የአንድ ሀገር የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መገለጫ ናቸው ከሚባሉት አንዱ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲዊ ምርጫ ማከናወን ነው። ከዚህ አንጻር ጥሩ ታሪክ እንደሌላት የሚነገርላት ኢትዮጵያ 6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ የትክክለኛ ምርጫ ምሳሌ ለማድረግ ስትዘጋጅ መክረሟ ይታወሳል። በተለይም የሲቪክ ማህበራት በዲሞክራሲ ግንባታ ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የነበሩትን አሳሪ ህጎች በአዳዲስ ህጎች በማሻሻል በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ መደላድል ፈጥራለች።
በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው የሲቪክ ማህበራት በአዲስ መልክ እየተደራጁ የዲሞክራሲ ግንባታውን ለማገዝ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ይስተዋላል። የሲቪክ ማህበራቱ በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የነበራቸው ሚና ምን ነበር ? ምን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ታይተዋል? የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ምርጫውን እንዴት ገመገመው? በሚሉትና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከኢፌዲሪ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቧል።
አዲስ ዘመን፡- የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ተልዕኮ ምድነው?
አቶ ፋሲካው፡- እንደሚታወቀው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በሰላም እንዲሁም በሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ከፍተኛ ሚና እና ሃላፊነት ወስዶ የሚንቀሳቀስ ኤጀንሲ ነው። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በተለይም ከለውጡ ወዲህ የተቀየረውን አዲስ ህግ ስራ ላይ በማዋል ተልዕኮውን እየፈጸመ ነው። ዋናው ምሰሶው የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ሲሆኑ የዲሞክራሲያዊ ሽግግር፣ ልምምድና ባህል እንዲገነባ የተጣለበትን ሃላፊነት ይዞ እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሲቪክ ማህበራት ከዚህ በፊት የነበረባቸው ተግዳሮት ምንድነው ? አሁንስ ከለውጡ ወዲህ ያላቸው ቁመና ምን ይመስላል ?
አቶ ፋሲካው፡– ትልቁ ተግዳሮት በኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበራት ታሪክ በህግ የሚተዳደር ዘመናዊ የሲቪክ ማህበር ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ አለመሆኑ ነበር። በተለያዩ መንግስታት የተለያዩ ፈተናዎች ገጥመውታል። ኤጀንሲው በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተጀመረ መሆኑ ቢታወቅም በገለልተኝነት ይሰራ ነበር ማለት አያስደፍርም። በደርግ ዘመነ መንግስትም ብዙ ጭቆና ይደረግበት ነበር። በኋላም በኢህአዴግ በመጀመሪዎቹ የሽግግር ጊዜዎች ጥሩ ነገሮች ቢታዩም የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ በ2001 ዓ.ም ላይ የወጣው አዋጅ ቁጥር 6/21 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ብዙ ገዳቢ ነገሮች ነበሩት።
በተለይም ከውጭ ሀገር ሀብትን አሰባስቦ ከዲሞክራሲ፣ ከሰብዓዊ መብት፣ ከህግ የበላይነትና ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ የሲቪክ ማህበራት እንዲሰሩ አይበረታቱም ነበር። የተፈቀዱላቸውን ስራዎች ለመስራት እንኳን ሀብት ማሰባሰብ የሚችሉት ከሀገር ውስጥ ብቻ ነበር። ከውጭ ሀገር ሀብት ማሰባሰብ የሚቻለው አስር በመቶ ብቻ እንዲሆን ህጉ ይገድብ ነበር። በዚህ ምክንያት አብዛኛዎቹ ሲቪክ ማህበራት በማህበራዊ አገልግሎት ማለትም በትምህርት፣ በጤና በመጠጥ በመሳሰሉት ላይ ለመስራት ተገደው ነበር። የዜጎችን መብት በማረጋገጥ ጉዳይ ላይ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ማህበራት ቁጥር በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ።
ስለሆነም የቀድሞው በጎ አድራጎትና ማህበራት ኤጀንሲ የሚተዳደረው በቦርድ ነው። ቦርዱ የሚወስነው ውሳኔ የመጨረሻ ነው። ሲቪክ ማህበራቱ ፍርድ ቤት ሄደው መሞገት የሚችሉበት እድል አልነበራቸውም። የመንግስት ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ነበር። በመንግስት ሲቪክ ማህበራት መንግስትን የሚያግዙ ልማትን የሚያከናውኑ ናቸው ብሎ አያምንም። ይልቁንም የፖለቲካ አጀንዳን ያራምዳሉ በሚል በጥርጣሬ ይመለከታቸው ነበር።
በዚህ የተነሳ በወቅቱ በሲቪክ ማህበራትና በመንግስት፤ በሲቪክ ማህበራትና በኤጀንሲው መካከል የነበረው ግንኙነት በመጠራጠር ላይ የተመሰረተ ነበር። አንዱ ሌላውን በመደገፍ ፋንታ ያጠፋኛል ብሎ የሚጠራጠርበት ሁኔታ ነው የነበረው።
አንዳንድ ሲቪክ ማህበሮች በህዝብ ስም የመጣ ገንዘብን ለግል ጥቅማቸው ስለሚያውሉ ሲቪክማህበራትን ለሀገር ጥቅም የሚሰጡ ሳይሆን የግል ሀብት ማካበቻ አድርጎ የመረዳት የተሳሳተ ግንዛቤም ነበር። በአጠቃላይ ሴክተሩ ምቹ ሁኔታ ውስጥ ያልነበረበት፤ መንግስት ድጋፍ የማያደርግበት እና ህብረተሰቡና ሲቪክ ማህበራቱ እንዲሁም መንግስት ሆድና ጀርባ የነበሩበት ወቅት ነው።
አዲሱ ህግ ግን ሲቪክ ማህበሩ ነጻነት እንዲሰማውና መንግስት እንዲደግፈው የሚያስችል ነው። ያም ሆኖ አሁንም ያልተቀረፉ ችግሮች አሉባቸው በተለይም ከምርጫው ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮች ማሳያ መሆን ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል አንዳንድ ሲቪክ ማህበራት የመንግስት ጥገኞች እንደሆኑ ይነገራል፤ አሁንስ ገለልተኝነታቸው በምን ይረጋገጣል?
