የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ እንደ ማንኛውም የሀገሪቱ ህዝብ የለውጡ ትርፋት ተቋዳሽ እንዲሆን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ አልፏል፤ ብዙ ዋጋም ከፍሏል። ከፍጥረቱ በለውጥ መንፈስ ከማመንዘር ባለፈ ህዝባዊ ባህሪ የሌለውን የጁንታውን ስብስብ የለውጡ አካል ለማድረግ የሄደበት ርቀትም የትናትን ጥፋቶችንና ወንጀሎችን በይቅርታ እስከማለፍ የዘለቀ እንደነበር ይታወሳል።
ለውጡ ካለው ሀገራዊ ፋይዳው አንጻር ከትናንት ይልቅ ለዛሬ ከፍ ያለ ቦታ በመስጠቱ በብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የህዝብ ሃብት ዘረፋ የተሳተፉ የአሸባሪው ጁንታ ቡድን አባላት የያዙትን ይዘው የለውጡ አካል እንዲሆኑ፤ መሆን እንኳን ካልቻሉ ለውጡን ለማደናቀፍ እየሄዱበት ካለው የተለመደ የሴራ ተግባራቸው እንዲመለሱ ልመና በሚመስል መልኩ ሰፊ አድል ሰጥቷቸዋል ።
የትግራይ ህዝብ ለነጻነት ፣ ለዴሞክራሲና ለሀገር ሉአላዊነት ከከፈለው ትልቅ ዋጋ አንጻር ለውጡ እና ለውጡ ይዞት የመጣው ተስፋ ልጆቹ በተለያዩ ወቅቶች ለነጻነት ፣ ለዴሞክራሲና ለሀገር ሉአላዊነት የከፈሉት መስዋእትነት ፍሬ መገለጫ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ መቀሌ ድረስ በመሄድ የለውጥ ሀይሉ ለትግራይ ህዝብ የነገ ተስፋዎች ታማኝ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል። በዚህም በህዝቡ ውስጥ መነሳሳትን መፍጠር ችለው ነበር።
የትግራይ ህዝብ እጣ ፈንታ ከሌላው የአገሪቱ ህዝብ ጋር የተጋመደ፤ ከዛም በላይ ህዝቡ የራሱን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የሚያስችል አቅም ባለቤት መሆኑን በማሳወቅ የለውጡ ትሩፋት ተካፋይ እንዲሆንና ሃገራዊ ለውጡ የትግራይን ሕዝብ ችግሮችን የመፍታት አቅምና ተልዕኮ እንዳለው ጭምር ለማሳየት ጥረዋል።
ለትግራይ ህዝብ የቀደመ የነጻነት ትግል ታሪክ እውቅና ከመስጠት አንስቶ ይህ የትግል ልምዱ ድህነትን ለማሸነፍም ሆነ የዴሞክራሲ ስርአትን ለመገንባት በሚደረገው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ተጨማሪ ሀገራዊ አቅም ሊፈጥር እንደሚችል፣ ለዚህ አቅም የለውጥ ሀይሉ እውቅና እንደሚሰጥ ቅንነትና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተሞላበት መንገድ ለማስረዳት ሞክረዋል።
ይህ ሁሉ ጥረት የትግራይ ህዝብ በነጻነትና በዴሞክራሲ ስም ለጁንታው ቡድን ስልጣን የገበራቸውን ልጆቹን ህልምና ተስፋ እንዲጨብጥና የልጆቹን የመስዋእትነት ተጋድሎ ታሪክ ትክክለኛ መሰረት ላይ እንዲዋቀር በማድረግ የታሪክን ቀጣይነት ለማሳየት ጭምር ነበር። ጥረቱ ግን ከጁንታው ፍጥረታዊ ማንነት ጋር ሊጣጣም የማይችል በመሆኑ በፈጠረው ዕብሪትና የዕብሪት ትርክቶች የተጠበቀውን ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም።
በርግጥ የትግራይ ሕዝብ ሀገራዊ ለውጡ ካመጣው የለውጥ አስተሳሰብ ተካፋይ የመሆን መነሳሳቶች ቢኖሩትም ጁንታው የትግራይ ህዝብ እና እኔ አንድ ነን በሚል መሰረት አልባ ትርክት ሕዝቡ በተለይም፣ በህዝቡ ውስጥ ያለውን የለውጥ ሀይል በማሸማቀቅ፤ ራሱን የለውጥ ሀይል አድርጎ እንዳይገልጥ በተለመደው የፍረጃ ትርክት በማሸማቀቅ እና በማስፈራራት የለውጡ መንፈስ ወደ ህዝቡ እንዳይወርድ ብርቱ ፈተና ሆኗል።
