ሰላም እንደምንሰነበታችሁ ውድ አዲስ ዘመን ቤተሰቦች፤ አዲስ ዘመን የተለያዩ ወቅታዊ መረጃዎችን ወደእናንተ ማድረሱን እንደቀጠለ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በወቅታዊ አምዳችን ከምንሸፍናቸው ርዕሰ ጉዳዮቻችን ውስጥ በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ንግግሮችና ማብራሪያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በዛሬው የወቅታዊ ጉዳያችንም ሰሞኑን በትግራይ የተካሄደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች የሰጡትን ማብራሪያ ሙሉ ቃል አቅርበንላችኋል፤ መልካም ንባብ፡፡
ወደኋላ መለስ ብላችሁ የዛሬ ሁለት ዓመታት አካባቢ ከውጭ ወራሪ ሊያጠቃን ያስባል ፣ይፈልጋል ፣ይዘጋጃል። የውጭ ወራሪን አስቀድመን መከላከል ስላለብን ትጥቃችንን እናውጣ። ወታደሮቻችንን እናውጣ የሚለውን ጥያቄ ምን ያህል እንደተወያየንበት አስታውሱ። ልናወጣ ስንሞክር አትችሉም እየተባለ ወጣቶች እየተኙ ትጥቁም የኛ ነው፤ ሰራዊቱም አይወጣም በሚል ለሁለት ዓመት ያህል የነበረው ክርክር አግጦና አፍጦ አስከመጣው ግጭት ድረስ የነበረው ሁኔታ ትጥቆቻችንን እናውጣና አታወጡም ነበር። ይሄንን ታስታውሳላችሁ። ይህ ጉዳይ አሁን በተካሄደው ኦፕሬሽን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተሳከቷል። የምንፈልገውን አውጥተናል፤ ሰራዊታችንንም አውጥተናል። ሌሎች ሃይሎች የሚፈልጉት ነገር ካለ ለመዘጋጀት ሰፊ እድል አግኝተንበታል። ትናንት ካየኋቸው አንዳንድ አስተያየቶች በመነሳት ህዝቡን እንድታስተምሩ አናንተም እሳቤያችሁን እንድታስተካክሉ ጥቂት ነገር ማለት እፈልጋለሁ።
ትናንት ወታደር ወጣ ሲባል አማራ ጉድህ ፈላ፣ ተካድክ፣ ወዘተ የሚሉ አክቲቪስቶች ጋዘጠኛ ነን የሚሉ ሰዎች፣ ስልክ ያላቸው ሰዎች ነበሩ። ምን ማለት ነው ይህ ንግግር? ቆም ብሎ ማየት ያስፈልጋል። አማራ ከትግራይም ፣ ከሱዳንም ከሌላው ክፍል ከፍቅር ውጪ ሰው በጉልበት በሃይል ሊያንበረክከው ከፈለገ ራሱን መከላከል የሚችል ህዝብና በዛም የሚታወቅ ህዝብ መሆኑን መካድ ነው። መካድ ብቻ አይደለም። ጠፍተሃል ወድቀሃልና እኔን ካልሰማህና ካላየኸኝ ዋጋ የለህም አይነት በውድቀት፣ በስንፍና ውስጥ ጎልቶ የመታየት መሻት ነው፡፡