አቶ ፋሲካው፡– ማንኛውም ሲቪክ ማህበር፤ ማህበር ለመባል አንደኛው መመዘኛ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ያለመወገን ነው። አዲሱ ህግም ሲወጣ ሲቪክ ማህበሩ በዚሁ መንገድ እንዲንቀሳቀስ እድል የሰጠ ነው። ነጻ ገለልተኛ ሆኖ ካልተደራጀ አሁንም እንደ ድሮው መንግስትን ወይም ፓርቲን የሚደግፍ ሆኖ የሚቀረጽ ከሆነ ቅቡልነት የሌለው ሴክተር ይሆናል። ይህ ማለት ደግሞ ሁሉም ነገር በዜሮ ተባዛ ማለት ነው። ሲቪክ ማህበረሰብን የሚያስተዳድረው ይህ ኤጀንሲ ነው። ይህን መመስከር የሚችለው ኤጀንሲው ነው። ከዚህ አንጻር ህጉ ክፍተት ስለሌለበት ማህበራቱ እየተንቀሳቀሱ ያሉበት በነጻነት ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የእናት ልጅና የእንጀራ ልጅ የሆነ ሲቪክ ማህበር የለም። ይህንን ከሲቪክ ማህበራቱ ጋር በተለያዩ መድረኮች በግልጽ እንነጋገራለን። በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል። እያንዳንዷን የአሰራር ስርዓት መስፈርት አሟልቶ ሲያቀርብ ሁሉም በእኩል ይስተናገዳል። ከዚህ ቀደም እንደሚሰማው አንዳንዶች በተለየ መንገድ የሚስተናገዱበት አንዳንዶች የሚገፉበት አሰራር የለም።
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ መንግስት ጣልቃ እንዲገባና ያልተገባ እርምጃ እንዲውስድ እድል የሚሰጥ አይደለም። መንግስት የሚፈጽማቸው ያልተገቡ ጫናዎች ቢኖሩ እንኳን ፍርድ ቤት አቁሞ መጠየቅ የሚቻልበት ስርዓት ተዘርግቷል።
ከዚህ አንጻር መንግስትም ግልጽ የሆነ አቅጣጫ አስቀምጧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት መንግስት ትክክለኛ ስራ ካልሰራ ትክክል አልሰራህም ብሎ በድፍረት የሚናገር፤ በእውነት፣ በመርህ በመረጃ ላይ የሚሰራ ገለልተኛ እና ነጻ ሲቪክ ማህበራት ያስፈልጉናል ነው ያሉት። ይህን ዘርፍ የሚስተዳድረውም ኤጀንሲ በዚህ ልክ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ሴክተሩ እራሱን በራሱ የሚስተዳድርበትና መብቱን የሚያስከብርበት አሰራር ስለተፈጠረ እንደከዚህ ቀደሙ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲዊና ሰላማዊ እንዲሆን ኤጀንሲው ያደረገው ዝግጅት ምን ይመስላል?
