት በተሳሳተ መረጃ መንግስት የችግሩ ምንጭ ተደርጓል። ትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም ከወታደራዊ መስክ ውጭ ለተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና ቀለብ ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል ብለዋል። በየትኛውም መንደር ወታደር ሲሄድ ምንም ጠላት አያይም፣ ህዝብ ነው የሚያየው፤ ሰራዊቱ የክልሉን ነዋሪ ለመጠበቅ በሚያደርገው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው በሚጠብቀው ማህበረሰብ ውስጥ ከጀርባ እየተወጋ ነው ሲሉም የሀገር መከታ የሆነው መከለከያ በብዙ መንገድ እየተጎዳ ስለመሆኑም ይናገራሉ። የመከላከያ ሰራዊቱ እንዲወጣ የተደረገው ውሳኔ ህዝብም የሚበጀውን እንዲለይ የጥሞና ጊዜ ያስፈልገዋል፤ አርሶ አደሩም በተረጋጋ መልኩ ወደ ግብርና ስራው እንዲመለስ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሰሞኑ የታወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት እና ወታደሮችን ከመቀሌ የማስወጣቱ ሂደት በተመለከተ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ህወሓት ኤርትራ ተመልሳ ወደ ጦርነት እንድትገባ እየጋበዘ መሆኑንና ጠብ አጫሪነቱ እየለየለትና ወደባሰ ውጥንቅጥ የመግባት ፍላጎት እየጨመረ ነው።
የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ፤ ህወሓት የሽምቅ ውጊያውን ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ከመዋጋት ይልቅ ሕዝቡን ከፊት አድርጎ ሲዋጋ እንደነበር ገልጸው፤ ይህ እጅጉን አሳዛኝ እና በብዙ መንገድ አሳዛኝ እንደሆነ ዓለም እውነታውን የሚረዳበት ጊዜ ላይ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ‹‹ህወሓት መከላከያውን በዘር ነበር ያደራጁት። አሁንም በዘር ሲቀሰቅሱ የመጀመሪያቸው አይደለም›› ያሉት ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደሌ፤ የህዝብ ንብረት እንደተወሰደ በማስመሰል ህዝቡን ለማሳመን አሊያም ህዝቡን እየገደሉ በማስፈራራት ውጊያው ከህዝቡ ጋር እንዲሆን ቀይረዋል። የተለያዩ ቦታዎች ላይ በተለይም ደግሞ ተምቤን በተባለው አካባቢ ላይ ህዝቡ ከሀገር መከላከያ ጋር እንዲጋጭ እኩይ ስራቸውን በሰፊ መስራታቸውን አመልክተዋል።
እንደ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ፤ ቀደም ሲልም ህብረተሰቡን በማነሳሳት አስገድዶ በመድፈር፤ ለዘር ቅስቀሳ ማነሳሻ ዳርገዋል። የህወሓት ታጣቂዎች፣ የሀገር መከለከያን የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ለብሰው ሴቶችን መድፈራቸውንና ከዛም በኋላ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ማሳበባቸውን አስታውሰው፤ ይህ ሁሉ የተሸናፊዎች የማያልቀው ድራማ መሆኑን ገልጸዋል። ህዝቡ የሚያምነውና ብዙ መስዋዕትነት የከፈለለት አሸባሪው የጁንታ ቡድን አሁን እየታየ ባለው መልኩ በግልጽ ህዝቡን እየጎዳው ስለመሆኑ የአካባቢውን ፖለቲካ ጠንቅቀው የሚውቁት እየተናገሩ ነው።
ህዝቡ ጥቅምና ጉዳቱን ይለይ ዘንድ ትንሽ የማሰቢያ ጊዜ እንዲያገኝ መደረጉ መልካም መሆኑን በመጠቆም፤ ህዝቡ ዕድል ተጠቅሞ፤ አስቦና አሰላስሎ ወደራሱ ተመልሶ የሚጠቅምና የሚጎዳውን መለየት ከቻለ፤ በመንግሥት ከተወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ተጠቃሚ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ የተኩስ አቁም ብሎ ስምምነት የለም ወደ ሰሜን ሄደን ኤርትራን፤ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ተመልሰን አማራ ክልልን እንወጋለን ሲሉ ዛቻቸውን ቀጥለዋል። የሽብርተኛው ህወሓት አፈቀላጤ አቶ ጌታቸው ረዳ እና በሀገር ክህደት ውስጥ ሚናቸው የጎላው የቀድሞ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ፃድቃን ከተደበቁበት ሥፍራ ልባቸው ድው ድው እያለች በደመነፍስ መደንፋታቸውን ቀጥለዋል። ታዲያ ጉዳዩ በቀላሉ እንደማይታይ አጸፋውም ቀላል እንዳልሆነ መንግስት እወቁልኝ ብሏል።
‹‹የአማራ ህዝብ በሽብርተኞች ሂሳብ እንዲወራረድበት አይፈቅድም›› ሲል የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት፤ የአማራ ህዝብ በሽብርተኞች ሂሳብ እንዲወራረድበት አይፈቅድም ብሏል። የአሸባሪው ትህነግ አመራሮች በተደጋጋሚ ለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት የአማራን ‹‹ኢሊት›› ተጠያቂ በማድረግ ሂሳብ እንደሚያወራርዱ ነግረውናል። ትህነጎች የሚያወራርዱትን ሂሳብ ‹‹ከአማራ ልሂቃን›› ጋር ያያይዙት እንጂ እውነታው ግን የአማራን ህዝብ ስለማለታቸው ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለንም። ለዚህ ተጨባጭ ግምገማ አስረጅ ምሳሌው ትህነግ በታሪካዊ ጠላትነት የፈረጀው የአማራን ህዝብ እንደአጠቃላይ እንጂ የአማራን ልሂቃን በለየ ሁኔታ አይደለም።
