አንዳንድ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ፍላጎታቸውን በሀገሪቱ ላይ ለመጫን ሰፊ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ከጀመሩ ውለው አድረዋል ። ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድና ሁለተኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለመሙላት ዝግጅቷን አጠናቃለች።ታዲያ በዚህ ወቅት አሜሪካ እና ወዳጆቿ ስለምን በዚህ ወቅት ጣታቸውን ቀሰሩ? የሚል ሀሳብ ይዘን በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጄ እንግዳ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ደረጄ:– አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ ያለው ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ እንደ ሀገር ከምንጊዜውም በላይ አሜሪካና ምዕራባውያን ተባብረው ተጽዕኖ እያደረጉ ይገኛሉ።ይህ ደግሞ ለማንኛውም ዜጋ የተሰወረ አይደለም። ከምን የመነጨ ለሚለው ለማንም የተሰወረ አይመስለኝም።ምን አልባት ጉዳዩን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ችግር ሳቢያ ሊመስል ይችላል።ጉዳዩ ከዚህ ያለፈ ብዙ አንድምታዎች አሉት።የሰብአዊ መብት ቢያሳስባቸው አሜሪካና አጋሮቿ በተለያዩ ሀገሮች ውስጥ የሚካሄዱ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ባስጨነቋቸው ነበር።
ሁልጊዜ የምናየው እና የምንሰማው የተለያዩ አይነት ችግሮች በተለያዩ ሀገሮች ውስጥ አሉ።ነገር ግን ለሰብዓዊ መብት መጣስ እንቆረቆራለን የሚሉት የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳጣ ሲሆን ነው።ለምሳሌ በሰብዓዊ መብት ከታየ ስም መጥቀስ አያስፈልግም እንጂ በርካታ ሀገሮች አሉ።ጦርነት ከተባለም የእስራኤል ጋዛ ጦርነት፣ በየመን የሚካሄደው ጨዋታ ሳይሆን ጦርነት ነው፣ ለዚህ አሜሪካ በእኛ ጉዳይ ላይ መግባቷ በተዘዋዋሪ አቅም እንዳይኖረን የማድረግ ዕቅድና የቆየ ትልም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አቅም እንዳይኖራት ለማድረግ የሚሰሩት ምን ፍላጎት ስላላቸው ነው?
ዶክተር ደረጄ፡– ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስከብራ የቆየች ታሪካዊ ሀገር ናት።ይህን ነጻነት ማመን አይፈልጉም።አሁን ላይ ያለው ዋናው ጉዳይ ግን ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በመገንባት ሁለተኛውን የውሃ ሙሊት የምታከናውንበት፣ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫን ማካሄዷ ነው።ይህን ማከናወኗ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች ውስጥ ጉልህ ሚና ይኖራታል የሚል የጥላቻ እይታ ስላላቸው የሚያደርጉት ጫና ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከሳምንታት በፊት አሜሪካ በትግራይ በተካሄደው የህግ ማስከበር ሂደት ሰብአዊ መብት ተጣሰ በሚል ሰበብ በባለስልጣናት ላይ የጣለችው የጉዞ እገዳ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ደረጄ፡- አሜሪካ የጉዞ እገዳ በመጣል ሌሎች ማእቀቦችን እጥላለሁ በማለት የምትሯሯጥበትን ሁኔታ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ሞልታ በኢኮኖሚ ያደገች ሀገር እንድትሆን ካለመፈለግ የመነጨና የግብጽን ጥቅም ለማስጠበቅ የምታደርገው ነው።ይህም ባይደን ከመምጣቱ በፊት ዶናልድ ትራምፕ በግልጽ “ግድቡን ግብጽ ልታጋየው ትችላለች” ብለው የተናገሩት ማሳያ ነው።የግድቡን ድርድር እኛ ካልመራነው ብለው ከዲፕሎማሲ መስመሩ አውጥተው ወደገንዘብ በመውሰድ ትሪዠሪው እንዲመራው ማድረግ ዋና ማሳያ ምልክቶች ናቸው።ይህ ጉዳይ ከህዳሴው ግድብ ጋር የተያያዘ በተዘዋዋሪ ህዳሴ ግድቡን እንዳንጨርስና በኢኮኖሚ አቅም እንዳይኖረን ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በራሷ አንጡራ ሀብት የተፋሰሱን ሀገራት ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መንገድ ልጠቀም የሚል ፍህታዊ ጥያቄ ይዛ ጫናው መበርታቱ የዲፕሎማሲውን ግንኙነት አያሻክረውም?
