ጅግጅጋ፡- የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ የሚከናወኑ ተግባራት በሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ሊመሰረቱ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሚና ለማጎልበት እንዲያስችል የወጣው የፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ተፈጻሚ ያልሆኑ ቃሎች የበዙበት እንደነበርም አንድ ጥናት አመላክቷል፡፡ በጅግጅጋ እየተካሄደ ያለውን የከተሞች ፎረም ምክንያት በማድረግ ትናንት ለውይይት የቀረበ ጥናት እንዳመለከተው፤ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጣው የፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ በተግባር ያልተገለጹ ቃሎች የበዙበት ነበር፡፡ በመሆኑም፤ በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረቱ ሊሆን ይገባል፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር አለማየሁ ደበበ ጥናቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ ሴቶችን ያላሳተፈና ተጠቃሚ ያላደረገ ጉዞ ለውጤት ይደርሳል ብሎ ማሰብ አይቻ ልም፡፡ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ የስትራቴጂ ሰነድ ተዘጋጅቶ ወደሥራ ቢገባም፤ በሰነዱ የተቀመጠውና በተግባር የተገለጸው የተራራቀ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ እንዲቻል የሴቶችን ኢኮኖሚ በማሳደግ ላይ አተኩሮ መስራት ይገባል፡፡
እንደ ዶክተር አለማየሁ ገለጻ፤ ከኢኮኖሚ አኳያ በስትራቴጂ ሰነዱ የሴቶችን የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጥ፣ በንብረቱም የማዘዝና የመወሰን መብት እንዲኖራቸው ማስቻል፣ እንዲሁም የተለያዩ ድጋ ፎችን በማድረግ የስራ ፈጠራ አቅማቸውን ማሳደግ የሚሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ተቀምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ፤ በአራት ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተደረገ የዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው፤ ሴቶች ይሄን እድል እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ የተሰራው ሥራ እምብዛም ውጤት ያልታየበት፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይም ተሰራ በማያስብል ደረጃ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌም፣ በከተማ ያሉ ሴቶች፣ ገቢያቸው በሚጠበቀው መልኩ አላደገም፤ ወጥና ተከታታይነት ያለው ድጋፍ አልተደረገም፤ የሥራ እድል ፈጠራውም በተገቢው መልኩ አልተሰራበትም፡፡
ሥራ ለመፍጠር የሚያስችላቸው የስልጠና ድጋፍም እያገኙ አይደለም። መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተሳትፈው እንዲሰሩ አልተደረገም፡፡ በገጠር ላሉ ሴቶችም ጉልበት ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች እምብዛም አልቀረቡላቸውም። የግብርና ግብዓት አቅርቦቱም አናሳ ነው። የመስኖ ውሃ ተጠቃሚነታቸውም ዝቅተኛ ነው። ለምርቶቻቸውም የገበያ ትስስር አልተፈጠረላቸውም። የብድር አቅርቦቱም በፈተና የታጠረ ነው፡፡ መሻሻል የታየበት የሴቶች የቁጠባ ባህልም ቢሆን 41 በመቶ ነው፡፡ በአጠቃላይ በሰነዱ ይሰራል የተባለው ጉዳይ ሲፈተሽ የተባለውን ያክል እንዳልተሰራና ሰነዱም በተግባር ያልተገለጹ ቃሎች የበዙበት እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር አለማየሁ፤ የሴቶ ችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስ ችል ሜዳና መደላድል መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በዚህ መልኩ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሲያድግና አሳሪ ከሆነው ድህነት ሲላቀቁ የፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንደሚያድግ፤ ለአገር ማበርከት የሚገባቸውን ሚናም መወጣት እንደሚችሉ፤ የመደራደር አቅማቸው እንደሚያድግ፤ የኢኮኖሚ እድገቱም የስርዓተ ጾታ እኩልነት የተረጋገጠበት እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዜር ገብረ እግዚኣብሔር በበኩላቸው እንዳሉት፤ የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አኳያ በ1997 የተዘጋጀውን የፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ከትግበራው ጋር ያለውን መራራቅ ጥናቱ በዚህ መልኩ ፈትሾ ማቅረቡ ለቀጣይ ስራቸው ግብዓት ይሆናል፡፡ ከብድር፣ ከስራ ቦታና መሰረተ ልማት፣ በሃብት ማመንጨትም ሆነ መጠቀም፣ ወዘተ. ጉዳዮች የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትም የበለጠ መስራት እንደሚገባ ያመላከቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም፤ የተገለጹ ግኝቶችን በመለየትና ምክረ ሃሳቦቹንም በመውሰድ የሴቶችን የኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግ ይሰራል፡፡ ለዚህም፣ ችግሩ ከፖሊሲ ከሆነ ፖሊሲውን የማስተካከል ሥራ ይሰራል፤ ክፍተቱ ከአሰራርም ከሆነም ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመወያየት ድጋፍ ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
ወንድወሰን ሽመልስ