በነገራችን ላይ እዛ አካባቢ ሄዳችሁ አይታችሁ ይሆናል፤ የወልቃይት አርማጮ ህዝብ እንኳን አሁን ባለው ሁኔታ ባለፉት 30 ዓመታት ያሁሉ ዱላ እየወረደበት ኢትዮጵያዊነቱንም የበጌምድር ሰው መሆኑንም እየተናገረ እየሞተ ዛሬም አለ። ሸብረክ ያለ አካባቢ አይደለም። በትንሹም የሚል አካባቢ አይደለም። ይሄ ነገር ለእኛ ፖለቲካ ሊሆን ይችላል። ቁማር ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ለልጆቻችን ምን እያልናቸው ነው። አትችልም አንተ። ከሌላ ቦታ ጸብ ሲፈጠር ፍራ። እያልን ነው የሚለውን ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። የሚዲያ ሰዎች እንደዚህ ያለ ትርክት ፈሪ አንድን አካባቢ አጉልተው የሚያዩ ራሳቸውን አኮስስው የሚያዩ ትውልድ የመፍጠር አንድ ጡብ እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል።
ሁለተኛው የዛሬ ሁለት ዓመት ያለው የሃይል ሚዛን ነው። የኢኮኖሚ ዝግጁነት ፣ የወታደራዊ ሃይል ዝግጁነት ፣ የመንግስታዊ ውቅር፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ክልል የነበረውን ከሌሎች ክልሎች ስናወዳድር አይመጣጠንም። አሁን በነበረው ሁኔታ ወይ ዝቅታ ወይም ደግሞ የተቀራረበ ነገር ነው ያለው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ትናንት በነበረው ሁኔታ ልጠቃ እችላለሁ የሚል ፍርሃት ሊፈጠር የሚችልበት ምንም አይነት መሰረት ፣ አውነት የለም። በእነዚህ ምክንያቶች እንደነዚህ አይነት ትርክቶችን የማሸነፍና የመሸነፍ ብቻ ሳይሆን አንድን ህዝብ እንደ ህዝብ በስጋት በጭንቀትእንዲኖር የሚያደርጉ ስለሆነ ጋዜጠኞች ይሄንን ነገር በከፍተኛ ጥንቃቄ ማየትና ማስተማር ይጠበቅባችኋል። እውነትም አይደለም። ድሎችንም የሚያራክስ ስለሆነ።
ሌላው መቀሌን መልቀቅ ስንጀመር በጣም ብዙ ሰዎች ተደናግጠዋል። እናንተም ተደናግጣችኋል። መቀሌ የዛሬ ሰባት ስምንት ወር ስንሄድ የነበረው ግጭት የስበት ማዕከል፣ የመንግስት ማዕከል፣ የምናውቀውና የማናውቀው ሪሶርስ ማዕከል ነው የነበረው። ዛሬ ግን ስንወጣ በውስጡ የተሰገሰጉ የተትረፈረፉ ሰዎችን የሚዘርፍ የሚቀሙ 80 ሺህ የሚጠጉ ከመጨመሩ ውጪ ከአቢይአዲ ወይም ከሽራሮ ወይም ከበሻሻ የሚለየው ነገር የለም። የስበት ማዕከልነቱን አጥቷል አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ። በተለየ መንገድ የምናየው ነገር አይደለም፡፡ መቀሌ ወይም አብይአዲ ወይም የሆነ ቦታ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በሚሊተሪ አይታ ሲታይ ምነም ነገር የለውም።