ዶክተር ደረጄ፡– የዲፕሎማሲውን ጉዳይ ዲፕሎማቶች በደንብ የሚያብራሩት ነው።ነገር ግን በዲፕሎማሲ ጽኑ ወዳጅ ጽኑ ጠላት የለም።ከአሜሪካ ጋር የ120 ዓመት ግንኙነት አለን።ይህን ግንኙነት ያሻከረው የአሜሪካ ህዝብ ሳይሆን የትራምፕና የባይደን አስተዳደ ነው።ስለዚህ የሻከረውን ዲፕሎማሲ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት መመለስ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካ ብዙ ጩኸቶችን የምታሰማው በትግራይ ክልል ያለው የሰብአዊነት ጉዳይ አሳስቧት ነው?
ዶክተር ደረጄ፡- ለአሜሪካ የህግ ማስከበር ዘመቻው በግብጽ ላይ የምታደርገው ድጋፍ ምክንያት ሆነላት እንጂ የትግራ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው፣ ለህዝቡ የሚጨነቀው የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ እንጂ አሜሪካ አይደለችም።ችግሩ ቢያሳስባት ችግሩን ማን ፈጠረው ብላ ትጠይቅ ነበር።ጉዳዩ ግን ይህ ሳይሆን ቀድሜ እንደገለጽኩት ኢትዮጵያ ጠንክራ እንዳትወጣ ካለመፈለግ የመነጨ ነው።‹‹አያ ጅቦ ሳታመሃኝ ብላኝ›› እንደሚባለው አይነት ስለሆነ ነው “በምንም አይነት ሁኔታና መመዘኛ ከሰብአዊ መብት መቆርቆር ጋር የተያያዘ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካ በዚህ አይነት ሁኔታ ጣልቃ ለመግባት የምታደርገው ሩጫ በተዘዋዋሪ በህዳሴው ግድብ ላይ ጫና ለማሳደር ነው?
ዶክተር ደረጄ፡- ይህን ለመተንበይ የሮኬት ሳይንቲስት መሆን አያስፈልግም፣ የአደባባይ ሚስጥር ነው።የጣልቃ ገብነቱ ሩጫ ምንድን ነው ተብሎ ሲታሰብ ተደራራቢ ጉዳዮች አሉ።በምርጫው ተሳክቶ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ተቋቋመ ማለት ሀገሪቱ ጠንካራ ትሆናለች።ይህ ሲሆን ወደ ህዳሴ ግድቡ የሚያተኩሩ ናቸው ብለው ያስባሉ።ለዚህም ማሳያዎች በርካታ ናቸው።ለምሳሌ አንድም ጊዜ የእኔነው ብላ የማታውቀው ሱዳን ቤንሻንጉል ጉሙዝ የኔ ነው፣ በመተማ በኩል ድንበር ጥሳ ወረራ የፈጸመችው መሬት ፍለጋ ሳይሆን የህዳሴው ግድብ ለማስተጉዋጎል በአሜሪካና ግብጽ ተልዕኮ ተሰጥቷት ስለምትሰራ ነው።
ሱዳን የምትተነኩሰው ታዛ እንጂ የሱዳናውያን ፍላጎት አይደለም።ምክንያቱም ችግር ውስጥ በገባችበት ወቅት ከማንም ቀድማ የታደገቻት ኢትዮጵያ እንደሆነች ለማንም የተሰወረ አይደለም።እነሱም ያውቁታል። ስለዚህ ምርጫው እንዳይካሄድ፣ ሁኔታዎች እንዳይሳኩ ወሳኙ ጊዜያችን አሁን ነው ብለው አቅደው እየሰሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የውጪ ጣልቃ ገብነትን እንዴት መቀልበስ ይቻላል?