ስለሆነም የትህነጎች ሂሳብ ማወራረጃ የአማራ ህዝብ እንጂ ልሂቁ ብቻ አይደለም። ይህ አዲሱ ማደናገሪያቸው ነው። ጥላቻቸው በአማራ ህዝብ ላይ ነው። ስሁት ትርክት የፈጠሩት፣ ለዚህ ማስፈጸሚያ መዋቅር ያነበሩት ልሂቁን ብቻ ሳይሆን አማራን እንደህዝብ ለመጉዳት ሆነ ብለው አስበው፣ አቅደውና አጥንተው ነው። ጥላቻው አፈር የሚገፋው የአማራ አርሶ አደር ጓዳ ድረስ የዘለቀ ነው። በተግባር ፈጽሞ የማይሳካ ቢሆንም በፕሮፖጋንዳ ደረጃ ዛሬ ‹‹ሂሳብ እናወራርዳለን›› ሲሉ ቢሳካላቸው የአማራ አርሶ አደር ጓዳ ድረስ የዘለቀ የሰይፍ በትር የመዘርጋት ሰይጣናዊ ተነሳሽነት አላቸው።
በትህነግ የሂሳብ ማወራረድ እሳቤ የሚዘረፈው ንብረት የአማራ ህዝብ ንብረት ሲሆን፤ ሊደፈሩ የታሰበው ደግሞ የአማራ እናትና እህት ናቸው። ተገዳዩ ደግሞ ሁሉም አማራ ነው። ይሁንና ዛሬ መላው የአማራ ህዝብ በትህነግ ዳግም ሊሰነዘርበት የታሰበውን የጥፋት ሰይፍ በደንብ ተረድቶታል። የብሔራዊ ንቃት ስሜቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አድጓል። የሞራል ልዕልና ከፍታውን ባለበት አስጠብቋል። በፍቅር ለመጣ በተለመደ ሰብዓዊ ጀግንነቱ እጁን ይዘረጋል፤ በጥላቻ ለሚመጣ ተገቢውንና የማያዳግም ትምህርት ሰጥቶ ይመልሳል።
የአማራ ህዝብ የትኛውንም በቀል ለመበቀል ፍጹም አልተዘጋጀም። ይህ ማለት ግን ‹‹ሂሳብ እናወራርዳለን›› ባዮችን በዝምታ ይታገሳል ማለት አይደለም። ከዳተኛና ጸረ-ህዝብ የሆኑ የትኞቹንም ጠላቶቹን ያለ ምህረት ይታገላል። ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምትና ራያ በራሳቸው መስዋትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች መሆናቸውን በድጋሚ እናሳውቃችኋለን። እነዚህን አካባቢዎች ደግሞ ከህግ ውጭ በጉልበት ወስዶ ለመጠቅለል ፍላጎት ካለ፣ ለነፃነቱ ሲል ዋጋ የማይከፍል አማራ የሌለ መሆኑን ደግመን ደጋግመን እናረጋግጥላችኋለን ብሏል።
ከዚህ መግለጫ በተጨማሪም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከወትሮ በተለየ መንገድ ዝግጁ መሆኑን ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ አስገንዝበዋል። ዋና አስተባባሪው ‹‹የኛ ዓላማ የህዝቡን ህይወት መጠበቅ እንጂ መሳሪያ አለኝ ብሎ መረሸን አይደለም፤ የነበረውን የሽምቅ ውጊያ አካሔድ ወደዚህ ቀይረዋል።›› በመንግስት የሚፈለጉት ጄኔራሎች አስር ፤ ሲቪሎቹ ደግሞ ከስምንት የማይበልጡ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ ወደ 50ሺ ሰራዊት ትግራይ ገብቶ እንደነበር አንስተዋል።
መንግስት ትግራይን ለቆ ለመውጣት የወሰነው፤ ዓላማው የህግ የበላይነትን ማስከበር እንጂ መቀሌን መያዝ አለመሆኑን ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ ጠቅሰዋል። መቀሌ ከዚህ በፊት የነበራት ወታደራዊ ዋጋ እና አሁን ያለው ሁኔታ እንደሚለያይ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ያኔ ስጋት እንደነበረ ገልጸው፤ እዛ የተሰማራው የወንጀል ኃይል እና እስረኞች ‹‹ከኛ ወታደር በላይ ነው›› ብለዋል።
ለኛ አሁን ላይ መቀሌ ያንን ያህል ኃይል ማስቀመጥ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም ያሉት ዋና ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ፤ ህወሓት አሁን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት አለመሆኑን ጠቅሰዋል። ህወሓት ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም እንደሚጓዝ መግለጹን ተከትሎ አሸባሪ አይታወቅምና ‹‹ህወሓት ወደ ወልቃይትና ራያ እንዳይመጣ ሰራዊቱ በተጠንቀቅ ቆሟል›› ብለዋል። ሕወሓት አሁን ላይ ስጋት እንዳልሆነም ተገልጿል። ‹‹ህወሓት ትንኮሳ ካደረገ ምላሹ የእጥፍ እጥፍ ነው የሚሆነው›› ያሉት ሌተናል ጀኔራል ባጫ፤ ቡድኑ መጀመሪያ ያቀደው፤ በአማራ እና በአፋር ክልል አድርጎ አዲስ አበባ መግባት እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ላይ ይህ ስጋት ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል ነው ያሉት። አሁን ላይ ህወሓት ይጠናከራል የሚለው የሚያሳስብ ነገር እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን ይሁንና የኢትዮጵያ ሰራዊት ለሁሉም ነገር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/ 2013