የተለየ የስበት ማዕከል የሚያደርገውና የሚያጓጓን እንደሄድንበት ጊዜ የሚጓጓን ነገር የለውም። አንደኛ ወረራ አይደለም አላማችን፤ ትጥቃችን ተይዟል፤ ወታደራሮቻችን ተይዘውብናል ፣ ሰዎች ህግ ጥሰዋል ነው የነበረው እንጂ መቀሌን ነጻ እናውጣ ብለን አይደለም የሄድነው። ታውቃላችሁ ይሄንን። ተሳትፋችሁበታልም። አሁን ግን ለመውጣት የወሰንባቸው ውሳኔዎች በተወሰነ ደረጃ አነሳላችኋለሁ። እነዚህ ትርክቶች እርማት ስለሚፈልጉ ነው ያነሳሁላችሁ። ሁለተኛው ጠላት አሸንፌ መትቼ ነው የያዘኩት ይላል? ተሸንፈን ነው ወይ የሚል ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ይታያሉ እዚህም እዚያም።
“በነገራችን ላይ ጠላት ተሸንፎ አያውቅም ፤እኛ መቀሌ ስንገባ እኮ አንድ ሳምንት እንድንዝናናበት ፈቅደውልን ነው የገባነው እንጂ ተሸንፎ አይደለም። በየቀኑ ይደመስሱናል ፣ በየቀኑ ያጠፉናል፣ በየቀኑ ይገድሉናል ፣ በየቀኑ እኮ ነው የምንሸነፈው” – በፌስቡክና በቲውተር። እና ብዙ የሚያስገርም በተለይ እናንተን አይመስለኝም። ምክንያቱም እያጠቃን ስንሄድም እንኳን እናንተ በቅርበት ሪፖርት እያደረጋችሁ የሚዘገበው ነገር አሸነፍን 23 ኛን ደመሰስን ፤25 ኛን ደመሰስን። እነእትናን ገደልን፤ አበባውን ገደልን፤ ባጫን ማረክን…. አታቁም ይሄን?። ይሄ ሃይል አሁንም ቢዋሽ መደነቅ የሚያስፈልግ አይመስለኝም ።
ነገር ግን ከሚዲያ አንጻር ቅደም እንዳነሳሁት ትርክት አንድ አደገኛ ችግር አለ። ሳታውቁ ወይም የኛ ጓደኞች ሳያውቁ የሚያጠፉት ጥፋት፡፡ የጠላትን የተዛባ ዜና የማባዛት፤ የማድረስና የወገንን የማራከስ በሽታ ልክ እንደ ኮሮና ነው እኛ ውስጥ ያለው። ጠላት አንድ ውሸት ሲዘራ ሁሉም መደበኛውም ኢ- መደበኛውም ሚዲያ ጆሮ የሚሰጠው የሚያባዛው እሱን ነው። ምን ማለት ነው ይሄ ከሚዲያ አንጻር ፤ጠላት ደጋግሞ የሚነገርህ በውስጡ ያለውን መሻት በውስጡ ያለውን ድካም በውስጡ ያለውን ስንፍና ሲተነፍስ እሱን ነው የምታስተጋባለት ማለት ነው።
አንዱ በዚህ ጦርነት ከሳይኮሎጂካል ዋር ፌር አንጻር አሁንም ትምህርት መውሰድ ያለብን ከየትኛውም ወገን ይሁን የራስን ድል ለማግዘፍና ሌላውን ለማኮሰስ የሚደረጉ የውሸት ፕሮፖጋንዳዎችን ስናይ አይተን አላየንም ሰምተን አልሰማንም በማለት ብቻ ልንቀጣው እንችላለን። ብዙ ባየን ቁጥር ግን ተመልካች አለው የሚል እሳቤ ስለሚፈጥር ውሸት የለመደ ሰው በየቀኑ እየዋሸ ይቀጥላል። ውሸቱ እንዲቀጥል ግን እኛ ተባባሪዎች ነበር ማለት ነው። አሁንም ይታያል ይሄ ዝንባሌ፤ የሚዲያ ባለሙያዎች ይሄንን ማወቅ፣ መከላከል፣ ማስተማር፣