ዶክተር ደረጄ፡– ከአሜሪካ ጋር ያለንን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጥበብ በተሞላበት መንገድ ሊመራ ይገባዋል።እሷ እጇ ረጅም በመሆኑ የምትመጣበትን መስመር በማጤን በሰላማዊ መንገድ መሄድ ወሳኝ ነው።ቁልፉ መፍትሔ ደግሞ በእጃችን ነው።ይህም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ለማስከበር ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በማጠንከር በህብረት መቆም ያለብን ጊዜ ቢኖር አሁን ነው።የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይህን አመለካከት ማራመድ የሚቻለው አገር ስትኖር ብቻ ነው።ሀገር አሁን ጥቃት እየደረሰባት ነው።ድሮ በጣሊያን አባቶቻችን ከሁሉም አቅጣጫ በአንድነት ዘምተው ድል አድርገዋል።አሁንም የሚያዋጣን አንድነታችን ነው።
በሀገር የመጣን ጠላትን ለመመለስ መድኃኒቱ አንድነት ብቻ ነው።ጥሩ ምሳሌ ናት ብዬ ባላስብም ሰሜን ኮሪያ ላይ አሜሪካ ማዕቀብ ብትጥልባትም አሁንም ድረስ ክብሯን አስጠብቃ እየኖረች ነው።ጭቆና ሌላ ጥያቄ ነው፣ ነገር ግን የሀገርን ሉአላዊነት ማስከበር ትልቅ ክብር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚም ከዚያም የሚከሰቱ ግጭቶች አንድነታችንን አላልቶታል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ደረጄ፡– ከዚህም ከዚያም የሚከሰቱ ግጭቶች ዋና መንስኤአቸው ኢትዮጵያ አንድ እንዳትሆን ለማድረግ ነው።እነሱ ብር ከፍለው በቅጥረኞች የእኛን እረፍት ለመንሳት ይሰራሉ።ነገሮችን ለውጭ ከማስተጋባት በመቆጠብ ነቅተን ሊከፋፈሉን የሚያስቡትን ማሳፈር ነው።እኛ የራሳችን ውስጣዊ አንድነት አስጠብቀን ማሳየት አለብን።በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን በርትቶ በመስራት እጃቸውን እንዲሰበስቡ ማድረግ ያስፈልጋል።ምቾት የማይሰጡ ነገሮችን በማራገብ መወጠር አይገባም።እኛ መስራት ያለብን በሀገራዊ አንድነት ላይ ነው።ሁሉም ሰው ለሀገሩ እንደ ወታደር ዘብ መቆም፣ ዲፕሎማት መሆን የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ ነን።
አዲስ ዘመን፡- ከውጭ የሚመጡ ጫናዎችን ለመቋቋም እንዴትና በምን መልኩ መሰራት አለበት ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ደረጄ፡– የኢትዮጵያን ማደግ ሳይሆን መፍረስ የሚመኙ አካላት ማንኛውንም ነገር በእኛ ላይ የደረሰ ነገር ያስደስታቸዋል። ርሃብ፣ ቸነፈር፣ እና ግጭት ቢመጣ ለእነሱ ደስታቸው ነው።ለምን ቢባል የእኛን መለወጥ አይፈልጉም።ዋና አላማቸውም በቀጣናው ጠንካራ ሆነን እንዳንወጣ የሚያደርጉት ተፅዕኖ መሆኑን በመገንዘብ መስራት ነው።
ለአብነት ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በብዙ መልኩ በቀጠናው ጎልታ እየመጣች ነበር።ይህ መሆኑ አይናቸውን ያቀላዋል።የአሁኑ የግብጽና የሱዳን ዙሪያውን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከዚህ የሚመነጭ ነው።ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላት ሚና ጎልቶ መውጣቱ እና ለመለወጥ የምታደርገው ጥረት እንቅልፍ የነሳቸው ይመስላል።ስለሆነም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚከሰቱ ግጭቶች ደራሲዎች እነሱ መሆናቸውን በግልጽ ማሳየትና መረዳት ይገባል።እነሱ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ አጀንዳ እየፈጠሩልን ነው።በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ሥራ መስራት ያስፈልጋል።ለእኛ አጀንዳ ሲሰጡ ከጥንትም ጀምሮ ሀገር የምታበቅላቸው ባንዳዎች አሉ።ይህን ከውስጥ ሆነው ለጠላት መረጃ የሚያቀብሉ የሚላላኩአሉ።ለምሳሌ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ተጣለ ብሎ እልል የሚል ኢትዮጵያዊ ባንዳ አለ ፣ ነገም ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራትን ገናናነትና አንድነት እንዴት መመለስ ይቻላል?