አቶ ፋሲካው፡- 6ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የዲሞክራሲው ስርዓት ልምምድ የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ ትልቁን እድል ይዞ የመጣ ነው። የሲቪል ማህበራት ህግ በሚፈቅድላቸው ልክ በንቃት በመሳተፍ ለዚች ሀገር የዲሞክራሲ ግንባታ ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት ሁነት ነው። ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ ሴክተሩ ሃላፊነቱን አልተወጣም የሚባልበትም ነበር።
ይህንን መነሻ በማድረግ በዚህ ምርጫ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እንደ ኤጀንሲ ሰራዎችን ሰርተናል። የመጀመሪያ ስራችን ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ጋር በመነጋገር የሲቪል ማህበሮች በምርጫው በሚሳተፉበትና ኤጀንሲው ድጋፍ በሚያደርግበት ሁኔታ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ምክክር አድርገናል።
በተቀመጠው ህግ መሰረት አንድ ሲቪል ማህበር ኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ የሚችለው በዓላማው መሰረት ነው። በምርጫ ጉዳይ ላይ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት ያላቸው የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ያስቀመጡትን ዓላማ በመለየት በምርጫው እንዲሳተፉ ከምርጫ ቦርድ ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል።
ተሳትፎውም ትርጉም ያለው መሆን አለበት። ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማድረግ ደግሞ ቀድመው ይህን ስራ ለመስራት እቅድ ያወጡና በጉዳዩ ላይ እውቀት ያላቸው ሲቪክ ማህበራት ቢሳተፉበት መልካም ነው በሚል ግልጽ የሆነ አረዳድ መፍጠር ተችሏል። ከዚያም ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋል። በምርጫ ዙሪያ የሚሰሩት ሀገር በቀል የሲቪክ ማህበራት ብቻ ናቸው። የውጭ ድርጅቶች በምርጫ ጉዳይ፣ በፖለቲካ ፕሮግራም ማስተዋወቅ፣ ስለምርጫው ግንዛቤ በማስጨበጥና በምርጫ ዝግጁነት ላይ መሳተፍ እንደሌለባቸው አዋጁ ይደነግጋል።
ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር ሲቪክ ማህበራት መረጃንና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል። የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በሲዳማ ሪፈረንደም ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መሰራቱ ጥሩ ልምድ የተገኘበት አጋጣሚም ነበር። ይህ ተሞክሮ ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍታዊ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲዊ ለማድረግ የኤጀንሲው ሰራተኞች ስልጠናዎችን በመስጠት አስተዋጽኦ ማበርከት ችለዋል። የሲቪክ ማህበረሰቡ ሚና አይተኬ እንዲሆን ኤጀንሲው ምን ድጋፍ ማድረግ አለበት? ስራዎች እንዴት በህግና በስርዓት መከናወን አለባቸው? ምን አይነት ክትትል ማድረግ ይገባል? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ከምርጫ ቦርድና ከተለያዩ ተቋማት ከመጡ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦችን ለማስጨበጥ ተሞክሯል።
ሲቪክ ማህበራት በኤጀንሲው ከተመዘገቡና እውቅና ከተሠጣቸው በኋላ በወረዳ፣ በዞን፣ በክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ሄደው የሚሰሩ መሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ፎረም መመስረት ተችሏል። ይህ የጋራ ፎረም በዋናነት ሲቪክ ማህበራት ስራዎቻቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል በመንግስት ተቋማት መካከል የተናበበ ስራ እንዴት መኖር አለበት? ምን አይነት ድጋፍ መደረግ አለበት? በአንድ አካባቢ ያለን መልካም ተሞክሮ ሌላ አካባቢ ተግባራዊ ማድረግና ችግሮችን እየለዩ የጋራ መፍትሄ በማስቀመጥ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች የሚገመገሙበት መድረክ ነው። የጋራ መግባቢያ ሰነዶችም የተፈረሙበት ነው። የፋይናንስ ቢሮዎች ጠቅላይ አቃቤ ህጎችም የዚሁ አካል ነበሩ።
በአጠቃላይ ስራዎች ህግና ስርዓትን ተከትለው መከናወን እንዲችሉ ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጋራ ውይይት ተደርጓል። ኤጀንሲው ማንኛውም ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ በሩን ክፍት አድርጎ ሲቪል ማህበራት ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚያስችላቸውን ድጋፍ የማድረግ ሲስተም ዘርግቷል። ከከፍተኛ አመራሩ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያለው የኤጀንሲው ሰራተኛ ሲቪክ ማህበራት ለሚያቀርቡት ችግር አፋጣኝ መፍትሄ የመስጠት ስርዓት ዘርግተን ነበር ወደ እንቅስቃሴ የገባነው። ይህ ሁሉ ቅድመ ዝግጅትና እንቅስቃሴ ለምርጫው ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ይህን ምርጫ ለየት የሚደርገውም ኢትዮጵያዊ የሆኑ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በመራጮች ትምህርት በምርጫ መታዘብ የተሳተፉበት መሆኑና ውጤታማ መሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምርጫውን በመታዘቡ ሂደት የነበራችሁ ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር ?