አለባችሁ። የምንፈልገውን ነው ደጋግመን የምናገረው እንጂ የሚሰድበንን፣ የሚቀጥፈውን፣ የምናስተጋባ ከሆነ የሚዲያው ጉዳይ በታጠረ ቦታ የሚቀመጥ አይደለም፡፡ ከቁጥጥራችን ውጭ በጣም በርካታ ሰዎች የሚያዩት ነው፤ ህጻናትም ጭምር። በዚያ ምክንያት የተሳሳተ ታሪክ እንዲያድግ ስለሚያደርግ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።
የቲፒኤልኤፍ /TPLF/ ዓላማ ማሸነፍ አይደለም፤ በተደጋጋሚ ሰሞኑን ሲናገሩ ሰምታችኋል፡፡ እንደዚህ ቀደሙ መንግስት እንሁን ምናምን አይደለም። አመድ ሆኛለሁ እና ተያይዘን አመድ እንሁን ፤ አቧራ ለብሻለሁና ተያይዘን አቧራ እንልበስ ፤ ተከስክሻለሁና ተያይዘን እንከስከስ….ፓራ ሹት የሚባል ነገር እንዳላይ የሚል ታክቲክና ስትራቴጂ ነው የሚሰሩት። ይሄ ነው ዓላማቸው። ለዚህ ማሳያ በጣም ብዙ ነገር ላነሳላችሁ እችላለሁ።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሮና አለ ፤ እግዚአብሄር ይመስገን ኮሮናው በተባለው ልክ አይደለም ግን አለ። ሰዎች የኢትዮጵያ መንግስት ኦክስጂን በበቂ ማቅረብ አለበት ብለው ይጠይቃሉ። ሙያችሁ ስለሆነ ትሰማላችሁ። በሌላ በኩል ህዳሴ የሚባል የሁላችሁም ህልምና መሻት አለ። ሰዎች ህዳሴ አልቆ ኃይል እንዲያመነጭ ይፈልጋሉ ፤በሌላ በኩል ሰዎች ከህዳሴው ጋር ተያይዞ አንዳንድ ጉዳዮች 40 ፣50 ሺህ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ይመለሱ፤ በዚህ እናስጨንቃቸው ብለው ሰዎች ይመልሳሉ። እነዚህን ሰዎች ማምጣትም፣ ትራንስፖርት ማድረግም ለተወሰኑ ቀናትም ቢሆን መቀለብም ለመንግስት እዳ ነው።
ኢትዮጵያ ኮሮና፣ ህዳሴ ፣የሚሰደዱ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በዋጋ ንረት ምክንያት በከተሞች ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች ምናልባትም እናንተን ጨምሮ በቀን ያማራቸውን ለመብላት ይቅርና የሚያውላቸውን ለመብላት የሚከፍሉት ነገር ከአቅማቸው በላይ ሆኗል ። ይህ ማለት ስንዴ የተወሰነ ዘይት የተወሰነ ስኳር የተወሰነ ብናስገባ እንኳን አሁን ባለው የዋጋ ንረት ሊያረጋጋው ይችላል። ይሄ ሁሉ ጉዳይ እያለብን ባለፉት ስምንት ወራት በወታደራዊው መስክ ካለው ወጪ ውጪ ጥይቱን ምግቡን ልብሱን አይመለከትም።