ዶክተር ደረጄ ፡- የተለያዩ ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ፣ ይህን ሁሉ ልናራምድ የምንችው ሀገር ሲኖር ነው።ስለዚህ አሁን ላይ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ተጋርጦብናል። የፈለገ የሰፋ ልዩነት ቢኖረንም መጀመሪያ በጋራ ጠላታችንን መመከት ነው። ጅብ ሰፈር ውስጥ ሲገባ ከጎረቤቴ ጋር ተጣልቻለሁ ብሎ ቁጭ አይባልም።በጋራ ወጥተን ጅቡን ከመለስን በኋላ ጠብ ካለም በሀገር ላይ ስለሚያምር መጣላትና መከራከር ይቻላል።የእኛ ጥል ለውጪዎች ቀዳዳ ይፈጥራል።ስለዚህ እያንዳንዱ ዜጋ በሚሰራበት፣ በሚኖርበትና በሌሎች አጋጣሚዎች የራሱን ብሎም የማህበረሰቡን ደህንነት መጠበቅ አለበት።
ከምንጽፈው ጀምሮ የምንናገረውን ነገር በመለየት ከመጥፎ ንግግር መቆጠብ አለብን።ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም ነገር መጻፍና ጥፋቱን ደግሞ ማራገብ ሌላ ጥፋት ነው።መቻቻል፣ አይቶ ማለፍ ትልቅ ነገር ነው።ያየነውን ነገር ላይ ሁሉ መጻፍ የለብንም።አሁን መዝመት ያለብን በውስጣችን ጉዳይ ሳይሆን በውጭ በሚደረግብን ጫና ነው።በተለይም እንደ ባንዳ ሆነው ለውጭ የሚሰሩ የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት አጋጣሚውን ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ።ውጭውም አሰፍስፎ እንደመጣ ይቆጠራል።ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ጊዜ ገጥሞን አያውቅም።ከውጭ በላይም በታችም የተወጠርንበት ጊዜ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የውጪ ጣልቃ ገብነት እየተስተዋለ ነው፣ ሁነቱ ለአንድነታችን ማጠናከሪያ መንገድ መሆን አይችልም?