እልፍ ሲልም የትግራይን ህዝብ የጦርነት ጋሻ በማድረግ የጦርነት ጉሰማዎችን ከማስጎሰም ባለፈ የህዝቡን ጥሪትና በስልጣን ዘመኑ ከህዝብ የዘረፈውን ሀብት በመጠቀም በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በልቶ ለማደር በማይችልበት ሁኔታ ከፍ ያለ የጦርነት ድግስ ደግሶ ወደ ግጭት ገብቷል። የግጭት ሴራው ከሀገር አልፎ የአፍሪካ ቀንድን የሁከትና የትርምስ ቀጠና የማድረግ ዓላማ ቢኖረውም ጁንታው ባልጠበቀው ሁኔታና ታሪካዊ በሆነ መንገድ የሽንፈትና የውርደት ታሪኩ በአጭር ጊዜ ተጠናቋል ።
መንግስት የትግራይ ህዝብ የለውጡ ትሩፋት ተጠቃሚ እንዲሆን ከነበረው መሻት የተነሳም የጁንታው ዕብሪትና ከዕብሪቱ የመነጩ ተግባራቱ በሰላም ማስከበር ዘመቻው ብዙ ዋጋ እንዲከፍል አድርገውታል። ከዘመቻው ማግስት ጀምሮም በነበሩ አስቸጋሪ ሀገራዊ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን የትግራይን ህዝብ ታሳቢ ያደረጉ ከፍ ያሉ ስራዎችን ሰርቷል።
ህዝቡ የለውጥ መንፈስ በታጠቁና ለህዝቡ የተሻለ ተስፋ በሰነቁ ልጆቹ እንዲመራ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እና የፓርቲ አስተሳሰብ ያልተገዙ ልጆቹን በማሰባሰብ ጊዜያዊ አስተዳደር አዋቅወሯል፤ አስተዳደሩ በተሻለ ሁኔታ ኃላፊነቱን እንዲወጣና የትግራይ ህዝብ እንዳይጎዳ ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማፍሰስ የመልሶ ግንባታው ውጤታማ እንዲሆን ተንቀሳቅሷል።
ለትግራይ ህዝብ የዕለት ደራሽ እርዳታዎችን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚሸከመው በላይ ወጪ በማድረግ ለማድረስ ሞክሯል፤ በጁንታው የወደሙ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን በልዩ ሁኔታ ጠግኖ ወደስራ አስገብቷል፤ ሕዝቡን ጁንታው ከፈጠረው ችግር ለመታደግ በታማኝነት ተንቀሳቅሷል። የእርዳታ እቅርቦቱ ለህዝቡ በወቅቱ እንዳይደርስ ዋነኛ ችግር የሆነውን የጁንታው ርዝራዥ ታጣቂ ሀይል ለመከላከል ጦር አሰልፎ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሏል ።
ከትግራይ ክልል ዓመታዊ በጀት በአስር እጥፍ የሚበልጥ የህዝብ ሀብት በክልሉ በማፍሰስ ለህዝቡ ነገዎች ያለውን ተስፋና የተስፋ አጋርነት ከቋንቋ ባለፈ በተግባር እውን አድርጎ አሳይቷል። የትግራይ ህዝብን በጁንታው ከተነዙ የጥላቻ እና ህዝቡን ከሚነጥሉ ትርክቶች እንዲወጣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግራይን በመታደግ ሄደት ተሳታፊ እንዲሆን ተደርጓል ።
የክልል መንግስታት አስቸጋሪ በሆነው አገራዊ የኑሮ ውድነት ችግር ውስጥ ካለው ህዝብ ጉሮሮ ተናጥቀው ለትግራይ ህዝብ ለመድረስ ረጅም ርቅተ ሄደዋል። የጁንታው የጥላቻ ትርክቶች መሰረት እንደሌላቸው፤ ከዛ ይልቅ የትግራይ ችግር ዛሬም የመላው ህዝብ ችግር መሆኑን በተጨባጭ አሳይተዋል።
ይህ ሁሉ አገራዊ ጥረት የትግራይ ህዝብ የለውጡ ተጠቃሜ እንዲሆን በወንድምነትና በበጎ ህሊና መንፈስ የተደረገ ነው። የትግራይ ህዝብ ልጆቹ ለዴሞክራሲና ለነጻነት ከከፈሉት ከፍ ያለ ዋጋ አንጻር አሁን እየኖረ ያለው የጭቆናና የስጋት ህይወት አይመጥነውም፣ አይገባውም ከሚል የመነጨም ነው።
የመላው ህዝባችንም ሆነ የለውጡ ኃይሉ የእስካሁኑ ጉዞ፤ ዘመናቸውን ሙሉ የትግራይን ህዝብ የፖለቲካ ሸቀጥ አድርገው በሚነግዱ፣ በስሙ እየማሉ በመከራ በስቃዩ፣ በሞቱና በስደቱ የህይወት እስትንፋስ በመሰብሰብ እድሜያቸውን ከሚያረዝሙ፤ በተጨባጭ በልጆቹ የትግል ተስፋና በህዝቡ እጣ ፈንታ ከሚቆምሩ ሾተላዮች መታደግ ነው !
አዲስ ዘመን ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም