ሽብርተኝነት ድንገት የሚወረስ እና ድንገት የሚለቅ ባህሪ አይደለም። ከተዛባ አስተሳሰብ የሚመነጭና በሂደት ደንዳና ልብ በመፍጠር ማንነት ሆኖ በማህበረሰብ ውስጥ በቡድኖች የሚገለጽ ከፍ ያለ ዋጋ የሚያስከፍል ማኅበራዊ ነቀርሳ እንጂ። ቀድሞ መከላከል ፤ አልፎም ከሄደ ቆርጦ መጣል ካልተቻለ እንደየትኛውም የነቀርሳ በሽታ ፍጻሜው የከፋ ነው።
ሽብርተኝነት በተለያዩ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች የሚሸመንና ማህበራዊ መሰረት ለመያዝ አደገኛ ማህበራዊ ትርክቶችን የሚሸከም ነው። ከዚህ አንጻርም ጠንካራ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስረት በሌላቸው ማህበረሰቦች ውስጥ በቀላሉ ሊያድግና የከፋ ሰብዓዊና ማህበራዊ ቀውስ ሊፈጥር የሚችል ነው።
በማህበረሰብ ስነ ልቦና ውስጥ ፍርሀትና ጭንቀትን በመዝራትና በማወክ ፤ የደህንነት ስሜት እንዳይሰማው፣ በነገዎቹ ላይ ተስፋ እንዳያደርግ ፤የሰላም እንቅልፍ እንዳይተኛ ፣ ህይወቱ በሙሉ የስጋትና የግራ መጋባት እንዲሆን በማድረግ ቀስ በቀስ አጠቃላይ ማህበረሰቡን ወደ ውድቀት የሚወስድ መዘዙ የከፋ የአስተሳሰብ እርግማን ነው።
በኛም ሀገር በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ከፍረጃው በፊትም ሆነ ፣ ከዚያም ቀደም ብሎ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ይከተለው የነበረው የፖለቲካ አካሄድና አካሂዱ የተገዛበት የአስተሳሰብ መሰረት ህዝቡን በፈጠራ ትርክቶች ስጋት ውስጥ በመክተትና ደህንነት እንዳይሰማው በማድረግ ራሱን ለፈጠረው የስጋት ትርክት ጋሻ አድርጎ ማቅረብ ነበር።
ቡድኑ የፈጠራቸውን የስጋት ትርክቶች ስጋና ደም ለማልበስ የሄደበት አስከፊ የሴራ መንገድ እራሱ ግድሎ የማልቀስ የክፉ ስነ ልቦና ባለቤት እንዲሆን አድርጎታል። ብዛት ያላቸው የትግራይ ልጆችም የዚህ ሴራ ሰለባ ሆነዋል። የትግራይ እናቶችም ተስፋቸውን በተስፋ ነኝ ባዩ በዚህ ቡድን ተነጥቀው ቀጣይ ዘመናቸው ተስፋ አልባ እንዲሆን ተደርገዋል።
የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በደረሱበት የአስተሳሰብ ልክ ለመወሰን የሞከሩ የማህበረሰቡን አባላት የተለያዩ አግላይ ስሞችን ከመስጠት ጀምሮ እነዚህ ግለሰቦች ራሳቸውን ለመሆን ያደረጉትን ጥረት እንደ ድፍረት ቆጥሮ በጠራራ ፀሐይ መቀጣጫ አድርጎ በአደባባይ ገድሏል፤ አፍኖ በመውሰድ ዱካቸው እንዲጠፋም አድርጓል። ለማህበረሰቡ ሕያው የህይወት ዘር እንዳይሆኑ አምክኗቸዋልም። ሕዝቡ አማራጭ ህይወትም ሆነ አማራጭ አስተሳሰብ እንዳይኖረው አዕምሮውን ተናጥቆታል።
በአንድ በኩል ጭካኔ በተሞላው ተግባሩ በማህበረሰቡ ውስጥ በፈጠረው ፍርሀትና ጭንቀት ሕዝቡ ጥላውን ሳይቀር እንዲፈራ ሲያደርግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ገድሎ ነጠላ አዘቅዝቆ ለያዥ ለገላጋይ በማይመች መልኩ አልቃሽ ሆኖ የመገኘቱ ምስጢር ህዝቡ በቡድኑ የክፋት ወጥመዱ ውስጥ እንዲገባና የወጥመድ ውስጥ ሕይወት እንዲኖር አድርጎታል።
ገና ከፍጥረቱ አንስቶ ዕድሜውን ለማስቀጠል በፈጠራቸው የጥላቻ ትርክቶች የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ነፃ በሆነ ህሊና ህብረት /አንድነት / እንዳይፈጥር ፤ ከዚህ ይልቅ ጎረቤቶቹን ሳይቀር በጥርጣሬና በስጋት እንዲመለከት አድርጓል። ባልተፈጠረ ጠላት የስጋት ህይወት እንዲመራም ሆኗል።