ዶክተር ደረጄ፡- አዎ።ሁኔታው ለአንድነታችን ጥሩ አጋጣሚ ነው።በብሔር፣ በኃይማኖትና በዘር ሲከፋፍሉ የቆዩትን የሰሩትን የምንጠግንበት እና አንድ ከሚያደርጉን አጋጣሚዎች አንዱ በመሆኑ መሰባሰብ አለብን።ተለያይተን አንድ የምታደርገን እናት ሀገራችን ነች።ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ተለያይተናል ስንባል አንድ የምንሆን፣ ደክመዋል ስንባል የምንበረታ ነን።ለአብነትም ጥቅምት 24 የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሽብርተኛው ህውሓት ተጠቃ ሲባል ከአራቱም አቅጣጫ ቁጣውን በመግለፅ ህግ ለማስከበር ህይወቱን የገበረ ዛሬም እንደ አያቶቻችን ለመሆናችን ምስክር ነው።መከላከያ ተነካ ሲባል ህዝቡ ሆ ብሎ ነው የወጣው።አሁን እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ጫና ቢመስሉም እኛን የሚያጣብቁንና የሚያበረቱን ሙጫዎች ናቸው።ስለዚህ የውጭ ጫናን ለአንድነት ማጠናከሪያ ልንጠቀምበት ይገባል።ስለዚህ አንድነታችን ላይ ጠንክረን ካሸነፍን በኋላ ሌሎች ጉዳዮቻችንን መስራት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ሱዳን የሀገርን ሉአላዊነት ተዳፍራ በምትገኝበት በዚህ ወቅት በዲፕሎማሲ እንድትመለስ ማድረግ ያልተቻለው የዲፕሎማሲ ክፍተት ነው ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ደረጄ፡– ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው የውጭ ዲፕሎማሲ ጎረቤት ሀገራትን ያስቀደመ ነው።ዜጋ ተኮር የሆነ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት የሚል የውጭ የዲፕሎማሲ መርህ እየተከተለች ነው።ነገር ግን የጎረቤት ሀገራት ተመልሰው ያልተገባ ተግባር ሲፈጽሙ ይታያል።የሱዳን ጉዳይ የጥቅም ጉዳይ ነው።ሱዳን እኮ ፈርሳ ነበር፣ የታደገቻት ኢትዮጵያ ናት።አልበሽር በወረደበት ጊዜ ከፍተኛ ችግር ሲከሰት የኢትዮጵያ መሪዎች ሂደው ነው ያዳኗት።ይሁን እንጂ ‹‹ትናንትን ከረሳህ ነገን አትሆንም›› እንደሚባለው ራሳቸውን ረስተው ነው።በወቅቱ የሽግግር መንግሥት እንድትመሰርት የቻለችው በኢትዮጵያ ጥረት ነው።
ነገር ግን ሀገር የማዳን ተግባር ለሰራች ጎረቤት ኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው ገቡ ከተባለ የተለያዩ ጥቅሞች አሏቸው።ስለዚህ ጥቅም ምንጊዜም ያጋጭሃል።ሱዳን በአሜሪካ አሸባሪ ተብላ ተመዝግባ ማዕቀብ ውስጥ የነበረች ሀገር ናት።ስለዚህ ከሱዳን ላይ የተጣለው ማእቀብ ባለስልጣኖቻቸው እንኳ ወደ አሜሪካ እንዳይሄዱ አድርገዋቸው ነበር።አልበሽር ከወረደ በኋላ ሱዳን ይህንን ሥራ ከሰራሽ እስራኤልን ከተቀበልሽ እንዲህ ይደረግልሻል ተብላ ነው።
ኢትዮጵያ ደከም ብላለች ከቻልን የእነሱን መሬት እንውሰድ ካልቻልን ደግሞ የህዳሴ ግድቡ እንዳይሞላ እናደርጋለን።ይህ የሚሆነው ከበስተጀርባ ሌላ ጉዳይ አለ።ግብጽ ከጎን አለች፤ ወታደራዊ ልምምድ በጋራ እያደረጉ ነው።በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪካ በሱዳን በኩል ካርድ ትመዛለች።ይህም ግብጽን ለማስደሰት የታለመ ኢትዮጵያን የማዳከሚያ መንገድ ነው ብለው ስላሰቡ ነው።ግድቡ እንደማይጎዳቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ መርህን መሰረት በማድረግ ዓልማ ባለችበት ወቅት እንደ አጥፊ ሁሉም ሀገራት በዝምታ የሚመለከቱት ለምንድን ነው?