ከዚህ ውጪ መንገድ መብራት ጤና ትምህርት እና ሌሎች ግንባታዎችን ቀለብን ጨምሮ ለመፈጸም ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ትግራይ ውስጥ አውጥተናል። 100 ቢሊዮን ብር ማለት ዘንድሮ የምንይዘው በጀት 20 በመቶ ማለት ነው ፤ 100 ቢሊዮን ብር ማለት ለትግራይ ከምንመድበው ዓመታዊ በጀት ከ13 ከ14 በመቶ እጥፍ በላይ ትልቅ ማለት ነው። ስምንት ቢሊዮን ነው የምንይዘው መቶ ቢሊዮን ብዙ ነው። ይሄን ሁሉ ድካምና ወጪ ካደረግን በኋላ ግን በአንድም አካባቢ በኢንተርናሽናል ኮሚኒቲው በአንድ ሃይል መብራት ለመቀጠል ሰዎች እየሄዱ ሞተዋል፤ ምግብ እያደረሱ ተገድለዋል ፤ስልክ እና ሌሎች ኢንፍራስትራክቸር ለመገንባት ሄደው አደጋ ደርሶባቸዋል። አንድም ሰው ጥሩ ሥራ እየሰራችሁ ነው በርቱ ቀጥሉበት አላለንም።
በናንተ ምክንያት ረሃብ ሊመጣ ነው ፤ በናንተ ምክንያት ህዝቡ ወደ ችግር እየገባ ነው አክሰስ ከለከላችሁ ውጊያ አላቆማችሁም እንደዚህ አላደረጋችሁም፤ የኤርትራ ሰራዊት ፈቀዳችሁ አይነት ክሶች ብቻ ነው የነበሩት። ይሄ ሳያንስ እኛ ከሄድን በኋላ የምንይዘውን ይዘን የምንመታውን መተን ትጥቆቻችንን ወስደን የመቆየት ዓላማ አልነበረንም። ምክንያቱም ፍላጎታችን የነበረው መጀመሪያ ወጥተን ወደሌሎች ግንባሮች መዞር ነበር። ሌላ የሚያሰጋን ሃይል ስላለ ለዛ ዝግጅት ያስፈልገን ነበር። የፕራዮሪቲ ጉዳይ አለ ፤ አንድ ሀገር ዛሬ ያላት ፕራዮሪቲ ነገ ካላት ፕራዮሪቲ ይለያል። ዩኒቨርሲቲ ያለ ሰው ጋዜጠኛ መሆን ቢመኝም ዛሬ አግባ ብትለው ግድ የለም መጀመሪያ ስራ ልያዝና ከዚያ አገባለሁ ነው የሚለው። አላገባም አይልም ግን መጀመሪያ ስራ ልያዝ ይላል። ሀገርም እንደዚያ ናት። ቅደም ተከተል አላት፤ ፍላጎቶቿን በቅደም ተከተል ነው ሃንድል የምታደርገው።
አምና እንደምንሰጋው አይነት ስጋት በኢኮኖሚም ፣ በወታደርም፣ በምንም ስለሌለ አሁን ያለብንን ትተን እዛያ ብንጋጋጥ ሁለቱንም ያጣ ከመሆን ባለፈ ጥቅም አይገኝበትም። ምክንያቱም ፋቲክ ውስጥ ገብተናል። መጀመሪያ እንደመንግስት ዩኒፎርም የለበሰ ፣ መስመር ያለው ፣ የሚቆምበትን የሚያውቅ ጦር ነው የገጠመን።
15 አልያም 20 ቀን ነው የፈጀብን። እንደዚያ ላለ ውጊያ እምብዛም አልተቸገርንም። ቀጥሎ በተወሰነ ደረጃ ቢቀንስም በሽፍታነት የተደራጀ የተወሰነ ግሩፕ ነው የገጠመን ፤እሱንም እየፈለጉ ከመልካ ምድሩ አንጻር የሚያስቸግር ቢሆንም የተወሰኑትን ለመያዝ አንዳንዶቹንም ለመደምሰስ ተችሎ ነበር። ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ስለሚያስችል። አሁን ያለው ውጊያ ግን ተቀይሯል። አሁን ያለው ውጊያ የትኛውም መንደር ወታደር ሲሄድ ምንም ጠላት አያይም። ህዝብ ነው የሚያየው። እዛ የገባው ወታደር ቁጥሩ ያነሰ ከሆነ ምንም ጠላት የለም ብሎ አልፎ ሳይጨርስ ከጀርባው በርከት ያሉ ሰዎች ወረውት በክላሽም በገጀራም ይጨፈጭፉታል።