አቶ ፋሲካው፡– የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምርጫው ነጻ ፍትሃዊና ዲሞክራሲዊ እንዲሆን በማድረግ ሂደት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በሶስት ከፍሎ መመልከት ይቻላል። እነዚህም ቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እለትና ከምርጫ በኋላ ብሎ መመልከት ይቻላል። በቅድመ ምርጫ ወቅት ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰሩት ዋና ስራ ለመራጮች ትምህርት የመስጠት ስራ ነው። በዚህ ውስጥ 170 የሚሆኑ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ቦርድ እውቅናና ፈቃድ አግኝተዋል። ከነዚህ ውስጥ ሃላፊነታቸውን በንቃት የተወጡትና ስራውን ያከናወኑት ከመቶ ትንሽ አለፍ የሚል ቁጥር ያላቸው ናቸው።
እነዚህ ድርጅቶች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት የምርጫ ህግጋትና የመራጮች ትምህርት በሚሉት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ተደርገዋል። ካከናወኗቸው ስራዎችም የመጀመሪያው ሚዲያዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ሽግግር በተሻለ መሰረት ላይ ለመጣል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው፤ የዲሞክራሲ ልምምድ አካል እንደሆነ፤ የመምረጥ መብትን መጠቀም የዜግነት ግዴታ እንደሆነ፤ ህብረተሰቡ ካርድ ከመውሰድ ጀምሮ እስከምርጫው ቀን ድረስ የሚጠቀምበትን ሃላፊነት በሰላማዊ መንገድ እንዲወጣ በተለያዩ ሚዲያዎች መልእክት አስተላልፈዋል።
ሁለተኛው የተለያዩ የሶሻል ሚዲያዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡ ምርጫውን አስመልክቶ ስለሚጠበቅበት ሃላፊነት እና ማድረግ ስለሚገባው ጉዳይ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምርጫውን በምርጫ ህጉ መሰረት እንዲያስኬዱ፤ ሚዲያዎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ፤ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
ስለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ዝርዝር ሀሳቦችን በመጻፍ በሊፍሌቶች፣ በበራሪ ወረቀቶችና ብሮሸሮች ማሰራጨት ተችሏል። ህዝቡን የሚያነቃቁ ፖስተሮችንም ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች በመለጠፍ የማነቃቃት ስራ ተሰርቷል።
ከዚሁ ጎን በጎዳናዎች ላይ ትምህርት የመስጠት ስራም ተሰርቷል። በአጭር የጽሁፍ መልዕክቶች (SMS) አማካኝነትም ግንዛቤ የማስጨበጫ ትምህርቶችና መረጃዎች ተላልፈዋል። ይህም ለበርካታ ዜጎች ግንዛቤ ፈጥሯል ብለን እናስባለን። ህብረተሰቡን ሰብስቦ ገጽ ለገጽ በመራጮች መብትና ግዴታ ዙሪያ ትምህርት የመስጠት ስራም ተከናውኗል። አንድ ድርጅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በተለያዩ መንገዶች ተደራሽ አድርጓል ማለት ነው።
ከዚህም ባሻገር የክርክር መድረኮችንም ማዘጋጀት ተችሏል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳቦቻቸውን ለህብረተሰቡ እንዲያስደምጡ የምርጫ ክርክሮችን ያስደረጉ ሲቪክ ማህበራትም በርካታ ናቸው። ይህ በፌደራል ብቻ ሳይሆን በክልል ሚዲያዎችም ጭምር የተከናወነ ነው። በተለይም በሴቶች እና በአካል ጉዳተኞች መብትና ጥቅም፤ በመሬት ጉዳይ እና በመሳሰሉት ላይ አጀንዳ እየቀረጹ እንዲከራከሩ አድርገዋል። ይህም በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ፈጥሯል ተብሎ ይታመናል። ዜጎች ይሆነናል፤ ይበጀናል የሚሉትን እጩ እንዲመርጡ እድል ሰጥቷል። እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች በድህረ ምርጫ ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በጥሞና ጊዜ ህብረተሰቡ በምርጫው ወቅት ለሚመረጠው አካል በሰላማዊ መንገድ ድምጹን እንዲሰጥ፤ ካርድ የወሰደ በሙሉ መምረጥ እንደሚገባው፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን በጸጋ መቀበል እንዳለባቸው፤ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ሰርተዋል። እስከ ምርጫው እለት ድረስ በዚህ መልክ ስራዎች ተከናውነዋል።
በኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበራት ታሪክ በምርጫ ላይ በነበረው ሚና በዚህ ልክ ትርጉም ያለው ገለልተኝነት የተረጋገጠበት ስራ እስከ አሁን ተሰርቷል ማለት አይቻልም። ብዙ ልምዶች ተገኝተውበታል።
በምርጫው ቀን ደግሞ 45 የሚሆኑ ሲቪክ ማህበራት ምርጫውን ለመታዘብ ከምርጫ ቦርድ እውቅና ወስደው ወደ ስራ ገብተዋል። ስለምርጫ ህግጋትና ስለታዛቢዎች ሚና በወሰዱት ስልጠና መሰረት ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ታዛቢዎች የተዘጋጀላቸውን ባጅ በመያዝ በበርካታ ምርጫ ጣቢያዎች ተገኝተው ምርጫውን ተከታትለዋል።
ፈቃድ የወሰዱት 45 ሲቪክ ማህበራት ቢሆኑም በውስጣቸው በርካታ ድርጅቶችም ነበሩ። በተናጠል ካየናቸው ቁጥራቸው ወደ 200 ይጠጋል። በዚሁ መሰረት 44 ሺ የምርጫ ታዛቢዎች በምርጫው ላይ በታዛቢነት ተሳትፈዋል። ይህን በሬሾ ካየነው ለአንድ የምርጫ ጣቢያ አንድ ሰው ተመድቦ ነበር ማለት ይቻላል። ነገር ግን በፋይናንስ እና በጸጥታ ምክንያት ታዛቢዎች ሽፋን ያልሰጧቸው ጣቢያዎች መኖራቸው መታወቅ አለበት።
