አዲስ አበባ፤ የኦሮሚያ ክልል ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መስፈርት ለመረጣቸውና በ2010/ 2011 የምርት ዘመን ከግብርና ጋር ተያያዥነት ባላቸው ዘርፎች ብቻ ውጤታማ በመሆን ሃብት ማፍራት ለቻሉ 717 አርሶ አደሮች የሽልማትና እውቅና መርሃ ግብር ማዘጋጀቱን አስታወቀ። የክልሉ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ትላንት በሰጡት መግለጫ፥በክልሉ በ2010/2011 የምርት ዘመን የግብርና ፓኬጆችን በሙሉ በመጠቀም የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ አርሶ አደሮች፤ የልማት ሰራተኞችና ተመራማሪዎች የሽልማትና የእውቅ መርሃ ግብር አዘጋጅቷል።
የዘንድሮውን ሽልማትና እውቅና የሚያገኙትን ለመመረጥም ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መልኩ ከቢሮ እስከቀበሌ ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ የተለያዩ መስፈርቶች ወጥተዋል። ገለልተኛ ኮሚቴዎችም ተሸላሚዎችን የመመልመል ተግባር ፈፅመዋል። «በዚህም እንደከዚህ ቀደሙ ሳይሆን ከግብርና ጋር ተያያዥነት ባላቸው ዘርፎች ብቻ ውጤታማ ለሆኑና ሃብት ማፍራት ለቻሉት እውቅናና ሽልማቱ ይሰጣል» ያሉት የቢሮው ኃላፊ፤ ሙሉ የግብርና ፓኬጆችን በመጠቀም ራሳቸውንና አካባቢያቸው የለወጡ፤ እንዲሁም ካፒታላቸው ለኢንቨስትመንት የበቃ አርሶ አደሮች የሽልማቱ ተቋዳሽ እንደሚሆኑም አብራርተዋል።
«በመደመር ፍልስፍና ሺዎችን በማበረታታት ሚሊዮኖችን ማፍራት» በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው መርሃ ግብርም የፊታችን እሁድ የካቲት 17 2011 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አባገዳ አዳራሽ ይካሄዳል» ብለዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2011
ታምራት ተስፋዬ