ለምሳሌ አንድ መንደር የገጠመን ፤ ጁንታው ይረሽናል ፣ ሰው ይገላል አልደገፈኝም የሚለውን ሰዎች ህዝብ እያየ ይረሽናል። እየረሸኑን ነው ጥበቃ አታደርጉልንም? ብለው ወታደሩን ጠየቁ። ወታደሩ እንደምታውቁት 50 ሺህ ፣ 100 ሺህ እንኳን ቢሆን ፤ ትግራይ ያለው ወታደር ዝም ብሎ እንኳን 20 ሺው መቀሌ 20 ሺው አዲግራት ካልተቀመጠ በስተቀር ሁሉንም ተራሮች የሚያካልል ካልሆነ በስተቀር የግድ 50፣100 ካልሆነ በስተቀር አይቻልም። ተበጣጥሶ የሚንቀሳቀስ ነው። እና በዛ መንደር ጠብቁን መጥተው ይገድሉናል ብለው መከላከያን ሲጠይቁ መከላከያ አመናቸውና በቁጥር ከ20 እምብዛም የማይበልጡ ሰዎች አስቀምጦ አሰሳውን ቀጠለ። ጠዋት ጠብቁን እንዳትሄዱብን ያሉ ሰዎች ከሰዓት እነዚያን ጥቂት ሰዎች በብዛት ወጥተው ፈጇቸው። ይሄ ነገር ከቦታ ቦታ እየበዛ እየበዛ ሲሄድ በዚች 15 ቀን በነበረው የውጊያ ሁኔታ ዝርዝሩን ባላነሳላችሁም አንድ የታጠቀ ሰው የሆነ የተከማቸ ኃይል ይመጣበታል፡፡ ብዙ ሰው ገድሎ ጥይት ጨርሶ የሚሞትበት ፣ በጣም ብዙ የማትገምቷቸው ጀግኖች፣ ትላልቅ ሃላፊዎች ደግሞ በጥይት ራሳቸውን የገደሉበት ሁኔታ አጋጥሟል።
ለምሳሌ የብርጌድ ኮማንድ፣ የተፈጥሮ ኮማንድ የሚባልበት አካባቢ ጥቂት ሰው ነው የሚኖረው፤ ዋናው ሃይል በየተራራው ይሰማራል። እዛ አካባቢ ላይ እነዛን ሰዎች ባልኳችሁ መንገድ ሰዎች ሲመጡባቸው ራሳቸውን የገደሉ አሉ። ብዙዎች ገድለው ጥይት ጨርሰው የተያዙ ፣ የሞቱ አሉ። ይሄ ጉዳይ ኢንሲደንት ሲሆን ችግር የለውም። አንዳንድ ቦታ ሲያጋጥም ገምግሞ ማስተካከል ይቻላል። በኋላ በኋላ ግን እንደ ባህልም ስለሆነ ፤ በተለይ መቀሌ ላይ ግልጽ እንድትሆኑ እዛ የነበረን ሃይል ትልቅ ነው፤ ወደ አራት ክፍለ ጦር ይጠጋል መቀሌ አካባቢ ያለው፡፡ ከ20 ሺህ በላይ ነው። እንኳን ጁንታው ምንም ነገር ቢሆን የመከላከል ብቃት አለው። ነገር ግን ይሄ ቅድም ያልኳችሁ ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ ጦሩ ውስጥ ገብቷል፤ ሁሉንም የሚያየውን ሰው ጠላት ነው ብሎ አስቧል። አንዳንድ ቦታ ቄሶች ክላሽና ማይክራፎን ይዘው ተነስ ብለው ሲሰብኩ ሰምቷል።