ማንነትን መሰረት ያደረጉ ያልተገቡ ትርክቶችን ህዝቡ ውስጥ በማስረጽም ህዝቡ ራሱን በተገቢው መንገድ እንዳያይ ከማድረግ ባለፈ ትርክቶቹ የፈጠሩትን ማንነት ለመላበስ ባደረጋቸው ጥረቶች ከቀደመው ባህሉና ሃይማኖታዊ እሴቶቹ እንዲፋታ አድርገውታል። በሕይወቱ ለተቃርኖ አስተሳሰቦች ዋጋ እንዲከፍልም ተገዷል።
ይህ ሁሉ የህዝቡን የማሰብና የመሆን ሰብአዊ ነፃነት የተናጠቀው የጁንታው የሽብር የክፋት መንገድ የትግራይን ህዝብ የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለው ከራሱ ከትግራይ ህዝብ የበለጠ ምስክር አይኖርም። በዚህ ሽብርተኛ ቡድን ዘመኑን በብዙ ፍርሐትና ጭንቅት ለመኖር ተገዷል። ዛሬም ቢሆን የቀደመው የጭካኔ ተግባሩ በህዝቡ ህይወት ላይ የፈጠረው ድቅድቅ ጥላ ነው።
ልጆቹን ተስፋ ላደረገው ሰላም እና ከሰላም ለሚመነጭ የተረጋጋ ህይወት መርቆ ለትግል ቢልክም የልጆቹ የመስዋእትነት ትግል ተስፋ ያደረገውን ሰላም እና የተረጋጋ ህይወት ሊያስገኝለት አልቻለም። በልጆቹ መስዋዕትነት የተገኘው ድል በራሱ ላይ አዲስ አምባገነን ከመፍጠር ያለፈ ትርጉም አላመጣለትም።
ዛሬም ይህ አሻባሪ ቡድን ከፍጥረታዊ ማንነቱ ሊፋታ የሚችል የአስተሳሰብ መሰረት የሌለው በመሆኑ በትናንት ማንነቱ የትግራይን ህዝብ ጭካኔ በተሞላው ተግባሩ ከፍ ባለ ፍርሐትና ጭንቀት ውስጥ ከቷል። ለህዝቡ ጠላት እየፈጠረ ለእኩይ ተግባሩ ለማሰለፍ እየሞከረና ህዝቡም ከሴራው በስተጀርባ ያለውን እውነታ ባለመገንዘብ የአስተሳሰቡ ሰለባ እየሆነ ነው።
የትግራይ ህዝብ ከዚህ መሰሪ ቡድን የጥፋት አስተሳሰብ ትናንት ልጆቹን ገብሮ ያተረፈው ነገር እንዳልኖረ ሁሉ ዛሬም በህዝቡ መከራና ስቃይ ፤ ሞትና እንግልት ህይወት ለመዝራት እያደረገ ካለው የጥፋት መንገድ ሊያተርፍ የሚችለው አንድም ነገር አይኖርም። ትናንት በልጆቹ የመስዋእትነት ደም ተስፋ ያደረገው ሕይወት በቡድኑ ሴራ እንደመከነ ሁሉ፤ ዛሬም በቡድኑ የጥፋት መንገድ ሊወርሰው የሚችለው የተስፋ ህይወት ሊኖረው አይችልም።
የትግራይ ህዝብ ከትናንት የጨነገፈ የልጆቹ የመስዋዕትነት ታሪክ ትምህርት በመውሰድ በራሱን ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን ወደ ራሱ ነፃ ኅሊና ሊመለስና ተረጋግቶ በጥሞና ሊያስብ ይገባል። ከመጀመሪያው ስህተት የሁለተኛው እንደሚባለው የመጀመሪያው ስህተት የፈጠራቸው ክፉ ቀናቶች ማብቂያ ሳያገኙ ሁለተኛው ስህተት ሊፈጥረው የሚችለውን አደጋ የቱን ያህል የከፋ እንደሚሆን መረዳት ለትግራይ ህዝብ አይከብደውም።
ወቅቱ የትግራይ ህዝብ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ያልተገቡ ትርክቶች ከፈጠሩበት ጥላ ወጥቶ ከቀደመው ባህሉና ሃይማኖታዊ እሴቶቹ ሊታረቅ፤ ብዙ ዋጋ ካስከፈሉት የተቃርኖ አስተሳሰቦች እና ከቡድኑ የሴራ ትብታብ ወጥቶ የማሰብና የመሆን ሰብዓዊ ነፃነቱን በእጁ ለመያዝ በቁርጠኝነት ከራሱ ጋር የሚታገልበት ነው።
ትግሉ በሚጠይቀው ጽናት አሸናፊ ሆኖ የመውጣቱ እውነታ ከራሱ አልፎ ለመጪው ትውልድ ያለበትን ባላደራነት በስኬት ለመወጣት የሚያስችለው ፤ የመጣበትን የስቃይ፣ የመከራ፤ የሞትና የእንግልት ሕይወት የፍጻሜ ማህተም የሚሆን ፤ የአዲስ ታሪክ አዲስ ጅማሬ ነው። ለዚህ ደግሞ አልረፈደም !
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/ 2013