በምርጫው ህዝቡ አይሳተፍም፣የምርጫው ሁኔታ የደበዘዘ ነው ።ዲሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ አይሆንም። አገሪቱ ጸጥታ ጉዳይ ምርጫ ማድረግ አያስችልም፤ የከፋ መዘዝ ይዞ ይመጣልና ሌላም ሌላም አሉታዊ ነገር ብለዋል። በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የነበረው ሂደት አፍራሽ ኃይሎች እንዳስወሩት ሳይሆን ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ ነው የተካሄደው ።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አካል ጉዳተኛ፣አዛውንትና ወጣት ሳይል በነቂስ በመውጣት ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ ምርጫ ጣቢያ በመሄድ የሚፈልገውን ፓርቲ መርጧል።የዚህ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤትም የምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ወዲያው በምርጫ ጣቢያዎችና በምርጫ ክልሎች ይፋ ሆኗል። የ378 የምርጫ ክልሎች ውጤትም ወደ ምርጫ ቦርድ መጥቶ እርክክብ ተደርጓል። ቀሪዎቹ የምርጫ ክልሎችም ለማስረከብ በሂደት ላይ ናቸው።
በጥቅሉ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻና ዲሞክራሲያዊና ታአማኔ ሆኖ ተጠናቋል። ይህንንም የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎችና የምርጫውን የታዘቡ የሲቪል ማህበራት ጭምር ምስክርነት ሰጥተዋል።ይህ ምርጫ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የዲያስፖራው አበርክቶ ምንድነው?
ዲያስፖራው በአገር ውስጥ የሚካሄደውን የምርጫ እንቅስቃሴ በመከታተል፣ በምርጫው ወቅት የሚያጋጥሙ ፈተናዎች በመተንተንና ኢትዮጵያ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት መመስረት እንደሚኖርባት በሚያስገነዝቡ ጉዳዮች ዙሪያ በቴክኖሎጂ የታገዙ ውይይቶችን በማዘጋጀትና ስብሰባዎችን በማካሄድ ለምርጫው ሰላማዊነት በጎ ሚና መጫወቱን የሚገልጹት የኢትዮጵየ የዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ናቸው።በተለይ ዲያስፖራው በማህበራዊና በመደበኛ ሚዲያዎች በመጠቀም የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶችና ጹሁፎች አገር ውስጥ የሚደረገው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስተዋጸኦ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ጠንካራና በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ያስፈልጋታል። ከዚህ አኳያ ዲያስፖራው በኢትዮጵያ ህጋዊ መንግሥት እንዲመሰረትና ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ስለዚህ በኢትዮጵያ በምርጫም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ለመግባት የምትፈልጉ ሃይሎች ጣልቃ አትግቡ በሚል ዲያስፖራው ከፍተኛ ትግል አካሄዷል፣በአገር ውስጥ ያለው ህዝብም እንዲመርጥ፣ እንዲመዘገብና ዲሞክራሲያዊ መብቱን እንዲጠቀም በሚዲያዎቻችን አማካኝነት ምርጫው ሰላማዊና የህዝብ ንቁ ተሳትፎ የታከለበት እንዲሆን ከፍተኛ ቅስቀሳ ያደረጉበት ነው ሲሉ ወይዘሮ ሰላማዊት ይገልጻሉ።
ምርጫው መጠናቀቁንም ተከትሎ ኢትዮጵያ እስካሁን ካደረገቻቸው ምርጫዎች በጣም የተሻለ እንደነበርና ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ የመረጠበት ምርጫ መሆኑን እንደሚያምኑም አመልክተዋል።በተለይ በምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጻና ፍትሀዊ ሆኖ ስለመጠናቀቁ ጉዳይ ላይ በዲያስፖራው መካከል ልዩነት ቢኖርም አብዛኛው ዲያስፖራ ምርጫው ሰላማዊ፣ዲሞክራሲያዊ፣ነጻና ፍትሀዊ ሆኖ መጠናቀቁን እንዳስደሰተው ነግረውናል።
አብዛኛው ዲያስፖራ በአንዳንድ መንግሥታትና አካላት ምርጫው እንዳይደረግና እንዲደናቀፍ ይነሱ የነበሩ አፍራሽ ሀሳቦችን በመቃወም ከመነሻውም ጀምሮ ምርጫው መደረግ አለበት ብሎ ይሞግትና ለሌሎች ለማስረዳትም ሁለተናዊ ጥረት ማድረጉ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ዲያስፖራዎች በብዙ ነገር በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዳይፈጠር ሲከላከሉና ሲመክቱ ቆይተዋል።አብዛኛዎቹ በሰልፍ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻና በቴክኖሎጂ የታገዙ ስብስባዎች በማድረግ ጭምር ምርጫ መደረጉ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት አስፈላጊ መሆኑንና ምርጫው የተደረገበትን ሂደትና የህዝቡን ተሳትፎም አድቀዋል ሲሉ አብራርተዋል።
