መንግስት ሰኞ ሰኔ 21 ቀን በትግራይ የተናጠል ተኩስ ማቆም ስምምነት ማወጁ ይታወቃል። በትግራይ ውስጥ ገበሬው ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን እና የእርዳታ ሥራው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ሆኖ እንዲሰራጭ እንዲሁም ሰላምን የሚመርጡ አካላት ወደ ሰላም እንዲመጡ ለማስቻል በሚል በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተጠየቀው የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነት በፌዴራል መንግስት በኩል ተቀባይነት አግኝቶ ታውጇል።
የታወጀው የተኩስ አቁም ስምምነት ግን በመንግስት በኩል የተወሰደ ውሳኔ እንጂ የተቃራኒ ወገንን ያማከለ አይደለም። ይህ በመሆኑ ደግሞ የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት በሚል እየተጠራ ነው። ይህ ከሆነ የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት ማለት ምን ማለት ነው? በማለት ተደጋጋሚ ጥያቄዎች በመነሳት ላይ ናቸው።
ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነት ምን ማለት ነው? ከሚለው እንነሳ። እርስ በእርስ የሚጣሉ ሀገሮች ወይም ቡድኖች ውጊያን ለማቆም የሚስማሙበት ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት ይባላል። ጦርነቱን ለማስቆም ዘላቂ ስምምነት እንዲደረግ ለተወሰነ ጊዜ ጦርነትን ማቆም ማለትን የያዘ ሲሆን፤ የአንድ ወገን ተኩስ አቁም ስምምነት ግን ስሙ እንደሚያመለክተው ምንም እንኳ ተኩስ ውስጥ የገቡት ሁለት አካላት ቢሆኑም፤ ተኩሱን ለማቆም ያሰበው ወይም የፈለገው አንድ ወገን ብቻ ሲያውጅ የአንድ ወገን ወይም አንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነት ውሳኔ ሲጸና ነው።
ስምንት ወራትን ያስቆጠረው የህወሓት ቡድን የሰሜን ዕዝ ጥቃት ምንም እንኳ ሁለት ሳምንት ባልፈጀ ጊዜ ውስጥ በመንግስት ህግ የማስከበር ሥራ ለማጠናቀቅ ቢቻልም፤ ቡድኑ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም ክልሉን ወደ ከፋ ቀውስ መክተቱ ሳያንስ፤ መንግስት ክልሉን ከቀውስ ለማውጣት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማስተጓጎል ሲጥር ቆይቷል።
የፌዴራል መንግስትና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይ ህዝብ ለረሃብና ችግር እንዳይጋለጥ መላው ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። መሰረተ ልማቶችን ጠግኖ ወደ አገልግሎት ማስገባት፣ ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንዲሁም የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ የማድረግ ስራ ቢሰራም፤ አሸባሪ ቡድኑ የተለያዩ የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በማሰራጨት የትግራይ ህዝብ ይህን በቅጡ እንዳይገነዘብ ከማድረግ ባሻገር በተለመደው መልኩ ህዝብ ውስጥ ተሸሽጎ ከኋላ አሲሮ ማጥቃትን እንደስልት በመውሰዱ፤ የትግራይ ህዝብ የባሰ ዋጋ እንዲከፍል በማድረግ ላይ ይገኛል። የፌዴራል መንግስትም የህግ ማስከበር ዘመቻውን ባጠናቀቀ ማግስት የትግራይን ህዝብ በመደገፍ ክልሉን መልሶ ለማቋቋም በርካታ ተግባራትን ቢያከናውንም፤ በድህነት ውስጥ በርካታ ችግሮችን ማሳለፉ የሚነገርለት የትግራይ ህዝብ፤ ህወሓት በፊት ብቻ ሳይሆን አሁንም ህዝቡን ለራሱና ለአጋሮቹ መጠቀሚያ እንዲያደርገው መፍቀዱ መከላከያንም ሆነ በአጠቃላይ መንግስትን ዋጋ እያስከፈለው ነው።
የፌዴራል መንግስት እንደገለጸው በመንግስት የተወሰደው የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነት በህውሓት የሽብር ቡድን መጠቀሚያ የሆነው የትግራይ ህዝብ እንዲያጤነው እና መርምሮ በሚገባ እንዲያስበው ዕድል ለመስጠት የሚያግዝ ነው።
መከላከያ መጀመሪያ ጦርነቱ እንደተጀመረ የገጠመው የተደራጀ፤ የታጠቀና የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) የለበሰ ኃይል በመሆኑ፤ ቡድኑን በሁለት እና በሦስት ሳምንታት ውስጥ ካስወገደ በኋላ የጎሬላ ውጊያ አጋጥሞታል። መከላከያ በየመንደሩ በመሄድ ማጣራት ሲያደርግ ደግሞ ሲያጋጥመው የነበረው የተደራጀ ጦር ሳይሆን ህዝብ ውስጥ የተሰገሰገው አሸባሪ ሰራዊቱን ከጀርባ እያጠቃ ሲገድል ሰራዊት ሲሞት ህዝብ እየሆነ የተከበረውን መከላከያ ሰራዊት በዓለም አቀፍ ሚዲያ ችምር ስሙ እንዲብጠለጠል ሲያደርግ ቆይቷል።