ዶክተር ደረጄ፡– ከእኛ ይበልጣሉ ብለው ምቀኛነት የተጠናወታቸው ሀሳብ ስለያዙ ነው።ሌሎች ሀገሮች ለምን ዝም አሉ ብሎ ሲታሰብ ለምሳሌ የአፍሪካ ሀገራት ለሰብአዊነት ክብር ለኢትዮጵያ እውነቱን ቢናገሩ እኮ ከአሜሪካ ጋር መጣላት ነው ብለው ስላሰቡ ነው።ስለዚህ የሌሎች ሀገራት ዝምታ አሜሪካ ታላቅ ጌታ ሁና መታየት ለምትፈልገው ነገር አጋዥ ነው።ዲፕሎማሲው ላይ ብዙ ሥራዎች አሉ፤ ነገር ግን አሁን እየደረሰብን ያለው ጫና የዲፕሎማሲው ክፍተት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በዲፕሎማሲው ጎረቤት ሀገራትን ያስቀደመ ፖሊሲ እየተከተለች ቢሆንም የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የበረታው ከምን አንጻር ነው?
ዶክተር ደረጄ፡– የአሜሪካ መንግሥት እኔ ልዳኛችሁ፣ በእኔ ይሁንታ ኑሮ ስትል እኛ እኮ እንደ ሌሎች ሀገራት በእናንተ አንዳኝም ነው የተባሉት።አሁን ያለው የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን ‹‹ይች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም›› አይነት ሀሳብ ይዘው ተፅዕኖ ለማሳደር እየሰሩ ያሉት።ለአብነት የህዳሴውን ግድብ ድርድር በእናንተ ሳይሆን በአፍሪካ ህብረት ነው ምንዳኘው ስላልን ውሃ እንዳትሞሉ ተባለ፤ እንሞላለን አልን።ስለዚህ ቃላቸውን አልሰማም ስለተባሉ የእነሱ አሻንጉሊት መሆን ስላልቻልን የመጣባቸው ስጋት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በጋዛና በእስራኤል መካከል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ግብጽ አሸማጋይ ሆና ታይታለች፤ ሁኔታውን እንዴት ታዘቡት?
ዶክተር ደረጄ፡– በእስራኤልና ጋዛ በተካሄደው ጦርነት በሁለቱ መካከል የተኩስ አቁም አሸማጋይ ግብጽ ሆና ታይታለች።ይህ የሚያሳው አንቺ ይህን ከሰራሽ እኔም ላንቺ ይህን እሰራለሁ የሚል ሀሳብ ውስጥ እንዲገባ በማሰብ የመነጨ ይመስለኛል። ስለዚህ ይህን ጉዳይ በአጽዕኖት መመልከት ተገቢ ነው።በብዙ መልኩ ጫና ውስጥ ለማስገባት ሲጥሩ እየተስተዋለ ነው።ለምሳሌ በትግራይ ክልል ሰብአዊ ጥሰት ከልብ የሚያሳስባቸው ከሆነ ማይካድራ ላይ ስለተፈጸመው ነገር ለምን አይናገሩም ነበር ፤ የሞቱት ሰዎች ስለሆኑ ስለእነሱም ይከራከሩ ነበር።ነገር ግን አንዱን ወገን ብቻ ለይተው ብቻ መቆርቆር ከማስመሰል ውጪ ሌላ ጉዳይ የለው።
አዲስ ዘመን፡- በሀሰተኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ በዘመኑ ቴክኖሎጂ የታገዘ የማህበራዊ ሚዲያ ጦርነትን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ዶክተር ደረጄ፡- አሁን ዓለም እየተመራች ያለችው በማህበራዊ ሚዲያ ነው።ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ መሪዎች፣ ግለሰቦችና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች አሉ።በዚህም ክፍያ የሚያገኙ አካላት አሉ።የውጪው ዓለም በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ይበልጠናል።ለዚህም ነው በማህበራዊ ሚዲያ በሚራገቡ ሀሰተኛ መረጃዎች አማካኝነት ተፅዕኖ እየደረሰብን ያለው ። ስለዚህ ይህን ለመቀልበስ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ማስተካከልና እነሱን መገዳደር መቻል ያስፈልጋል።ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትውልዱን የማንቃት ሥራ መስራት አለባቸው።
ዲፕሎማሲውም አሁን እየተመራ ያለው በማህበራዊ ትስስር ገጾች በመሆኑ በማህበራዊ ሚዲያው እኩል ከእነ ግብጽ መገዳደር መቻል ያስፈልጋል።ከሳምንታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩት ተብሎ የተለቀቀው ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት አጀንዳ በመስጠት ህዝቡን ለማደናገር እየሰሩ ነው። ይህን ለመቅረፍ የረጅም ጊዜ ሥራን ይጠይቃል።እንደ ሀገር አንድ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ብስለት የጎደለው ነው።ፌስቡካችን ቢታይ እርስ በርሳችን አንዱ ኢትዮጰያዊ አንዱን ስንጠላለፍ የሚያሳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የተዛባውን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እንዴት ማስተካከል ይቻላል?