ምርጫው፣የህዳሴን ግድብና የአገራችንን ሰላም በተመለከተ የኢትዮጵያና የህዝቧ ጉዳይ ብቻ ነው።ከዚህ ውጭ ማንም አካል የእኛን ስራ ሊሰራልንና የምንሰራውን ስራ ሊነግረን አይገባም፣ የሚለው ጉዳይ በዲያስፖራው ሲቀነቀን የነበረ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ የዲያስፖራው መልዕክቶችም ብዙ አገራትም ቆም ብለው ሀሳባቸውን እንዲያዩ ያደረገ ተግባር መሆኑን አውስተዋል።ይህ ደግሞ ዲያስፖራው ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ጋር በጋራ መቆሙን የሚያሳይ ነው።በቀጣይም በአገር ውስጥና በውጭ አንድ ሆነን መቆማችን ለጠላቶቻችን እንዳንመች እንደሚያደርግ በተግባር ያየንበት ምርጫ በመሆኑ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮችም ዲያስፖራው ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ።ምክንያቱም ምርጫ አንዱ አገራዊ ጉዳያችን ነው። ሌሎችም ብዙ አገራዊ ጉዳዮች አሉብን ።እነዚህን አገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮች በጋራ አብረን መስራት ይኖርብናል።ዲያስፖራው ይህን ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዲያስፖራዎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እንደሚሳተፉት ሁሉ እንደ ሌሎች አገሮች በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው ዲያስፖራዎች በምርጫው የሚሳትፉበት ዕድል ለመፍጠር ምን እየሰራችሁ ነው የሚል ጥያቄ ለወይዘሮ ሰላማዊት አቅርበንላቸዋል።
የእሳቸው ምላሽም ዲያስፖራው በተለይ ደግሞ ዜግነታቸውን ያልቀየሩ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምርጫ እንዲመርጡ በፖሊሲ ደረጃ ተቀምጧል።ነገር ግን ይህን ፖሊሲ ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችል አሰራር ገና አልተዘረጋም።በዚህ ጉዳይ ከብዙዎቹ ዲያስፖራ አባላት ጋር ተወያይተንበታል።በተግባር የሚመርጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጊዜ፣ገንዘብና አሰራር ያስፈልጋል። ስለዚህ በፖሊሲ ደረጃ የተቀመጠውን እንዴት ወደ መሬት ይውረድ የሚለው የራሱ የሆነ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎች ሊሰሩለት ይገባል።ይህ ወደ ፊት የምንሰራው ይሆናል።
እርግጥ ነው ብዙ አገራት በውጭ ያሉ ዜጎቻቸው በኢምባሲዎች አማካኝነት ድምጻቸውን አሰባስበው ወደ አገር ቤት ያመጣሉ፤እኛም ይህንን የምናደርግበት ሁኔታ ለመፍጠር መስራታችን የማይቀር ጉዳይ ነው። ስለዚህ ምንም እንኳን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአሁኑ ምርጫ ድምጻቸውን በመስጠት መሳተፉ ባይችሉም የውጭ ጫና እንዲቀንስ ህዝቡ በምርጫው በንቃት እንዲሳተፍ፣ሌሎች አካላት እንዲገነዘቡ መስራታቸው ትልቅ አስተዋጸኦ መሆኑን ገልጸዋል።በመጪው ምርጫ ግን መሳተፍ የሚችሉበትን መንገድ ዙሪያ ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ሳይጠቅሱ አላለፉም።ኤጀንሲው በውጭ የሚኖሩ ዜጎች መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ እና ዲያስፖራው በሀገሩ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ሁኔታዎችን ለማመቻቸትም በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ሰኔ 14 ቀን 2013ዓ.ም የተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከ37 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ድምጹን ለመስጠት የተመዘገበ ሲሆን በምርጫው ቀንም አብዛኛው ህዝብ በነቂስ በመውጣት ድምጽን ለሚፈልገው ፓርቲ ሰጥቷል።ምርጫውም ሰላማዊ ሆኖ ተጠናቋል።ይህ እንግዲህ አንዱ የዲያስፖራው የተሳትፎ ውጤት ነው፡፡
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2013