ስለዚህ በምርጫው እለት የሲቪክ ማህበራት የመታዘብ ስራቸውን በሚገባ ተወጥተዋል ተብሎ ይታመናል። አብዛኛዎቹ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምረው ቀኑን ሙሉ ሲታዘቡ ውለው ሌሊት ድምጽ አስቆጥረው ወጥተዋል። የድምፅ ቆጠራው እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሲቪክ ማህበራት የነበራቸው ሚና የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ሽግግር በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል እንላለን። ከፍተኛ ተስፋም የታየበት ነው። ለዚህም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።
አንዳንዶቹ ከምርጫው በኋላ የተጠቃለለ ሪፖርት አቅርበዋል። አንዳንዶቹም በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት ውስጥ ምልከታቸውን በሪፖርት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። እያንዳንዱ ታዛቢ ያየውን ለድርጅቶቹ ሪፖርት ካቀረበ በኋላ ድርጅቶቹ በአንድ ወር ውስጥ አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን የሚያሳይ ሪፖርት ለምርጫ ቦርድ ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአዲሱ ህግ እንደተቀመጠው ሲቪክ ማህበራትን በዋናነት የሚቆጣጠረው መንግስት ሳይሆን ሴክተሩ ራሱ ነው። ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር በመሆኑ የህግ መጣስን የሚጠየፍ፣ ለህዝብና ለሀገር ጥቅም የሚሰራ፣ ቀናኢ የሆነ ሴክተር እንዲፈጠር ነው የሚፈለገው። ይህ እንዲሆን የተቋቋመው አንዱ የሲቪክ ማህበራት ምክር ቤት ነው። ስለዚህ ማህበራቱም የሚሰሩት ምክር ቤቱ ባወጣው የስነምግባር ደንብ መሰረት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በምርጫው ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች የኖሩ ይሆን?
አቶ ፋሲካው፡- ሲቪክ ማህበራት ምርጫውን በመታዘብ ሂደት እስከ አሁን የጎላ ችግር አጋጥሞናል አላሉንም። አስቀድመን ችግር እንኳ ቢፈጠር በሚል ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር ነጻ የስልክ መስመሮች ተመቻችተዋል። በማንኛውም ሰዓት ምርጫውን በመታዘብ ሂደት ችግሮች ካጋጠሟቸው ሪፖርት የሚያደርጉበት ስርዓት ተዘርግቶላቸዋል። ከምርጫ ቦርድ ባገኘሁት መረጃ መሰረት ያን ያህል የጎላ ችግር አልተከሰተም። ነገር ግን የፋይናንስ ችግር ስራቸውን እንዳስተጓጎለባቸው ተናግረውናል። የምርጫ ታዛቢነት ስራን ለመስራት በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች መገኘት የመጀመሪያው ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፋይናንስ አቅም ሊኖር ይገባል። ምርጫው ላይ ለመሳተፍ ፈቃድ ወስደው ያልተሰማሩ ማህበራት አንድ ምክንያት የሚያደርጉት ፋይናንስን ነው። የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተወሰኑትን ለመደገፍ ሞክሯል። በጎ አድራጊ ድርጅቶችም ድጋፍ አድርገዋል፤ ግን ደግሞ ቀላል የማይባሉ ማህበራት በፋይናንስ ችግር ምክንያት ስራቸውን ማከናወን እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲሱ ህግ እንደዘላቂ መፍትሄ የሚያስቀምጠው ሲቪል ማህበሩ በምርጫውም ይሁን ሌላ የልማትና የዲሞክራሲ ስራ ለመስራት የፋይናንስ ነጻነት ማግኘት እንዳለበት ነው። የራሱ የሆነ ዘላቂ የፋይናንስ ገቢ ሊኖረው ይገባል ይላል። አዲሱ አዋጅ ማንኛውም ሲቪክ ማህበር በንግድ ስራ ላይ እንዲሰማራ ፈቅዷል። በንግድና ኢንቨስትመንት ስራ ሲሰማራ የሀገሪቱን የንግድ፣ የታክስ፣ የቢዝነስ ህጎች እንደማንኛውም ሌላ ተቋም ተፈጻሚ ማድረግ ይኖርበታል። የሚያገኘው ትርፍ መቶ በመቶ ለሲቪክ ማህበረሰብ ዓላማ ማስፈጸሚያ የሚውል ይሆናል። ይህ እንደመፍትሄ የተቀመጠ አቅጣጫ ሲሆን ወደፊት በሰፊው ይሠራበታል። የመንግስት ተቋማት ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮችን መደገፍ አለባቸው ተብሎ ይታሰባል። አዲሱ አዋጅ የሲቪክ ማህበራት ፈንድ የሚባል አቋቁሟል። የሲቪክ ማህበሩ ጠንካራና ገለልተኛ አቅም ያለው፤ ለሀገር አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችል ሴክተር ለመገንባት የፋይናንስ አቅሙን ማጠናከር ያስፈልጋል። ይህን ፈንድ ለማጠናከር ኤጀንሲው ዲፓርትመንት አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ፈንዱ የሚተዳደርበት መመሪያም በኤጀንሲው ቦርድ ጸድቋል።
የፋይናንስ ችግር ብቻ ሳይሆን የአቅም ውሱንነት ችግርም ነበር። ከአርባ አምስቱ ሲቪክ ማህበራት ውስጥ ሁሉም በሚገባ ደረጃ አልተንቀሳቀሱም። ይህም የአቅም አለመኖር እንደሆነ መገንዘብ ተችሏል። ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለማድረግ ሴክተሩ መጀመሪያ አቅሙን መገንባት አለበት። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቁርጠኝነት ችግርም ተስተውሏል። ምርጫ የሀገርን መጻኢ እድል የሚወስን እንደመሆኑ በፋይናንስና በተለያዩ ችግሮች አሳበን ትተነው የምንቀመጠው ጉዳይ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ከምርጫው ምን ልምድ ተገኘ?
አቶ ፋሲካው፡- በዚህ የምርጫ ሂደት ብዙ ልምዶችን ማግኘት ተችሏል። ሲቪክ ማህበራት ነጻና ገለልተኛ ሆነው ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸው የተንቀሳቀሱ መሆናቸው ነው። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ታዛቢዎች ወደ ቦታው እንዳይሄዱ አድርጓል። አንዳንድ ቦታ ላይ ደግሞ እታች ባለው የመንግስት መዋቅር የሚከሰት ችግርም ተስተውለዋል። ከዚህ ውጭ ግን ነጻና ገለልተኛ ሆነው የመራጮች ትምህርት መስጠትና የመታዘብ ስራ ሰርተዋል።
ይህም ጥሩ ልምድ የተገኘበት ነው። የተገኘው ልምድ በቅርቡ ጳጉሜ አንድ በተቀሩት ውስን ቦታዎች ለሚደረገው ምርጫ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለን እናስባለን። የዲሞክራሲ ግንባታን ለመፍጠር በሚኖሩ ሁነቶች ላይ ሲቪል ማህበራት አቅምና ልምድ በማካበት የተሻለ ለመስራት የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል። መንግስትም ማህበራቱን በምን መልክ መደገፍ እንዳለበት ያመላከተ ነው።
ለምሳሌ 45ቱ ማህበራት በንቃት የተንቀሳቀሱት 38 የሚሆኑት ናቸው። እነዚህ በጋራ አንድ ሪፖርት የሚያወጡ ቢሆኑ ይመረጣል። የዘንድሮው ተሞክሮ ወደፊት እንዲህ አይነቱን ሁኔታ ያስተካክላል ተብሎ ይታመናል። ተናቦ ለመስራት እድል ይፈጥራል። የሰው ሃይልና የሀብት ብክነት እንዳይፈጠር ትምህርት የሰጠ ልምድ ነው። ተቋማችንም ሲቪክ ማህበራቱ በዲሞክራሲ ግንባታው ስላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ዓለም ከዚህ ምርጫ ምን ሊገነዘብ ይችላል? ኢትዮጵያ ሰላማዊና ዲሞክራሲዊ ምርጫ ማድረጓስ ምን መልእክት ያስተላልፋል?
አቶ ፋሲካው፡– ሁሉም ነገር መጨረሻ በሚገኘው ውጤትና ሪፖርት የሚረጋገጥ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እስከአሁን ባለው ሁኔታ አንዱ ያገኘነው ጥቅም በሀገር በቀል ሲቪክ ማህበራት አቅም ኢትዮጵያውያን ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በራሳቸው አቅም ማካሄድ ይችላሉ የሚል አስተሳሰብ ፈጥሯል፤ በተግባርም የታየው ይህ ነው። ኢትዮጵያዊያን ለውጭ ሃይሎችም መልዕክት አስተላልፈዋል። ለምሳሌ የአውሮፓ ህብረት ባሉት የተለያዩ ፍላጎቶች ምክንያት ከመንግስት ጋር ቅሬታ ውስጥ በመግባት ምርጫውን አልታዘብም ብሎ ቀርቷል። የኢትዮጵያ ምርጫ ፍትሃዊ ነጻ ሰላማዊ አይሆንም በሚል ምኞት መሰል መግለጫ የሚሰጡም የውጭ አካላት ነበሩ። ምርጫው ይህን ሁሉ ፉርሽ አድርጓል። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ውጭም ምርጫን የሚታዘቡበትን አቅምና ልምድ አግኝተዋል። አሁን ባለው ሂደት አንድ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን የሚያረጋግጡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶች አሉ። ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩል ሜዳ የተለያዩ መድረኮች ተፈጥረውላቸው ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ተደርገዋል። በዚህ ሂደት የሲቪክ ማህበራት ያዘጋጇቸው መድረኮች በጣም ብዙ ነበሩ። ዜጎች ስለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ግንዛቤ እንዲጨብጡና ድምጽ መስጫ ካርድ ወስደው በምርጫው ቀን እንዲመርጡ የሚለው አንዱ መለኪያ ነው።
ሲቪክ ማህበራቱ ከሌሎች ተዋናዮች ጋር በሰሩት ትልቅ ስራ በርካታ ህዝብ የምርጫ ካርድ ወስዶ ድምጹን ለሚፈልገው አካል እንዲሰጥ አድርገዋል። የምርጫው ሂደትም ሰላማዊ እንደነበር መታዘብ ችለዋል፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት ገልጸዋል፤ ዜጎችም በነጻነት መርጠዋል። ይህንን ተፎካካሪ ፓርቲዎችም መስክረዋል። በእርግጥ አንዳንድ ቦታ ላይ የሎጂስቲክ ችግርና የምርጫ ጣቢያዎች በጊዜ ያለመከፈት ችግሮች እንደነበሩ ተጠቅሷል። እነዚህ ችግሮች ግን የምርጫውን ዲሞክራሲያዊነት ሰላማዊ ሂደትና ውጤት የማይቀይሩ ናቸው።
እናም ምርጫው የሚካሄደው ለኢትዮጵያውያን ነው፤ ምርጫውን ያካሄዱትም ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ጥቅሙም ለኢትዮጵያዊያን ነው። ከኢትዮጵያ በላይ የሚመለከተው አካልም የለም። ነጻ ገለልተኛ የሆኑ ሲቪክ ማህበራትም የሚያስፈልጉት ለዚሁ ነው። ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ነው እንዲባል የሌላን አካል ይሁንታና በረከት መጠበቅ የለብንም። መሆንም የለበትም። የራሳችን ነጻና ገለልተኛ የሆኑት ሲቪክ ማህበራትን በደንብ ማደራጀት ከቻልን ከዚህ በኋላ በታማኝነት የሚሰሩ የምርጫ ህግጋትን የሚያከብሩ፣ ዓላማቸውን ለመፈጸም የሚተጉ የሲቪክ ማህበራትን እያበቃን እንመጣለን። የሲቪክ ማህበራትን አቅም ከዚህም በላይ ካጠናከርን ወደፊት በራሳችን አቅም ምርጫ አዘጋጅተን፤ በራሳችን አቅም ታዝበን ተአማኒና ቅቡልነት ያለው ምርጫማድረግ እንችላለን። ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫም ይህንኑ አረጋግጦልናል። ለዚህ ነው የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን ማመስገን ያስፈለገን። ብዙዎቹ ብዙ ነገር ባልተመቻቸበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንደሰሩም ይታወቃል።
ሲቪል ማህበራት ለሀገር ዲሞክራሲ፣ ሰላምና ልማት ይጠቅማሉ ስንልም አንዱ ማሳየው ይህ ነው። ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለኤጀንሲው ለህብረተሰቡም ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብም የሲቪክ ማህበራትን አስተዋጽኦና አቅም ያሳየ ነው። ዘርፉ ቢታገዝ አሁን ምርጫ ላይ ባደረገው አስተዋጽኦ ልክ በሁሉም ዘርፍ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል ተገንዝበናል።
ምርጫው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አፍሪካ ሀገራትም የሚሰጠው ትርጉም ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና፤ ተሰሚነት ያላትና የትልቅ ህዝብ ባለቤትም ነች። በማህበራዊም ይሁን በኢኮኖሚው ዘርፍ መነቃቃት የሚታይባት ሀገር እንደመሆኗ እዚህ ሀገር ላይ የሚከሰተው ነገር ወደ ሌሎች ሀገራት የመተላለፍና የሌሎችን ትኩረት የማግኘት እድሉ ትልቅ ነው። ኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ለማድረግ ለሚሞክሩ አካላት ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ጉዳይ ሲገጥማቸው በጋራ የሚቆሙ ጠንካራ ህዝቦች መሆናቸውን መልዕክት ያስተላለፈ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኤጀንሲው ምርጫውን እንዴት አገኘው?