በጣም በርካታ ቤተክርስቲያን ሰዎች ሞተው ተቀበሩ የተባለበት ቦታ /ያው ታውቃላችሁ ቤተክርስቲያን ወይም መስጂድ ሰው ሲቀበር ጉርጓድ መቆፈር በኢትዮጵያ ባህል ያው ይገባችኋል/ግን ልክ እንደሰው እሬሳ የተቀበረው አብዛኛው ትጥቅ ነው። በየቦታው ሰው ሞተ እየተባለ ትጥቅ ይቀበራል። መቀሌ ያለው ጦር ምናልባት ሳምንት ብናቆየው የዚህ ቤት ድንጋጤ መቶ ፐርሰንት የተገላበጠ ይሆናል። ለአንድ ወገን ገብተህ የምትዋጋው …… ለምሳሌ ሻዕቢያ ጋር ስንዋጋ መጀመሪያ ባድመ ላይ ተዋጋን ፣ቀጥለን አልፈን ቶኮምቢያ ባሬንቱ ስንደርስ እንድንመለስ የተወሰነበት አንዱ ምክንያት ከደጀን እየራቅን ሄድን ፤ ባድመ እያለን ግን ከፊት ያለው ይዋጋል፣ ሲቆስል ችግር የለም ወደኋላ ነው። ችግር የለም ደጀን አለ ፤ተገን አለ። ውጊያ በእንደዛ መልኩ ካልሆነ ፋቲክ ነው የሚሆነው። ድሮ እንደ ተዋጋነው አስራ ምናምን ዓመት እንደሆነው ነው የምንሆነው።
እኛ የወሰነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ማስ የሆነውን ህዝብ እንደ ጠላት ወስዶ በታሪኩ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ፣ እሱም የሚሸማቀቅበት ዓለምም በብዙ ዱላ ኢትዮጵያ ላይ የሚነሳበት ነገር ከሚፈጠር ደጀን ወደምንለው ህዝብ ጠጋ ብለን ፤ ከኋላችን ደጀን አስቀምጠን በምርጫው የጥሞና ጊዜ እንደተባለው የጥሞና ጊዜ ለህዝቡ እንስጠው ብለን ነው የወሰነው። እርግጠኛ ነኝ 15 ቀን አንድ ወር ሁለት ወር ስንቆይ እናየዋለን ፤ የመከላከያንና የኢትዮጵያን መንግስት ጥረትና ድካም በብዙ እጅ ሴንስ ማድረግ ሲጀምርና ለሞተውም ፣ ለተራበውም ፣ ለቆሰለውም ለእያንዳንዱ ጉዳይ ወንጀለኛ የሆነው የሌለውን ሀብት እያፈሰሰ ያለው ወገኔ ብሎ ጀርባውን ሰጥቶ የሚሄደው ሃይልም በየቀኑ ጥቃት እየደረሰበት ስለሆነ የእፎይታ ጊዜ ብንሰጥ ዓምና የምንሰጋው ዛሬ አያሰጋንም። ሚሳኤሉን አውጥተናል ፣ መሳሪያችንን አውጥተናል፣ እንደትናንትናው ብለን የምንፈራው ጉዳይ የለንም።
ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ ቅድሚያ የምንሰጠው ፤ ቢያንስ እቺን ክረምት ቅድሚያ የምንሰጠው ሌላ ጉዳይ ስላለን ሰዋችን፣ ገንዘባችንን፣ ትጥቃችንን ቆጠብ አድርገን ወደ ዋናው ጉዳይ ብናተኩር ብለን ነው። ይሄ ባይሆንስ የዛሬ ውሳኔ የጊዜ ጉዳይ ነው። ወያኔ ከደርግ መንግስት ጋር ኢትዮጵያ ትቅደም ጋር የነበረው ውጊያ የማሸነፊያ አንዱና መሰረታዊ የነበረው ነገር የደርግ ትጥቅ ፣ የደርግ ስልጠና፣ የደርግ ቀለብ እየበላ ነበር። ወታደር ከማረከ በኋላ አሰልጥንልን ይለዋል፤ ያሰለጥናል ፤ትጥቁን ይወስዳል፤ ስንቁን ይወስዳል ….. እሱን እየያዘ ነበር ወያኔ ወደተደራጀ አቅም ያደገው። አሁን የፋሽዝም መልክ ሲኖረው ልብስ መሰረቅ ፣ ውሃ መስረቅ፣ ጎማ ማስተንፈስ፣ መኪና የሚሄድ ከሆነ መንገድ ላይ ድንጋይ መደርደርና እንቅስቃሴ መግታት። እየዋልን እያደርን በሄድን ቁጥር የምናስታጥቅ ሆንን። ከምግብ አንጻር አንድ ቤተሰብ አምስት ቤተሰብ ካለው ሰባት፣ ስምንት ፣ አስር ብሎ ያስመዘግባል ፤ የአስር ሰው ይወስዳል፤ አምስቱን ይበላል፤ አምስቱን ለጁንታው ይሰጣል።