መከላከያ ሠራዊቱ መስዋዕትነት ሊከፍልለት በተዘጋጀው ህዝብ እንደ ባዕድ መታየቱ እና ህዝቡም ከስህትቱ እንዲማር እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም እውነታውን መረዳት እንዲችል ታስቦ ጭምር የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት ታውጇል። የትግራይ ህዝብ ይህን ተገንዝቦ መከራና ችግር ያመጣበትን ቡድን የተሳሳተ አመለካከት ከመደገፍ እንዲታቀብ እንዲሁም ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት በትግራይ ክልል የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ መሆኑን መንግስት መግለጹ ይታወቃል።
የህግ ባለሙያው አቶ ቸርነት ሆርዶፋ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የተኩስ አቁም ስምምነት የተለመደ ነው። አንዳንዴ በአገሮች መካከል አንዳንዴ ደግሞ እንዲህ እንደ ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ችግር ሲፈጠር ለሰብአዊ መብት ክብር ሲባል፤ ወደፊት ሰላም የሚመጣበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በሁለቱም አካል ስምምነት ወይም በአንድ አካል ፈቃደኝነት በተኩስ ማቆም ከግጭት ነፃ የሚደረግበት እና ተኩስ አቁም የሚታወጅበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ስምምነት ለሰላም ዕድል ለመስጠት፤ የሰብአዊ ቀውስ እንዳይባባስ የሚከወን ሲሆን በኢትዮጵያም መነሻ ምክንያቱ ይኸው ነው። መጀመሪያ ወደ ህግ ማስከበር የተሄደው የአገር መከላከያ ሰራዊት በመጠቃቱ እና አገር የማፍረስ ዕቅድ በመኖሩ ያንን ለመቀልበስ እንደነበር አስታውሰው፤ በተያያዥነት የህግ ማስከበሩ ዓላማ 80 በመቶ የሚሆነውን ተተኳሽ በእጃቸው አስገብተው ስለነበር ያንን ለማስመለስ እና የማይመለሰውንም ለማውደም ነበር። ይህንን ማድረግ ተችሏል። የያዟቸውን የመከላከያ አባላትም ለማስለቀቅ የታቀደ ሲሆን፤ ይህም በተሳካ መልኩ ተከናውኗል። በሌላ በኩል ይህንን ያቀናበሩ ዋነኞቹን ወንጀለኞች ለህግ ማቅረብ ሲሆን፤ ይህም ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በአብዛኛው ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
እንደአቶ ቸርነት ገለፃ፤ መንግስት በተጨማሪነት ክልሉን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስገባት ጥረት ቢያደርግም፤ በግላጭ በነበረው ጥቃት ሲሸነፉ ወደ ሽምቅ ውጊያ የገቡት የጁንታው አባላት በሽምቁም ስላልተሳካላቸው አሁን ደግሞ ፋሽስታዊ አስተሳሰብን በማስረጽ ‹‹ትግራዮች ሊያልቁ ነው››፤ የሚል ሰበካ በማካሄድ ሰዎች ከራሳቸው ህይወት ይልቅ ለቡድን መኖርን ታሳቢ አድርገው ሁሉንም ወደ ማጥቃት ዘመቻ በመገባቱ ይህንን አስተሳሰብ ለማስቆም መንግስት የተናጥል የተኩስ ስምምነት ውሳኔ ላይ ለመድረስ አስገድዶታል ብለዋል።
በአጠቃላይ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚካሄደው አንዳች ጥቅምን ማዕከል በማድረግ የሚካሄድ ሲሆን፤ በጥቅሙ ያመኑ ሁለቱም አካላት ተኩስ ማቆምን ሊወስኑ ይችላሉ። ነገር ግን ሁለቱም የግድ የተኩስ አቁሙ ስምምነቱን ላያምኑበት እና ላይቀበሉት የሚችሉበት አጋጣሚ ሲኖር ደግሞ በዚህ ጊዜ የተኩስ አቁሙ ተኩስ ከማድረግ የተሻለ ጥቅም ያስገኝልኛል በሚል ያመነው አካል በተናጥል ተኩስ አቁሜያለሁ ሊል ይችላል። እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ተኩስ ማቆም ዘላቂ ላይሆን ይችላል። ተኩስ አቁሜያለሁ ብሎ ያወጀው አካል አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ጦርነትን ወይም ተኩስን ማወጅ የሚችል መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
በዓለም ላይ የተለያዩ የተኩስ አቁም ስምምነት ዓይነቶች የሚገኙ ሲሆን፤ አንደኛው ወሳኝ የተኩስ ማቆም (Substantive ceasefires) የሚባለው ተጠቃሽ ነው። ይህ ለረዥም ጊዜ የሚፈጸም የተኩስ ማቆም ስምምነት ነው። ሌላኛው ደግሞ ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም (interim ceasefires) ስምምነት ሲሆን፤ ይህም ለጥቂት ጊዜ ተመጣጣኝ በሆኑ ሃይሎች መካከል የሚካሄድ የተኩስ አቁም ስምምነት ነው። አስገዳጅ የተኩስ ማቆም (Coercive ceasefires) በሚል የሚጠቀሰው የስምምነት ዓይነት፤ የሰዎችን መብት ማእከል የሚያደርግ ነው።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/ 2013