አቶ ፋሲካው፡- ምርጫን በተመለከተ የበለጠ ጥሩ የሚሆነው ምርጫ ቦርድ መግለጫ ቢሰጥ ነው። ሲቪክ ማህበራትን የምናስተዳድር የመንግስት ተቋም ስለሆንን የነበረን ሚና ሲቪክ ማህበራት በምርጫው ላይ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ነው። ይህም ተሳክቷል እንላለን። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እስከ አሁን ባሉ ሂደቶች በሙሉ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በምርጫው ለነበረው ስኬት ትልቁን ድርሻ ከሚወስዱት አካላት መካከል ሲቪክ ማህበራት የመጀመሪያዎቹ ናቸው። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ቀና ትብብር በማድረግ ማህበራቱ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የተቻለውን በማድረጉ ሊመሰገን የሚገባው ነው። ሲቪክ ማህበራት በምርጫ ሂደትና በምርጫው ዕለት ያሳዩት ጥሩ ልምምድ ነው። በተለይም ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅና ግጭት እንዳይፈጠር፤ ቢፈጠር እንኳን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ድንቅ ነበር።
ከኢትዮጵያ ባሻገር ምስራቅ አፍሪካ ከዚያም አፍሪካን እያሰቡ ሲሰራ ነው ትልቅ አቅም መፍጠር የሚቻለው። ከዚያም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሀገራት ምርጫዎችን መታዘብ አስቦ መንቀሳቀስ ሲቻል ነው አቅምን ማሳደግ የሚቻለው። እስከ አሁን የነበረው ሂደትም ይህንን ማድረግ እንደሚቻል ያመላከተ ነው።
ምርጫው የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ወይም የመንግስት ብቻም አይደለም። ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ማጠናቀቅ ማለት ኢትዮጵያን ሰላሟን አስጠብቆ ማስቀጠል ማለት ነው። የሁሉም ዜጋ ህልውና ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተሳሰረ ነው። ስለሆነም ምርጫው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሰላሙ ጉዳይ ዘብ እንደሚቆምና ለሰላሙ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በደንብ መልዕክት ያስተላለፈ ምርጫ ነው። ኢትዮጵያዊያን ነጻነት ከተሰጣቸው ድጋፍ ከተደረገላቸው በራሳቸው አቅም ምርጫን የማድረግ አቅም አላቸው የሚለውንም ያረጋገጠ ነው።
ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። የዲሞክራሲ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ትውፊቶች፣ ባህሎች አኗኗሮች አሉን። እነርሱን ትተን የምዕራባውያኑን ለመቀበል በምናደርገው ጥረት ብዙ ነገሮችን አሳጥቶናል። የባህል የሰላምና የዲሞክራሲ እሴቶቻችንን በደንብ እየፈተሽን በርካታ ስራዎችን የምንሰራ ከሆነ አይደልም ለራሳችን ለሌሎች ዲሞክራሲን ማስተማር እንችላለን።
መንግስት፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና ህዝብ ሰላማዊና ዲማክራሲዊ ምርጫ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል። ከዚህ በፊት በዚህ ደረጃ ልምምድ አልነበረም። በአንጻራዊነት ሲታይ ትልቅ መሻሻል ነው።
በሌላ መንገድ ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገው ጫና ተገቢነት የሌለው መሆኑንም መልእክት ያስተላለፈ ምርጫ ነው። የሚደግፉን አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉበትና ጫና ለመፍጠር ያሰቡም አካሄዳቸውን እንዲፈትሹ የሚያደርግ ክስተት ነው።
ምርጫው ዲሞክራሲን ለመለማመድ ጥረት ያደረግንበት የዲሞክራሲ መሰረት የጣልንበት ነው። ከዚህ በኋላ ዲሞክራሲ በሁለት እግሩ የሚቆምበትና በደንብ የምናጸናው ይሆናል። ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ረገድ በአፍሪካም በዓለምም የምትጠቀስ ሀገር ትሆናለች ብዬ አስባለሁ። እንደሀገር ለሁላችን የምትመች ዲሞክራሲ ያበበባት፣ የበለጸገች፣ ፍትህ የነገሰባት፣ ማንም ሰው በማንነቱ የማይበደልባት ሀገር ለመፍጠር ጅማሮ የታየባት ነች። በዚህ ሂደትም የሲቪክ ማህበራት አስተዋጽኦቸው የጎላ ነው።
መንግስት፤ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ህብረተሰቡም ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። ሁሉም ለሀገር ቅድሚያ ሰጥቶ የቆመበት የኢትዮጵያን አንድነትና መተሳሰር ከአባይ ግድብ ቀጥሎ ያስመሰከረበት ታላቅ ሁነት ነው።
የምርጫው የመጨረሻ ውሳኔ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እስከሚገለጽ ድረስ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት ይገባዋል። ከዚህ በኋላ የማህበራቱን ሪፖርቶችና አስተያየቶች በመውሰድ እንደ ኤጀንሲ ለወደፊት መስተካከል ያለባቸውንና የሲቪል ማህበረሰቡን ሚና ውጤታማ ለማድረግ የሚጠቅሙ ጉዳዮችን በእቅዶቻችን አካተን የምናከናውናቸው ይሆናል።
አሁን ባለው ሁኔታ ኤጀንሲው ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለት እየሰራ ይገኛል። አዲሱ ህግ ከወጣ በኋላ ወደ 1ሺ 450 ማህበራት ወደ ስራ ገብተዋል። አጠቃላይ 3ሺ 300 ገደማ የሚሆኑ ማህበራት በቁጥር ሳይሆን በተግባር በንቃት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። በሪፎርሙ ጥልቅ ተሐድሶ ከተደረገባቸው ተቋማት ውስጥ ሲቪክ ማህበራት አንዱ ነው። በሁለት ዓመት ውስጥ የተሰሩ ስራዎች በምርጫው ሂደቱ ፍሬ ማፍራታቸውን አይተናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
አቶ ፋሲካው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/ 2013