የመከላከያ ሰራዊት ኮንቲኒየስ ኢንጌጅመንት ውጊያ ሲኖር ውሃ እንዳያገኙ ይደረጋል ፤ ጁንታ የምንለው ሃይል ግን ሃይላንድና የስ ይጠጣል። ማስተናገድ የለብንም በሚል ለሳምንታት ስንወያይ ቆይተን ነው የወሰንነው። ትናንት ከመቀሌ ስንወጣ መቀሌ ተያዘ የተባለው አንድም የጁንታው ሃይል ቅድም እስከመጣሁበት ድረስ መቀሌ የደረሰ የለም። ከመቀሌ እየወጣ የጨፈረው እዛው ተከማችቶ የነበረው ክላሹን የደበቀው ፣ ጊዜ እየጠበቀ የነበረው ሃይል ነው፡፡ አዲግራትም በቀደም ያያችሁት ፤ አሁንም ያያችሁት። እኛ ስንዴ እየሰጠን እኛ ዞር ስንል የሚጨፍር ከሆነ የጥሞና ጊዜ ያስፈልገዋል ማለት ነው። መያዝ የሚገባንና መቆየት ያስፈልጋል የምንላቸውን ቦታዎች እንይዛለን ፤ወደዛ በተደራጀ መልኩ የሚመጣ ሃይል ካለም በደስታ እናስተናግዳለን። ምክንያቱም የኛ ችግር ያ አይደለም፤ የኛ ችግር ህዝባዊ የሆነው ምልከታ ነው።
እንደዚህ አይነት ውሳኔ ሲወሰን ኢትዮጵያውያን ቶሎ የማሸነፍ ፍላጎትና ስሜት ስላላቸው ለመቀበል ይቸገራሉ። ግን እኛ መሪ የሆነው በእንደዛ አይነት ስሜት ልንነዳ ሳይሆን ቆም ብለን ኢትዮጵያን የሚያሻግራትን ነገር ለመወሰን ነው። ኤርትራን የምናስገነጥል ከሆነ ያ ሁሉ ውጊያ አስፈላጊ አይደለም ፤ኪሳራ ነው። ኢትዮጵያን ፣ ኢትዮጵያዊነትን ማንም አያሸንፍም። ኢትዮጵያን ፣ኢትዮጵያዊነትን አሸናፊ የሚያደርገው ግን ፈጣሪን መፍራት ፣ መጸለይ ፣ ኢትዮጵያን ፣ ኢትዮጵያዊነትን አሸናፊ የሚያደርገው የአባቶችን ብልሃትና ጥበብን መጠቀም ፤ ኢትዮጵያን አሸናፊ የሚያደርገው የጎረምሶችን ጉልበት መጠቀም ፣ኢትዮጵያን በአንድ ናሬሽን ማምጣትና ማስተባበር ነው እንጂ አንዴ ገብቼበታለሁና ዝም ብዬ እላፋለሁ ብሎ መጋጋጥ አይደለም። አሁን ዊዝደም ያስፈልገናል ፤ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፤ ህዝቦቿም ተለውጠው እናያለን ፣ አስደማሚ ድሎች አስመዝግበናል፤ ይሄም ይቀጥላል። የናንተም ሚና ግን ከፍተኛ ስለሆነ ልባችሁ፣ አእምሮአችሁም ነገን አሻግሮ የሚያይ ባለ ብሩህ አእምሮና በዛ ልክ የምትመላለሱ ጀግኖች እንድትሆኑ አደራ እላለሁ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/ 2013