ዶክተር ደረጄ፡– አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያስተምረን ከዚህ በኋላ በሚቀጥሉት ጊዚያት ጦርነትን ማሸነፍ የምንችለው በሁሉም መስክ ነው።ጋሻ፣ ጎራዴ፣ ታንክ፣ መድፍ መያዝ የሚገባን ጊዜ ነበር።አሁን አያስፈልገንም ሳይሆን ሌላ የሳይበር ሴኩሪቲ ጦርነት በአሁኑ ወቅት አለ።ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ሊረዱ የሚገባው በሳይበር ሴኩሪቲ በሀገር ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ መከላከል ነው። በዚህ ዘመን ሁሉም ነገር የተገናኘ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
አሁን በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚራገበውን ወሬ ትክክለኛውን ሳይሆን በአሉ አሉ መጠመድ አይበጅም።በተለይም የመረጃውን ተክክለኛነት እና ጠቃሚነት አረጋግጦ የሚቀበል ትውልድ መፍጠር ይገባናል።በሚቀጥሉት ዓመታት ምክንታዊ ትውልድ እንዲፈጠር ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።አሁን ያለው ጨዋታ በቴክኖሎጂ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ሀገርን ከጥቃት ሊከላከሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ ሊሰሩ ይገባል።
ግብጾች በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ እየሰሩ ያሉት በማህበራዊ ሚዲያ ሁሉ ጦርነት ከፍተዋል።ይህን የሚያደርጉት በውጪ ሆነው የትግራ ተወላጆች ነን እንዲህ ነን እያሉ የሚወጡት የጁንታው አባላት የሴናተሮችን ቲውተር ሀሽ ታግ እያደረጉ የሚታዩት በርካታ ሰው ከሆነ ለምንድን ነው ብሎ ይሄዳል።በእኛ በኩል ግን ሲደረግ አይስተዋልም። ዳር ቆሞ ከማየት ውጪ የያገባኛል ስሜት ባለመዳበሩ ነው።110 ሚሊዮን ህዝብ ይዘን ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ለሀገሩ በሚጠቅም መንገድ ስንት ሰው ይጠቀማል ቢባል ውስን ነው።ሰለዚህ ይህን በማስተካከል አይናችንን መግለጥ መቻል አለብን።
በሰበብ አስባቡ የውጭ ጣላቶች እያደረጉ ያሉትን ጫና ለመቋቋም ልዩነታችን በማጥፋት አንድ መሆን ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ነው ።ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን የውጭ ኃይሎች የሚነዙትን አጀንዳ ማራገብ ሳይሆን ህዝብን ወደ አንድ በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ሊሰሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ጊዜዎትን ሰውተው ስላካፈሉን ሰፋ ያለ ማብራሪያ እናመሰግናለን።
ዶክተር ደረጄ፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2013